ጌታችንና መድኃኒታችን በስቅለተ አርብ የሞትን ጽዋ ጠጥቶ ሕይወቱን ለእኛ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ “እሁድ በትንሳኤ ስለምነሳ ችግር የለውም” በማለት አልነበረም። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱሳችን ስለ ሁኔታው ሲናገር “በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር” ይላል (ሉቃስ 23፡44)። በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ጌታችን በጌተሰማኒ በተደጋጋሚ በሚፀልይበት ጊዜ አብረውት የነበሩት ደቀመዛሙርት በፀሎት ሊተጉ ባለመቻላቸው በእንቅልፍ ተወስደው ሳለ እርሱ ግን “ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ” ሆኖ እስኪፈስ ድረስ በጣዕርና በጭንቀት ይፀልይ ነበር።
በብዙዎች እንደሚታመነው ሰው ሲሞት ነፍሱ ከእርሱ ወጥታ የምትሄድ ቢሆን ኖሮ ይህንን ሁሉ ጭንቀት ባላስፈለገው ነበር። ከዚህ ይልቅ እርሱ የደም ሥሮቹ እስኪበጣጠሱና በላብ መልክ ደሙ እስኪፈስ ያደረሰው መመለሻ የሌለበትን የዘላለምን ሞት ከሥላሴ በመለየት ብቻውን በመጋፈጡ ነው። ምክንያቱም ኃጢአት ደመወዝ አለው፤ ዋጋ ያስከፍላል፤ ዋጋውም የዘላለም ሞት ነው (ሮሜ 6፡23)። መድኃኒዓለም ለእኛ የዘላለም ህይወትን ለመስጠት እርሱ የዘላለም ሞት ሞተልን። በዚያች አርብ ዕለት መራራውን የሞት ጽዋ ሲጠጣ በብዙዎች እንደሚታመነው ነፍሱ ከእርሱ ወጥታ ወደ ሰማይ አልሄደችም፤ ለዚህም ማስረጃው አብሮት የተሰቀለው ሌባ ነው። ኃጢአተኛነቱን የተረዳው ሌባ “ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” በማለት ክርስቶስን ሲማጸን ጌታችንና መድኃኒታችን የመለሰለት “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት ነበር (ሉቃ. 23:42፣43)። ይህ ማለት ሁለቱም በሞቱበት ዓርብ ቀን በገነት ተገናኝተው ነበር ማለት ነው?
ጌታ ክርስቶስ በሞተበት ቀን ወደ ሰማይ አላረገም። ለዚህ ማስረጃው በትንሳኤው ቀን ለመግደላዊት ማርያም የሚከተለውን መናገሩ ነው፤ “ኢየሱስም፣ ‘ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ … አላት’”። (ዮሐ. 20:17) ጌታችን እግዚአብሔር አብ ወዳለበት ሰማይ ያረገው ከትንሳኤው በኋላ ነው። (የሐዋ. 1:9-10) ከዚህ የተነሳ በስቅለቱ ቀን ቀድሞ ገነት ደርሶ ያመነበትን ሌባ አስተናገደ የሚለው ነገር ትክክለኛ አይደለም።
ይህን ሃሳብ ጥያቄው ላይ ከቀረበው ጥቅስ ጋር ለማስታረቅ ስለ አዲስ ኪዳን አፃፃፍ ማወቅ ያለብን ነገር አለ። አዲስ ኪዳን ሲፃፍ ሥርዓተ ነጥብ (punctuation) አልነበረውም። ይህ ብቻ ሳይሆን በቃላት መካከል ወይም በዓረፍተ ነገሮች መካከል ምንም ዓይነት ክፍት ቦታ ሳይኖር ግጥምጥም ብሎ (Scriptio continua or continuous script) ነበር የተጻፈው። ለምሳሌ ይህን አናባቢ የሌለውን በእንግሊዝኛ ፊደል የተፃፈ ጽሑፍ እንዴት ያነቡታል? “CMPTRNTWRK” ይህ እንግዲህ “computer network” ወይም “come Peter into work?” ሊሆን ይችላል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የምንባቡን ዐውድ በሚገባ በማስተዋል ይህንን ዓይነት ስህተት ከመፈጸም ተቆጥበዋል። ሆኖም ሥርዓተ ነጥቦችን አስመልክቶ ግን የተፈጸሙ ግድፈቶች እንዳሉ ይህ የሉቃስ 23፡43 ጥቅስ አንዱ ማስረጃ ነው። (በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜው ቅጽ 1 ቁጥር 1 ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቶበታል)።
በመሆኑም ጥያቄው ላይ ያለው ጥቅስ ውስጥ የተካተተው ድርብ ሰረዝ በሐዋርያው ሉቃስ የተፃፈ አይደለም ማለት ነው። ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የድርብ ሰርዙን ቦታ በመቀየር ጌታ ለማርያም ከተናገራት ነገር ጋር የሚጣጣም ዓረፍተነገር ማግኘት ይቻላል። የጥቅሱ እውነተኛ አቀማመጥ የሚከተለው ነው፤ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ (አሁን ተሰቅዬ ሳለሁ)፤ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።” ጌታ ክርስቶስ ለሌባው ሊያረጋግጥለት የፈለገው ነገር “ዛሬውኑ” ገነት እንደሚገባ ሳይሆን የመዳኑ ጉዳይ “ዛሬውኑ” ወይም በዚያው ቀን እርግጠኛ መሆኑን ነው። ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ጌታችን በስቅለተ አርብ ዕለት ሲሞት ሁለቱ ሌቦች ግን ገና ስላልሞቱ ጭናቸውን ሰብረው ከመስቀል እንዳወረዷቸው ዮሐንስ 19፡30-33 ላይ እናነባለን። በወቅቱ አዲስ ኪዳን ከተጻፈበት ሁኔታ በተጨማሪ ሌባው አርብ ዕለት አለመሞቱ በዚያን ቀን ገነት ላለመግባቱ ሌላው ማስረጃ ነው። መቼም ገነት ገብቷል ብሎ ለማመን ቢያንስ መሞት ይጠበቅበታል።
ታዲያ ሌባውና ሌሎች አምነው የሞቱ ሰዎች የሚነሱት መቼ ነው?
በክርስቶስ አምነው ስለሞቱ ሰዎች መነሳት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፤ “በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህን ነው፤ እኛ በሕይወት ያለንና ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን” (1ተሰ. 4:15-17)።
መፅሐፍ ቅዱስ ሞትን በእንቅልፍ ይመስለዋል። ለምሳሌ ስለ ዳዊት ሞት ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ” (1ነገ. 2:10)። በዚህ ምክንያት ጳውሎስም “ያንቀላፉት” ብሎ የሚጠራው ሟቾችን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። እንደ ሐዋርያው አገላለፅ አምነው የሞቱ ከሞት እንቅልፍ የሚቀሰቀሱበት ታላቅ የትንሳኤ ቀን ይመጣል። ያ ጊዜ ጌታ ከሰማይ የሚወርድበት መሆኑን ይነግረናል። ያኔ ነው ክርስቶስን አምነው የሞቱት ተነስተው በሕይወት ጌታን ከሚቀበሉት ጋር በመሆን ወደ ሰማይ የሚነጠቁት። ነፍሳቸው ሳትሞት ከእነርሱ ተለይታ የነበረች ከሆነ ታዲያ ትንሣኤ ለምን ያስፈልጋል?
ይህ ከሆነ ሙታን አሁን የት ናቸው?
ሙታን እንደ ሕያዋን አለመሆናቸውን መፅሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና” (መክ. 9:5)።
በተጨማሪ ሙታንን አስመልክቶ ቃሉ እንዲህ ይላል፤ “ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ፣ ፈጣሪህን አስብ።” (መክ. 12:7) ይህ ጥቅስ እንደሚጠቁመው ሰው ሲሞት ዐፈር (አካሉ) ወደ መሬት፣ መንፈሱ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄድ ነው።
መንፈስ ምንድነው?
መንፈስ ከሥጋ ተለይቶ ሕያው ሆኖ የሚኖር ነገር አይደለም። ቃሉ እንደሚለው “ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ. 2:26)። ሰው ውስጥ ስላለው መንፈስ ምንነት ቃሉ ሲተነትን እንዲህ ይላል፤ “በውስጤ የሕይወት እስትንፋስ፣ በአፍንጫዬም ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እስካለ ድረስ …” (ኢዮብ 27:3)። ይህ የሚያሳየው መንፈስ የተባለው ነገርና የሕይወት እስትንፋስ አንድ መሆናቸውን ነው።
የሕይወት እስትንፋስ ከአምላክ የተቀበልነው ስጦታ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” (ዘፍ. 2:7)። ጌታ እፍ ያለው ነገር በራሱ የሚያስብና የሚንቀሳቀስ የሰው ምናብ ወይም ማንነት አለመሆኑ ግልፅ ነው። ፍጥረት የሚያሳየው የምድር አፈርና የአምላክ እስትንፋስ ሰውን “ሕያው ነፍስ” እንደሚያደርጉት ነው። እስትንፋስና አካል የነፍስ ወይም የሰው ኅልውና መሥራቾች ናቸው። ተለያይተው የግል ኑሮ አይኖሩም፤ አንድ ህያው ሰው ማለት አንድ ነፍስ ነው። ከመንፈስ የተለየ አካል (ሥጋ) ሙት ነው። (በዚህ ጉዳይ በተለይ ዘፍ. 2፡7 ላይ ስለተጠቀሰው ጊዜው መጽሔት ቅጽ 1፤ ቁጥር 2 ከገጽ 26-28 ባለው ክፍል የተሰጠውን ሰፋ ያለ መረጃ ማንበብ ይጠቅማል)።
ነፍስ ይሞታል?
“ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” (ሕዝ 18:20)። ከላይ እንደተመለከትነው “ነፍስ” ማለት ሰው ነው፤ ስለዚህ ሰው ሟች ነው፤ ይሞታል። የማይሞተው እግዚአብሔር ብቻ ነው። “እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን” (1 ጢሞ 6:16)።
ስለዚህ በስቅለት ቀን ጌታን ያመነው ሌባ እስከ ትንሳኤው ቀን ሕያው አይሆንም ማለት ነው?
አዎ። እርሱ ብቻ ሳይሆን በቅድስና ኖረው የሞቱ ሁሉ እስከ ታላቁ ትንሣኤ ቀን ከሞት አይነሱም። እነዚህ ቅዱሳን በዚያ ቀን በትንሳኤ የሚነሱት ሟች አካል ይዘው ሳይሆን ዘላለማዊ ሆነው ነው። “ይህም የሚሆነው የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ድንገት በቅጽበተ ዐይን ነው። መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ “ሞት በድል ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል” (1ቆሮ. 15:52-54)።
እንደዚያ ከሆነ በሉቃስ 16:19-31 ላይ ያለው ምሳሌ ያልዳኑ ሙታን በሲኦል እሳት እየተሰቃዩ መሆኑን አያስተምርም?
አያስተምርም፤ በሉቃስ 16:19-31 ላይ ያለው ምሳሌ በሕይወት ሳለ በድሃ ባልንጀራው ላይ ይጨክን ስለነበረ ሃብታም ሰው ነው የሚናገረው። ይህ ሃብታም ሰው ሲሞት በገሃነም እሳት መሰቃየት ጀመረ። በአንፃሩ ደግሞ ድሃ ባልንጀራው ሲሞት በአብርሃም ጉያ በምቾት ተቀመጠ። ይህ በእግርጥ የተከሰተ ሳይሆን ምሳሌ ነው።
ጌታ ክርስቶስ ነገሮችን በምሳሌ የመናገር ባህርይ ነበረው። ለምሳሌ “እውነተኛው የወይን ተክል እኔ ነኝ፤ አትክልተኛውም አባቴ ነው” ብሏል (ዮሐ 15:1)። ይህን ቃል አንብቦ መድኃኒዓለምን ፍለጋ ወደ ወይን እርሻ የሚሄድ የዋህ የለም። አባቱም ቢሆን በየቀኑ እንደምናያቸው ዓይነት አትክልተኞች አለመሆኑ ግልፅ ነው።
ነገር በምሳሌ እንዲባል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፉት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ዋና ዓላማ ሰዎች በሚረዷቸው ነገሮች አዳዲስ ትምህርቶችን በቀላሉ ለማስተማር ሲባል ነው። ሰዎች የወይን ግብርናን ያውቁ ስለነበር ጌታ ክርስቶስ ማንነቱን በወይን ግንድ አማካይነት ገለፀ። ቅርንጫፎች በወይን ግንድ ላይ ተደግፈው ፍሬያማ እንደሚሆኑ ሁሉ እኛም ጌታችንና መድኃኒታችንን ተደግፈን የባህርይ ለውጥ ምስክር የሆኑትን የቅድስና ፍሬዎች እናፈራለን። ገበሬ የወይን አትክልቱን እንደሚገርዝና እንደሚኮተኩት እኛንም እግዚአብሔር እየቀጣ ወደ ቀናው መንገድ ያደርሰናል። የምሳሌው ትምህርት ይህ ነው።
ሉቃስ 16 ላይ ያለው ምሳሌም በዚሁ መንገድ ሊታይ ይገባል። ዋና ትኩረታችንን መሳብ ያለበት ከምሳሌው ጀርባ ያለው ትምህርት ወይም ምሳሌው የተጻፈበት ዐውድ እንጂ ትምህርቱ የተላለፈበት ምሳሌያዊ አነጋገር አይደለም። ይህ ምሳሌ በተጻፈ ጊዜ የነበረው ዋንኛ አስተምህሮ ሰው ደሃ የሚሆነው ስለተረገመ ሃብታም የሚሆነው ደግሞ ስለተባረከ ነው የሚል ነበር። ምዕራፉን ከቁጥር አንድ ጀምሮ ቢያነቡ ዋናው ዐውድ ይህንኑ የሚስተምር እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል።
ጌታ ክርስቶስ በዚያ ምሳሌ አማካይነት ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምድራዊ ሀብትና ዝና በቅድስና ካልተያዘ በፈጣሪ ዘንድ ክብር እንደሌለው ነው። በአንፃሩ ምስኪን ድሃ ሆኖ በምድር ክብር የተነፈገ አማኝ ሁሉ በአምላክ ዘንድ ታላቅ ክብር እንዳለውና ለአብርሃም የተሰጠው ክብር እንደሚጠብቀው ይጠቁማል።
ከዚህ ሌላ በዚህ ምሳሌ የተጠቀሰውን ትክክል እንደሆነ አድርገን የምንወስድ ከሆነ ቁጥር 22 ላይ “ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት” እንዲሁ በቀጥታው መውሰድ አለብን። ይህ ደግሞ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል፤ በአብርሃም ዕቅፍ ውስጥ ስንት ሰው ነው መግባት የሚችለው? ወይም አብርሃም ስንቱን ነው ማቀፍ የሚችለው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። “የአብርሃም ዕቅፍ” ምሳሌ ነው ካልን ሌላውንም ጉሳይ በምሳሌነት ላለመውሰድ ምክንያት የለንም።
በተጨማሪ በራዕይ 14:11 ላይ ስለ ሙታን ሲናገር “የሥቃያቸውም ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ወደ ላይ ይወጣል። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ ወይም የስሙንም ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም” የሚለው ሙታን በስቃይ እንደሚኖሩ አያሳይም?
ከዚህ ጥቅስ የአገላለፅ ዘይቤ ጋር የሚመሳሰል ጥቅስ በይሁዳ መፅሐፍ ላይ በሚከተለው መንገድ ቀርቧል፤ “እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል” (ይሁዳ 7)።
ሰዶሞና ገሞራ ከጠፉ ከሶስት ሺህ ዓምታት በላይ ተቆጥረዋል። እንዴት ነው ታዲያ አሁንም ድረስ “በዘላለም እሳት እየተቀጡ” ነው ማለት የሚቻለው? እግዚአብሔር በሰዶም ላይ የወሰደው እርምጃ ዘላለማዊ ውጤት ያለው ነው። ሟች ሁሉ ያለ ተስፋ ወደ መቃብር አይወርድም። በጌታ ክርስቶስ የሚያምኑ ከሞት ይነሳሉ። ከኃጢአት አንላቀቅም ብለው መዳንን ችላ ያሉ ግን መመለሻ በሌለው ዘላለማዊ ሞት ውስጥ ይቆለፋሉ።
የሰዶምና ገሞራ ከተሞች ዛሬ በጥፋት እሳት እየነደዱ አይደለም። አንዴ ተቃጥለው ጠፍተዋል። ቢሆንም “በዘላለም እሳት እየተቀጡ ለሚሰቃዩት ምሳሌ ሆነዋል”። ይህ ማለት የሰዶምና የገሞራ እልቂት የማይሻር እንደመሆኑ ሁሉ ወደፊት በእሳት የሚቀጡትም ተቃጥለው ሲያልቁ ውጤቱ ዘላለማዊ ይሆናል ማለት ነው።
በራዕይ ላይ የተጠቀሰው እሳት ምንነት እዚያው መፅሐፍ ውስጥ ተፈቷል፤ “ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው” (ራዕይ 20:14)። በጥቅሱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በእሳቱ ሞትና ሲኦልም እንደሚቃጠሉ ተፅፏል። ይህ ማለት ሞት፣ ሲዖል እና ስቃይ ለዘላለም አይኖርም ማለት ነው። ሰይጣንና ተከታዮቹ ለዘላለም እየተሰቃዩ ሞትና ሲኦል ተቃጥለዋል ማለት ፈጽሞ አይቻልም።
በተጨማሪ ጌታ እንዲህ ይላል፤ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና” (ራዕ 21:4)። በአዲሱ ሰማይና ምድር ድብቅ የስቃይ ጓዳ አይኖርም። ተፈጥሮ ሁሉ ከጣዕርና ከሞት የፀዳ ይሆናል። ይህ ሊሆን የሚችለው ሰይጣንና ግብረአበሮቹ ለዘላለም ሲጠፉ፤ ከመኖር በፍፁም ወደ አለመኖር ሲሄዱ ነው። ለዘላለም መቃጠል ማለትም ይኸው ነው፤ ለዘላለም አለመኖር፤ ፍጹም ተቃጥሎ መጥፋት ማለት ነው።
“ነፍስ አትሞትም” የሚለው ፅንሰ ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ እንዴት በክርስትናው ዓለም ተቀባይነትን አገኘ?
ሰው በተፈጥሮው ሞትን መቀበል አይፈልግም። ሕልምና ተስፋው ከተቀበሩ ወዳጆቹ ጋር መገናኘትና መነጋገር ነው። ይህ ስለሆነ ከጥንት ጀምሮ በዓለም ያሉ ኃይማኖቶችና አምልኮዎች ከሞት በኋላ ባለው ተስፋ ላይ ያጠነጥናሉ። በጥንት ዘመን የግብፅ ነገሥታት ሲሞቱ ነፍሳቸው ከሥጋ ተነጥሎ ወደ አዲስ ኑሮ እንደሚሸጋገር ያምኑ ነበር። ለዚህም ሽግግር ታላቅ ዝግጅት ይደረግ ነበር። እንዲሁም በእስያ ያሉ ሂንዱዎች፣ ቡዲስቶች፣ ዳዊስቶችና ሺንቶዎች ከሞት በኋላ ነፍስ ከሥጋ ተነጥሎ ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲሻገር ብዙ ትግልና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያስተምራሉ። በአገራችንም ያሉ አንዳንድ መናፍስት ጠሪዎች ከሙታን ጋር መነጋገር እንደሚችሉ ይታመናል።
በምዕራቡ ዓለምም ይህ ከመፅሐፍ ቅዱስ የራቀ አስተሳሰብ በግሪክ ፈላስፎችም ሲስተጋባ ቆይቷል። ነፍስ ቅዱስ፤ ሥጋ ደግሞ ክፉ ስለሆኑ ነፍስ ነፃ መውጣቱ ተገቢ ነው ብለው ያምኑ ነበር። በአጠቃላይ የነፍስ ዘላለማዊነት ዓለማቀፋዊ፣ ሥር የሰደደና ጥንታዊ እምነት ነው። ከዚህ የተነሳ ግብፃዊያንና ግሪኮች የክርስትናን እምነት ሲቀበሉ ይህንን ባዕዳዊ አስተሳሰብ እንደተሸከሙ ተጠመቁ፤ ወደ ክርስትና ይዘውት ገቡ። በፊትም ከሰዎች ምኞትና ፍልስፍና ጋር የተጣጣመ ስለነበር ወደ ክርስትና ሰርጎ ሲገባ ብዙ ተቃውሞ የገጠመው አይመስልም።
ሆኖም እውነት በሰዎች ፍላጎትና ጥንታዊ ፍልስፍናዎች የሚወሰን አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሞት የሚናገረው እውነት ለትዕቢተኛው ልባችን መራራ ነው። ገና ከውልደታችን ጀምሮ እጅግ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶችን ስንሰማና ስንማር ስለቆየን እውነተኛውን ትምህርት ለመቀበል ሊያዳግት ይችላል። ሆኖም መታወቅ ያለበት ዋንኛው ጉዳይ “የክፉ ሰው ነፍስ ለዘላለም እየተቃጠለች ትኖራለች” የሚለው አስተሳሰብና አስተምህሮ ከአፍቃሪ አምላክ ባህርይ ጋር ፈጽሞ የሚጣጣም አለመሆኑ ነው። በእርግጥ አፍቃሪው አምላካችን ሰዎችን ለዘላለም በማቃጠል የሚደሰት ነውን? ይህ ዓይነቱ የሰው ልጅ እንኳን ሊፈጽመው የማይችለው ጭከና እንዴት ነው ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን ሁሉ የወደደው እግዚአብሔር ዘንድ ሊኖር የሚችለው? እንዴት ነው አንድ ሰው በአማካይ በህይወት በሚኖራት 60 እና 70 ዓመት ለሠራው መጥፎ ሥራ ለዘላለም በመቃጠል የሚቀጣው? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በመጠየቅ ይህን ወሳኝ ጉዳይ በጥልቀት እንዲመረምሩ ልናሳስብዎ እንወዳለን። በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ተጨማሪ ጥያቄዎች ካለዎት ከአድራሻችን በአንዱ ይላኩልን።
ድርባ ፈቃዱ