giziew.org

ጾም እና ጤና

በአይሁድ፣ በክርስትና፣ በእስልምና፣ … ሃይማኖቶች መጾም የእምነቱን ሥርዓት የመከወን አንዱ ተግባር ነው። በቅዱስ መጽሐፍ እንደተወሳው መጾምና መጸለይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ይህ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሚገኘው አብዛኛው ህዝበ ክርስቲያን በጾም ላይ ያለበት ጊዜ ነው። በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ቀናት በመጾም የምናሳልፍ በርካታ ክርስቲያኖች ያለን ቢሆንም ይህ ወቅት ግን በብዙዎች ዘንድ በልዩ ሁኔታ ዐቢይ ጾም ተብሎ ይታወሳል። ዛሬ መጋቢት 24፤ 2014 ዓም ደግሞ ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ጾምን ይጀምራል። እንግዲህ ይህ ሁሉ ሕዝብ የሚከተለውን የሃይማኖት ትዕዛዝ አክብሮ፣ ለመንፈሳዊ ዓላማ ሲል ራሱን ከምግብና ከመጠጥ ለተወስነ ጊዜ ይከለክላል። መልካም ነው! ሁሉም በየእምነቱ ሲተጋ፣ ላመነበት ነገር ዋጋ ሲከፍል፣ ከምድራዊና ሥጋዊ አጀንዳ አስበልጦ የፈጣሪ ትዕዛዝ ነው ብሎ ያመነበትን ሃይማኖታዊ ልምምድ ለመፈጸም ሲጥር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚበረታታ ተግባር ነው። በመሆኑም ይህንን መልካም ሃይማኖታዊ ትግበራ እንደጥሩ አጋጣሚ አስበን በዚህ ዕትም ለጤናችን ዓምድ ላይ የጾምን የጤና ጠቀሜታዎች ለዳሰሳ ይዘን ቀርበናል።

እኛ ሰዎች በየምናምንበት የእምነት ስርዓት ስንጾም ከምናገኘው ሃይማኖታዊ በረከት ባሻገር፣ እንድንጾም የሚያበረታቱን ምን ምን የጤና ጠቀሜታዎች ይኖሩ ይሆን?  

የጥንት ግብጻውያን የሚጥል በሽታ (Epilepsy) ያለበትን ሰው በባዶ ቤት ውስጥ ዘግተው ምግብ በመከልከል ለማከም ይሞክሩ እንደነበር መዛግብት ይገልፃሉ። ምንም እንኳን ይህን ሲያደርጉ በወቅቱ በቂ ሳይንሳዊ ማስረጃ ባይኖራቸውም፣ ተግባራቸው ግን ተቀባይነት ያለው ሊሆን እንደሚችል የዚህ ዘመን ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይኸው የሚጥል በሽታ (Epilepsy፣ ጋኔን ተብሎ የተጠቀሰ) በመጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌላት ውስጥ ተጽፎ እናነባለን። ኢየሱስ ያን ብላቴና ከፈወሰ በኋላ “እንዲህ ዓይነቱ ወገን በጦምና በጸሎት ካልሆነ በቀር ሊወጣ አይችልም” ሲል ለደቀ መዛሙርቱ መናገሩ የጾምን መንፈሳዊ ጠቀሜታ ሳንስት የጤናንም ጠቀሜታ እንድናጤን ጥያቄን ያጭርብናል፤ ካልጫረብንም ግን ችግር የለውም።

የሆነው ሁኖ አሁን አሁን እየመጡ ያሉ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች፣ ጾም ለጤናችን ቀላል የማይባል ጠቀሜታ እንዳለው ያሳያሉ። እነዚህን የጾም የጤና ጥቅሞች ዘርዘር አድርገን ከመመልከታችን በፊት ግን ጾም ምንድን ነው? ጾም በምንጾምበት ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የሚሉትን ጥያቄዎች እንመለከታለን። በመጨረሻም ለጤናችን ጥቅማቸው የተረጋገጡ የጾም ዓይነቶች ምን ምን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ መልሰን፣ ትንሽ የጾምን መንፈሳዊ ጥቅም አውስተን ዳሰሳችንን እንጨርሳለን።

ጾም ምንድን ነው?

በዚህ ጽሑፍ እያየን ያለነው ጾም፣ በፈቃዳችን ለጤናችን ጥቅም ሲባል ራሳችንን ለአጭር ጊዜ ከምግብ መከልከልን የሚገልጽ ሲሆን፤ በአንጻሩ ግን በምግብ እጦት ሳቢያ መራብን፣ ያልተመጣጠነ የአመጋገብ ዘይቤ መከተልን፣ የረሃብ አድማን፣ ወይም በጤና ባለሞያ ጾም እንዳይጾም የተከለከለ ሰውን፣ ወዘተ… አያጠቃልልም። ለሃይማኖታዊ ዓላማ ብለን በምንጾምበት ጊዜ ደግሞ ጤናችንን በማይጎዳ መልኩ ካደረግነው በዚህ ጽሑፍ የተዘረዘሩትን የጾም ጠቀሜታዎች በማግኘት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደመምታት ያህል ነው።

ጾም በምንጾምበት ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ ምን ይከናወናል?

የሰውነታችን አብዛኛው የኃይል ምንጭ ግሉኮስ (Glucose) ከሚባል ስኳር የሚገኝ ነው። ይህ ስኳር በጉበታችንና በጡንቻዎቻችን ውስጥ በጊዜያዊነት በግላይኮጅን (Glycogen) መልክ ይጠራቀማል። ሆኖም ከግማሽ ቀን በላይ ምግብ የማንመገብ ከሆነ የተጠራቀመው ስኳር ሥራ ላይ ይውልና ያልቃል። በዚህን ጊዜ በጡንቻዎቻችንና በስብ መልክ ተጠራቅመው ካሉ ሌሎች እንደ ፕሮቲንና ቅባት የመሳሰሉ የኃይል አማራጮች ግሉኮስ መመረት ይጀምራል። ነገር ግን ከሁለት እስከ አምስት ባሉት ቀናት ውስጥ ምግብ ካልተመገብን የሰውነታችን የኃይል ምንጭ ከግሉኮስ ወደ ኪቶን ቦዲስ (Ketone bodies) ይዛወራል። ኪቶን ቦዲስ ከቅባት የሚሠሩ፣ በተለይም ለአንጎላችንና ለደም ሕዋሶቻችን ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው የኃይል ምንጭ ናቸው። በጣም በተራዘመ ጾም ወይም ረሃብ ይህ የሰውነታችን የኃይል ማስገኛ መንገድ እየተዳከመ የኃይል ዕጥረት ይከሰታል። በመሆኑም የሰው ልጅ ያለ ምግብ ከአርባ እስከ ስድሳ ቀናት ብቻ በሕይወት ሊቆይ የሚችል ሲሆን፤ ያለ ውሃ ግን ከሦስት ቀን በላይ መቆየት ያስቸግራል።

የጾም የጤና ጥቅሞች

በምንጾምበት ጊዜ ጨጓራችንን ጨምሮ ሌላው የአንጀታችን ክፍል ምግብን ከመፍጨት ዕረፍት ያገኛል። ሰውነታችንም  ምግብ ከመፍጨትና ከማጓጓዝ ትኩረቱን የተበላሹ ሕዋሶችን በማስወገድ ራሱን ወደ መጠገን ያደርጋል። በመጾማችን ምክንያት በአእምሯችን ላይ በሚደርስ አወንታዊ ጫና የተለያዩ የነርቭ ሴሎች ይፈጠራሉ። ጉዳት ሊያስከትል ይችል የነበረ የተጠራቀመ ስብም ለኃይል ምንጭነት ስለሚያገለግል ጉዳቱ ይቀራል።

በመሆኑም ስንጾም$

  • ውፍረት እንቀንሳለን
  • ጎጂ የደም ውስጥ ቅባት (ኮሌስተሮል) ይቀንሳል
  • ብግነትን (inflammation) ይቀንሳል
  • ለኳስርና ለደም ግፊት በሽታ መጋለጣችን ይቀንሳል
  • በአንጀት ካንሰር የመጋለጥ ዕድል ይቀንሳል
  • የማስታወስ ችሎታችን ይጨምራል
  • ዕድሜያችን ይጨምራል

የጾም ዓይነቶች

ለሃይማኖታዊ ዓላማ የሚጾሙ ልዩ ልዩ የጾም ዓይነቶች እንዳሉ ቢታወቅም፣ ለጤናችን ጠቀሜታ ግን በሚከተለው መንገድ በአንዱ ብንጾም ተመራማሪዎች ይመክራሉ።

ሀ) 16/8 ሰዓት መጾም፤ ይህማለት በቀን ውስጥ ማለትም በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ለተከታታይ 16 ሰዓት ምግብ አለመመገብ ማለት ሲሆን በቀሪው ስምንት ሰዓት ግን በተለመደው የአመጋገብ መንገድ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ማለት ነው። በቀን አንዴ ብቻ የሚመገቡ ሰዎችና ለሃይማኖታዊ ዓላማ ብለው የሚጾሙ ብዙ ሰዎች ይህን ዓይነት ጾም ከሚጾሙት ልንመድባቸው እንችላለን። ይህን የጾም ዓይነት እንደየችሎታችን በየቀኑ፣ በሳምንት ሁለቴ፣ ወዘተ… አድርገን ልንጾም እንችላለን። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ምግብ በምንመገብበት ጊዜ የጾምንበትን ሰዓት ለማካካስ ከመጠን በላይ አብዝተን መመገብ እንደሌለብን ነው።

ለ) በየሳልስቱ መጾም ይህ የጾም ዓይነት ደግሞ በየሳልስቱ ማለትም አንድ አንድ ቀን እየዘለሉ ለሃያ አራት ሰዓት መጾም ነው። በማንጾምባቸው ቀናት በተለመደው የአመጋገብ መንገድ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አለብን። ይህንንም የጾም ዓይነት እንደ ችሎታችን ደጋግመን ስንጾም ጥቅሙን እናገኛለን።

ሐ) በሳምንት ሁለት ጊዜ መጾም ይህ የጾም ዓይነት በሳምንቱ አምስት ቀናት በተለመደው አመጋገባችን እየተመገብን በቀሪው ሁለት ቀናት ግን በሌሎች አምስት ቀናት ከምንመገበው ሩቡን (አንድ አራተኛውን) ብቻ መመገብ ማለት ነው።

መ) ሌሎች ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ ሌሎች ለጤናችን የሚጠቅሙ የጾም ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም* ሥጋና ሌሎች  እንስሳት ተዋጽዖን ብቻ መጾም፣ ቀለል ያሉ ምግቦችን እየተመገቡ መጾም፣ የመሳሰሉት ናቸው።

ከላይ ባሉት የጾም ዓይነቶች በአንዱም ሆነ በሌላው መንገድ ለመጾም ብንመርጥ፣ የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ልብ ልንል ይገባል።

  • ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ መጾም አይመከርም
  • ስኳርን ጨምሮ ሌሎች የታወቁ ሕመሞች ያሉበት ሰው በመጾም የሚገኙ የጤና ጥቅሞችን ማግኘት ቢችልም፣ በጤና ባለሞያ ምክርና ክትትል መሆን አለበት
  • የትኛውንም የጾም ዓይነት ብንከተል፣ በቂ ውሃ መጠጣት እንዳለብን ይመከራል
  • በጣም የተራዘመ ጾም ለጤናችን ጠቃሚ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም

ጾመ ሃይማኖት

አሁን ደግሞ ከጾመ ጤና (ለጤናችን ከሚደረግ ጾም) አለፍ ብለን፣ ጾመ ሃይማኖትን (ለሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ዓላማ የሚደረግ ጾም) በአጭሩ እንመልከት። በጽሑፋችን መግቢያ ለመጥቀስ እንደሞከርነው በፈቃድ የመጾም ልምምድ መጀመሪያውንም ሲጀመር ዓላማው ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ነው። በአይሁድ፣ በክርስትና፣ በእስልምና፣ በቡዲዝም… ሃይማኖቶች መጾም የእምነቱን ሥርዓት የመከወን አንዱ ተግባር ነው። በቅዱስ መጽሐፍ እንደተወሳው መጾምና መጸለይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው። ነብያቱም ሐዋሪያቱም ይጾሙና ይጸልዩ እንደነበር ተመዝግቧል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ያለ ምግብ እንደጾመ እናስታውስ።

ስለዚህ ጾመ ሃይማኖትን ስንጾም፣ መጾማችን አስፈላጊ ነውና፣ ጥቅሞቹን ብናውቅ ይበልጥ መጾማችንን እንወደዋለን። ጾመ ጤና ያን ያህል ለአካላዊ ጤና ጠቀሜታ ያለው ነገር ከሆነ፣  ጾመ ሃይማኖትማ ለመንፈሳዊ ጤናችን እንዴት አብልጦ አይጠቅመን?

ስንጾም፡-

  • ከጨጓራችን ይልቅ አእምሯችን ይበልጥ ይሠራል፣ ብሩኅ ይሆናል። ይህ ደግሞ መንፈሳዊን ነገር በደንብ ለመረዳት ይረዳናል።
  • በአካላችን አላስፈላጊ የሆኑና የሞቱ ሕዋሶቻችን ተወግደው ዕድሳት እንደሚካሄድ፣ እንዲሁም ኅሊናችን በንስሐና በጸሎት ከኃጢያት ይነጻል፣ ከፈጣሪያችን ጋርም በተለየ ሁኔታ የመነቃቃትና የመታደስ ጊዜ ይኖረናል።
  • አካላችን ከግሉኮስ በተሻለ ከኪቶን ቦዲስ ኃይል እንደሚያገኝ፣ እንዲሁም ከተለመደው በላይ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እንቀበላለን።
  • በመንፈሳዊ ሕይወታችን ድካምን የሚፈጥሩ የኑሮ ጫናዎችን መቋቋም እንችላለን።
  • ወዘተረፈ…

መልካም ጾም ይሁንልን!!

ሐኪም አበበ ምህረት


2 thoughts on “ጾም እና ጤና”

  1. I would like to follow and have a knowledge of the Bible throughout your organization and how can I get it?

    1. Dear Tamiru Buche

      Thank you for your message. We have a weekly Bible discussion broadcasted on Hope Channel Ethiopia and posted here on our YouTube channel.

      Right now we are studying the Gospel of John.

      Please let us know if you have more questions.

      Thanks
      Editor

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *