giziew.org

ታሪክ የረሳው ቀን

“ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ። እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።"
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

እስካሁን ባሳለፉት የሕይወት ዘመን ዕረፍት የሚነሳ ነገር ገጥሞዎት ያውቃል? እንደ ዕንዝርት በምትሾር ዓለም የሰው ልጆች ሕይወት ዋስትና ባጣበትና ሊተነበይ በማይችል ለውጥ በሚበዛበት ህይወት ያለ ስጋት እፎይ ብሎ ማረፍ ምን ያህል መታደል ነው! የሰው ልጅ ነፍስ በፀጥታና በመታመን በአዳኙ ላይ ልታርፍ ያስፈልጋታል። ቅዱሱ ያምላካችን ቃል ስለ ዕረፍት ሲያነሳ ሰንበትን ቀዳሚ አድርጎ ያስቀምጣል። እግዚአብሔር ልጆቹ ሁለንተናዊ ዕረፍት እንዲሆንላቸው ሰንበትን አዘጋጀላቸው።

በብሉይም ይሁን በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ “ሰንበት” እያለ የሚጠራው ሰባተኛውን ቀን ሲሆን እርሱም ቅዳሜን ነው። ሰንበት የቃሉ ትርጉም “ዕረፍት” ማለት ሲሆን እግዚአብሔር ሰንበትን ለሰው ልጆች እንደፈጠረው መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፤ “ደግሞ፦ ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም” (ማር. 2፡27)።

ይህንን ለሰው ልጆች የተፈጠረ ሰንበት አገራችን ኢትዮጵያ “ቀዳሚት ሰንበት” በማለት የምታከብረው ነው። አሁን፣ አሁን በሚዲያው ጭምር እሁድን “ሰንበት” እያሉ በመጥራት ቀዳሚት ሰንበት እየተረሳች ብትመጣም በገጠሩ የአገራችን ክፍሎች አሁንም ቅዳሜ “ቀዳሚት ሰንበት” ተብላ በመጠራት ሥራ የማይሠራባት ቀን ሆና ትከበራለች። ከዚያ ሲያልፍም እስካሁን ድረስ አርብ ዕለት ውሃ እየተቀዳ፣ ቡናውም እየተዘጋጀ በሰንበት የተቀዳ ውሃ መጠጣት ኃጢአት እንደሆነ የሚቆጠርባቸው የአገራችን ክፍሎች አሉ። ወደ ኢየሩሳሌም ለስግደት የመጣው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ልክ እንደ ሐዋሪያት የዚሁ ቀዳሚት ሰንበት አክባሪ እንደሆነ ሊጠቀስ የሚችል ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ለሰው ልጅ የተፈጠረ ሰንበት ባለቤቱ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፤ “ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው” (ኢሳ.58፡13)።

“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ” (ዘጸ 31፡13)። ሰንበት የአንድ ሕዝብ ወይም የሃይማኖት ቡድን ንብረት ሳይሆን የእግዚአብሔር ነው፤ (“ሰንበቶቼን” በሚለው ቃለው ውስጥ “የእኔ” የሚል ያልተጠቀሰ አባባል አለበት) በመጽሐፍ ቅዱስ ሰንበት ከአካላዊ ድካም የምናርፍበት ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባለፈ ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም አለው።

1. ሰንበት ከየት መጣ? ከዕረፍት ቀንነቱ ባሻገርስ ምን የሚያመላክተው ነገር አለው?

“ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ። እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ። እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና” (ዘፍ. 2፡1-3)። “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴ. 11፡28-30)። ሰንበት የተሠራው እግዚአብሔር ዓለምን በፈጠረበት ጊዜ ነው። በዘፍጥረት መጽሐፍ እንደተጻፈው እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፍጹምና እንከን የለሽ አድርጎ በስድስት ቀናት ከፈጠረ በኋላ በሰባተኛው ቀን አረፈ። ሰባተኛውንም ቀን “ባረከው”፣ “ቀደሰውም”።

ባረከው፤ እንስሶችን በዘፍጥረት 1፡22፣28 እንደባረከ ሰንበትንም ባረከው። ይህ መለኮታዊ በረከት እዚያው ላይ የሚቆም ሳይሆን ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ የተለየ ትርጉም ኖሮት በቀጣይ የሚዘልቅ ነው።

ቀደሰው፤ ለተለየ መለኮታዊ አላማ ለየው። ይህ ማለት ከስድስቱ ቀናት ተነጥሎ ለመለኮታዊ ዓላማ ተለየ ማለት ነው። ይህ የሆነው ገና በፍጥረት ጊዜ ነው።

ምድር የተፈጠረች ጊዜ የተቋቋመው ሰንበት በስድስተኛው ቀን ለተፈጠሩት አዳምና ሔዋን (ዘፍ. 1፡26-31) ሕይወትን በዕረፍት የጀመሩበት ቀን ነው። እግዚአብሔር ፍጹምና ሙሉ የሆነውን ሥራውን ከፈጸመ በኋላ ሲያርፍ አዳምና ሔዋን ግን ከመሥራት ይልቅ በአምላካቸው የተሠራላቸውን በፀጋ በመቀበል ከእግዚአብሔር ጋር በማረፍ ሕይወትን ጀመሩ። እንደ ፍጥረት ሁሉ በመዳንም የተከሰተው እንዲሁ ነው። አንድ ክርስቲያን በመጀመሪያ ክርስቶስ በህይወቱና በሞቱ ሠርቶ በጨረሰው ፍጹምና ሙሉ የማዳን ሥራ በመቀበልና በዚያ በተፈጸመ ሥራ ላይ በማረፍ የክርስትና ሕይወትን ይጀምራል።

2. መድኃኒዓለም በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ በየትኛውን ቀን ያመልክ ነበር?

“ወዳደገበቱም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ” (ሉቃ. 4፡16)። ክርስቶስ ያመልክ የነበረው በሰንበት ቀን ነበር። በሳምንቱ ሰባተኛ ቀን ዘወትር አዳኛችን ወደ ምኩራብ ይሄድ ነበር። ይህም የሚያመለክተው ክርስቶስ የእግዚአብሔር የፈጣሪነት ምልክት የሆነውን የሰንበት ቀን ይጠብቅ እንደነበር ነው።

3. እግዚአብሔር በዐሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ስለ ሰንበት ምን አለ?

“የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም” (ዘፀ. 20፡8-11።) ከዐሥርቱ ትዕዛዛት አራተኛው ሰባተኛውን ቀን እንደ ቅዱስ ሰንበት እንድንጠብቀው ነግሮናል። ሰንበትን በመርሳት እንደምንቸገር ስላወቀ ትዕዛዙን ሲጀምር “አስብ” (አስታውስ) ብሏል።

4. ግን ዐሥርቱ ትዕዛዛት አልተቀየሩም እንዴ?

“ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም (መዝ. 89፡34)። “ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል” (ሉቃ. 16፡17)። እንኳን ይቅርና ሕጉ ሊሻር አንዷም በእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ ያለች ጭረት ወይም ነጥብ ልትሻር አትችልም። ሁሉም ሕጎች ዛሬም ይሠራሉ ዘጠኙ ትዕዛዛት እንዳልተቀየሩ ሁሉ ስለ ሰንበት የሚናገረው አራተኛውም አልተቀየረም።

. የሰንበትን ቀን የባረከው እግዚአብሔር ነው፤ “እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም” (ዘፀ.20፡11)። “እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም” (ዘፍ.2፡3)። እግዚአብሔር የባረከውንና የቀደሰውን ማንም ሊቀይረው አይችልም።

. ኢየሩሳሌም ከፈረሰች በኋላ (70 ዓም) እንኳን ክርስቶስ ሕዝቡ ሰንበትን ማክበር እንዲቀጥሉ ይጠብቅባቸው ነበር፤ የሮም ቄሳራዊ መንግሥት እኤአ በ70ዓም ላይ ኢየሩሳሌምን በሚያፈርሷት ጊዜ የክርስቲያኖች ስደት በክረምት ወቅት ወይም በሰንበት እንዳይሆን እንዲፀልዩ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ማስጠንቀቂያ ተናግሮ ነበር (ማቲ. 24፡20)። ይህ ማለት ጌታችን ከሞተና ከተነሳ ከ40ዓመት በኋላ እንኳን ሕዝቡ ሰንበትን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸው እንደነበር ማስረጃ ነው።

ሐ. የክርስቶስን አስከሬን ቅብዓ ቅዱስ ሊቀቡ የመጡት ሴቶች ሰንበትን አክብረው ነበር፤ (ማር. 15፡40-42)። ሕዝበ ክርስቲያን እንደሚያውቀው ይህ የሆነው ስቅለተ አርብ ነበር። በዚያን ዕለት የጌታን አስከሬን ሊቀቡ የመጡት ሴቶች ፀሐይ ስትገባ ሰንበት በመጀመሩ ሥራቸውን ሳያከናውኑ ወደቤታቸው መመለሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ “የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ” (ሉቃስ 23፡ 54-56)። (እዚህ ላይ መታወስ የሚገባው ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ አቆጣጠር አንዱ ቀን አልቆ ቀጣዩ ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትገባ ነው ዘፍ. 1፡5፤8፤ እንዲሁም “ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ” በማለት ለእስራኤላውያን ተነግሯቸው ነበር፤ ዘሌ. 23፡32።) ስለዚህ ሴቶቹ ስቅለት አርብ ፀሐይ ስትገባ ሰንበትን ለማክበር ወደቤታቸው ተመለሱ፤ “ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ” (ማር. 16፡1፣2)። ወደ መቃብሩ ሲመጡ ግን ጌታ ተነስቶ አገኙት፤ ይህም ብርሃነ ትንሳኤ በማለት በየዓመቱ ዕሁድ ዕለት የምናከብረው ነው። ስለዚህ “በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ” የሚለው በዐሥርቱ ቃላት ላይ ስለ ሰንበት በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ቅዳሜ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው።

መ. የሐዋርያት ሥራ ፀሐፊ የሆነው ሉቃስ ልክ ወንጌለ ሉቃስን እንደጻፈው ስለዚህኛውም ሲናገር “ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ” እንደጻፈና ሰንበትን አስመልክቶ ለውጥ ስለመኖሩ ምንም አለመናገሩን እናነባለን (ሐዋ. 1፡1-2)።

5. ሐዋሪያት ሰንበት ብለው ያከብሩ የነበሩት የትኛውን ቀን ነበር?

“ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር” (ሐዋ. 17፡2)። “እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ” (ሐዋ. 13:14)። የሐዋሪያት ሥራ ግልፅ እንዳደረገው ጳውሎስና የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሰንበትን ይጠብቁ ነበር። ስለዚህ ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ ሐዋርያት ሰንበትን ይጠብቁ ነበር ለማለት የሚያስችል ነው።

6. በአንድ ጥቅስ ብቻ የሐዋሪያትን ልምምድ መደምደም ይቻላል?

“በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኗቸው። ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሯቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዷቸው። በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ” (የሐ. ሥራ 13፡14፣42-44)። “በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን” (ሐዋ. 16፡13)።

ሐዋሪያው ጳውሎስና በርናባስ ለተከታታይ ሁለት ሰንበቶች አምልኳቸውን በቅዳሜ ቀን ሲያቀርቡ እናያለን (ሐዋ. 13፡14፣42)። እንዲሁም ከክርስቶስ ልማድ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ስላደረገው ሲናገር “ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር” ይላል (ሐዋ. 17፡2)። በቀጣይም ሐዋርያው በቆሮንቶስ በቆየበት አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ (ሐዋ. 18፡1-18) በሳምንቱ ቀናት ድንኋኑን እየሰፋ “በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፥ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር” ይላል (ቁ.4)። እነዚህ ሁሉ ጥቅሶች የሚያስረዱት ሐዋሪያው ጳውሎስን ጨምሮ የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በሰባተኛው ቀን አርፈው እግዚአብሔርን ያመልኩ እንደነበር ነው። በተጨማሪም አይሁድ ብቻ ሳይሆኑ አህዛብም ጭምር በሰባተኛው ቀን ያርፉ እንደነበር እናነባለን (ዘፀ. 20፡10፤ ኢሳ. 56፡6፤ ሐዋ. 13፡42)። 

7. እሁድስ የጌታ ቀን አይደለምን?

“በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፥” (ራዕይ 1፡10)። “የሰው ልጅ (ክርስቶስ) የሰንበት ጌታ ነውና” (ማቲ.12፡8፤ ማር. 2፡28፤ ሉቃ. 6፡5)። “የጌታ ቀን” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል አምላካችን የራሱ ቀን እንዳለው የሚያመላክት ነው። ለዚህም ነው በማቴዎስ ላይ የተጠቀሰው ቃል ክርስቶ ራሱ የሰንበት ጌታ እንደሆነ የተናገረው። ሆኖም በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ እሁድ የጌታ ቀን ተብሎ ተጠቅሶ አናነብም፤ ምንም ጥቅስ የለም። ስለዚህ የብሉይ ኪዳኑ ስለ ሰንበት የሚያወሩት ጥቅሶች ከአዲስ ኪዳን አስተምህሮ ጋር ተነጻጽረው ሲታዩ “የጌታ ቀን” ተብሎ የተገለጸው ቀን ሰባተኛው ቀን ሰንበት (ቅዳሜ) ብቻ ነው።

ከዚህ ሌላ በመፅሀፍ ቅዱስ እንደምንመለከተው ክርስቶስም ይሁን ሐዋሪያቱ የሰንበትን ቀን በየትኛውም ጊዜና ቦታ ከሰባተኛው ቀን ቅዳሜ ወደ መጀመሪያው ቀን እሁድ ስለመቀየራቸው ምንም ፍንጭ የለም። ከሰባተኛው ቀን በተጨማሪ ሌላ ቀን “የዕረፍት ቀን” ተብሎ ሲሰየም አንመለከትም።

8. የክርስቶስን ትንሳኤ ለማክበር ስንል እሁድን እንደ ሰንበት ብናከብረውስ?

ከክርስቶስ ትንሳኤ ጋር ለመተባበር እንድንችል የተሰጠን ምክር በጥምቀት ከእርሱ ጋር በሞቱና በትንሳኤው እንድንመስለው ነው (ሮሜ 6፡3-6 ከዚህ ጥቅስ ጋር በተያያዘ ስለ ጥምቀት የተሰጠውን ትንታኔ በገጽ 14 ላይ ይመልከቱ)። እግዚአብሔርን ለማክበር ይልቁንም እርሱ እንዳዘዘን ሕግጋቱን በፀጋ ብንከተል ነው የሚሻለው። በመጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ክፍል እሁድን ቅዱስ አድርገን እንድንጠብቅ የተሰጠ ትዕዛዝ የለም። “ብትወዱኝ ትዕዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ.14፡15) እንዳለው የመድኃኒዓለም ወዳጆች መሆናችንን የምናሳየው ሕግጋቱን በመቀየርና የሚመቸንን በመጠበቅ ሳይሆን እርሱ ላዘዘን ትዕዛዝ በመገዛት ነው። የእርሱን ዘላለማዊ ሕግ በሰው ሠራሽ ሕግጋት ለመለወጥ ማሰቡ ቅድስና የለበትም።

9. እሁድን ሰንበት አድርጎ መጠበቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተደገፈ ከሆነ ታዲያ እንዴት እሁድ ሰንበት ሆኖ ሊከበር ቻለ?

“ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል” (ዳን. 7፡25)። “ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። … የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል” (ማቴ. 15፡6፣9)። “ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል፤ … እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል” (ሕዝ. 22፣26፣18)።

ከጌታችንና መድኃኒታችን ዕርገት 300መቶ ዓመታት በኋላ አመለካከታቸው የተዛባ ሰዎች በአይሁዶች ላይ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ የእግዚአብሔርን ቅዱስ የአምልኮ ቀን ከቅዳሜ ወደ እሁድ ቀየሩ። እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ ይህ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። ይህ ስህተት ለትውልድ ሲተላለፍ ቆየ። ነገርግን የሰው ወግና ሥርዓት የሆነው የእሁድ ቀን እንደ ሰንበት ማክበር ሰባተኛውን ቀን ሰንበት አድርገህ አክብር ያለውን የታላቁንና የኃያሉን አምላክ ትዕዛዝ መተላለፍ ነው። ምክንያቱም አንድን ቀን ቅዱስ ብሎ መጥራት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ ነው። ሰው እግዚአብሔር የቀደሰውን መቀየርም ሆነ የፈለገውን ቀን በራሱ ቅዱስ ማድረግ አይችልም (ዘኁ.23፡20)። በተለይ መታወቅ የሚገባው ጉዳይ ይህ የቀን ጉዳይ ሳይሆን ልክ እንደሌሎቹ ትዕዛዛት ማለትም ጣዖትን ማምለክን ወይም መስረቅን ወይም ማመንዘርን ወይም መግደልን ትክክል አይደለም እንደምንለው ሁሉ የሰንበትን ቀን ቅድስና ከቅዳሜ ወደ እሁድ በመቀየር የማክበር ድፍረትን በቀላሉ ልናየው አይገባም።

10. ሕጉን እንደሚመች አድርጎ ማስተካከሉ ወይም መጨመርና መቀነስ ምን ችግር አለው?

“እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም” (ዘዳ.4፡2)። “የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንከን የለበትም፤ እርሱ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻቸው ነው። በእርሱ ቃል ላይ አንዳች አትጨምር፤ አለዚያ ይዘልፍሃል፤ ሐሰተኛም ያደርግሃል” (ምሳ.30፡5፣6)። በእግዚአብሐየር ሕግ ላይ የሚጨመር፣ የሚቀነስ ወይም የሚሻሻል ነገር የለም። የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹምና ቅዱስ ነው፤ ይህንን መነካካትና ወደፈለጉት ሃሳብ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ቅድስና የለበትም። የእግዚአብሔር ሕግ የተሰጠን “አድርግ”፣ “አታድርግ” ለማለት ሳይሆን ራሳችንን ከክፋት እንድንጠብቅና ወደርሱ መቅረብ እንድንችል ለመምራት ነው።

11. እግዚአብሔር ግን የሰንበትን ቀን የሰጠው ለምንድነው?

. የፍጥረት ተምሳሌት እንድትሆን ነው፤ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። … እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም” (ዘጸ. 20፡8፣11)።

ለ. የመዳንና የመቀደስ ተምሳሌት እንድትሆን ነው፤ “የምቀድሳቸውም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው” (ሕዝ. 20፡12)። እግዚአብሔር ሰንበትን ሲሰጥ ድርብ ምልክት ያለው በማድረግ ነበር። አንደኛው፤ እርሱ ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ የፈጠረ ለመሆኑ ምልክት እንዲሆን እና ሁለተኛ፤ እርሱ ሕዝቡን የሚያድን፣ የሚቤዥና የሚቀድስ ታላቅ የእግዚአብሔር ኃይል እንደሆነ የሚያሳይ በመሆኑ ነው (ሕዝ. 31፡13፣16፣17፤ ሕዝ. 20፡20)። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ሕግ አቅልሎ ማየትና እንደፈለጉ ማድረግ በጣም አግባብነት የሌለው ተግባር ነው፤ ያልተቀደሰ አካሄድም ነው። በኢሳያስ 58፡13ና 14 ላይ መባረክ የሚፈልጉ ሁሉ እግሮቻቸው የተቀደሰውን ቀን ሰንበትን እንዳይሽሩ መጠንቀቅ እንዳለባቸው እግዚአብሔር ይናገራል።

12. ሰንበት ዘላለማዊና በአዲሲቱ ምድርም የምናከብረው ነው?

“እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር” (ኢሳ. 66፡22፣23)። በርግጥም ከጥቅሱ እንደምንረዳው የዳኑት ሁሉ ኃጢአት በሌለባት አዲሲቱ ምድር ሰንበት ለዘላለም እያከበሩ በእግዚአብሔር ፊት ይሰግዳሉ።

ስለዚህ ሰንበት ከዚህ ዓለም ሃሳብና ሁካታ ወጣ ብለን ከአምላካችን ጋር የሃያ አራት ሰዓታት ጊዜ የምናሳልፍበት ልዩ በዓል ነው። ይህ ማለት በሌሎቹ ቀናት ከአምላካችን ጋር አንገናኝም ማለት አይደለም። ነገርግን በሰንበት ቀን ከመደበኛ ሥራችን፣ ከኑሮ ውጣ ውረድ፣ ከሃሳብ፣ ከመባከን፣ ከትምህርት፣ ከፈተና፣ ከጥናት፣ ከማንኛውም በሌላ ቀን መደረግ ከሚችል ጉዳይ ሁሉ ርቀን ከሆነልን ከቤተሰባችና ከሚወዱን ጋር አምላካችንን ያለገደብ የምናመልክበት፣ ሌሎችን የምንጎበኝበት፣ ለሌሎች የምንራራበት፣ ቃሉን የምንሰማበት ብቻ ሳይሆን የምንመሰክርበት፣ “ጌታ አምላኬ፤ የእጆችን ፍጥረት በማየት እንዴት እገረማለሁ” በማለት ተፈጥሮን የምናደንቅበትና ፈጣሪነቱን የምናወድስበት፣ እኛ ለእርሱ ተለይተን የተሰጠን (የተቀደስን) መሆናችን በጥልቀት የምናሰላስልበት፣ ፍጥረትን ፍጹም አድርጎ ፈጥሮ ሲበቃ “ተፈጸመ” ያለው አምላክ የመዳናችን ዋስትና በመስቀል ላይ ምንም ባልጎደለበት ሁኔታ ዕጹብና ድንቅ አድርጎ ያሟላው አምላክ “ተፈጸመ” በማለት ደኅንነታችንን ያተመበትን ማኅተም በማሰብ የምናከብረው ፈጽሞ ልዩ የሆነ ቀን ነው። በዚህ ቀን አምላክዎን ለማክበርና ከእርሱ ጋር ለመገናኘት ፍላጎትዎ ነው?

ቅንብር፤ ፋንታሁን መላኩ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *