- በምዕራቡ ዓለም በርካታዎች መጽሐፍ ቅዱስን አያነቡም
በጥቅምት ወር በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከአሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ስድስቱ ብቻ አስፈላጊ መሆናቸውን ብሪታውያን ተናገሩ። አራቱ ትዕዛዛት በ21ኛው ክ.ዘ. ለመኖር “አስፈላጊ ያልሆኑ ናቸው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ በርካታ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን እንደማያነቡ መሰከሩ።
ጥናቱን ያደረገው YouGov.co.uk እንደተናገረው ከተሳታፊዎቹ 93 በመቶ የሚሆኑት “አትግደል” እና “አትስረቅ” የሚለው በዚህም ዘመን አስፈላጊ ትዕዛዝ ነው በማለት የመጀመሪያውን ሥፍራ ሰጥተዋል። 2 በመቶ ግን አያስፈልግም ብለዋል። “በባልንጀራህ ላይ በሃሰት አትመስክር” 87 በመቶ ለዚህ ዘመን አስፈላጊ ነው ሲሉ፤ 6 በመቶዎቹ ደግሞ አያስፈልግም ብለዋል። በ4ኛነት “አታመንዝር” የሚለው ትዕዛዝ 73 በመቶ አስፈላጊ ነው ተብሎለታል። ለዚህ ትዕዛዝ 19 በመቶዎቹ በዚህ ዘመን አያስፈልግም ብለዋል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሌሎቹን የአስርቱ ትዕዛዛት ሕግጋትን በተመለከተ ለዚህ ዘመን ያስፈልጋሉ ወይም አያስፈልጉም ለሚለው ጥያቄ የሚከተለው ምላሽ ተሰጥቷል።
ትዕዛዝ | ያስፈልጋል | አያስፈልግም |
“እናትና አባትህን አክብር” | 69 በመቶ | 22 በመቶ |
“የባልንጀራህን አትመኝ” | 61 በመቶ | 28 በመቶ |
“ስዕልና ምሳሌ አታድርግ” | 31 በመቶ | 56 በመቶ |
“የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ” | 23 በመቶ | 68 በመቶ |
“ከኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” | 20 በመቶ | 38 በመቶ |
“የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” | 19 በመቶ | 73 በመቶ |
ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የእንግሊዝ ቤ/ክ በምዕመናኑ ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ከአባላቱ 60 በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስን “በጭራሽ” አንብበው እንደማያውቁ ተናግረዋል። በሌላ ጥናት ደግሞ 77 በመቶ የሚሆኑ ብሪታኒያን መጽሐፍ ቅዱስን በጭራሽ አንብበው እንደማያውቁ ተረጋግጧል። ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በየሳምንቱ እንደሚያነቡ ሲናገሩ ሢሦው ደግሞ መቼም ጸልየው እንደማያውቁ መልሰዋል። ጥናቱ እንዳስረዳው፤ ዓለማዊነትን የመዋጊያ መሣሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ ሳለ በክርስቲያኖች ዘንድ አለመነበቡ ቤ/ክ እየሞተች ለመሄዷ እና ዓለማዊነት በቤ/ክ እየበረታ ለመሄዱ እንደማስረጃ ሊጠቀስ ይችላል ብሏል።

አሜሪካም በተመሳሳይ ችግር እንደተጠቃች የጆርጅ ጋላፕና ጂም ካስቴሊ ጥናት አመልክቷል። ከሁለት ሰዎች መካከል አንዱ እንኳን አራቱን ወንጌላት በስም ለመጥራት አለመቻሉን የጠቀሰው የጥናት መረጃ አሜሪካ “በመጽሐፍ ቅዱስ ድንቁርና” ውስጥ ነው የምትገኘው ብሏል። ከአራት አሜሪካውያን አንዱ እንኳን (24 በመቶ) መጽሐፍ ቅዱስ “ቃል በቃል የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው” ብሎ አያምንም። ከዚህ ሌላ 26 በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው የተጻፈ የተረት፣ የገድልና የታሪክ” መጽሐፍ ነው ብለው ያምናሉ።
በአሁኑ ዘመን ዓለማችን “ዋናው ነገር ለሰዎች ጥሩ ማድረግ፣ ጥሩ ማሰብ፣ ጥሩ ሰው መሆን፣ ሌላውን አለመጉዳት፣…” በተሰኙ አንጻራዊ የድኅረ-ዘመናዊነት (ፖስት ሞደርኒዝም) አስተምህሮት እየተጥለቀለቀች ባለችበት ጊዜ ይህ ዓይነቱ የጥናት ውጤት ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው መድኃኒዓለም “እውነት፣ ህይወትና መንገድ” ነው (ዮሐ. 14፡6)። ይህ ሁሉንም ሊያሳምን የሚችል ፍጹማዊ እውነታ ነው። ከዚህ ውጪ ሰዎች በዚህ ዘመን “የእኔ እውነት፣ ያንተ እውነት፣ ያንቺ እውነት፣ …” በማለት እውነትን በአንጻራዊነት ያስቀምጣሉ። ይህም ቃለ-እግዚአብሔር በሙላት የክርስቲያኖች የህይወት መመሪያ ገዢ ቃል እንዳይሆን አዳክሞታል።
የጨለማው ዘመን በሚባለው ረጅም ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የተወገዘ ከመሆኑ የተነሳ ሲያነብ የተገኘ ይገደል ነበር። ባንጻሩ ባለንበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ከእጅ ስልካችን ጀምሮ በተለያየ መልኩ በቀላሉ የሚገኝ ቢሆንም ዓለም ግን ይህንን መጽሐፍ ባለማንበብ “በመንፈሣዊ ድንቁርና” ውስጥ ትገኛለች። ነቢዩ አሞጽ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር፤ “እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም” ይላል (አሞጽ 8፡11)።
ሐዋሪያው ጳውሎስ ደግሞ ለጢሞቴዎስ ሲመክረው ይህንን ብሎት ነበር፤ “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ” 2ጢሞ. 4፡1-4።
“አንባቢው ያስተውል”