“ባንጀራዬ ማነው?” የሚለው ጥያቄ በተለይ በሃይማኖቱ ዓለም ሲጠየቅ የኖረ ነው፤ በቀዳሚነትም በአይሁዳውያን ዘንድ! ይህ ጥያቄ በተጠየቀ ቁጥር ከፍተኛ ክርክር አብሮ ይነሳል። ለአይሁዳውያን “ባልንጀራ” የሚለው ትርጉም ብዙ ውዝግብን የፈጠረ በመሆኑ ጌታችንና መድኃኒታችን ሁሉም ሰው ሊያስተውለው በሚችል ግሩም ምሳሌ አስተማረ። በዚህ ዕትማችንም ይህንን ታላቅ ጥያቄ ገዢ ርዕስ በማድረግ ጊዜው ቁጥር 3 ያላትን ለማካፈል ብቅ ብላለች። ለእኛስ ባልንጀራችን ማነው? በቅድሚያ ከሚገባው ጊዜ በላይ በመዘግየታችን ታላቅ ይቅርታ እንጠይቃለን።
ይህ ከአገራችንም ወቅታዊ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታ ጋር አግባብ አለው ብለን ያመንበት ርዕስ በሁለት መጣጥፎች ተተንትኗል። “ባልንጀራዬ ማነው?” የሚለው ቀዳሚ ርዕስ በጥሞና ጊዜ ዓምዳችን የተተነተነ ሲሆን በቤተሰብ ዓምድ ደግሞ ይህንኑ ርዕስ በሌላ ምልከታ ትንታኔ ተሰጥቶበታል። ባልንጀራችን የኔ ወገን፣ ጎሣ፣ ብሔር የሆነውን ነው? ወይስ መልኩ እኔን የሚመስል፣ የኔን ቋንቋን የሚናገር፣ ከእኔ ጋር አብሮ የሚያመልክ ነው? መልሱ በሁለቱ ዓምዶች ይገኛል።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ታሪኩ በተከታታይ ስናቀርብ የነበረው ጽሁፍ በክፍል ሦስት ዕትሙ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የምንለውና በዓለማችን በከፍተኛ ቁጥር ተሰራጭቶ የሚገኝ መጽሐፍ እንዴት ተጻፈ፣ ደራሲው ማነው፣ … የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስ እውነተኝነቱን የሚያረጋግጥ ሐተታ ይሰጣል።
ዓለማችን የዘነጋችው ታላቅ ስጦታ አለ የሚለን የመዳን ታሪክ ዓምዳችን በዚህኛው ዕትም ይህ ታላቅ ስጦታ ምን እንደሆነና ስጦታውን አስታውሶ የራስ ለማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ጊዜው ያላለፈ መሆኑን ይመክራል፤ ለሚቀበሉትም በረከቱን እነሆ ይላል።
ከሰላምታችን ጀምረን “ጤና ይስጥልኝ” መባባላችን ለራሳችንና ለሌላው ጤና መጠበቅ ምን ያህል ፍላጎት እንዳለን የሚያመለክት ነው። ጤናችንን ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ የመፀዳጃ ቤት መኖር እንደሆነ ሁላችንንም የምንስማማበት ነው። ይህ ለጤና አስፈላጊ የሆነ ቤት ከሌለን እንዴት በቀላሉ እንደምንሠራ፣ ካለን ደግሞ እንዴት በንጽህና እንደምንጠብቀው ለጤናችን ዓምድ ትንታኔ ተሰጥቶበታል።
“የማመልከው አምላክ ከሚገጥሙኝ ችግሮች ሁሉ በላይ ነው” በማለት በቅድሚያ ይህንን አምላክ እንዴት እንዳገኙት ሲቀጥልም እንዴት ከችግሮቻቸው በላይ እንደሆነ የሚያወጉንና “ይህ ነው ታሪኬ” የሚሉን ወንድም ምስክርነት ቁጥር 3 ዕትማችን ይዞ ቀርቧል።
የራዕይ መጽሐፍ በርካታ ለዘመናችን የሚሆኑ አስደናቂ እውነቶችን ያካተተ ነው። ጊዜው ቁጥር 3 “ነገድ እና ቋንቋ በራዕይ መነፅር” በሚል ርዕስ አራት መሠረታዊ ነጥቦችን በመጥቀስ ዕይታውን ያቀርባል።
ሰንበት የትኛው ቀን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ የተለያዩ መልሶችን ሰምተን ይሆናል። እሁድ ነው የሚሉ በርካቶች ያሉትን ያህል ቀዳሚት ሰንበት የተባለችው ቅዳሜ ነች የሚሉም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለሰንበት ቀንና አከባበሩ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምን ይላል የሚለው በጥያቄና መልስ ዓምዳችን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተደገፈ ምላሽ ሰጥቶበታል።
ከዚህ በፊት እንደምናደርገው ሁሉ በየዓምዶች መካከልም “አንባቢው ያስተውል” በሚል ዓምድ ወቅታዊ የዓለማችንን ሁኔታ የሚያሳይ የዜና ዘገባዎችን አካትተናል። ዜናው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለውን አግባብ በተመለከተ ከአዘጋጆቹ አስተያየት አክለናል። ባለፈው ላቀረብነው የሠንጠረዥ ጨዋታ ምላሽም አቅርበናል።
ዘመኑን ለመዋጀት ጊዜውን ያንብቡ!
አዘጋጆቹ