“ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር። በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል” (ራዕይ 13፡11-12)።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚነግረን አሜሪካ በመጀመሪያ እንደ በግ ትጀምርና ቀጥሎ ግን “እንደ ዘንዶ” መናገር ትጀምራለች።
በራዕይ 12፡9 እንደምናነበው ዘንዶ የሚያመለክተው ሰይጣንን ነው። ይኸው ምዕራፍ ሰይጣን እንዴት እንደሚሠራ በዝርዝር ሲያስረዳ በጣም ቁጡ፣ ጨካኝ እና አሳዳጅ ኃይል ነው ይለዋል (ቁጥር 4፣ 12፣ 13፣ 15፣ 17)። በጣም ጨካኝ በሆነው ኃይሉ ከፍተኛ ጥቃት ይሰነዝራል፤ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ስለሚጠላ ተከታዮቹንም እንዲሁ ይጠላቸዋል። ዓላማው በፊት እንደነበረው አሁንም ያው ነው፤ ይኸውም የእግዚአብሔርን ዙፋን በመንጠቅ ሰዎች ሁሉ እርሱን እንዲያመልኩና እንዲታዘዙ በግድ ማድረግ ነው (ኢሳይያስ 14፡12-14)።
አንድ መንግሥት እንዴት “ይናገራል” ብለን ከጠየቅን መልሱ በሚያወጣው ሕግና በሚነድፈው ፖሊሲ የሚለው ይሆናል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ዘንዶ ይናገራል” ሲል አሜሪካ ሕግ በማውጣትና ፖሊሲ በመተግበር የሰይጣንን ፍላጎት ያሳካል ማለት ነው።
በእርግጥ ይህ የሚያስደነግጥ ነገር ሊሆን ይችላል። እንዴት ነው እንደ አሜሪካ ያለ የነጻት አገር ይህንን የመሰለ አደገኛና አፋኝ ነገር የሚደርገው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። እስቲ አሜሪካንን የሚወክለው ሁለተኛውን አውሬ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በጽሞና እንከታተል፤
1. “በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል” (ራዕይ 13፡12)። እንደ ጳጳሳዊው ሮም አሜሪካም ውሎ አድሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማማ እና ግለሰባዊ የኅሊና ነጻነትን የሚገፍ አምልኮ እንዲተገበር አሳዳጅ ኃይል ይሆናል። በሌላ አነጋገር ሰዎች በግድ የሆነ እምነት እንዲከተሉ ያደርጋል።
2. “ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል” (ራዕይ 13፡12)። አሜሪካ ለእርሷ እንዲሰገድላት የምታደርግ ሳይሆን ከዚያ ይልቅ በዓለም የሚኖሩ ሁሉ ለመጀመሪያው አውሬ ወይም ለሐሳዊው መሢሕ ወይም ለጳጳሳዊው ኃይል እንዲሰግዱ ታስገድዳለች።
3. “የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል” (ራዕይ 13፡14)። ምስል ማለት የአካሉ ወይም የዋናው አምሳያ ማለት ነው። የፊተኛው አውሬ ምስል ማለት የጳጳሳዊ ሥርዓትን የሚወክል በሌላ አነጋገር የእርሱን ገጽታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምስል ማለት ነው። ስለዚህ አሜሪካ የጳጳሳዊ ሥርዓትን ምስል ለማቆም በቅድሚያ መሠረታዊ የሆነውን እና በቤተክህነትና በቤተመንግሥት መካከል ያለው ልዩነት በማስወገድ ሁለቱን ማዋኻድ አለባት። ይህንን በምታደርግበት ጊዜ ጳጳሳዊው ሥርዓት በጨለማው ዘመን እጅግ ገንኖ የነበረው ሥልጣኑ እንዲመለስ የሚያደርጉ ሃይማኖታዊ ሕግጋትን በማውጣትና በመተግበር ምስል የማቆም ሥራዋን ትፈጽማለች። ከዚያም ዓለም ሁሉ የእርሷን ፈለግ በመከተል ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ ተጽዕኖ ታሳድራለች።
4. “የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው” (ራዕይ 13፡15)። በጨለማው ዘመን ጳጳሳዊው ሥርዓት በእምነታቸው ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደገደለ ሁሉ አሜሪካም ተጽዕኖ የማድረግ ብቃቷን ተጠቅማ ለአውሬው ወይም ለምስሉ አንሰግድም በማለት በሚጸኑ ሁሉ ላይ የሞት ዓዋጅ ታውጃለች።
“እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ፣ መዳናችሁ ቀርቦአልና፤ ራሳችሁን ወደ ላይ ቀና አድርጉ” (ሉቃስ 21፡28)።
“አንባቢው ያስተውል”










