giziew.org

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና በታሪክ የተደገፈ አፈጻጸማቸው

ዳንኤል አራት አራዊት ከባህር ሲወጡ የተመለከተ ሲሆን እነዚህም አንበሳ፣ ድብ፣ ነብር እንዲሁም የምታስፈራውና አስር ቀንዶች የነበሯት አውሬ ነበሩ
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እንደሆነ በርካታ ማረጋገጫዎች ያሉ ቢሆንም በተለይ ግን ይሆናሉ ተብለው በመጽሐፍ ቅዱስ የተተነበዩ ትንቢቶች ከአያሌ ዓመታት በኋላ በአስደናቂ ሁኔታ በትክክል በታሪክ ተፈጽመው መገኘታቸው ለእውነተኛነቱ እንደ አንድ ማስረጃ መቅረብ የሚችል ነው። በተለይ አንዳንዶቹ ከበርካታ ዓመታት በፊት ዘርዘር ባለ መልኩ የተነገሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ አፈጻጸማቸው ደግሞ ያለ አንዳች ዕንከን መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን እጅግ አስደናቂ መጽሐፍ ያደርገዋል።

“እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ” (ኢሳ. 46፡9-10)።

ጥቂቶቹን ትንቢቶችና አፈጻጸማቸውን ለመግለጽ፤

  1. በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 2 እንዲሁም 7 ላይ ከባቢሎን ጀምሮ በተከታታይ የሚነሱት መንግሥታት በትንቢት ተጽፈዋል። በዳንኤል 2 ላይ ንጉሥ ናቡከደናጾር ባየው ሕልም ላይ የተመለከተው ምስል ራሱ የወርቅ (ባቢሎን (ከክርስቶስ ልደት በፊት) 606-538)፣ ደረቱና ክንዶቹ ብር (ሜዶና ፋርስ 538-331)፣ ሆዱና ወገቡ ነሐስ (ግሪክ 331-168)፣ ጭኖቹም ብረት (ሮም 168-476ዓም)፣ እግሮቹም ግማሹ የሸክላ ግማሹ የብረት (የተከፋፈለው አውሮጳ) ነበር። ይህም ዳንኤል በግልጽ እንደተነበየው የተፈጸመ ሲሆን የቀረው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና ምስሉን በማድቀቅ ታላቅ መንግሥት የመሠረተው የጌታችን ዳግም ምጽዓት ብቻ ነው።
  2. በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይም በተመሳሳይ መልኩ ነገሥታቱ በአውሬ ምስል ቀርበዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት አፈታት መሠረት አውሬ ማለት መንግሥታት ማለት ነው (ዳን.7፡17፣23)። ዳንኤል አራት አራዊት ከባህር ሲወጡ የተመለከተ ሲሆን እነዚህም አንበሳው ባቢሎንን፣ ድቡ ሜዶና ፋርስ፣ ነብሩ የታላቁ እስክንድርን ግሪክ እንዲሁም የምታስፈራውና አስር ቀንዶች የነበሯት አውሬ ሮምን የሚያመላክቱ ነበር፤ አሥሩ ቀንዶች ሮም ስትፈርስ የወጡት አሥር የአውሮጳ መንግሥታት ናቸው (ዳን.7፡1-7)።
  3. ባቢሎንን ድል የነሳው ንጉሥ ቂሮስ ከመወለዱ 150 ዓመታት በፊት በስም ተጠርቶ ትንቢት የተነገረለት ሲሆን እንደተባለውም ጊዜው ሲደርስ ባቢሎንን ድል ነስቷል (ኢሳ. 45፡1-3)። 
  4. ባቢሎን ከፈረሰች በኋላ ዳግመኛ እንደማትሠራ መጽሐፍ ቅዱስ የተነበየ ሲሆን ባቢሎንን ድጋሚ ለመሥራትና ለማንሠራራት የተደረጉት ሙከራዎች በሙሉ አልተሳኩም (ኢሳ. 13፡19፣20፤ ኤር.51፡37)።
  5. በመጨረሻው ዘመን የሞራል መላሸቅ እንደሚከሰት፣ ከዓመጽና ግፍ መብዛት የተነሳ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ መጽሐፍ ቅዱስ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የተነበየ ሲሆን ከዘረኝነት ጀምሮ እስከ ሰዶማዊነት፣ ተዘርዝሮ የማያልቅ ብልግና፣ ስድነት፣ ግፍና ልቅነት ዓለማችንን በከፍተኛ የማኅበራዊ ቀውስ እየናጣት ይገኛል (2ጢሞ.3፡1-5፤ ማቲ. 24)።

“ሙግታችሁን ይዛችሁ ቅረቡ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ማስረጃችሁን አምጡ” ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። “የሚሆነውን እንዲነግሩን፣ ጣዖቶቻችሁን አምጡ፤ እንድንገነዘብ፣ ፍጻሜአቸውን እንድናውቅ፣ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ነበሩ ንገሩን፤ ስለሚመጡትም ነገሮች ግለጹልን” (ኢሳ. 41፡21-22)።

“እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ” (ኢሳ. 46፡9-10)።

ከዝግጅት ክፍሉ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *