“የዘር ጥላቻ” የተጀመረው በእግዚአብሔር ነው! አስደንጋጭ ሃሳብ? ጉዳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ የተደገፈና በቂ ማስረጃ ሊቀርብበት የሚችል ነው።
ግን የትኛው ዓይነት የዘር ጥላቻ? ዓለማችንን ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ምስራቅ አውሮጳ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ሩቅ ምስራቅ እየናጣት ያለው “የእኔ ዘር ይበልጣል” ዓይነት “ጥላቻ”? ወይስ ሌላ ዓይነት? “ዘሩ” ምንድነው? “ጥላቻውስ”?
መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፤
“በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ” (ዘፍጥረት 3፡15)።
ብዙ የማይገቡ የሚመስሉ ጉዳዮች የተወሱበት ጥቅስ ነው። “አንተ”፤ “ሴቲቱ”፤ “እርሱ”፤ “ጠላትነት”፤ “ዘር”፤ … ። በዚህ ብቻ አያቆምም ራስን ስለ መቀጥቀጥ ይናገራል፤ ተረከዝንም እንዲሁ።
በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (ዘፍጥረት) ላይ እንደምናነበው እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት የሚኖርበትን ምድር ስድስት ቀናትን ወስዶ አሰናዳለት። እጅግ ጠንቃቃና ለማስተዋሉ ወሰን የሌለው አምላክ ሰውን የመውደዱ መጠን አስውቦ ባዘጋጀለት ምድር አሳየ።
በመጀመሪያው ቀን (እሁድ)፤ ብርሃንን ከጨለማ ለየ፤ ብርሃኑን “ቀን” አለው፤ ጨለማውን “ሌሊት” (ዘፍ. 1፡1-5)።
በሁለተኛው ቀን፤ ሰማይ የምንለውን “ጠፈር” ፈጠረ፤ ውሃውንም ከጠፈር በላይና በታች አድርጎ ለየው (ዘፍ. 1፡6-8)።
በሦስተኛው ቀን፤ ከሰማይ በታች ያለውን ውሃ ባንድ ሰብስቦ ምድር የምንለውን “የብስ” ፈጠረ፤ ባንድ የተከማቸውንም ውሃ “ባህር” አለው። በምድር ፍሬ የሚያፈሩ ዕፀዋትን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና ዛፎችን ፈጠረ (ዘፍ. 1፡9-13)።
በአራተኛው ቀን፤ ሰዓት፣ ቀን፣ ሳምንት፣ ወር፣ ዓመትና ወቅትን እንዲለዩ ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን በሰማይ ፈጠረ (ዘፍ. 1፡14-19)።
በአምስተኛው ቀን፤ በውሃ የሚኖሮ ዓሦችን፣ በአየር የሚበሩ ወፎችን ፈጠረ (ዘፍ. 1፡20-23)።
በስድስተኛው ቀን፤ በምድር የሚኖሩ የእንስሳት ዓይነቶችን ፈጠረ፤ (ዘፍ. 1፡24-31)። በዚሁ በስድስተኛ ቀን (አርብ) ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረ፤ ወንድና ሴት አድርጎም ፈጠራቸው። ለሁሉም እንዲራቡና እንዲበዙ የመዋለድን በረከት ሰጣቸው።
በሰባተኛው ቀን ሁሉ ተሰናድቶ ስላለቀ፤ የተፈጠረው ሁሉ “እጅግ መልካም” ስለነበር እግዚአብሔር መፍጠር አቆመ፤ የሰንበት ዕረፍት ሆነ፤ አዳምም ህይወቱን በዕረፍት ጀመረ! “እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ ወይም አቈመ። ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና” ዘፍ. 2፡2-3። በነዚህ ሁለት ጥቅሶች ላይ “ሰባተኛው” የሚለው ቃል አራት ጊዜ መደጋገሙን ልብ ይሏል። በድግግሞሽ ሃሳብ ይቀረጻል ይባላል፤ ሰንበትን እንዳንረሳው ሲያሳስበን ይሆን? (ዘጸአት 20፡8)
የፈጠረውን ሰው የምድር ገዢ አደረገው (ዘፍ. 1፡28)። በምድር ላይ ባሉ ማናቸውም ነገሮች ላይ ሥልጣን ሰጠው። የምድር ንጉሥ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “የክብርንና የሞገስን ዘውድ አቀዳጀኸው” ይላል መዝሙረ ዳዊት 8፡5። ሲቀጥልም እግዚአብሔር በሁሉ ላይ እንደሾመው እንዲህ በማለት ያስረዳል፤ “በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛህለት፤ በጎችንና ላሞችን ሁሉ፣ የዱር አራዊትንም፣ የሰማይ ወፎችንና፣ የባሕር ዓሦችን፣ በባሕር ውስጥ የሚርመሰመሱትንም ሁሉ አስገዛህለት” (መዝ. 8፡6-8)።
አዳም እንደ ገዢነቱ “ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው”። በመሆኑንም “አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ” (ዘፍ. 2፡19-20)።
ይህ የገዢነት ሥልጣን የተሰጠው ሰው ተጠሪነቱ ለእግዚአብሔር ነበር። ፈጣሪውን በፈቃዱ ለመታዘዝና ለእርሱ ለመገዛት መወሰን ነበረበት። እግዚአብሔር ስለፈጠረው ብቻ በግድ መገዛት ስላልነበረበት የመወሰን፣ የመታዘዝ፣ ያለመታዘዝ፣ የማሰብ፣ የማመጽ ፍጹም ነጻነት እግዚአብሔር ሰጠው። ይህ ስጦታ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር የተሰጠ ልዩ መብት ነው። እግዚአብሔር ይህንን ነጻነት በሰው ውስጥ ሲያስቀምጥ ሰው አልታዘዝም ብሎ ቢያምጽ ጌታ አምላክ ዕዳውንም አብሮ ለመቀበል የወሰነ መሆኑን ልንጠራጠር አንችልም።
“እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው (ኤድን ገነት) ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ” (ዘፍ. 2፡16-17)።
ይህ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ በጣም ቀላል፣ አጭርና ፍጹም ግልጽ ነበር። ሰዎች እንደሚያስቡት የአምላክ ትዕዛዝ የተወሳሰበና ለመረዳት የሚያስቸግር ሆኖ አያውቅም። ችግሩ ያለው ላለመታዘዝ ስንፈልግ ትዕዛዙ እንዳልገባን ማስመሰላችን ላይ ነው። የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ደግሞ እንደ ምድር ገዢዎች ሰውን የመጨቆኛ ወይም መብት የመንፈጊያ መሣሪያ ሳይሆን የፍቅር መመሪያ ነው። የምንወደው ሰው እንድናደርግ የሚጠይቀንን ነገር “ትዕዛዝ” ብለን እንደማንጠራው፤ እንዲያውም የጠየቀንን ብቻ ሳይሆን ያልጠየቀንን ጭምር በደስታ እንደምንፈጽም ሁሉ የእግዚአብሔርም ሕግ እንዲሁ ደረቅና ጨካኝ ትዕዛዝ አይደለም። “ፍቅር የሕግ ፍጻሜ (መፈጸሚያ) ነው” (ሮሜ 13፡10)።
ስለዚህ ሰው በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚገዛ መሆኑን ለመወሰን እግዚአብሔር የሚበላውን ዓይነት ሁሉ ለሰው ሰጥቶ ከዚያ ውስጥ አንዷን ዛፍ የራሱ አደረገ። ሰውንም “ባለመብላት” ለጌታው እንዲታዘዝ በፍቅር ለመነው። ራበኝ፤ አይበቃኝም እንዳይል የምድር ሁሉ ተክል የእርሱ ነው። ጌታ ነው፤ ንጉሥ ነው፤ ምንም የቀረበት ነገር የለም፤ በስድስቱ ቀናት ያልተሟላለት ነገር የለም፤ የተሰናዳ ቤት ውስጥ ነበር የገባው፤ እጅግ ውብ ዕጹብና ድንቅ የሆነች ምድር ነው የተሰጠው! ምን ጎደለው? ከሚበላው ዛፍ ሁሉ ሰጥቶ አንዲቱን ብቻ አትብላ እንዳለው ሁሉ እንዲሁ ከሰባት ቀናት ውስጥ ስድስቱን ለሰው ልጅ ሰጥቶ ሰባተኛውን ቀን “ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው” ማለቱን መዘንጋት የለብንም (ዘጸአት 20፡10)። ለእግዚአብሔር የተባለ ነገር ሁሉ ቅዱስ ነው፤ ቁርባን ነው፤ አይነካም። አምላካችንም ከበቂ በላይ ሳይሰጥ አንዱን ለእኔ የሚል አመጸኛ አይደለም።
በኤድን ገነት የሰው ልጅ ከመቀመጡ በፊት የብርሃን መልዓክ የነበረው ሉሲፈር በዓመጹ ዲያቢሎስ ሆኗል። የእግዚአብሔር የሆነውን ለራሱ ለማድረግ በማሰብ ከአምላኩና ፈጣሪው በላይ ለመሆን በመወሰን ፍቅርን ገልብጦ ሥልጣን በግድ መያዝ ፈለገ። እንዲህ ነበር የተመኘው “ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት (መላዕክት) በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤ … ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ” ኢሳ. 14፡13-15። ፍጡር መሆኑን ዘንግቶ ራሱን ፈጣሪ እግዚአብሔር ማድረግ ፈለገ፤ “እንደ እግዚአብሔር መሆን” ተመኘ! የተሰጠውን የመምረጥ ነጻነት ክፉ ለመምረጥ ተጠቀመበት።
ሉሲፈር ይህንን በፈቃዱ እንዳደረገ ሁሉ ሰውም እንዲሁ በእግዚአብሔር በመፈጠሩ ብቻ ለእግዚአብሔር መገዛት ስለሌለበት በፍቅር ለመታዘዝ ውሳኔ ማድረግ ነበረበት። ሠይጣን አለመታዘዝን በመምረጡ ክፋት ስለመጣ እግዚአብሔር “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ” በማለት ለሰው ተናገረ (ዘፍ. 2፡17)።
ጉዳዩ ያለው የአንድ ዛፍ ፍሬ ከመብላትና ካለመብላት ሳይሆን ፈጣሪ አምላክን “አምንሃለሁ” ከማለት፤ ከመታዘዝና ካለመታዘዝ የፈቃድ ውሳኔ ጋር የተገናኘ ነው። በሌላ አነጋገር ከበላ ከክፉው ጋር ይወግናል ማለት ነው። ክፉው ዲያቢሎስ ደግሞ ነፍሰ ገዳይና የሃሰት አባት ነው (ዮሐ. 8፡44)። ከእርሱ ጋር መወገን ደግሞ ሞትን ያመጣል። ስለዚህ ለሰው ልጅ ፈጣሪውን መታዘዝ ለዘላለም በህይወት እንዲኖር የሚያደርግና የምድር ንጉሥነቱን የሚያስቀጥልለት ሲሆን አልታዘዝም ብሎ በፈቀደው መንገድ መሄድ ደግሞ ላሳሳተው መታዘዝ፣ ንግሥናውን አሳልፎ መስጠትና ሞትን መምረጥ መሆኑ በግልጽ የተቀመጠ ጉዳይ ነበር። የውሳኔ ሰዓት ሲደርስ የሰው ልጅ በአፍቃሪ አምላኩ ላይ አመጸ!
በእባብ የተመሰለው ዲያቢሎስ ሰውን አሳሳተ። እርሱ እንደ እግዚአብሔር ለመሆን (“ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ” በማለት) እንደተመኘው ሁሉ ይህንኑ የሐሰት ምኞት ለሔዋን በመንገር አታለላት። እግዚአብሔር “አትብሉ” ብሎናል፤ ከበላን እንሞታለን በማለት ሔዋን ስትናገር፤ የሐሰት አባት የሆነው ሰይጣን “መሞት እንኳን አትሞቱም” በማለት እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ለማድረግ ሞከረ። ከዚያ አልፎም፤ ይልቅ እግዚአብሔር ከእናንተ የደበቀውና የከለከለው ነገር አለ፤ ዓናችሁን አሳውሮታል፤ ስለዚህ አሁን አታዩም፤ ይህንን ፍሬ ብትበሉ ግን ዓይናችሁ እንደሚከፈት እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው በማለት ገና ከጅምሩ የእርሱ ምኞት የሆነውን ሃሳብ በመንገር ሔዋንን አጠራጠራት፤ ቀጥሎም አሳመናት (ዘፍ. 3፡1-7)።
እርሷም ለእግዚአብሔር የማትታዘዝ መሆኗን በመብላት አሳየች፤ ባሏም የእርሷን ፈለግ በመከተል የእግዚአብሔርን ሕግ ተላለፈ። ዓይናቸው ሲከፈት ግን እንደ እግዚአብሔር ሳይሆን አምላካቸው ያለበሳቸው የክብር ብርሃን ሲገፈፍና ራቁት ሲሆኑ ነው ያዩት። በውጤቱም አዳም ለዲቢያሎስ በመታዘዝ ንግሥናውን ላታለለው ለሰይጣን አስረከበ፤ ሰይጣንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ “የዚህ ዓለም ገዢ” ሆነ (ዮሐ. 14፡30 እና ማቴ. 4፡8-9)።
“ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ”(ሮሜ 5፡12)።
ከዚህ በፊት ከአምላካቸው ጋር በደስታ ይኖሩ የነበሩት አዳምና ሔዋን አሁን ፍርሃት የሚባል አዲስ ነገር ጨመደዳቸው። የእግዚአብሔር አባታቸውን ድምጽ ሲሰሙ ወደ አባታቸው በደስታ መሄድ አስፈራቸው። “አዳም ወዴት ነህ?” ብሎ እግዚአብሔር እስኪጠይቀው ድረስ አዳም ከአባቱና ከፈጣሪው ተደበቀ። ለጥያቄው ሲመልስም ከዚህ በፊት ምን እንደሆነ የማያውቀውን አዲስ ነገር ተናገረ፤ “ፈራሁ” አለ (ዘፍ. 3፡10)። በዚህ ብቻ አላቆመም። “ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” በማለት በደስታ የመሰከረላትን ሚስቱን ሔዋንን እና ጌታ አምላኩን በጅምላ ወነጀላቸው (ዘፍ. 2፡23)። “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ (ዘፍ. 3፡12)። ፈጽሞ አስቦት የማውቀው አዲስ ነገር – ፍርሃት፣ ውንጀላ፣ ክስ!
ሔዋንም በተሰጣት የኅሊና ነጻነት ተጠቅማ እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ይልቅ እባቡ አሳስቷት ለሰይጣን ለመገዛት መወሰኗን “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” ስትል ገለጸች። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ከጠየቀ በኋላ ከእግዚአብሔር በላይ እሆናለሁ፤ ዙፋኔን ከፍ አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ራሴ እግዚአብሔር እሆናለሁ በማለት ያመጸውንና አሁን ደግሞ በእባብ ተመስሎ ሔዋንን ያሳተውን ሰይጣንን ግን ምንም የሚጠይቀው አልነበረም። አስቀድሞ አቋሙን ገልጾዋል።
እግዚአብሔር እንደፈጣሪነቱ ኃላፊነት የሚወስድ አዳኝም ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ ሲናገር “ሁሉ ነገር በእርሱ (በክርስቶስ) ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ … ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል” ይላል (ቆላስይስ 1፡16-17)። በክርስቶስ በዕቅድ ሁሉን ነገር እንደፈጠረ ሁሉ አሁን ደግሞ ኃላፊነት ወስዶ “መድኃኒዓለም” የሚሆንበትን ዕቅድ ይፋ አደረገ። አዳም በሰይጣን የተነጠቀውን ለማስመለስ እግዚአብሔር የመጀመሪያውን “የጠላትነት” ዕቅድ አስተዋወቀ። እንዲህ አለ፤
“በአንተ (በእባብ በተመሰለው ሰይጣን) እና በሴቲቱ (የህያዋን ሁሉ እናት በሆነችው ሔዋን)፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ (የሴቲቱ ዘር) ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም (ሰይጣን) ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ” ዘፍ. 3፡15።
ጌታ የነደፈው ዕቅድ ግልጽ ነው። ከዚህ በኋላ ውዝግቡ (ጠላትነቱ) በሦስት መስመሮች የሚካሄድ ይሆናል። በሰይጣንና በሴቲቱ መካከል፤ የሰይጣንን መንገድ በሚከተሉ የክፉው ዘር (“የሰው ልጆች”) እና የእግዚአብሔርን መንገድ በሚከተሉ የመልካሙ ዘር (“የእግዚአብሔር ልጆች”) መካከል፤ ሦስተኛውና ዋናው ግን የሰይጣንን ራስ በሚቀጠቅጠው የሴቲቱ ዘር ክርስቶስ እና የእርሱን ተረከዝ በሚቀጠቅጠው ሰይጣን መካከል ይሆናል።
ይህ የሰይጣንን ሥርዓት ከሥሩ ያናጋ የ“ጠላትነት” ዕቅድ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ “ጠላትነት” ምክንያት የሰይጣን ራስ ይቀጠቀጣል! ሰይጣንም ይህንን በይፋ የተደገሰለትን ሰምቶ ዝም የሚል ጠላት አለመሆኑን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማሳየት ጀመረ!
ይህ “የዘር ጥላቻ” ባይመሠረት ኖሮ አዳም ያስረከበውን ገዢነት ለዘላለም በማጣት የእርሱ ዘሮች በሙሉ በዘላለማዊ ኩንኔ ውስጥ ይወድቁ ነበር። ምክንያቱም አዳምን ያሸነፈው የክፉው ኃይል ያለከልካይ በዚህች ምድር ላይ በመንሰራፋት የእግዚአብሔር የሆነ አንዳች ነገር እንዳይኖር ያደርግ ነበር። ነገርግን አምላክ ይህንን “ጠላትነት” በሁለቱ ዘሮች መካከል በማድረጉ በጠላት ወረዳ ውስጥ (በዚህች ምድር) ለእግዚአብሔር የሚታዘዙ ሊኖሩ ችለዋል፤ አሁንም አሉ፤ እስከ ዳግም ምፅዓት ወደፊትም ይኖራሉ። እንዲህ ዓይነት ታማኞች እንዲኖሩ ያስቻለው ደግሞ “ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር ‹ለዘሮቹ›” የተባለለት ሳይሆን “ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ ‹ለዘርህ›” የተባለለት “እርሱም ክርስቶስ ነው” (ገላ. 3፡16)።
በሚቀጥለው ዕትማችን ሰው ከኤድን ገነት ከተባረረ በኋላ “በዘርህና በዘሯ መካከል” ተብሎ የተነገረውንና ወዲያውኑ የተጀመረውን “ጠላትነት” እንዳስሳለን።
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ