የሰማይ አባት ምድርን የፈጠረው በልጁ በክርስቶስ በኩል መሆኑን ሐዋርያው ዮሐንስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም።” (ዮሐ 1: 3) በስድስት ተከታታይ ቀናት ክርስቶስ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ድንቅ ነገሮች ሁሉ ፈጠረ (ዘጸ 20:11)።
ባማሩ ኮረብቶች መካከል ወንዞች ለስላሳ ድምፅ እያሰሙ እንዲፈሱና የፀሐይን ድምቀት እንዲያንፀባርቁ አድርጎ አስዋባቸው። ልዩ ልዩ የሣር ዓይነቶች፣ ያማሩ ሐረጎችና እንደ ሊባኖስ ዝግባ እጅግ ረጅም የሆኑ ዛፎች በኮረብቶች ላይና በወንዞቹ ዳር እንዲበዙ አደረገ። ዛሬ በማይገኙ ቀለማት የደመቁ አበቦችም በሣር ሜዳዎች ላይ ተነጠፉ። በፍሬዎቻቸው ብዛትና ክብደት ዝቅ ያሉ ቅርንጫፎች ያሏቸው ዛፎች አየሩን ጥዑም መዓዛ ሞሉት።
ከዛፍ ወደ ዛፍ በደስታ እያዜሙ የሚበሩ ወፎች ቀለማት ሰማዩን አደመቀው። በወንዞቹ ውስጥ በፍጥነትና በቀስታ የሚዋኙ ዓሳዎች ተንቦጫረቁ። የውቅያኖሶች ጥልቀት ደግሞ ሚስጥራዊ የአኗኗር ብልሃት ባላቸው ትንንሽና ትልልቅ የውሃ ፍጡራን ይጎበኝ ነበር። በምድር ላይም ያሉ ፍጡራን በእርካታ ተሞልተው ሲቦርቁ ተመልካች መላእክት ተደነቁ (ኢዮ 38:7)። በእርግጥ ድብ ሣር እየጋጠ በኮረብታ ላይ ሲንከባለል፣ አናብስት ከበጎች ጋር ተቃቅፈው ፀሐይ ሲሞቁ፣ ጥንቸሎች ከነብሮች ጋር ያለ ፍርሀት ሲጫወቱ ማየቱ ለፈጣሪ ጥበብ አዲስ የምስጋና ቅኔ እንዲፈልቅ ግድ ይል ነበር። “ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድርም ሐሤት ታድርግ፤ ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ያስተጋባ፤ መስኩና በላዩ ያለው ሁሉ ይፈንጥዝ፤ ያን ጊዜ የዱር ዛፎች ሁሉ በደስታ ይዘምራሉ፤ እርሱ ይመጣልና በእግዚአብሔር ፊት ይዘምራሉ” (መዝ 96:11-13)።
ክርስቶስ እነዚህን አስደናቂ ነገሮች በቃሉ ፈጥሮ ሲያበቃ በስድስተኛው ቀን ወደ መሬት ዝቅ ብሎ አፈር ዘገነ። አፈሩን በእጆቹ ቅርፅ አስያዘ። ቀስ በቀስ በክርስቶስ እጅ የተቀረፀው አፈር የረጅም መልከ መልካም ወጣት ሰውነት መሰለ። ክርስቶስ ወደሠራው የአፈር የሃውልት (ቅርጽ) ጠጋ ብሎ አፍንጫው ውስጥ ተነፈሰ።
የአፈሩ ሃውልት ተንቀሳቀሰ፤ ሰው ሆነ። “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍ 2:7) ሰው ውብ ዓይኖቹን ከፍቶ ፈጣሪውን ተመለከተ። ክርስቶስ አባቱ መሆኑን ተረዳ (ሉቃ 3:38)። ቀጥሎም በዙሪያው ያለውን ገነት ወደርየለሽ ማስተዋል በሞላው አእምሮው ቃኘ። ያየው ሁሉ የአባቱ ሥራ መሆኑን በደስታ ተረዳ። ክርስቶስም ምድርን ያስዋበው ለልጁ – ለአዳም – መሆኑንና በምድር ላይ ሊሾመው እንደሚፈልግ ነገረው።
ከአፈር የተሠራው ሰው የአምላክ ልጅ ሆነ። አስደናቂ ፍቅር ላሳየው አባት አዳም ምን ይመልስ? አዳም በፈጣሪው ፍቅር ተሞላ። አባቱን በደስታ በመታዘዝ የፍቅር ምላሹን ለማሳየት ተነሳሳ። ፍቅር ፍቅርን ወለደ።
የሰው አፈጣጠር የአምላክን ድንቅ ጥበብና ፍቅር ያሳያል። ክርስቶስ የሕይወትን እስትንፋስ በአዳምና በእኛ ውስጥ ያኖረው ስለምንጠቅምው ሳይሆን እኛ እንድንጠቀም ነው። ስለ እኛ ያስባል፤ ይጨነቃል። በዚህ ግሩም የፍቅር ጥበብ የተደነቀው ዳዊት እንዲህ ብሏል “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” (መዝ. 8:4)።
ክርስቶስና አዳም ገነትን መጎብኘት ጀመሩ። የፈጠራቸውን እንስሳት እያቀረበ አዳም ስም እንዲያወጣላቸው ጋበዘው። አዳም የአራዊቱን ባህሪይ እያጠና ገጣሚ ስሞች ሰጣቸው። በዚህ መሃል አዳም አንድ ነገር ታዘበ። የሰየማቸው እንስሳት ሁሉ የተቃራኒ ጾታዎች ጥንዶች እንደሆኑ ተገነዘቦ የኑሮውን ደስታና ሃብት በእኩልነት የምትጋራ በአጠገቡ አለመኖሯ ሲገርመው ፈጣሪ ፅኑ እንቅልፍ ጣለበት።
ክርስቶስ ካንቀላፋው አዳም ጎን አጥነት አውጥቶ ከጎኑ የምትቆም ሌላ ሰው ፈጠረ። ሔዋን ሕያው ሆነች። አዳም ሲነቃ ውበቷን አየ። አነጋገራት፤ አዳመጣት። የባህሪዋ ልስላሴና የአእምሮዋ ጥልቀት ማረከው። መግባባታቸው አስገረመው፤ እሷንም እንዲሁ። በስሜት፣ በሃሳብና በአካል አንድ የመሆን ፅኑ ፍላጎት አደረባቸው። ሔዋን ለአዳም አጥንቱም ሥጋውም እንደሆነች አስተውሎ ፈጣሪው ባቀደለት መንገድ አብሯት መኖር ጀመረ (ዘፍ 2:23-24)። አንድነታቸውም የመጀመሪያው ትዳር ሆነ።
በሰማይ ቅዱስ ነዋሪዎች መካከል ያለውን መተማመን በምድር እንዲታይ ክርስቶስ ጋብቻን ለሰዎች ሰጠ። ፍቅር በመስጠት ሕይወት እንደሚገኝ ለማስገንዘብ ሲል በወንድ እና በሴት መካከል በሚኖረው ግንኙነት ሰዎች እንዲወለዱ አደረገ። ይህ የማንነታችንና የመገኛችን ምሥጢር በክርስቶስ አባታዊ ፍቅር እንድናምንና እንድንመሰጥ ይጋብዘናል። አፈጣጠራችን ምን ያህል ድንቅ እንደሆነ ስንረዳ ደግሞ ከክርስቶስ የትዳር ፈቃድ ውጪ መሆን ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል በጥልቅ እንረዳለን።
ብዙ ሰዎች ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ ነው። የትዳር ትስስር አድጎ ባልና ሚስት ለወላጆቻቸው ካላቸው ፍቅር መብለጥ እንዳለበት አምላክ ያስተምራል። “ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍ 3:24) ትዳር ከዚህ አንፃር ሲታይ በዘመናችን ዋጋ ማጣቱን ምን እንለዋለን? አዳም ዛሬ በሕይወት ቢኖር የዘመኑን ጋብቻ እንዴት ያየው ይሆን? ወጣቶች በዝሙት እሳት ተቃጥለው በየማታው አዲስ “ፍቅር” ሲያሳድዱ የሚመለከተው የፍቅር አምላክስ እንዴት ያዝን ይሆን? ወንዶች ከወንዶች ጋር ሴቶች ደግሞ ከሴቶች ጋር ርኩሰትንና ነውርን በሽሚያ ሲፈጽሙ መመልከቱ የፈጣሪን ልብ እንዴት ያቆስል ይሆን?
ክርስቶስ የመሠረተው ትዳር በፍቺ አይሸነፍም። ጌታ እንዳለው “ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” (ማቴ. 19:6) ፍቅርን የሚያደፈርሰው የክርስቶስ ጠላት ዲያብሎስ ነው። በሰማይ የመላእክት ማህበር ውስጥ ያሰራጨውን አለመተማመን በሰዎች መሃልም ያስፋፋል። በየቤቱ እየገባ ቅናትን ይዘራል። ትዳር የሚበታትኑ “ዘመዶችና ወገኖችን” ያነሳሳል። በልብወለድ ታሪኮችና ፊልሞች ጋብቻን አስቂኝ እስር ቤት፤ ዝሙትንና ብልግናን ደግሞ የብልጦች ምርጫ አድርጎ ይስላል። ከዚህ ሲያልፍም ወንድ ወንድነቱን ረስቶ ሴት ደግሞ ሴትነቷን ክዳ “በዘመናዊ” የእርኩሰት ሙከራዎች እንዲዋረዱ ያደርጋል፤ አሁንም እያደረገ ነው።
ዲያብሎስ ትዳርን በማፍረስ ብቻ አይረካም። የክርስቶስ አባትነት እንዲረሳ በፈጣሪ ሥራዎች ላይ ጨካኝ ጥቃቶች ይሰነዝራል። ሰዎች የክርስቶስ ክቡር እጅ ሥራዎች መሆናቸውን ረስተው አካል በሚያደነዝዙ ዕፆችና መጠጦች ራሳቸውን እንዲያስጨንቁ ይገፋፋል። ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን እንዲያጠፉም መንገዶችን አዘጋጅቶ ወደ ሲኦል ይጋብዛቸዋል። ጥላቻን ዘወትር በመቀስቀስ በፈጣሪ አምሳል የተሰሩ ሰዎችን ለማማት፣ ለመስደብና ለመግደልም ያነሳሳል። ሰዎች በራስወዳድነት ውብ ደኖች እንዲመነጥሩ፣ ሰላማዊ እንስሳትን በማደን እንዲዝናኑ፣ ወንዞችና አየሩን ለገንዘብ ሲሉ በመርዛማ ፈሳሾችና ጎጂ ጭሶች እንዲበክሉ ይገፋፋል።
ይህ የሰይጣንና የእርኩስ ተከታዮቹ ሥራ ግን ለዘላለም አይቀጥልም። ክርስቶስ ከመገለጡ በፊት ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር በልዩ ኃይል በዓለም ሁሉ ይሰማል። “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ…ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:14) አዳም ሲፈጠር በክርስቶስ ፊት ላይ ያየው አባታዊ ፍቅር ምድርን በአዲስ ድምቀት ያበራታል። ያኔ ብዙ ሰዎች ለክብር መፈጠራቸውን ተገንዝበው በንስሃ ከብዙ የውርደት እስራቶች ይፈታሉ።
በትዕቢትና በልብ መደንደን የቀዘቀዙ ትዳሮች በክርስቶስ ፍቅር ግለው ለጎረቤቶቻቸው ምሳሌ ይሆናሉ። በጫት፣ በሺሻና በመጠጥ የዛሉ አእምሮዎች የክርስቶስን አባትነት በሚያስተውል ልብ ተነቃቅተው ሱሶቻቸውን ይረሳሉ። ወደ ክርስቶስ አባታዊ ፍቅር የተመለሱ ሰዎች ለተፈጥሮ መጠንቀቅን ይለማመዳሉ። ትኅትና ጥልን አርቆ የክርስቶስን ልጆች በስምምነት ያቀራርባቸዋል። ሰውን መናቅ ፈጣሪን ከመናቅ ያላነሰ ኃጢአት መሆኑን መረዳት በፍቅር ላይ የተመሠረተ መከባበርን ያመጣል። “እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።” (ሚል. 4:5)።
ክርስቶስ በሰይጣን ውሸቶች ታስራ በስቃይ ያረጀችውን ምድር በቅርቡ አዲስ ያደርጋታል። ሰይጣንና ውሸቶቹ ከሞት ጋር ይደመሰሳሉ። “የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ ‘ሞት በድል ተዋጠ’ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል” (1ቆሮ. 15:54)። የገነት ኮረብቶች በአዲስ ውበት ምድርን ያሳምሯታል። አናብስት በድጋሚ ከበጎች ጋር ይጫወታሉ። ሰማይ፣ ምድርና ባህር ፍርሃት በሌለው ዜማ ስለ አምላክ ምሕረትና እውነት ይመሰክራሉ። ለዘመናት ከአባታቸው ጠፍተው የቆዩ የአዳም ልጆች ወደ ዕቅፉ ይገባሉ። አዳምና ሔዋንን በርኅራሄ ዓይኖቹ እያየ በደስታ ያጠግባቸው የነበረው የሰማይ አባት ፍቅር ተርበው በምድር የደከሙትን ልጆች አቅፎ ዘላለማዊውን የዕረፍት እንጀራ ያበላቸዋል።
ድርባ ፈቃዱ