giziew.org

መጽሐፍ ቅዱስ እና ታሪኩ ፩

መጽሐፍ ቅዱስ ከየት መጣ? በምን ቋንቋስ ተጻፈ? የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ዛሬ የት ይገኛሉ? ... ይህ ተከታታይ ጽሑፍ ምላሽ ይሰጣል
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

እንደ መነሻ

አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ጥያቄዎች ጠይቀን የምናገኘው ምላሽ ሊያስገርመን ወይም ሊያስፈግገን ይችላል። ለምሳሌ ከተማ ተወልደው ያደጉ ልጆችን “ወተት የሚገኘው ከየት ነው?” ብለን ብንጠይቃቸውና “ወተትማ የሚገኘው ከሱቅ ነው፤” ብለው ቢመልሱ በአግራሞት ፈገግ ሊያሰኘን ይችላል። መልሳቸው ግን እውነታ አለበት ምክንያቱም ለነዚህ ልጆች ላም ያሳያቸው ስለሌለ የወተትን መገኛ የሆነችውን እንስሳ እንዲዘነጉ አድርጓቸዋል። ሆኖም በእነዚህ ልጆች ምላሽ ልንፈርድ አንችልም፤ ምክንያቱም ካልተማሩ ሊያውቁ አይችሉም።

በተመሳሳይ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ከየት መጣ? ከሰማይ ወረደ? የስሙስ ትርጉም ምን ማለት ነው? መጀመሪያ የተጻፈው በምን ላይ ነው? በወረቀት? በቅጠል? በቆዳ? የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ዛሬ የት ይገኛሉ? ከዘመን ዘመን እጅግ በርካታ ዓመታትን አልፎ እንዴት በዚህ ዘመን በእጃችን ላይ ለመገኘት ቻለ? በምን ቋንቋስ ተጻፈ? ከጥፋትስ እንዴት ተጠበቀ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት 66ቱ መጻህፍትስ እንዴት ተሰባሰቡ? ወዘተ ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምን ይሆናል? እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች በዚህ መሰሉ መጣጥፍ በብቃት ለመመለስ አስቸጋሪ ቢሆንም ካሁን ጀምሮ በምናቀርበው ተከታታይ ጽሁፍ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን።

ባለንበት ዘመን በኮምፒውተር ወይም በስልካችን ላይ በቀላሉ ጠቆም በማድረግ በፍጥነት ከፈት አድርገን የምናነበው መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንት ከአፈጣጠሩ ወይም ከአዘገጃጀቱ ብዙ የሚገርሙ ሂደቶችን ያለፈ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች በፓፒረስ (ከደንገል በተሠራ ወረቀት) ከዚያም በብራና ላይ የተፃፉ ሲሆን ይህም የወረቀት መገኘት ከቻይና ወደ መካከለኛው ምስራቅ እስከመጣበት መካከለኛው ዘመን ድረስ የቀጠለ ልምድ ሆኖ እናገኘዋለን።

በጥንት ዘመን መልዕክት እንዴት ይተላለፍ ነበር?

ቀደም ባሉት ዘመናት መልዕክትን በጽሑፍ ማስተላለፍ ከመጀመሩ በፊት መልዕክቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉት በቃል ወይም በንግግር ነበር።  ይህ የግንኙነት መንገድ ምንም ያህል ጥንቃቄ ቢደረግበትም መልዕክቱ ከሰው ሰው እየተላለፈ ሲሄድና ዘመናት ሲቆጠሩ የመጀመሪያው የቃል (የንግግር) ይዘት ለመቀየርና ለመዛባት የተጋለጠ ነበር። ይህንን ለማረጋገጥ ያለ ቤተሙከራ ምርምር ሰዎች በተሰባሰቡበት ቦታ አንድን ዘገባ በቃል (በንግግር) በማስተላለፍ ብዙም ሳይቆይ እንዴት ተለውጦና ተጣምሞ የመጨረሻው ሰው ዘንድ እንደሚደርስ ለማወቅ ብዙዎቻችን የሚያዳግተን አይደለም። ደቀመዛሙርት እንኳን ጌታ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል በደንብ ሳያዳምጡ፤ የተናገረውን በስህተት አስተውለው ስህተተኛ መልዕክት እንዳስተላለፉ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ቁጥር 23 ላይ ተጽፎ እናገኛለን። በዚህም ምክንያት በአፈታሪክ ወይም በቃል የሚተላለፍ መልዕክትን ለማመን አስቸጋሪ ሆኖ እናገኘዋለን። በተቃራኒው በጽሑፍ የሚተላለፍ መልዕክት ግን እንደ ቃል መልዕክት የመዛባት ችግር ሳይገጥመው የተፈለገበት ቦታ የመድረስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ሳይጣመም በትክክል የመድረስ አቅም አለው፤ ደግሞ ደጋግሞም በተላለፈ ቁጥር ሳይዛባና ሳይበረዝ ወጥነቱን ጠብቆ በመተላለፍ ረገድ ከአፈታሪክ ይልቅ በእጅጉ የበለጠና የተሻለ ነው።

በእርግጥ እግዚአብሔር መልዕክቱን በመላዕክት ሊነግረን ይችል ነበር፤ ለነብያቱም እንደሚናገረው በራዕይና በህልም፣ በድምጽና ተዓምራዊ በሆኑ መንገዶች ሊገልጽልን ይችላል። እነዚህን መንገዶችን ግን አልተጠቀመም። ከዚህ ሁሉ ይልቅ በላቀ ሁኔታ በጽሑፍ የሚተላለፍ መልዕክት ግልጽና ያልተዛባ በመሆኑ ተዓማኒነቱን የበለጠ ከፍ ስለሚያደርገው ይህንን መንገድ ነው የተጠቀመው። ይህም ዘዴ መልዕክትን ለትውልድ አቆይቶ ለማስተላለፍ ከሁሉ የበለጠ ተመራጭ አድርጎታል።

መጽሐፍ ቅዱሳችን በዕብራውያን 1፡1 ላይ እግዚአብሔር “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና” ከጥንት ጀምሮ ሲናገር እንደነበር ያስረዳል። እንግዲህ ከአዳም እስከ ሙሴ በነበረው ዘመን መልዕክት በአብዛኛው በቃል ይተላለፍ የነበረበት ሲሆን ሃሳብን በጽሑፍ ማስተላለፍ ከተቻለ በኋላ ግን ሙሴ (1400 ከልደት በፊት ወይም ዓ.ዓ.) ከእግዚአብሔር የተላከልንን መልዕክት ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሁፍ ያስተላለፈ ሰው ሆኖ እናገኘዋለን።

መጽሐፍ ቅዱስ ስሙን ከየት አገኘ?

ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስሙን ያገኘው ከየት ነው? በአማርኛ “መጽሐፍ ቅዱስ”  በእንግሊዘኛ “ሆሊ ባይብል” (Holy Bible) የሚለው ስያሜ እንዴት እንደተሰጠ ለማወቅ ብዙም የሚያስቸግር አይደለም። በተለይ የእንግሊዝኛው “ባይብል” የሚለው ቃል የመጣው ላቲንኛው ከግሪክ ከወሰደው “ቢብልዮን” (biblion) ከሚለው ቃል ነው። ስያሜውም በፓፒረስ (ከደንገል በተሠራ ወረቀት) ላይ ለተጻፉ ጥቅልል ጽሑፎች ከተሰጡ ስያሜዎች መካከል አንዱ ሲሆን ትርጉሙም “መጽሐፍ” ማለት ነው። ይህ ደግሞ በአማርኛ ለመጽሐፉ ከተሰጠው ስያሜ ጋር ይስማማል። ፓፒረስ በጥንት ዘመን ጽሑፍን ለመፃፊያ የሚያገለግል ጥቅል የሚዘጋጅበት በግብጽ አገር በናይል ወንዝ አካባቢ የሚገኝ ተክል ነው። እነዚህ የፓፒረስ ተክሎች ግንዳቸው ተፍቆ ከተዘጋጁ በኋላ ተቀጣጥለው በጥቅል መልክ ለጽሑፍ መፃፊያነት በተፈለገው ርዝመት ይዘጋጃሉ። ጽሑፍ ከተጻፈባቸው በኋላም አንባቢው በአንድ እጁ የጥቅልሉን እጀታ ይዞ በሌላው እጁ ደግሞ ጥቅሉን እየተረተረ ያነባቸዋል። ታዲያ በግሪክ እንደዚህ አይነት የጽሑፍ ጥቅል “ቢብልዮን” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ትርጉሙም ጥቅልል ጽሑፍ ወይም ጥቅል መጽሐፍ ማለት ነው።

ሰብዓ ሊቃናት ወይም “ሴፕቱአጀንት (Septuagint)” (250 ዓዓ) በመባል የሚታወቀው ከእብራይስጥ ወደ ግሪክኛ የተተረጎመው ብሉይ ኪዳን ውስጥ፤ በዳንኤል 9፡2 ላይ “እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ” በሚለው ጥቅስ “በመጽሐፍ” በሚለው ቃል ፈንታ “ቢብሊያ” የሚለውን የግሪክ ቃል የተጠቀመበት ምክንያት ለዚህ ነው። ስለዚህ ግሪክ ተናጋሪ የነበሩት ክርስቲያኖች የአዲስና የብሉይ ኪዳን መፃህፍትን “ቢብሊያ” በማለት በመጥራታቸው ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛ “ባይብል” የሚለውን ስም እንዲይዝ አድርጎታል። ከዚህም ሌላ ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ይኖር የነበረ ክሊመንት የተባለ የሮም ቤተክርስቲያን ጳጳስ በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎችን “ቢብሊያ” በማለት እንደጠራቸው የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ።

ቅዱሳችን ውስጥ “ቢብሊያ” ከሚለው አጠራር ውጪ ሌሎች ስያሜዎችንም እናገኛለን። ከነዚህም ውስጥ በተለይ ተመሳሳይነት ያላቸው ሁለት የግሪክ ቃላት አሉ። እነርሱም “ሐይ ግራፋይ – hai graphai” (ማቴዎስ 21፡42፣ ማርቆስ 14፡49፣ 2ኛ ጢሞቲዎስ 3፡16፣ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡16ና ሮሜ 1፡22) እና “ታ-ሄራ ግራማታ – ta-hiera grammata” 2 ጢሞቲዎስ 3፡15 የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ሁለት የግሪክ ቃላት “ጽሑፎችና ቅዱሳን ጽሑፎች” ተብለው በቅደም ተከተል ሊተረጐሙ ይችላሉ። ስለዚህ የአማርኛችንም “መጽሐፍ ቅዱስ” የሚለው ስያሜ ከዚህ እንደተገኘ መገመት አያስቸግርም።

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዓላማ

እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተዘግቦ የሚገኘው መገለጥ ስለ ፈጣሪ አምላካችን የበለጠ እውቀት እንዲኖረንና ሕጉንና ስርዓቱን ለመታዘዝ ትልቅ ኃላፊነት እንዲሰማን የሚደርግ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችንን እንደ ታላቅ ስነጽሑፍ ወይም የእስራኤልንና የቀደመችው ቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚዘግብ የታሪክ መጽሐፍ ወይም ስነ መለኮታዊ ይዘት እንዳለው ጽሑፍ ብቻ በመመልከት ልናነበው እንችል ይሆናል። ነገር ግን የተፃፈበት ዓላማ ከዚህ በላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ስለ እግዚአብሔር ሊገልጥልንና ሕይወታችንም ከእርሱ ጋር በሚኖረን ሕብረት እንዲለወጥ ለማድረግ ነው። 2ኛ ጢሞቲዎስ 3፡15-16 መጽሐፍቱ የተጻፉበትን ዓላማ በመዘርዘር እግዚአብሔርን በመታዘዝ እንድንኖር ያደፋፍረናል። ከዚህ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ የተባሉትን የሰው ልጆችን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ የመመለስ ታላቅ ዓላማ እንዳለው ለመገንዘብ እንችላለን።

ሰዎች ሃሳባቸውን በጽሑፍ መግለጽ ከመቻላቸው በፊት መረጃ የሚተላለፈው በቃል ወይም በንግግር እንደነበር ቀደም ብለን ጠቅሰናል። የሚተላለፈው መረጃ ትክክለኛነት በመልዕክት አቅራቢው የማስታወስ ችሎታ ላይ የሚወሰን ነበር። ነገር ግን ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳቸውን በትክክል በጽሑፍ ለመግለጽ እንዲችሉ የተለያዩ ዘዴዎችን ፈልስፈዋል፤ ለምሳሌ ስዕልን ተጠቅመዋል። አንዳንድ ድምጾችንና ሃሳቦችን ከተራ ስዕል ጠንከር ባሉ አገላለፆች ለማስረዳት ሲሉ ሥዕላዊ አጻጻፍን (Pictograms) እና እንደ ጃፓንና ቻይና ፊደላት ያሉ (Logograms) ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

በመቀጠልም አንዳንድ ድምጽን ሊወክሉ የሚችሉ ምልክቶችን (Syllabic writing) ፈጥረዋል። በመጨረሻ ግን ሃሳባቸውን ሊገልፁ የሚችሉበት ፊደላት (alphabets) በመፍጠር ጥልቅ የሆኑ ሃሳቦችን እንኳ ሳይቀር ፊደላቱን በማገናኘት መግለጽ ችለዋል። በዚህም ፈጠራ አማካኝነት አንድ ፊደል አንድን ድምጽ እንዲወክል አድርገዋል። የእግሊዝኛው ፊደል ወይም “አልፋቤት” ከግሪኩ “አልፋ፣ ቤታ” ወይም ከፊኖሺያውኑና ከዕብራውያኑ “አሌፍ፣ ቤት” ከሚሉት የመጀመሪያ ሁለት ፊደላት ጥምረት የተጠፈረ ነው። ሰዎች መናገር የሚፈልጉትን፤ በአእምሯቸው ውስጥ ያለውን ሃሳብ ሌሎች እንዲገባቸው አድርገው በእነዚህ ፊደላት በመጠቀም ራሳቸውን መግለጽ መቻላቸው ስለለመድነው ምንም ላይመስለን ይችላል እንጂ እጅግ የሚያስገርም ክስተት ነው! (ግሪክና ዕብራይስጥ 22 ፊደላት፣ እንግሊዝኛ 26፣ አማርኛ ከ250 በላይ ቻይንኛና ጃፓንኛ ከ1800 በላይ ፊደላት እንዳሏቸው ይነገራል።)

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ቋንቋ

መጽሐፍ ቅዱሳችን መጀመሪያ የተፃፈው በቻይንኛ ወይም በጃፓንኛ ፊደሎች ወይም ቋንቋ ሳይሆን በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክ ቋንቋ መሆኑንስ ያውቁ ኖሯል?

የብሉይ ኪዳን ሰላሳ ዘጠኙም መፃህፍት ሁሉም በሚያስብል መልኩ የተፃፉት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን የአዲስ ኪዳን ሃያ ሰባቱም መጻህፍት በግሪክኛ የተጻፉ ናቸው። ከብሉይ ኪዳን ውስጥ ጥቂት የሚባሉ ጽሑፎች በአረማይክ ቋንቋ ተጽፈው ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ትንቢተ ዳንኤል ከ2፡4 እስከ 7፡28፣ እዝራ 4፡8-16፣18 እና 7፡12-26 የተጻፉት በአረማይክ ነው። እስራኤላውያን ወደ ባቢሎን በምርኮ ከሄዱ በኋላ አረማይክ በዚያን ዘመኑ ፍልስጤም (ፓለስታይን) በሚገኙ ኗሪዎች መካከል የሚነገር ቋንቋ ስለነበር፤ አብዛኞቹ እስራኤላውያኖች ዕብራይስጥን ረስተው በአረማይክ ቋንቋ መጠቀም ጀመሩ። በዚህም ምክንያት በነህምያ 8፡8 እንደምናየው ሕዝቡ ቅዱሳት መፃህፍትን እንዲያስተውል ከእብራይስጥ ወደ አራማይክ ቋንቋ ይተረጎሙላቸው ነበር።

እንዲያውም ከእብራይስጥ ወደ አረማይክ የተተረጐሙ ጹሑፎች “ታርገም” በመባል ይታወቃሉ። ዕብራይስጥና አረማይክ አንድ አይነት ፊደላት የሚጠቀሙ ሲሆን አሁንም ጭምር በየመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ ፊደሎቻቸውን እናገኛለን። ለምሳሌ በመዝሙር 119 በቁጥር 1፣9፣17 ወዘተ ማለት ከእያንዳንዱ 8 ቁጥሮች በኋላ እነዚህ የእብራይስጥ ወይም የአረማይክ ፊደሎች ከ“አሌፍ” እስከ መጨረሻው “ታው” የተባለው ፊደል ድረስ 22ቱንም ተጽፈው እናገኛቸዋለን። በሰቆቃው ኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥም እነዚህኑ ፊደላት እናገኛለን። አንዳንድ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህ የሌላቸው ሊሆን ይችላል፤ አብዛኞቹ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ግን እነዚህ ፊደሎች ከነስሞቻቸው ይገኙባቸዋል።

ያለ አናባቢ፣ ያለ ክፍተትና ያለ ስርዓተ-ነጥብ

የመጽሐፍ ቅዱስን አጻጻፍ በተመለከተ ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ በተፃፈበት ዘመን የዕብራውያን ፊደል ምንም አይነት አናባቢ (vowels) ሳይኖረው መፃፉ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በቃላት መካከል ወይም በዓረፍተ ነገሮች መካከል ምንም አይነት ክፍት ቦታ ሳይኖር ግጥምጥም ብሎ (Scriptio continua or continuous script) መጻፉ ሌላው አስደናቂ ነገር ነው። ለምሳሌ ይህን አናባቢ የሌለውን በእንግሊዝኛ ፊደል የተፃፈ ጽሑፍ እንዴት ያነቡታል?   “CMPTRNTWRK” ይህ እንግዲህ “computer network” ወይም “come Peter into work?” ሊሆን ይችላል። በተጨማሪ ዮሐንስ 3፡16ን በእንግሊዝኛ ቃላት መካከል ምንም ክፍት ቦታ ሳይኖር ፊደላቱ እንደተገጣጠሙ ለማንበብ እስኪ ይሞክሩ።

FORGODSOLOVEDTHEWORLDHEGAVEHISONEANDONLYSONTHATWHOEVERBELIEVESINHIMSHALLNOTPERISHBUTHAVEETERNALLIFE

ለማመን ቢያስቸግርም የመጀመሪያው ብሉይም ሆነ አዲስ ኪዳናት የተጻፉት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ቃላቱ ተገጣጥመው ያለአንዳች ክፍተት ነበር። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ስርአተ ነጥብ አልነበራቸውም።

የብሉይ ኪዳን ሰላሳ ዘጠኙም መፃህፍት ሁሉም በሚያስብል መልኩ የተፃፉት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን የአዲስ ኪዳን ሃያ ሰባቱም መጻህፍት በግሪክኛ የተጻፉ ናቸው። ከብሉይ ኪዳን ውስጥ ጥቂት የሚባሉ ጽሑፎች በአረማይክ ቋንቋ ተጽፈው ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ትንቢተ ዳንኤል ከ2፡4 እስከ 7፡28፣ እዝራ 4፡8-16፣18 እና 7፡12-26 የተጻፉት በአረማይክ ነው። እስራኤላውያን ወደ ባቢሎን በምርኮ ከሄዱ በኋላ አረማይክ በዚያን ዘመኑ ፍልስጤም (ፓለስታይን) በሚገኙ ኗሪዎች መካከል የሚነገር ቋንቋ ስለነበር፤ አብዛኞቹ እስራኤላውያኖች ዕብራይስጥን ረስተው በአረማይክ ቋንቋ መጠቀም ጀመሩ። በዚህም ምክንያት በነህምያ 8፡8 እንደምናየው ሕዝቡ ቅዱሳት መፃህፍትን እንዲያስተውል ከእብራይስጥ ወደ አራማይክ ቋንቋ ይተረጎሙላቸው ነበር። እንዲያውም ከእብራይስጥ ወደ አረማይክ የተተረጐሙ ጹሑፎች “ታርገም” በመባል ይታወቃሉ። ዕብራይስጥና አረማይክ አንድ አይነት ፊደላት የሚጠቀሙ ሲሆን አሁንም ጭምር በየመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ ፊደሎቻቸውን እናገኛለን። ለምሳሌ በመዝሙር 119 በቁጥር 1፣9፣17 ወዘተ ማለት ከእያንዳንዱ 8 ቁጥሮች በኋላ እነዚህ የእብራይስጥ ወይም የአረማይክ ፊደሎች ከ“አሌፍ” እስከ መጨረሻው “ታው” የተባለው ፊደል ድረስ 22ቱንም ተጽፈው እናገኛቸዋለን። በሰቆቃው ኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥም እነዚህኑ ፊደላት እናገኛለን። አንዳንድ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህ የሌላቸው ሊሆን ይችላል፤ አብዛኞቹ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ግን እነዚህ ፊደሎች ከነስሞቻቸው ይገኙባቸዋል።

በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ውስጥ ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ በብዛት ይነጋገሩ የነበሩት በአረማይክ ቋንቋ ቢሆንም አዲስ ኪዳን የተፃፈው ግን በግሪክ ነው። ይህም የሆነው አብዛኛው ሕዝብ የሚገለገልበት ቋንቋ ግሪክ ስለነበር ነው። አልፎ አልፎ ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቂት የአረማይክ ቃላትን እናገኝበታለን። ስለዚህ ሃያ ሰባቱም የአዲስ ኪዳን መፃህፍት በግሪክ ቋንቋ የተፃፉ ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት በወቅቱ አብዛኛው ሰው የሚግባባበት ቋንቋ ግሪክኛ በመሆኑ በዚያው እንዲያነበው መፃፍ ስለነበረበት ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሁፎች በምን ላይ ነበር የተጻፉት?

በጥንት ዘመን ጽሑፎች የሚፃፉት በድንጋይ፣ በሸክላ ጡቦች፣ ለመጻፊያ በተዘጋጀ ፓፒረስ፣ በተፋቁ የእንሰሳት ቆዳዎች ወይም ብራናዎች፣ በእንጨት፣ በዝሆን ጥርስ፣ በስብርባሪ ሸክላዎች፣ በብረት ዕቃዎች ላይ ነበር። በመጨረሻ በእኛ ዘመን በወረቀት ላይ ሆነ። የአፃፃፍ ሂደቱ ደግሞ አብዛኛው ሰው በጥቂቱም ቢሆን መፃፍ የሚችል ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ደብዳቤዎች ወይም ጽሑፎች ግን የሚጻፉት ጥሩ መጻፍ በሚችሉ ፀሐፊዎች ነበር (በአገራችን የቁም ጸሃፊዎች የሚባሉትን ያስታውሷል)። አንዳንዶቹ መንደር ውስጥ የሚገኙ የግል ጸሐፊዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በክፍያ የሚሰሩ ጸሐፊዎች ነበሩ። በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ አማተር ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በክፍያ የሚሰሩ ፕሮፌሽናል ፀሐፊዎች ነበሩ ማለት ነው። 

ጸሐፊዎቹ በፓፒረስ ላይ በሚጽፉበት ጊዜ በፖፒረሱ ላይ የሚገኙትን መስመሮች ለጽሑፎቻቸው በሚያመች መልኩ ወደ አግድሞሽ አዙረው ፓፒረሶቹ ላይ በሚገኘው ተፈጥሯዊ መስመር በመከተል ጽሑፎቻቸውን ሳያንጋድዱ ይጽፋሉ። በብራና ሲጠቀሙ ግን ቀለም ባልነካው ሹል ነገር ጽሑፎቻቸው እንዳይንጋደዱ የሚረዷቸውን አግድም መስመሮች ያሰምራሉ በተጨማሪም ሁለት ወይም ሦስት አምድና ኅዳግ (margin) ለመስራት የሚያመቹ መስመሮችን ጽሑፍ ከመጀመራቸው በፊት ያዘጋጃሉ።

ይህ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ዘመን እየተለወጠ ሲመጣ፤ እነዚህ ከፓፒረስ ለመፃፊያነት የተዘጋጁ ቅጠሎች እርስ በርሳቸው ተደራርበውና ታጥፈው ሲሰፉ፤ ከጥቅሉ (scroll) በተሻለ እንደ ዘመናችን መጽሐፍ በሚመስል መልክ ተዘጋጅተው ቀረቡ። በተጨማሪ ከፓፒረስ ተክል ከተዘጋጁት ጥንታዊ የመጽሐፍ ጥቅሎች ይልቅ፤በተመሳሳይ መንገድ ከእንሰሳት ቆዳ ተፍቆ በሚሰራ ብራና ላይ መፃፍ አመቺ ሆኖ ተገኘ። ይህም አዲስ ግኝት በቀላሉ ከቦታ ቦታ ለማዘዋወርና ለረጅም ዘመን ለማገልገል ስለሚያስችል ተፈላጊ ሆነ። ስለዚህ ከፓፒረስና ከብራና የተዘጋጁት እነዚህ መጽሐፍት፤ በተለያዩ ሰዎች የተጻፉ ጽሑፎችን በአንድ ጥራዝ ለማድረግ በማስቻላቸው ተወዳጅነትን አተረፉ። ስማቸውም “የተጠረዘ የጥንት ጽሁፍ” “codex” በመባል ታወቀ፤ የመጻሕፍት አዘገጃጀትም ከጥቅልል ወደ ጥራዝ ተቀየረ። በተለይ ከብራና የሚዘጋጀው የጥራዝ ጽሁፍ (ኮዴክስ) አዲስ ግኝት በቀላሉ ጹሑፍን በፊትና በጀርባው ለመፃፍ ከማስቻሉም በተጨማሪ ረዘም ያሉ ጽሑፎችን ለመጻፍ ስላስቻለ ተመራጭ እየሆነ መጣ። በዚህ የጥራዝ አሠራር መነሻነትም የወረቀት ጽሁፍና ጥራዝ መነሻ በማግኘት እስከዘመናችን ድረስ በአገልግሎት ላይ የዋለ መገልገያ ለመሆን ችሏል።

ማስታወሻ፤ በዚህ በተከታታይ በምናወጣው ጽሁፍ የመጀመሪያ ክፍል በጥንት ጊዜ መልእክት እንዴት ይተላለፍ እንደነበር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስሙን ከየት እንዳገኘ፤ የተጻፈበት ዓላማ ምን እንደሆነ፤ የተጻፈበት ቋንቋ ምን እንደሆነና በምን ላይ እንደተጻፈ ጠቅለል ያለ ሃሳብ ለመዳሰስ ሞክረናል። በቀጣዩ ክፍሎች መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እኛ ለሚያደርሰው መልዕክት የተጠቀመባቸውን አራት ተያያዥ ሒደቶችንና ሌሎች ጉዳዮችን እንመለከታለን።

ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ

ለዚህ ጽሁፍ በዋቢነት የሚከተሉትን መጻሕፍት ተጠቅመናል፤

Paul D. Wegner, The Journey from Texts to Translations, Grand Rapids, Michigan Baker Academic 2004.

Norman L. Geisler and William E. Nix, A General Introduction

to the Bible Revised and Expanded, Chicago, Ill. : Moody Press, ©1968

Bruce M. Metzger, The Text of the New Testament, Its Transmission, Corruption, and Restoration, New York, Oxford: Oxford UP, 1992.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *