- በዚህ ምድር ላይ የመጀመሪያው የሰይጣን ውሸት ምንድን ነበር?
“እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም” (ዘፍ. 3፡4)። “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራዕይ 12፡9)። በኤድን ገነት ሔዋንን ያሳታት “እባብ” ተብሎ የተጠቀሰው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ራዕይ 12፡9 ተርጉሞታል። በወቅቱም ሰይጣን በእባብ ተመስሎ ለሔዋን ያላትና የመጀመሪያው ውሸት “አትሞቱም” የሚለው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን “ከፍሬዋ በበላችሁ ጊዜ ሞትን ትሞታላች” ብሎ ነበር። አሁንም ከዋንኞቹ የሰይጣንን ማሳሳቻ ትምህርቶች አንዱ “አትሞቱም” የሚለው ሲሆን ይህም ማለት ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ገነት ወይም ወደ ሲዖል ትሄዳለች፣ ነፍስ አትሞትም፣ ከሙታን ጋር እናገኛለን፣ ወዘተ የሚባሉት የክርስትናን ካባ የደረቡ ትምህርቶች ናቸው። (ለምሳሌ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማንበብ ይጠቅመናል፤ የግብፅ አስማተኞችና ጠንቋዮች—ዘፀ. 7፡11፤ በዓይንዶር የምትገኘዋ መናፍስት ጠሪ—1ሳሙ. 28፡3-25፤ የባቢሎን ጠንቋዮች—ዳን. 2፡2፤ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት አንዲት ሴት—ሐዋ.16፡16-18)።
ሰይጣን – እንደ ብርሃን መልአክ፤ ሰይጣንና መላዕክቱ እጅግ በርካታ ሰዎችን ለማታለል በፊት የሞቱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትን፣ ሐዋርያትንና ቅዱሳንን በመምሰል የብርሃን መልአክ መስሎ ይገለጻል፤ “…ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” (2ቆሮ.11፡13)። እንዲሁ በተዓምራት ሰዎችን ለመጥለፍ በረቀቀ መልኩ ሰይጣን ይጠቀማል። የተለያዩ በሽታዎችን “ፈውስ” አስመልክቶ “ተዓምራት” ከማድረግ ጀምሮ ሙታንን ያስነሳ እስኪመስል ድንቆችን ያደርጋል። በመሆኑም “ሙታን በሆነ መልኩ በሕይወት አሉ፤ ነፍሳቸው አልሞተችም” ብለው የሚያምኑ ሰዎች በእንደዚህ ዓይነቱ የሰይጣን ማታለያ ተጠልፎ ለመውደቅ በጣም ቅርብ ናቸው።
- ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?
“ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ፣ ፈጣሪህን አስብ” (መክብብ 12፡7)። እዚህ ላይ የምንረዳው ሰው ሲሞት አካሉ ወደ አፈር (መሬት)፣ እስትንፋሱ ደግሞ ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር እንደሚመለስ ነው፤ ይህ ክስተት የሚፈጸመው በዚህ ምድር ላይ በሚገኙ ኃጥአንም ሆነ ጻድቃን ላይ ልዩነት ሳያደርግ ነው። እዚህ ላይ በተጨማሪ ልብ ማለት ያለብን ከላይ የተጠቀሰውን “ሳይመለስ” የሚለውን ቃል ነው። ከቃሉ በምናገኘው መረዳት መሠረት ሞት ማለት ሁሉ ነገር ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ማለት ነው፤ ሞት ዐፈሩን (የሰውን አካል) ወደ መሬት፤ እስትንፋሱን ደግሞ ወደ ሰጠው እግዚአብሔር ይመልሳልና። ለምሳሌ በኬምስትሪ ትምህርት መሠረት ውሃ የሁለት እጅ ሃይድሮጅንና የአንድ እጅ ኦክስጅን ውህደት ውጤት ነው። እነዚህ ሁለት ንጥረነገሮች ሲዋሃዱ ውሃ ይፈጠራል፤ ሲለያዩ ደግሞ ውሃ አይኖርም። የሰውም በሕይወት መኖር የአምላክ እስትንፋስና የምድር ዐፈር ውህደት የፈጠረው ሲሆን ሰው ሞተ ስንል ደግሞ የእነዚህ ሁለት ነገሮች ተነጣጥለው ወደ መጡበት መመለስ ነው።
- ሰው ሲሞት ከእርሱ ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር የሚሄደው እስትንፋስ ምንድነው?
“ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ. 2፡27)። “በውስጤ የሕይወት እስትንፋስ፣ በአፍንጫዬም ወስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እስካለ ድረስ” (ኢዮብ 27፡3)። በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር ከሰው ወደ እግዚአብሔር የሚመለሰው መንፈስ የሕይወት እስትንፋስ ነው። ይህ እስትንፋስ ወይም መንፈስ ከአካል ተለይቶ የሟቹን ግለሰብ የሚወክል ጥበብ ወይም እውቀት ሆነ ስሜት ወይም ማንነት እንዳለው የሚያስረዳ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።
- ታዲያ ነፍስ ማለት ምን ማለት ነው?
ከላይ በተጠቀሰው ዘፍጥረት 2፡7 መሠረት “ነፍስ” ማለት የሕይወት እስትንፋስ ከአፈር ከተሠራው አካል ጋር ሲገናኝ የሚፈጠረው ሕይወት ያለው ፍጡር ነው። ይህ ነፍስ ወደ ኅልውና የመጣው እስትንፋስና አካል ተገናኝቶ ወይም ተደምሮ በመሆኑ ሁለቱ በተለያዩ ቀን የነፍስ ኅልውና ያከትማል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ “ነፍስ” ተብሎ እንደሚጠራ እናነባለን። በቀላሉ “አምስት ሰዎች” ያሉበት ቦታ “አምስት ነፍሳት” ያሉበት ሊባል ይቻላል።
- ነፍስ ይሞታል?
“ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” (ሕዝ. 18፡20)። “በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ” (ራዕይ 16፡3)። እንደ እግዚአብሔር ቃል አገላለጽ ነፍስ ይሞታል። ምክንያቱም የአምላክ እስትንፋስና የአፈር ውኁድ የሆነው ሰው ነፍስ ነው፤ ነፍስ (ሰው) ደግሞ ይሞታል፤ ስለዚህ ሰዎች ሁሉ ሟች ናቸው (ኢዮብ 4፡17)። የማይሞተው እግዚአብሔር ብቻ ነው (1ጢሞ. 6፡15፣16)። ይህ በመሆኑም ሰው ሲሞት ተለይታ የምትወጣ የዘላለማዊ ነፍስ (የማይሞት ነፍስ) አለች የሚለው ጽንሰሀሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።
- መልካም ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?
“በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” (ዮሐ. 5፡28፣29)። “ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። … ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና” (የሐዋ. 2፡29፣34)። ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይም ሆነ ወደ ገሃነም አይሄዱም። ይልቁኑ እስከ ትንሳዔ ቀን ድረስ በመቃብራቸው ሆነው እንደ ዳዊት የትንሣኤን ቀን ይጠብቃሉ።
- ሰው ከሞተ በኋላ ምን ያህል ያስተውላል?
“ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቷልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። … አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ” (መክብብ 9፡5፣6፣10)። “አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም፥ ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ” (መዝ. 115፡17)። በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ሙታን አንዳች አያውቁም።
- ሙታን ሕያዋን የሚሠሩትን ያውቃሉ? ከሕያዋን ጋር መገናኘት፣ መነጋገር ይችላሉን?
“ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም። … ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም” (ኢዮብ 14፡12፣21)። “ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም” (መክብብ 9፡6)። ሙታን በዚህ ምድር ላይ በሚፈጸመው ማንኛውም ነገር ላይ ተሳትፎ የላቸውም። ስለዚህ ማንኛውንም ሕያው ሰው አያናግሩም፤ በዚህ ምድር ላይ የሚፈጸምን አንዳች ነገር አያውቁም፤ ሃሳባቸው ሁሉ ጠፍቷል (መዝ. 146፡4)።
- ክርስቶስ ሞትን ዕንቅልፍ ይለዋል (ዮሐ.11፡11-14)፤ታዲያ ሙታን ለምን ያህል ጊዜ ያንቀላፋሉ?
“ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም” (ኢዮብ 14፡12)። “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ” (2 ጴጥ. 3፡10)። ሙታን በመቃብራቸው ውስጥ በእንቅልፍ የሚቆዩት ክርስቶስ ዳግም እስከሚመጣ ነው። እስከዚያ ድረስ ግን አንዳች የሚያውቁት ሳይኖር በመቃብራቸው ውስጥ ይቆያሉ፤ ያንቀላፋሉ። ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ የሞቱት ጻድቃን ይነሳሉ (1ተሰ. 4፡16፣17፤ 1ቆሮ. 15፡51-53)። ሙታን በትንሳኤ ቀን በማይሞት ሥጋ ይነሳሉ። ጌታን በአየር ላይ ለመገናኘት ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። እንግዲህ ሰዎች እንደሞቱ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ የትንሳኤን አስፈላጊነት ይህን ያህል አጉልቶ አይናገርም ነበር።
ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ