giziew.org

ከነቢይም ሁሉ የሚበልጥ

ይህ ከነቢይም ሁሉ የሚበልጥ እንደተባለለት ሰው ምድራዊ ምቾትና የገንዘብን ፍቅር የካዱ ነቢያትና ሐዋርያት ዛሬ የማናየው ለምንድነው? መንፈስ ቅዱስ በዘመናት አሠራሩን ቀይሮ ይሆን?
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ሰዎች ለመዳን የልብ ዝግጅት ማድረግ ነበረባቸው። የሰው ተፈጥሯዊ ራስወዳድነት በሰማያዊ ፍቅር፤ ትዕቢት ደግሞ በትህትና መተካት ነበረበት። ሰውን ከአምላክ የለየው የልብ መደንደን ስለነበረ በድንጋያማው የሰው ስሜትና አስተሳሰብ ውስጥ የፈጣሪ ርኅሩኅ ሃሳብ የሚገባበት መንገድ መዘጋጀት ነበረበት።

ያንን ቀና መንገድ በራሱ መቀየስ የሚችል ሰው ግን የለም። “እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድም እንኳ፤ አስተዋይ የለም፤ አግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም” (ሮሜ 3:10-11)። በዚህ ምክንያት ጌታ ራሱ ይህን ከባድ ኃላፊነት እንዴት እንደሚወጣው በነቢዩ ሚልክያስ በኩል ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ በፊቴ መንገድ እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ” (ሚል. 3:1)።

ያ ትንቢት ተነግሮ አራት መቶ ዓመታት ከተቆጠሩ በኋላ ከአምላክ ጋር ጥብቅ ግኑኝነት የነበረው ዘካርያስ የተባለ ትሁት ካህን እንደ ኦሪት ደንብ ዕጣን ለማጠን ወደ ቤተመቅደስ ገባ። ወደ ዕጣኑ መሰውያም ሲደርስ ያልጠበቀው እንግዳ አገኘው፤ መልአከ ገብርኤልን አይቶ ፍርሃት ዋጠው። “መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ ‘ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል። ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል’” (ሉቃ. 1:13-17)።

ቅዱስ ገብርኤል ለዘካርያስ የተናገረው ነገር የሚልክያስና የኢሳያስ ትንቢቶች ፍጻሜ ነው (ኢሳ. 40:3)። ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከመገለጡ በፊት “ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት” የተመረጠው ሰው ዮሐንስ ነበር። ይህ ዮሐንስ ተራ ሰው አልነበረም። ገና በእናቱ “ማህፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል” ተብሎለታል (ሉቃ. 1:15)። ይህ ማለት ዮሐንስ ራሱን ገና ሳያውቅ ተልዕኮውን ለማሟላት የሚያስችለው መለኮታዊ ኃይል መርቶ ያሳድገዋል ማለት ነው።

“በኤልያስ መንፈስና ኃይል በጌታ ፊት ይሄዳል” የተባለው ዮሐንስ በእርግጥም ተራ ሰው አልነበረም። ቅዱስ ገብርኤል ስለ ማንነቱ ሲናገር “በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል” ብሏል። የታላቅነቱ ምሥጢር ደግሞ ከመፀነሱ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱ ነው። ይህን ሰው ተጠቅሞ ነው እግዚአብሔር “የማይታዘዙትን ወደ ፃድቃን ጥበብ” ለመመለስ የተሰናዳው።

በምድር ታላላቅ የሚባሉ ሰዎች ገድላቸው ብዙ ነው። በከንቱ ደም ያፈሰሱ ወይም የሚያስጎመጅ ሀብት ያፈሩ ሰዎች ይከበራሉ። በጥበባቸው ዓለምን ያስደነቁ ተመራማሪዎች በተለያዩ ሽልማቶች ይዋባሉ፤ በሕይወት የሌሉቱም ይዘከራሉ። በጌታ ፊት ታላቅ የሆኑትስ?

ዮሐንስ የወይን ጠጅና ሌሎች አስካሪ መጠጦችን ቀምሶ አያውቅም። ስለሆነም አእምሮውና መንፈሱ የተሳሉ ነበሩ። ምግቡም ቢሆን ምላስን አታልለው ጤና በሚያውኩ የጥብስ ቅባቶችና ሰው ሰራሽ ስኳር የተበላሸ አልነበረም። መብሉ ለሆድ የሚቀል፤ በኦሪት የተፈቀደው “አንበጣና የበረሃ ማር ነበር” (ማቴ. 3:4)። የተጎናፀፈው ደግሞ የነገሥታትን ሐምራዊ ካባ ሳይሆን የግመል ጠጉር ነበር፤ የወገቡም ቀበቶ ጠፈር ነበር።

ዮሐንስ በአበላሉና በአለባበሱ ጠንቃቃ የነበረው ግብዝ በሆነ ትህትና የሰዎችን ቀልብ ሊስብ ፈልጎ አይደለም። ለጥቂት ጊዜ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ራሱን ገዝቶ የተጠራበትን ታላቅ ዓላማ ለመፈፀም ፅኑ ጉጉት ስለነበረው ነው። ኑሮው ሆድን በማጥገብ፣ በመጠጥና በመዝናናት ላይ ያተኮረ ሳይሆን፤ መንገድ ጠራጊ በመሆን ሰዎች ክርስቶስን እንዲቀበሉ ለማዘጋጀት በቅዱስ ጽሞና ላይ የቆመ ነበር። ይህ ደግሞ አደንዛዥ ከሆኑ ምድራዊ ፍላጎቶች ተላቅቆ ራስን በቃሉ ወደ መመርመርና በማያቋርጥ ጸሎት ኃይል ወደ አምላክ መቅረብን ግድ ይላል። ዮሐንስ ለሥጋው ሳይሆን ለነፍሱ ያደረ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሰው ስለነበር አኗኗሩ በመለኮታዊ ሥልጣን ሥር ነበር። መብል፣ መጠጥና አለባበሱ ለጌታ የመጀመሪያ ምጽዓት የሚያዘጋጁ ነበሩ። 

እስቲ ይህንን ለነፍሱ ያደረ ለእግዚአብሔር የኖረ ታላቅ የእምነት ሰው በዚህ ዘመን ታላላቅ ከሚባሉ ነቢያትና ሃዋርያት ጋር እናነጻጽረው? በዘመናችን የጌታ ዳግም ምጽዓት መቃረቡን የሚያሳዩና ለዚያ ደግሞ መንገዱን እንድንጠርግ የሚጠቁሙ ብዙ ምልክቶች እያየን ነው። ፍጻሜ ዓለም የሚሆንበት የክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ደግሞ ከመጀመሪያው ምጽዓት የበለጠ ዝግጅት እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። ታዲያ እንደ ዮሐንስ ምድራዊ ምቾትና የገንዘብን ፍቅር የካዱ ነቢያትና ሐዋርያት ዛሬ የማናየው ለምንድነው? መንፈስ ቅዱስ በዘመናት አሠራሩን ቀይሮ ይሆን?

መለኮታዊ ሕይወት ልዩ ኃይል አለው። ዮሐንስ አጥብቆ የሚስብ ሕይወት ነበረው። ቃሉ እንደሚለው “ከኢየሩሳሌም፣ ከመላው ይሁዳና በዮርዳኖስ ዙሪያ ካለው አገር ሁሉ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይጎርፉ፣ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ ይጠመቁ ነበር” (ማቴ. 3:5-6)።

በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሰው የሚሠራው የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ነው፤ ያ መንፈስ ሲገለጥ ደግሞ “ዓለምን ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሳል” (ዮሐ. 16:8)።

ርኩሰት እንደ ጽድቅ በሚቆጠርበት በዚህ የተገላቢጦሽ ዘመን፤ ኃጢአተኞች ከልብ እየተናዘዙ ቢጠመቁ ምንኛ ምድሪቱ ሰላም ታገኝ ነበር! ግን ሰዎች ወደ ንስሐ እንዳይጎርፉ የከለከለው ምንድነው? መንፈስ ቅዱስን ተሞልተናል በሚሉና፤ ሌሎችን በቀላሉ እንሞላለን የሚሉ ሰባኪያን በገነኑበት አገር ላይ ኃጢአት መለኪያ እስኪያጣ የተትረፈረፈው ለምንድነው?

ስለ ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክር እንዲህ አለ፤ “እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ለማየት ይሆን? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ለማየት የወጣችሁት ከነቢይም የሚበልጠውን ነው። … እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም” (ሉቃ. 7:26)።

ይህ “ከሴት ከተወለዱት መካከል” ሁሉ ታላቅ የነበረው ዮሐንስ አንድም በሽተኛ አልፈወሰም፤ አንዳችም የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል አልጻፈም። በእግዚአብሔር ፊት ግን ታላቅ ሰው ነበር። “ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም” ማለት ቀይ ባህርን በጌታ ኃይል ከከፈለው ሙሴ፤ ዮሐንስ ይበልጣል ማለት ነው፤ በብሉይ ዘመን ብዙ ድንቅና ታምራት ከሠራው ኤልሳዕም ይበልጣል ማለት ነው።

ይህ ከነቢያት ሁሉ የሚልቀው ዮሐንስ ልዩ ያደረገው ሕይወቱ ነው። ዮሐንስ ንብረት፣ ሚስትና ቤተሰብ አልነበረውም። ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ ባተኮረ ምድራዊ ሙያ አንድም ቀን ተጠምዶ አያውቅም። ከመፀነሱ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ጉዳዩና ሕይወቱ የእግዚአብሔር መንግሥት ብቻ ነበር።   

ዛሬ በውድ አልባሳት አጊጠው፤ በዘመናዊ መኪናዎችና የሚንሸራሸሩ “ነቢያት”ና “ሐዋርያት”ን ከዮሐንስ ጋር ስናነፃፅር ምን ይታያል? በመድረክ ከሚሠሯቸው “ድንቆች” በላይ የሚደንቀው አጭበርባሪ ባሕርያቸው ውስጥ የጎላው ሰይጣናዊ ተዓምር ነው። መንፈስ ቅዱስ ከኃጢአት እንድንላቀቅ ሲተጋ፤ ታምራት ሠሪዎቹ ደግሞ ለኃጢአት ሽፋን ፍለጋ ድንቅ ትርኢት ለማቅረብ ይሯሯጣሉ። ሰዎች ዓይናቸውን ከአንገብጋቢው የቅድስና አስፈላጊነት ላይ አንስተው በአቋራጭ ለሚገኝ ጊዜያዊ ጥቅም እንዲተራመሱ ጥድፊያ ይፈጥራሉ። ከኃጢአት ባርነት እንዳንላቀቅ የሚፈልገው ሰይጣን ተዓምራዊ መስተፋቅሩን ያለ ገደብ አፍስሶባቸው ተወዳጅ ዘራፊዎች አድርጓቸዋል።

የዘመኑ ቤተክርስቲያኖች በውሸታም ነቢያትና የተኩላ ልብ ባላቸው እረኞች የተሞሉ ናቸው። አምላክ ሕዝቡን በጤናና በገነት ወርቅ ዛሬውኑ እንደሚክብ የሚያስተምሩ ሁሉ፤ በምድር ሕይወቱ ቤትና ቅያሪ ልብስ ያልነበረውን ትሁቱን ክርስቶስ እንዴት ሊወክሉት ይችላሉ? ለመሆኑ ቃሉ ሥጋዊ ምቾት የቅድስና ውጤት መሆኑን ያስተምራል?

የታመመና በድህነት ቅርቃር ውስጥ የታሰረ ሁሉ ከአምላክ ፈቃድ ውጪ የሚኖር ነው? ዮሐንስ መጥመቁ ድሃ ነበር። ታስሮ የተገደለው ደግሞ እውነትን በድፍረት ለንጉሥ ሄሮድስ በመናገሩ ነው። መጥመቁ ታስሮ ሳለ ነው ጌታ “ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም” ያለው። ታላቁ ነቢይ ኤልያስም መጠለያና ምግብ አጥቶ ከአንዲት መበለት ቤት ተጠግቶ ይኖር ነበር። ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የሚያስተምርበት የግል ምኩራብ አልነበረውም፤ ቆሞ ያስተማረበት መርከብ እንኳን የራሱ አልነበረም።

የዛሬ “ነቢያት” እንደ ጥንቱ በልዓም ለገንዘብ በመስገብገብ እውነተኛ ጥሪያቸውን ክደው ምድራዊ ቪላዎቻቸውን ለማሳመር ይቅነዘነዛሉ፤ ምስኪኑን ያጭበረብራሉ። በእግር የተንከራተተውን ክርስቶስ ረግጠው በምቹ መኪናዎች ሲሄዱ በሮቻቸውን ለመክፈት በሚፎካከሩ ሰዎች ይከበባሉ። ታዲያ ምኑን የጌታ ተከታዮች ሆኑ? ኅሊናቸውስ እንዴት ዝም አለ? ክርስቶስ እዩኝ ብሎ እየጮኸ በታምራት ቲያትር ተከታዮቹን አጡዟል?

የዛሬ “ነቢያት” ርካሽ የሥጋ ነጋዴዎች ናቸው። በራስ ወዳድ ልቅነት ቅዱስ ቃሉን አጣመው፤ ተከታዮቻቸውን በራሳቸው ጠማማ የእርኩሰት አምሳያ እየቀረፁ ነው። በጎቻቸውን በሙዚቃና በተምታታ መንፈሳዊ ድንጋጤ አደንዝዘው የሰዎችን ክቡር ጊዜና ልብ አባክነዋል። ልብሶቻቸው በቅሚያ ኪሶች የተሞሉ ናቸው። መድረኮቻቸው ደግሞ የቅጥፈትና የዝርፊያ መሰውያዎች ሆነዋል። 

ራስን መግዛትና ኃጢአትን የመተው መለኮታዊ ተዓምር ከሁሉ የላቀ ድንቅ ነገር መሆኑ በሰፊው የማይታወቀው እንደ ዮሐንስ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የቆየ ግኑኝነት ያላቸው ነቢያትና ሐዋርያት ስለሌሉ ነው። አገራችን በእረኞች ስንፍናና ደፋር ስግብግብነት ምክንያት መንፈሳዊ ኪሣራ ውስጥ ገብታለች። ክርስቶስ ግን ዝም አይልም።

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በእረኞች ላይ ተነሥቻለሁ፤ ስለ መንጋዬ እጠይቃቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ እረኞች ራሳቸውን መመገብ እንዳይችሉ፣ መንጋዬን እንዳያሰማሩ አደርጋለሁ። መንጋዬን ከአፋቸው አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህም ምግብ አይሆናቸውም”። …

በፍርዱ ተስፋ የማይነፍገው “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋቸዋለሁ፤ እጠብቃቸዋለሁም። እረኛ ከመንጋው ጋር ሳለ፣ የተበተኑበትን በጎች እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እኔም በጎቼን እፈልጋለሁ። በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። … በመልካሙ ስፍራ አሰማራቸዋለሁ፤ የእስራኤል ተራሮች ከፍታም የግጦሽ መሬት ይሆናቸዋል። በመልካሙ ግጦሽ መሬት ላይ ይተኛሉ፤ እዚያም በእስራኤል ተራሮች ለምለም መስክ ላይ ይመገባሉ። እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸዋለሁም’” (ሕዝ. 34:11-15)።

መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ እረኞች ምክንያት የእግዚአብሔር ዓላማ አይስተጓጎልም። ከነቢይ የሚበልጠውን ዮሐንስን ልኮ፣ ኃጢአተኞችን ወደ ጻድቃን ጥበብ ተመልሰው በሥጋ የሚገለጠውን አዳኝ ለመቀበል የሠራው አምላክ ዛሬም ለበጎቹ ይራራል። ዳግም በክብር ከመገለጡ በፊትም እንደ ዮሐንስ ያሉ፤ በኤልያስ መንፈስና ኃይል የጌታን በጎች ወደ ቀናው መንገድ የሚመልሱ ሰዎችን ይልካል። በነውር ውስጥ ለተመቻቹት ውሸታም እረኞች ግን የሀፍረት ቀን ይመጣል። “‘ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት” (ሚል. 3:5)።

ድርባ ፈቃዱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *