giziew.org

በዘመናዊ ጥንቆላ ትምህርቶች 61 በመቶ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ያምናሉ

በቅርቡ በተደረገ ጥናት የኒው ኤጅ አስተምህሮ የሆኑ አራት ነጥቦች ለክርስቲያኖች ቀርበውላቸው የሚቀበሏቸው እንደሆኑ ተጠይቀው ነበር። ጥያቄዎቹም፤ ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ባለንበት ዓለም በርካታ ትምህርቶች ለብዙዎች የሥነልቦና፣ የሳይንስ፣ ወዘተ ትምህርት ተደርገው ቢቀርቡም ውስጣቸው በመርዝ ውጫቸው ግን በማር የተለወሱ ናቸው። በተለይ ዘመናዊነትን የሕይወታቸው መመሪያ ባደረጉ ዘንድ እነዚህን ትምህርቶች መቀበል የመዘመን አንዱ መገለጫ ተደርገው ይታያሉ።

ዲፓክ ቾፓርና ኤክሃርት ቶል የመሳሰሉ የዘመናችን ሰዎች በእነ ኦፕራ ዊንፍሬይ እየታገዙ የሚያስተምሩት በማር የተለወሰ የአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ (ኒው ኤጅ) መርዝ ክርስትናን እየበረዘ እንደሆነ ብዙዎች የሚናገሩት ነው። ከዚህ ጋር በተመሳሳይ በአገራችን የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ የመጣው የኦሾ “ፍልስፍና” እየተባለ የሚነገረው የክርስቲያኖችን እምነት እያናጋ የመጣ ከምስራቃዊ የጣዖት ትምህርት የተወሰደ የዘመኑ አስተምህሮ ነው።

ጥናቶች እንደሚመለክቱት ከአሜሪካ ሕዝብ 27በመቶ የሚሆኑት ራሳቸውን “ሃይማኖታዊ ሳይሆን መንፈሣዊ” በማለት የሚጠሩ ሲሆን ከእነዚህም 35በመቶው የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮች ናቸው። በሌላ በቅርቡ በተደረገ ጥናት የኒው ኤጅ አስተምህሮ የሆኑ አራት ነጥቦች ለክርስቲያኖች ቀርበውላቸው የሚቀበሏቸው እንደሆኑ ተጠይቀው ነበር። ጥያቄዎቹም፤

1) በማንኛውም ቁስ ውስጥ መንፈሣዊ ኃይል አለ፤

2) ሳይኪክ (ጥንቆላ በመጠቀም ክስተቶችን የሚናገሩ) ወይም ስለወደፊቱ ለማወቅ ተዓማኒነት ያላቸው ናቸው፤

3) ከሞት በኋላ በሌላ ቅርፅና ይዘት እንደገና ወደ ህይወት መምጣት (ሪኢንካርኔሽን) ይቻላል እና

4) ኮከብ በመቁጠር መጠንቆል (አስትሮሎጂ) ትክክል ነው የሚሉ ነበሩ። ጥያቄው ከቀረበላቸው ሰዎች 62በመቶው ከአራቱ ነጥቦች ቢያንስ አንዱን እንደሚቀበሏቸው ተናግረዋል። ከሁሉ የሚገርመው ግን 61 በመቶ የሚሆኑ ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ ሁኔታ መልስ መስጠታቸው ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራውያን 9፡27 ላይ “ሰው አንድ ጊዜ ሊሞት ከዚያም በኋላ በፍርድ ፊት ሊቆም ተወስኖበታል” የሚል ቢሆንም ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሢሦው ያህሉ ከሞትን በኋላ በአንድም ይሁን በሌላ ተመልሰን ወደዚህች ምድር እንመጣለን ብለው እንደሚያምኑ ጠቁሟል። ይህ የሪኢንካርኔሽን ሃሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ቢሆንም አብዛኛው ክርስቲያን በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ እንደሆነ ነው የተመለከተው።

ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ መናፍስት ጠሪ ወይም በድግምት ወደሚጠነቁል ወይም ሟርተኛ ወይም የወደፊቱን እናገራለሁ ወደሚል እንዳንሄድ በግልጽ ቢናገርም (ዘዳ. 18፡1-12) ከአስር ክርስቲያኖች አራቱ በእንደዚህ ዓይነቱ መናፍስት ጠሪዎች (ሳይኪክስ) የወደፊት ትንበያዎች እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የአዘጋጆቹ ማስታወሻ፤ ከላይ የተጠቀሱት የአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ (ኒው ኤጅ) መምህራን ከድኅረ ዘመናዊነት ጋር የተጣመረ ሰላማዊ አንዳንዴም ክርስቲያናዊ የሚመስሉ ትምህርቶችን ያስተምራሉ። እያንዳንዱ ሰው በውስጡ መልካምነት አለው፤ ያንን ማዳበር ነው የሚገባው፤ እውነት አንድ ብቻ አይደለም ብዙ እውነቶች አሉ፤ ሁሉም ወደሰማይ ያደርሱናል፤ ዋናው ነገር መልካም ማድረግ፣ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር ነው እንጂ የዚህ ወይም የዚያኛው ሃይማኖት ተከታይ መሆን አያስፈልግም፤ ወዘተ የሚሉ ትምህርቶች እውነተኛውን ክርስትና በስልት እያዳከሙት ይገኛሉ። በሚዲያ በስፋት የሚተላለፈውና አዋቂ ነን የሚሉ “የዘርፉ ባለሙያ” እየተባሉ የሚናገሩት በርካታ ክርስቲያኖችን የትኛው የኒው ኤጅ ትምህርት እንደሆነ እንዳያስተውሉ አድረጓቸዋል። በክርስትናውም ዓለም ስሜታዊነት፣ ብልጽግና፣ ታይታነትና የመሳሰሉት ሥር ሰደው ባሉበት ዘመን የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ስለማይሰበክ ሕዝበክርስቲያኑ ከማር ወለላ የሚጣፍጠውን የአምላክን ቃል ከመመገብ ይልቅ አሸዋ እየጠጣ በበረሃ መንከራተቱን የመረጠ ይመስላል። ሐዋሪያው ጳውሎስ በ2ጢሞ. 3፡1-5 ላይ “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ” ከተናገረ በኋላ በዚያ ዘመን የሚኖሩትን ሰዎች ምን ዓይነት እንደሚሆኑ ከዘረዘረ በኋላ “…ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል” ይላል። መፍትሔውንም እዚያው ላይ ሲናገር “ከእነዚህ ራቅ” በማለት ይመክራል። 

“አንባቢው ያስተውል”


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *