በ1966 ሰኔ 27 ዓ.ም ምስራቅ ጎጃም አብጊ አልያስ አካባቢ ከእናቴ ወርቅነሽ ተስፋው ከአባቴ ጫኔ ወርቅነህ ተወለድሁ። ከተወለድሁበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ጥበቃው ለኔ ልዩ ነው።
አምላኬ ካደረገልኝ አንዳንድ ነገሮች መካከል፤ በተወለድኩኝ በአንድ ወሬ በበራችን አካባቢ የሚያልፍ የመስኖ ውሃ ውስጥ ገብቼ ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው፤ እናቴ እኔን ለማዘል ከጀርባዋ ቁጭ እንዳደረገችኝ በድንገት ሹልክ በማለት ከዚያ መስኖ ውሃ ውስጥ ገባሁ። ወሩ ሐምሌ አካባቢ ስለነበር ውሃው ቢያንስ ከአንድ መካከለኛ መጠን ካለው ሰው ወገብ በላይ ይደርስ ነበር። እናም ከዚህ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ለ10 ሜትር ያህል ወደ ውስጥ ወሰደኝ። ከዚያ በኋላ ወደታች አካባቢ የነበረ አንድ ሰው እንዲያው ለሙከራ በማለት እጁን ወደ ውሃው ሲከት እኔን ያዘኝ።
ከዚህ ክስተት ሌላ ካደኩኝ በኋላ እግዚአብሔር ከብዙ አስፈሪ ነገሮች በተለይ ከውሃ ጋር ከተያያዙ ጠብቆኛል። ከ10 ዓመቴ ጀምሮ ህልም የማየት ስጦታ እግዚአብሔር ሰጥቶኝ ነበር። የምተረጉመውም እኔው ነበርኩ። ለምሳሌ ያህል በቤተሰብ ዙሪያ ጥሩ ወይም ክፉ ነገር የሚከሰት ሲሆን በህልም ይታየኝ ነበር። ለእናቴ ብዙ ጊዜ፤ “ዛሬ በህልሜ …” ብዬ ሳልጨርስ “ልጄ ክፉ ከሆነ እንዳትነግሪኝ” ትለኝ ነበር።
በ1984 ዓ.ም እናቴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች ከእናቴ ሌላ በዚህ አለም ለኔ የሚያስብልኝ ያለ አይመስለኝም ነበር እናም ከሞተች በኋላ በመኖሪያ ቦታዬ መቀመጥ አልቻልሁም። ምክንያቱ የአምላኬ ሀሳብ ነበር። ስለዚህ ካደግሁበት ቦታ መልቀቅ ግድ ሆነብኝ።
ከዚያም ላልመለስ ሀገሬን ትቼ ወጣሁ። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። ነገርግን እግዚአብሔር አልተለየኝም ነበር፤ በመንገድ ላይ እያለሁኝ አጎቴን እንደድንገት አገኘሁት። “የት ልትሄጅ ነው?” ሲለኝ “የት እንደምሄድ አላውቅም” አልኩት። እሱም በጣም አዘነ፣ አለቀሰ፤ “ከእንግዲህ የትም አትሄጂም፤ ከእኛ ጋር አብረን እንኖራለን” አለኝ ከዚያ በኋላ ወደሚሠራበት አገር ወሰደኝ። እኔም እዚያ ደስ ብሎኝ መኖር ጀመርኩኝ። ለሁለት ዓመት ያህል በሰላም ኖርኩ። በ1987ዓም ላይ በደም ግፊት እና በልብ ድካም ተስፋበሌለው ሁኔታ ታመምኩ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኔ ዓላማ ነበረው። በደብረማርቆስ እና ፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ተመረመርኩ፤ ግን ተስፋ የለሽም አሉኝ። አጎቴ ባየኝ ቁጥር ያዝን ነበር። ዶክተሮቹ አለመቻላቸውን ሲነግሩኝ፤ መድኃኒዓለም ግን ሊያድነኝ እንደሚችል ሊያሳየኝ ብቅ አለ።
በግንቦት ወር 1987ዓም መጀመሪያ አካባቢ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሕልም አለምሁ። በሕልሜ ሁለት ህፃናት ወደኔ አካባቢ መጥተው ተቀመጡ፤ ቢያንስ የሁለት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው። አንደኛው እንደታመምሁ ያውቃልና እንዲህ አለኝ፤ “መዳን ትፈልጊያለሽ?” እኔም፤ “አዎን” አልሁት። እርሱም “በየሱስ ክርስቶስ ስም ብለሽ ፀልይ ከዚያም ትድኛለሽ” አለኝ። እኔም “እንዴት አድርጌ ነው የምፀልየው?” አልኩት። እርሱም ዘወር አለና በመንበርከክ ፀልዮ አሳየኝ።
ጠዋት እርሱ እንዳሳየኝ አድርጌ ከፀለይሁ በኋላ እኔን የፈጠረኝ እግዚአብሔር እንደሆነ ገባኝ። የፈጠረኝ አምላክ መፃህፍት ማንበብ እንድችል ማድረግ አያቅተውም በማለት ለ15 ቀናት ለመፀለይ ወሰንሁ። አስተምረኝ እያልኩ እየፀለይሁ 15ቀናት አለፉ።
አጎቴ ከሰይጣን ቢጠብቀኝ ብሎ መፅሀፍ ቅዱስ ከትራሱ ያስቀምጥ ነበር። ፀሎቴን ስጨርስ አምላኬ ፈቅዶልኝ እንደሆነ ብዬ መፅሐፍ ቅዱሱን ከፈትኩት ከዚያም ሕዝቅኤል ውስጥ የተሰባበሩና የደረቁ አጥንቶችን እግዚአብሔር ወደ ህያውነት እንደሚቀይር የሚያሳየውን ጥቅስ አነበብኩ። ከዚያ በኋላ በየቀኑ እፀልይ ነበር። ከአንድ ወር በፊት ከአጎቴ ቤት ግድግዳ ላይ ያሉ ጽሁፎችን አንብቡልኝ እያልኩ ያነቡልኝ ነበር። አሁን ግን ከወር በኋላ እነዚያን የግድግዳ ፅሁፎች አነበብኳቸው። ያን ጊዜ የአጎቴ ሚስት በጣም ተቆጣች፤ ምክንያቱም ያታለልኳት መስሏት ነው። “አልተማርኩም አላልሽም? ውሸታም፤ ተምረሻል” እያለች በጣም አዘነችብኝ። እኔ ግን “እትዬ አትዘኝ አንዳንዴ እንዲህ ያለ ነገር ይከሰታል” በማለት አረጋጋት ነበር።
ከዚያ በኋላ ለክረምት ያቀድኳቸው ብዙ እቅዶች ነበሩኝ። እነርሱን በአስቸኳይ ከጨረስኩኝ በኋላ ታላቅ እህቴን፣ አጎቴንና የአጎቴን ሚስት እሁድ ቀን ቀጠርኳቸው። በጣም እንደምፈልጋቸው ነግሬያቸው ስለነበር ምን ይሆን በማለት በጉጉት ይጠብቁ ነበር። እሁድ በመጣ ጊዜ በይ ንገሪን አሉኝ ነገሩ ከባድ ስለሆነብኝ በጣም ስፀልይ ነበር። እኔም “እግዚአብሔር መርቶኛል ፍቀዱልኝ ወይም አሰናብቱኝ” አልኳቸው። ከዚያ በኋላ ሶስቱም በአንድ ጊዜ ጮሁ። አጎቴ ለተወሰነ ጊዜ አንገቱን ደፍቶ ከቆየ በኋላ ሴቶቹ ዝም እንዲሉ አዘዛቸው። ምክንያቱም ብዙ ሰው ተሰብስቦ ነገሩ ምንድነው እያለ ይገረም ነበር። አጎቴ አንድ የሚያናግረው ሰው እንዳለ ጠቅሶ “እርሱን ልጥራው” በማለት ወጣ። ማንን ሊጠራ እንደወጣ ስላወቅሁኝ ዓይኔን ወደ ሰማይ አድርጌ አጎቴ የፈለገውን ሰው እንዳያገኝ ፀለይኩ። አጎቴ ሦስት ቦታ ሄዶ ከፈለገው በኋላ ሳያገኘው ሲቀር እያዘነ ወደቤት መጣ። “ከአሁን በኋላ አትናገሯት” በማለት ሁሉንም በመናገር ወደ እኔ ዞር ብሎ “ለምን እንደዚህ አደረግሽ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም “ካለምኩት ካሰብኩት አልመለስም” ብዬ ነገርኩት። እሱም ተስፋ ቆርጦ “እሺ ለመንገድ ይሁንሽ” ብሎ 70 ብር ሰጠኝ።
መንገዴን ስጀምር ከቀኑ 10ሰዓት ነበር ትንሽ እንደሄድኩ አንድ ሰው በፊት ለፊቴ መጣና “ወዴት እየሄድሽ ነው?” አለኝ። እኔም “ተወው የምሄድበትን የምናውቀው እኔና እግዚአብሔር ነን” አልኩት። እርሱም “ካልነገርሽኝ አትሄጂም፤ ዝም ብለሽ የገጠመሽን ችግር ንገሪኝ” ብሎ ሲያፋጥጠኝ ሁሉንም ነገር ነገርኩት። እርሱም እየሰማ ያለውን ነገር ማመን አቅቶት ደንዝዞ ቆሞ ነበር። እኔም “ደህና እደር” ብዬ ልሄድ ስል ስቅስቅ ብሎ አለቀሰና “ነይ እኔ ወደ ቤተክርስቲያን እወስድሻለሁ” ብሎ ወሰደኝ። እኔም እንደልቤ መፀለይም ቻልኩ፤ የምፈልገውን እግዚአብሔርን መጠየቅ ጀመርኩ። ከጥያቄዬ አንዱና ለህይወቴ መሠረት የሆነው ጥቅስ ዘፀአት 20፡8 “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፤ ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህን አድረግ 7ኛው ቀን ግን የአምላክህ ሰንበት ነው” የሚል ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስን በማነብበት ጊዜ ስለሰንበት ጉዳይ እግዚአብሔርን መጠየቄን አላቋረጥኩም። ብዙ ሰዎችን ጠየቅኳቸው ግን ሁሉም ሰንበት እንደተሻረ ነበር የሚነግሩኝ። ሆኖም ጊዜው ሲደርስ አምላኬ ሁሉንም አስተማረኝ። በዚህ ሁሉ ወቅት ባህርዳር ከተማ ስኖር ነበርኩና የምተዳደረው ደግሞ ምግብ በኮንትራት በመሥራት ነበር። አንድ ጊዜ ሁለት ሰዎች ምግብ እንድሠራላቸው ጠየቁኝና በዋጋ ተስማማን። ከሁለቱ አንዱ ፓስተር እሱባለው ምህረት ይባላል ሌላው ደግሞ አቶ ዘውዱ ሰብለወርቅ ነበር፤ እርሱም በሕንጻ ግንባታ ሥራ የተሰማራ ነበር።
አንድ ቀን ፓስተር እሱባለው “እኛ ቅዳሜ ሥራ አንሰራም፤ ስለዚህ ምግብ አርብ ነው የምትሠሪው” አለኝ። እኔም “ለምን?” አልኩት። እርሱም የሰጠኝ መልስ ሁለት ዓመት የለፋሁበትን የዘፀ20፡8 የፀሎት ጥያቄ ነበር። እኔም በጣም ደስ አለኝ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቅዳሜ ሰንበትን ለማክበር ወሰንኩ። የእግዚአብሔር ቃል በዚያ ቤት ሙሉ ደስታ ሆነ እንደሚለው ለእኔም በዚያን ጊዜ ሙሉ ደስታ ሆነልኝ። ለኔ ሁለት ዓመት የለፋሁበት የፀሎቴ ውጤት ሲሆን ለነርሱ ደግሞ ያልታሰበ ደስታ ነው። ከዚያም ለረጅም ጊዜ እከታተልበት ወደነበረው ቤተክርስቲያን ሄጄ የቤተክርስቲያኑን ሽማግሌ “ከአሁን በኋላ የት ጠፋች ብላችሁ እንዳትፈልጉኝ ማስታወቂያ ለመናገር ትንሽ ደቂቃ ስጠኝ” ብዬ ጠየቅሁት። “ለምን ትጠፊያለሽ?” አለኝ እኔም “ስለ ሰንበት የነበረኝ ጥያቄ መልስ ስላገኘሁኝ ነው” ብዬ ነገርኩት። እርሱም “አይ ተይው በቃ እኔ ለወንጌላዊያን እነግራቸዋለሁ፤ ይቅር” አለኝና ተለያየን።
ለዓመታት የነበረኝ ጥያቄ ከተመለሰልኝ ወዲህ የእግዚአብሔርን ሰንበት እያከበርኩና እርሱን እየታዘዝኩ በደስታ አለሁ።
በዚህ አጋጣሚ በህይወቴ ከምወዳቸው ጥቅሶች መካካል ሁለቱን ልጥቀስ፤ ለነዚህ ጥቅሶች የተለየ ትርጉም አለኝ። አንደኛው ዮሐንስ 14፡1-8 ሲሆን ሁለተኛው ጥቅስ 2ኛ ዜና 7፡13-15 ደግሞ እንዲህ ይነበባል፤ “ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣ በማዝበት ጊዜ፣ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር በምሰድበት ጊዜ፣ በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ወደሚጸለየው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ያዳምጣሉ”።
ጥያቄዬን የመለሰ አምላኬና ጌታዬ እግዚአብሔር ይመስገን።
ውዴ ጫኔ ወርቅነህ