በቻይና የሔናን ጠቅላይ ግዛት በሚገኙ አብያተክርስቲያናት ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ዐሥርቱ ትዕዛዛት በቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ አባባሎች እንዲተኩ ባለሥልጣናት እያስገደዱ መሆናቸው ተሰማ። ውሳኔውን የተቃወሙ ቤተክርስቲያናት እየተዘጉ ነው።
ከሃይማኖት ነጻነት አኳያ በቻይና የሚሆነውን ሁሉ የሚከታተለው Bitter Winter የተሰኘው የድረገጽ መጽሔት እንደዘገበው የቻይና መንግሥት የሚቆጣጠረው “Three-Self Church” ተብሎ የሚጠራው ቤ/ክ ከአምልኮው ቦታ ላይ ዐሥርቱ ትዕዛዛትን አውርዶ በፕሬዚዳንቱ የንግግር ጥቅሶች ተክቷል። ሆኖም ግን ቤ/ክኑ ዘግይቶ በማድረጉ ከባለሥልጣናቱ ወቀሳ ቀርቦበታል። “በማንኛውም መልኩ የሚሰጠውን የፓርቲውን ትዕዛዝ መታዘዝ የግድ ነው፤ ፓርቲው የሚላችሁን ማድረግ አለባችሁ፤ ይህንን እንቃወማለን የምትሉ ከሆነ ቤተክርስቲያናችሁ ወዲያውኑ ይዘጋል” በማለት አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ለምዕመናኑ ባለፈው ሰኔ ወር መናገራቸውን መጽሔቱ ዘግቧል።



ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ምዕመን እንደተናገረው፤ ከእያንዳንዱ Three-Self Church ዐሥርቱ ትዕዛዛት ተነስተው በፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ አባባሎችና ጥቅሶች ተተክተዋል ብሏል። አንዳንድ ትዕዛዙን ተግባራዊ አናደርግም ያሉ ቤተክርስቲያናት ተዘግተው እንደነበር ይኸው አማኝ የተናገረ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ በመንግሥት የጥቁር መዝገብ ውስጥ እንደሚገቡ ተነግሯቸዋል። ይህም ማለት ወደተለያየ ቦታ የሚያደርጉት ጉዞ ውሱን ይሆናል፤ የእነሱና የልጆቻቸው ሥራ፣ ትምህርት እና ሌሎች ለህይወት ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ማለት እንደሆነ ተገልጾዋል። በሌላ አነጋገር ትዕዛዙን አለመቀበል የኮሙኒስት ፓርቲውን መቃወም ተደርጎ እንደሚወሰድ የመንግሥት ባለሥልጣኑ ተናግሯል። “የኮሙኒስት ፓርቲው የመጨረሻ ግብ ራሱን አምላክ ማድረግ ሲሆን ይህ ደግሞ ሰይጣን ሁልጊዜ ሲያደርገው የኖረ ነገር ነው” በማት አንድ ሰባኪ ተናግሯል።
ይህ ለረጅም ጊዜ ሲደረግ የኖረ ተግባር እንደሆነ የዘገበው መጽሔት በተለይ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ” የሚለውን የመጀመሪያውን ትዕዛዝ በቅድሚያ ከየአብያተክርስቲያናቱ እንዲነሳ ተደርጎ ነበር፤ ምክንያቱም ሺ ዢንፒንግ ይህንን ትዕዛዝ ይቃወማሉ። ከሔናን ውጭ ባሉት የአገሪቱ ቦታዎች ዐሥርቱ ትዕዛዛት በማዖ ዜዶንግ እና በሺ ዢንፒንግ ምስሎች እንዲሁም በኮሙኒስት ፓርቲው ፕሮፓጋንዳ እንዲቀየሩ መደረጉ ተዘግቧል።
“አንባቢው ያስተውል”