giziew.org

የቤት ውስጥ ትምህርት ቤት አስፈላጊነት

ኢየሱስ ትምህርቱን የተከታተለው በቤት ውስጥ ነበር። የመጀመሪያ ሰብዓዊ አስተማሪው እናቱ ነበረች። ከእርሷ አንደበትና ከነቢያት መጻሕፍት፣ ሰማያዊ ነገሮችን ተማረ
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ትምህርት ከቤት ይጀምራል፤ የአንድ ልጅ ትምህርት የሚጀምረው ከቤት ነው። ቤት የመጀመሪያው ትምህርቱ ቤቱ ነው። ወላጆቹ አስተማሪው በሚሆኑበት በዚያ ሥፍራ፣ በህይወት ዘመኑ ሁሉ የሚመራባቸውን ትምህርቶች ማለትም ሌሎችን የማክበር፣ ለሌሎች የመታዘዝ፣ ራስን የመግዛት ትምህርቶች ይማራል። ልጆች በቤታቸው የሚማሩት ትምህርት ተጽዕኖ ለመልካም ወይም ለክፉ ወሳኝ የሆነ ኃይል አለው። በቤት ውስጥ የሚማሯቸው ትምህርቶች በብዙ መልኩ ጸጥ እና ቀስ ብለው የሚከናወኑ ቢሆኑም፣ ልጅን በእውነትና በጽድቅ ለመምራት ትልቅ ኃይል አላቸው። ልጆች በዚህ በቤት ውስጥ ትምህርት ቤት በትክክል ካልተመሩ፣ ሰይጣን በእርሱ ምርጥ ወኪሎች ያስተምራቸዋል። በእርግጥም የቤት ውስጥ ትምህርት ቤት እንዴት ወሳኝ ነው!

መሠረቱ የሚጣለው በቤት ውስጥ ነው፤ ለልጆቻቸው አካላዊ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ መመሪያን መስጠት በወላጆች ሁሉ ላይ የተጣለ ግዴታ ነው። ልጃቸው በደንብ የተገነባ ባህርይ እንዲኖረው ማድረግ የወላጅ ሁሉ ዓላማ ሊሆን ይገባል። ይህ ቀላል ሥራ አይደለም። ይልቁንም በጥልቀት ማሰብንና መጸለይን እንዲሁም በትእግስትና ተስፋ ባለመቁረጥ መትጋትን የሚጠይቅ ሥራ ነው። ትክክለኛና ጠንካራ መሠረት ሊጣል ይገባል። ከዚያም በየዕለቱ ግንባታውና የማሳመሩ ሥራ ወደ ፊት ሊገሰግስ ይገባል።

ልጅ ሁሉ ቀርቶበት ግን ይህን ቢያገኝ ይሻላል፤ ወላጆች፣ ቤታችሁ፣ ለሰማያዊ ቤት መዘጋጀት ያለባቸው ልጆቻችሁ የሚሰለጥኑበት ትምህርት ቤት መሆኑን አስታውሱ። በለጋ ዕድሜያቸው የሚማሩት ይህንን ትምህርት ከሚያጡ ይልቅ ማንኛውንም ነገር ብትከለክሏቸው ይሻላል። በቤታችሁ ምንም ዓይነት የቁጣ ቃል እንዲነገር አትፈቀዱ። ልጆቻችሁ ርኅሩኅና ታጋሽ እንዲሆኑ አስተምሯቸው። ስለሌሎች ግድ የሚላቸው እንዲሆኑ አስተምሯቸው። በዚህ መልኩ በመንፈሳዊ ነገር ለከፍተኛ አገልግሎት ልታዘጋጇቸው ትችላላችሁ። ልጆችና ወጣቶች ለጌታ አገልግሎት ገጣሚ ለመሆንና በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወደሚገኘው ከፍተኛ ትምህርት ቤት ለመግባት የሚያዘጋጃቸውን ትምህርት የሚያገኙበት የመሰናዶ ትምህርት ቤት (ቤታቸው) ነው።

ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፤ የቤት ውስጥ ትምህርት ቤት ዋና እንዳልሆነ ነገር ተደርጎ ሊታይ አይገባም። እንዲያውም በማንኛውም እውነተኛ የትምህርት አሰጣጥ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የሚይዝ ነው። እናትና አባት የልጆቻቸውን አእምሮ የመቅረጽ አደራ ተጥሎባቸዋል። “ተጣምሞ ያደገ ዛፍ ለማቃናት ይቸግራል” እንደሚባል፣ ልጆችን በማሰልጠን ረገድ ይህንን ማሰቡ ጠቃሚ ነው። ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁን ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ የማስተማር ኃላፊነት እንደ ቅዱስ አደራ ለእናንተ እንደተሰጣችሁ ምን ያህል ታስባላችሁ? እነዚህ ትንንሽ ችግኞች፣ በጌታ የአትክልት ቦታ ላይ ማደግ ይችሉ ዘንድ በገርነት ሊሰለጥኑ ይገባል። የቤት ውስጥ ትምህርት ቤት በምንም መልኩ ችላ ሊባል አይገባም። ይህንን ችላ የሚሉ ሁሉ ሃይማኖታዊ ግዴታቸው (ከጌታ የተሰጣቸውን አደራ) ችላ እያሉ ነው።

የቤት ውስጥ ትምህርት ሰፊ አድማስ፤ በቤት ውስጥ የሚቀሰመው ትምህርት ጥልቅና አድማሱም ሰፊ ነው። አብርሃም “የሚያምኑ ሁሉ አባት” ተብሎ ተጠርቷል። አብርሃምን መንፈሳዊ ህይወት ታላቅ ተምሳሌት ካደረጉት ነገሮች መካከል በቤቱ ለእግዚአብሔር ትዕዛዛት የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ነው። እምነትን በቤቱ ውስጥ አሳደገ። በየቤቱ የሚሰጠውን ትምህርት የሚያየውና የዚያንም ትምህርት ተጽዕኖ የሚመዝነው ጌታ፣ ስለ እርሱ እንዲህ አለ፤ “ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤተሰቦቹን እንዲያዝ መርጬዋለሁ” (ዘፍ 18:19)። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ልጆቻቸውን የእርሱን ሥርዓት እንዲያስተምሯቸው ለሕዝቡም ያደረገውን ነገር ሁሉ እንዲያሳውቋቸው አዟል። ለእነርሱ ቤትና ትምህርት ቤት አንድ ነበሩ። ልጆች በማያውቁት ሰው አንደበት ሳይሆን፣ ከሚወዷቸው እናትና አባት መመሪያ ይሰጣቸው ነበር። በዕለት ተለት ኑሮ በቤት ውስጥ በሚሆኑት ነግሮች ሁሉ የእግዚአብሔርን ነገር እንዲያስቡ ይደረግ ነበር። እግዚአብሔር እንዴት ሕዝቡን (ከግብጽ ባርነት) በድንቅ ነጻ እንዳወጣ በሚጣፍጥና ለአምላክ አክብሮትን በሚጨምር መልኩ ይነገር ነበር። ሁሉን የሚያዘጋጅ እግዚአብሔር መሆኑንና ስለ ወደፊቱ ሕይወት ያለው የእርሱ ዓላማ በእነዚህ ለጋ አእምሮዎች ላይ ይታተም ነበር። በዚህም እውነተኛ፣ መልካምና ውብ በሆነ ሃሳብ አእምሮአቸው ይሞላ ነበር።

ትምህርቶቹ በምሳሌ ተደግፈው ስለሚሰጡ በቀላሉ በአእምሮ ውስጥ ይቆያሉ። በእነዚህ ስዕላዊ መግለጫዎች ልጆች ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ወላጆቻቸው ተስፋ ወደሚያደርጉት የእግዚአብሔር ጥበብና ጥልቅ ነገር በማስተዋል ያድጋሉ። በዚህም ከሚታየውና ከሚጠፋው ነገር ባሻገር ያለውን የማይታየውንና ዘላለማዊ ነገር ያስባሉ።

የቤት ውስጥ ትምህርት ቤት ልጆችን ለመደበኛ ትምህርት ያዘጋጃል፤ የወላጆች ሥራ የአስተማሪዎችን ሥራ ይቀደማል። የልጆች የመጀመሪያ የትምህርት ክፍል በቤታቸው ሲሆን፣ ወላጆችም በጥንቃቄና በጸሎት በዚህ ደረጃ ለልጆቻቸው ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ካወቁና በተግባር ላይ ካዋሉት፣ ልጆቻቸው በጥሩ ዝግጅት ወደ ሚቀጥለው ደረጃ – ወደ መደበኛው ትምህርት – ማለፍ ይሆንላቸዋል።  

ባህርይን ይቀርጻል፤ ቤት ልጆች በሰማይ መንግሥት አምሳል ባህሪያቸው የሚቀረጽበት ትምህርት ቤት ነው።

ትምህርት በናዝሬት ቤት፤ ኢየሱስ ትምህርቱን የተከታተለው በቤት ውስጥ ነበር። የመጀመሪያ ሰብዓዊ አስተማሪው እናቱ ነበረች። ከእርሷ አንደበትና ከነቢያት መጻሕፍት፣ ሰማያዊ ነገሮችን ተማረ። ኑሮ ደረጃቸው ዝቀተኛ በሚባሉት ቤተሰቦች ውስጥ ያደገ ሲሆን በታማኝነትና በደስታ የራሱን ድርሻ ይወጣ ነበር። የሰማይ ሠራዊት አለቃ የነበረው ጌታ አሁን ፈቃደኛ አገልጋይ፣ አፍቃሪና ታዛዥ ልጅ ሆነ። የእጅ ሙያም በመማር በዮሴፍ የእንጨት መሥሪያ ተግቶ ይሠራ ነበር።   

ምንጭ፤ Child Guidance, EGW, 1954 Pages 10-12፤ ትርጉም ፓ/ር መልአክ ዓለማየሁ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *