giziew.org

የጉንዳን መንገድ

“አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን”
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በጥበቡ እጅግ የላቀው ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ይላል፤ “አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን”። በዚህ ብቻ አያቆምም፤ ለምን ይህንን እንዳለ ሲቀጥልም “አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት፤ መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች” ይላል (ምሳሌ 6፡6-8)።

ስለ ጉንዳን ጥቂት አስደናቂ እውነታዎች፤ በዓለማችን ከ10ሺህ በላይ የጉንዳን ዓይነቶች አሉ ይባላል። ጉንዳኖች ሳምባ የላቸውም፤ የሚተነፍሱት (ኦክስጂን የሚያስገቡት) በሰውነታቸው ጎኖች ባሉ በርካታ ቀዳዳዎች ነው። ጆሮ የላቸው፤ የሚሰሙት በእርግብግብታ ነው። በዓለማችን ያሉት የጉንዳኖች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው – ጉዳዩን በንጽጽር ለማስቀመጥ ለእያንዳንዱ ሰው 1 ሚሊዮን ያህል ጉንዳን ሊደርሰው ይችላል። ጉንዳኖች አርቢዎች ናቸው፣ የሰው ልጅ በጎችን፣ ፍየሎችንና የመሳሰሉትን እንደሚያረባ ጉንዳኖችም “አፊድ” ተብለው የሚጠሩትን አረንጓዴና ጥቁር ትንኞችን ያረባሉ። ጉንዳኖች እነዚህ ትንኞች ከአዳኞች ይጠብቋቸዋል፤ በዝናብ ተጠርገው እንዳይሄዱ በጎጆአቸው ይንከባከቧቸዋል፤ ምክንያቱም ከእነርሱ የሚመነጨው እንደ ስኳር የሚያጣብቅ ፈሳሽ ለጉንዳኖች የማያቋርጥ ምግብ ስለሆነ ነው። ጉንዳኖች ሁለት ሆድ ነው ያላቸው፤ አንዱ ለራሳቸው የሚሆን ምግብ የሚይዙበት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከሌሎች ጉንዳኖች ጋር የሚጋሩትን ምግብ የሚይዙበት ሆድ ነው። ሌላው ጉዳይ ጉንዳኖች መዋኘት መቻላቸው ነው፤ ይህ ብቻ ሳይሆን በውሃ ውስጥም ትንፋሻቸውን ይዘው ለረጅም ጊዜ መቆየት ይችላሉ።   

መጽሐፍ ቅዱስ ከትንሿ ጉንዳን እንድንማር የሚፈልገው ምንድነው?

  • ጉንዳኖች በደንብ የተደራጁ ናቸው፤ በጉንዳን መንደር ውስጥ ሦስት የተለያዩ የጉንዳን ዓይነቶች አሉ፤ ሠራተኛ፣ ንግሥት እና ወንዶች። እያንዳንዱ ጉንዳን የራሱን የሆነ ሥራ ይሠራል። በደንብ የተደራጁ ስለሆነ በጉንዳን መንደር ሳይሠራ ውሎ የሚያድር ሥራ አይኖርም።
  • ጉንዳኖች በደንብ የተደራጁ ናቸው፤ በጉንዳን መንደር ውስጥ ሦስት የተለያዩ የጉንዳን ዓይነቶች አሉ፤ ሠራተኛ፣ ንግሥት እና ወንዶች። እያንዳንዱ ጉንዳን የራሱን የሆነ ሥራ ይሠራል። በደንብ የተደራጁ ስለሆነ በጉንዳን መንደር ሳይሠራ ውሎ የሚያድር ሥራ አይኖርም።
  • ያላቸውን ያካፍላሉ፤ ጉንዳኖች ያላቸውን በሙሉ ያካፍላሉ፤ ሰዎች አንድ ነገር ሲያገኙ ለራሳቸው እንደሚያከማቹትና ከሌላው እንደሚደብቁት ሳይሆን ጉንዳኖች ያገኙትን ለሌሎች ያካፍላሉ።
  • አስደናቂ ሥነሥርዓት አላቸው፤ ጉንዳኖች ሲጓዙ፣ ለሥራ ሲሰማሩ፣ ወዘተ አንዳች መዛነፍ ሳይኖር እንደስልጡን ወታደር ሥርዓታቸውን ጠብቀው ነው የሚጓዙት። ለመቅደም፣ ፈጥኖ ለመሄድ ወዘተ ሙከራ ሳያደርጉ በሥርዓት ይጓዛሉ።
  • ሥራቸውን በጊዜ ያከናውናሉ፤ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዳለው ጉንዳን “መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች”።
  • ከራስ ወዳድነት የጸዳ ኅብረት፤ ጉንዳኖች የሚበላ ነገር ሲያገኙ ወዲያውኑ መልዕክቱን ለሌሎች ጉንዳኖች ያስላልፋሉ።
  • አይታክቱም፤ ጉንዳኖች የሚሠሩት ቀኑን ሙሉ ነው። እንደው ሥራብዙ ሳይሆኑ ተግባራትን በማከናወን ነው ሳይታክቱ የሚሠሩት፤ ሥንፍና በጉንዳኖች ዘንድ የሚታወቅ አይደለም።
  • ጽኑ ናቸው፤ ጉንዳኖች በመንገዳቸው ላይ ዕክል በሚገጥማቸው ጊዜ ለችግሩ እጅ ሳይሰጡ የሚያሸንፉበትን መንገድ ሁልጊዜ ይቀይሳሉ። በህይወት ጎዳና ለሚገጥሙን ችግሮች፣ ኃጢአትን የማሸነፍ ተግዳሮቶችን ለማሸነፍ ጉንዳኖች ጥሩ ትምህርት ይሰጡናል፤ እምነት በሞላበት ጽናት ድል የማይቀር ሐቅ ነው።
  • ፍጥነታቸው ድንቅ ነው፤ እንደትንሽነታቸው ሳይሆን ጉንዳኖች በጣም ፈጣኖች ናቸው። ሥራቸውን የሚከውኑት በከፍተኛ ፍጥነት ሲሆን ይህም ውሳኔ ለመወሰንም ሆነ ተግባራችንን በፍጥነት ለመፈጸም ለምንቀረፈፍ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
  • ሲያቅዱ ጎበዞች ናቸው፤ በጥቅሱ ላይ እንደተገለጸው “መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች”። ብርዱ አንጀት እጅግ በሚያንሰፈስብበት ክረምት ጉንዳኖች የሚበሉት አያጡም። ምክንያቱም አስቀድመው ስለሚያቅዱ በቂ የምግብ ክምችት አላቸው።
  • ጥንካሬያቸው የላቀ ነው፤ ጉንዳኖች ደከመን ሰለቸኝ የሚባለውን “ቋንቋ” አያውቁትም፤ ከሰውነታቸው ክብደት  ከ10 እስከ 50 ጊዜ (የኢሲያ ሸማኔ ጉንዳኖች ደግሞ 100 ጊዜ) የሚበልጥ ክብደት በልበሙሉነት ተሸክመው ወደ መንደራቸው የመውሰድ ድፍረትና አካላዊ ብቃት አላቸው።
  • በኅብረት መሥራት ያውቁበታል፤ ጉንዳኖች ለዛሬ ይበቃናል፣ ለነገ እናሳድረው የሚባል ነገር አያውቁም። አንዳንዶቹ ጉድጓድ ይቆፍራሉ፤ ሌሎቹ ምግብ ይሰበስባሉ፤ ሌሎቹ ቁሳቁስ ያመላልሳሉ፣ ወዘተ። ሥራው በቡድን ነው የሚሠራው፤ ትልቅ ምግብ ከተገኘ ወዲያው እንደገና በመቀናጀት ኃይል አስተባብረውና የቡድን መሪ መርጠው በአንድ አቅጣጫ እየገፉ ወደ መንደራቸው ያደርሱታል።

የሰው ልጅ የጉንዳንን ህይወት በማጥናት ታላላቅ የህይወት ምሥጢራትን መረዳት ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን እንዴት መምራት እንዳለበት ቀላል ነገርግን ጥልቅና አስደናቂ ትምህርት ማግኘት ይችላል። “አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን”

(ከኢንተርኔት የተቀናበረ)


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *