የጌታ ዳግም ምፅዓት በሚለው ክፍል ለመዳሰስ እንደተሞከረው፤ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ሲመጣ በሕይወት ያሉ ኃጥኣን በክብሩ ብርሃን ይሞታሉ፤ እርሱ ከመምጣቱ በፊት የሞቱት ኃጥኣን ደግሞ እዚያው በመቃብራቸው ይቀራሉ። ሞተው የነበሩት ጻድቃን ከሞት ተነስተው በሕይወት ካሉት ጻድቃን ጋር በመሆን አዲስ አካል ለብሰው ጌታን ለመገናኘት ይነጠቃሉ። ከክርስቶም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ። በእነዚህ ዓመታት የሚሆነውን ቀጥለን እንመለከታለን፤
1. ሺህ ዓመት ከመጀመሩ በፊት የሚሆነው ምንድነው?
ትንሣኤ፤ “እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ” (ራዕይ 20፡4)።
2. ይህ ትንሣኤ ምን ይባላል? እነማን ናቸው የሚነሱት? ምን ይባላሉ?
“ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ” (ራዕይ 20፡5፣6)።
3. ሁለተኛ ትንሣኤስ አለ? ካለ እነማን ናቸው የሚነሱት?
“የቀሩት ሙታን ግን ሺሁ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም” (ራዕይ 20፡5)። “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ”(ዮሐ.5፡28፣29)። ስለዚህ ሁለተኛው ትንሣኤ የሚከሰተው ሺሁ ዓመት ሲጠናቀቅ ነው። በሌላ አነጋገር የዳኑት ሺሁ ዓመት ሲጀመር ይነሳሉ፤ ያልዳኑት ደግሞ ሺሁ ዓመት ሲጠናቀቅ ይነሳሉ።
4. ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ያልዳኑት ምን ይሆናሉ?
“ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት … ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል” (2ተሰ. 1፡7፣8)። “የቀሩት ሙታን ግን ሺሁ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም” (ራዕይ 20፡5)። “በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል” (ኢሳ.11፡4)። ክርስቶስ በራሱ ክብር፣ በአባቱ ክብርና በመላዕክት ክብር ሲመጣ በህይወት የሚገኙት ኃጥኣን ይህንን መቋቋ አቅቷቸው በክብሩ ብርሃን ይሞታሉ። ከዚያ በፊት ሞተው የነበሩት 1,000 ዓመት እስኪፈጸም በመቃብር ይቆያሉ።
5. በዳግም ምፅዓት ወቅት ያልዳኑት በሺሁ ዓመት ጊዜ ወንጌል ይሰበክላቸው ይሆን?
“በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ፤ እንደ ጉድፍ በምድር ላይ ይጣላሉ እንጂ፣ አይለቀስላቸውም፤ ሬሳቸውም አይሰበሰብም፤ አይቀበርምም” (ኤር. 25፡33)። በሺሁ ዓመት ጊዜ ንስሃ ለመግባትም ሆነ ወንጌልን ለመስማት የሚኖር ዕድል የለም። ምክንያቱም ጌታ ዳግም ሲመጣ የሰው ልጆች ጉዳይ ውሳኔ አግኝቷል፤ (ራዕይ 22፡11፣12) ስለዚህ ክርስቶስ ሲመጣ የዳኑትን ይዞ ወደ ሰማይ ይሄዳል፤ ያልዳኑት ደግሞ በክብሩ ብርሃን ይሞታሉ፤ ምድር ማንም አይኖርባትም (ራዕይ 20)፤ በዚያን ወቅት በምድር የሚገኙት ሠይጣንና እርኩሳን መላዕክቱ ናቸው፤ ጌታን ያልተቀበሉ ረፍዶባቸዋል።
6. በሺሁ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሰይጣን ምን ይሆናል? ቀጥሎስ?
“የጥልቁን መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። እርሱም የጥንቱን እባብ፣ ዘንዶውን፣ ማለትም ዲያብሎስን ወይም ሰይጣንን ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው። ሺሁ ዓመትም እስኪፈጸምም ድረስ … ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በእርሱም ላይ ማኅተም አደረገበት። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል” (ራዕይ 20፡1-3)።
በዚህ ጥቅስ ላይ “ጥልቁ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል ከግሪክ የተወሰደና “አቡሶስ” ተብሎ የሚጠራ ነው። ይኸው ቃል በዘፍጥረት 1፡2 ላይ “ጥልቅ” ወይም “ጥልቁ” ተብሎ ተገልጾዋል። ይህ ማለት ምድር ስትፈጠር ጥልቅ ጉድጓድ የነበረች ሳትሆን በጨለማ የተዋጠችና ገና ለመኖሪያነት ያልተዘጋጀች መሆኗን ሲገልጽ ነው። ስለዚህ በራዕይ 20 ላይ መልአኩ ሰይጣንን በጥልቁ ሲያስረው ጉድጓድ ውስጥ አስገብቶ በሰንሰለት አይደለም። ከላይ እንዳየነው ክርስቶስ ሲመጣ የዳኑት ወደ ሰማይ ስለሄዱ፣ ያልዳኑት ደግሞ በመቃብር ለሺህ ዓመት ስለሚቆዩ ምስቅልቅሏ የወጣች ምድር ውስጥ ሰይጣን በሁኔታዎች ታጥሮ ከእርኩሳን መላዕክቱ ጋር የትም እንዳይሄድ፣ በምድር ብቻ ተወስኖ መቀመጡ ነው “የታሰረ” የሚያስብለው። በኤርምያስ 4፡23፣25፣28 ላይ ምድር ወደኋላ ተመልሳ ቅርጽ አልባ፣ ብርሃን አልባ፣ ሰው አልባ ሆና ነቢዩ እንዳያት ይናገራል። የሚታሰርበት ሰንሰለትም እንዲሁ ምሳሌያዊ ሲሆን ይህም የሚያመለክተው በምድር ላይ ምንም የሚያስተው ሰው ስለማይኖር ምንም ማድረግ ባለመቻል “ታስሮ” ይቀመጣል። ከሺሁ ዓመት በኋላ ያልዳኑት ሙታን ሁሉ ስለሚነሱና እነርሱን አታልሎ ቅድስት ከተማ የሩሳሌምን ለመውረር ስለሚመጣ በጥቅሱ ላይ “ከዚያ (ከሺሁ ዓመት) በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል” ይላል። ስለዚህ የሚያስተው ሳይኖር “ይታሰራል”፤ የሚያስተው ሲኖር ደግሞ ይፈታል።
7. በሺሁ ዓመት ጊዜ በሰማይ ምን ይደረጋል?
“ቀጥሎም ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ተቀምጠው ነበር፤ … እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ” (ራዕይ 20፡4)። “ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? … በምድራዊ ሕይወት ጒዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን?” (1ቆሮ. 6፡2፣3)።
በሺሁ ዓመት የዳኑት በፍርድ ሥራ ላይ ይሰማራሉ። ማለትም ያልዳኑት ሙታን ለምን ሳይድኑ እንደቀሩ ጉዳያቸው ይመረመራል፤ ይህ ሥራ በጥቅሱ በግልጽ እንደተቀመጠው የሰይጣንንና የመላዕክቱንም ጉዳይ ጨምሮ የሚዳስስ ይሆናል። ይህ የፍርድ ሥርዓት በዳኑት ሰዎች አእምሮ ውስጥ ስላልዳኑት ያለ ማንኛውንም ጥያቄ የሚመልስና እግዚአብሔርም ለሁሉም ሰው ምንም ሳያዳላ የመዳን ዕድል የሰጠ አምላክ መሆኑን በገሃድ የሚያረጋግጥ ይሆናል። በመሆኑን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሳይገቡ የሚቀሩት በራሳቸው ምርጫና በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን ዕድል ባለመጠቀም እንደሆነ ፍጥረተ ዓለም የሚመሰክረው ጉዳይ ይሆናል።
8. ሺሁ ዓመት ሲጠናቀቅ ምን ይከሰታል?
“ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው” (ራዕይ 21፡2፣3)። “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ … በዚያን ቀን እግሮቹ ከየሩሳሌም በስተምሥራቅ በደብረዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤…ከዚያም አምላኬ እግዚአብሔር ይመጣል፤ ቅዱሳኑም ሁሉ አብረውት ይመጣሉ። ምድር ሁሉ ከጌባ አንሥቶ በየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሬሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች” (ዘካ. 14፡1፣4፣5፣10)።
አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ስትወርድ የደብረ ዘይት ተራራ ለሁለት ተከፍሎ የከተማዋ ማረፊያ ይሆናል። በከተማዋ ውስጥ መላዕክት (ማቴ. 25፡31)፣ የዳኑት (ዘካ. 14፡5)፤ እግዚአብሔር አብ (ራዕ. 21፡2፣3)፤ እግዚአብሔር ወልድ (ማቴ. 25፡31) ሁሉ አብረው ሆነው ነው የሚመጡት። ይህ የክርስቶስ ሦስተኛ ምፅዓት ነው፤ ዳግም የሚመጣው የዳኑትን ለመውሰድ ሲሆን ሦስተኛ የሚመጣው ደግሞ ከዳኑት ጋር ነው።
9. በቀጣይ የሚከሰተው ምንድነው? ሰይጣንና መላዕክቱስ ምን ይሆናሉ?
“ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በአራቱ የምድር ማእዘናት ያሉትን ሕዝቦች፦ ጎግንና ማጎግን እያሳተ ለጦርነት ሊያሰልፋቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸው በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነው። እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ወጥተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ” (ራዕ. 20፡7-9)።
ሺሁ ዓመት ሲጠናቀቅ ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ወደዚህች ምድር ይመጣል። በመቃብር ያሉት ኃጥዓን ይነሳሉ፤ ሰይጣንም ከእስራቱ ይፈታል። ቅድስቲቱን ከተማ በመውረር ለራሱ ለማድረግ የተነሱትን ኃጥኣን በማሳት አስተባብሮ ወረራ ለማድረግ ሰይጣን ቁርጥ ውሳኔው ያደርጋል። በዚያን ጊዜ “እሳት ከሰማይ ወርዶ ይበላቸዋል”(ራዕይ 20፡9)። ይህም እሣት ሰይጣንና መላዕክቱን ብቻ ሳይሆን ያልዳኑትንም ሁሉ ጭምር የሚበላ ይሆናል። “እኔ በምሠራበት ቀን ክፉዎችን ትረግጣላችሁ፤ ከእግራችሁ ጫማ በታች ዐመድ ይሆናሉ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት” (ሚል. 4፡3)።
10. ሰይጣን፣ መላዕክቱና ኃጥኣን በሙሉ ከጠፉ በኋላ የሚከሰተው ምንድነው?
“እነሆ፤ እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ” (ኢሳ. 65፡17)። “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ … በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ “እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ” (ራዕ. 21፡3፣5)። እግዚአብሔር አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን ይፈጥራል፤ የዚህ ምድር ዋና ከተማ አዲሲቷ የሩሳሌም ትሆናለች፤ ኃጢአትና የኃጢአት የሆኑ ነገሮች በሙሉ ይወገዳሉ፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ለዘላለም ከሕዝቡ ጋር ይኖራል። በቀጣዩ ክፍል ስለዚህች አስደናቂ ከተማ እንዲሁም ስለ አዲስ ምድር እና አዲስ ሰማይ ዘርዘር ያሉ ሃሳቦችን እንዳስሳለን፤
ቅንብር፤ ጥበበሥላሴ መንግሥቱ