መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጅ በሁለት ጽንፎች የሚናገር ይመስላል። በትንቢተ ኢሳይያስ 2፥22 ላይ “እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል?” ይላል። በመዝሙር 8፡5 ደግሞ “ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው” ይላል። ለመሆኑ ይህ ሰው ማነው? ጊዜው ቁጥር 2 ይህንን ለመዳሰስ ሞክሯል።
“ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው?” የሚለው የዚህ ሁለተኛ ዕትም ገዢ ርዕስ በመዳን ታሪክ ዓምድ በስፋት ተብራርቷል። ሰው ምንድር ነው? አፋጣጠሩስ? “የእግዚአብሔር ልጅ” የተባለው አዳምና ሚስቱ ሔዋን በእግዚአብሔር ዘንድ እንዴት ነው የታሰቡት? ጠላትስ ምን አመጣባቸው? አምላክ ለሰው ልጅ አሁን ያለው ዕቅድስ ምን ይመስላል?
የጥሞና መልዕክት ዓምዳችን “ሰውና አባቱ” በሚል ርዕስ መድኃኒዓለም በወንጌል የሰጠውን ምሳሌያዊ ትምህርት ይተነትናል። የሰማዩ አባት ለፈጠረው ልጅ እንዴት እንደሚያስብና ወደ እርሱ የሚመጡትን ሁልጊዜ ለማዳን እጁ የተዘረጋ እንደሆነ በንጽጽራዊ መልኩ ያስረዳል።
“ብዙ ተባዙ” ተብሎ የተነገረውና በፈጣሪው የተባረከው የሰው ልጅ የተሰጠው የአብሮነት ኃላፊነት ምን እንደሆነ የቤተሰብ ዓምድ ትኩረት የሰጠበት ነው። ይህ በባልና ሚስት መካከል የሚኖረውን ቃልኪዳን እንዴት መጠበቅ ይቻላል? ችግሮችስ ሲከሰቱ እንዴት ነው መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው? ወዘተ ጉዳዮች በምሳሌ ተብራርተዋል።
በእግዚአብሔር አምሳያ የተፈጠረው የሰው ልጅ የመንፈስ፣ የነፍስና የሥጋ (የአካል) ቅድስና እንደሚስፈልገው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የአካል ቅድስና ውስጥ ንጽህና አጠባበቅ እንዴት እንደተካተተ ጤናችን ዓምድ ያብራራል። ከእስራኤላውያን የምድረበዳ ተሞክሮ በመነሳት ከዘመናችን ሁኔታ ጋር በማጣመር ትምህርት ይሰጣል።
በቁጥር አንድ ዕትማችን የመጽሐፍ ቅዱስ ዓምድ ለሰው ልጅ መመሪያ ይሆን ዘንድ ስለተሰጠው መጽሐፍ ቅዱስና ታሪኩ ዝርዝር ትምህርት አቅርበን ነበር። ባሁኑ ዕትም ደግሞ ጠለቅ ወዳለ ጥናት በመግባት ስለ መገለጥ ሰፋ ያለ ትምህርት ይዞ ቀርቧል። መገለጥ ምንድነው? ለምን አስፈለገ? እና ሌሎች ርዕሰጉዳዮች የሚያስተምረው አለው። እህታችን ውዴ ጫኔ ወርቅነህ እግዚአብሔር እንዴት ወደርሱ እንደጠራት ታሪኬ ይህ ነው በማለት ታወጋናለች።
ሰው “ሕያው ነፍስ” ነው? ወይስ “ሕያው ነፍስ ያለው” ነው? የጥያቄና መልስ ዓምዳችን መልስ ሰጥቶበታል። አንባቢው ያስተውል በሚል የምናቀርበው ወቅታዊ ዜና የሰሞኑ የዓለማችንን ሃይማኖት ነክ የዜና ዘገባዎች ያስነብባል። ከትንቢት ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በማገናኘት የማንበቡን በረከት ለአንባቢዎቻችን አስተውሎ ትተነዋል። የዜና ዘገባዎቹ በየቦታው ተሰባጥረው ይገኛሉ።
በዚህ የቁጥር ሁለት ዕትማችን የቃላት ጨዋታ አቅርበናል። ምላሻችሁን ገጽ 3 ላይ ባለው አድራሻችን ላኩልን፤ በሚቀጥለው ዕትም እናወጣለን። “የዘር ጥላቻ” በሚል ባለፈው ዕትም ያወጣነውን ጽሁፍ ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው ዕትም ይዘን እንቀርባለን።
ዘመኑን ለመዋጀት ጊዜውን ያንብቡ!
አዘጋጆቹ