መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቀደምት መንግሥታትና አነሳስ ብዙ የተናገረው አለ። ስለ ባቢሎን፣ ሜዶና ፋርስ፣ ግሪክ፣ ሮምና የተከፋፈሉት የአውሮጳ መንግሥታት በዳንኤል 2 በትንቢት ተነግሮ እናገኛለን። የእነዚህ መንግሥታት አነሳስ ብቻ ሳይሆን አወዳደቃቸውና በቀጣዩ መንግሥት ሲተኩ ያለውን ሒደት መጽሐፍ ቅዱስ በቂ ትንተና ይሰጣል።
አሁን ባለንበት ዘመን ስላሉት መንግሥታት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል ብለን ብንጠይቅ ብዙ መልሶች ሊሰጡ ይችላሉ። በተለያዩ የሚዲያ መድረኮችና የስብከት ቦታዎች ስለ ዘመናችን የትንቢት አፈታትና የመንግሥታት ሁኔታ ትንቢታዊ ከሚባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እየተጠቀሰ ሲተነተን ሰምተን ሊሆን ይችላል።
ከዚህ ሁሉ ግን በጣም የሚያስደንቅ በሚባል መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሜሪካ አነሳስና የመንግሥታዊ አሠራር እንዲሁም የወደፊት ዕጣ ፈንታ በትንቢት ተናግሯል። አሜሪካ ለምን ተመሠረተች? በዓለም የመጨረሻ ታሪክ ውስጥ ያላት ሚና ምንድነው? የምድራችን ኃያል አገር ሆና በሃይማኖቱ መስመር የምትጫወተውስ ምንድነው? አሜሪካ ወደፊት መልኳን ትቀይር ይሆን? ነጻነትን የተላበሰው መንግሥታዊ አሠራሯ ይለወጥ ይሆን? ወዘተ የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎች በስፋት በዚህ ትምህርት እንዳስሳለን። ለዚህ ትምህርት ይረዳ ዘንድ ራዕይ ምዕራፍ 13፡11-18 ያሉት ጥቅሶች በቅድሚያ ሊነበቡ ይገባል።
1. በራዕይ 13 ሁለት የዓለም ኃይላት ተጠቅሰዋል፤ የመጀመሪያው ማነው?
ከዚህ በፊት እንዳጠናነው በራዕይ 13፡1-10 የተጠቀሰውና ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ የሮም ጳጳሳዊ ኃይል ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ “አውሬ” የሚለውን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ሲፈታው የዓለም መንግሥት ወይም ኃይል ነው ይለዋል። “እነዚህ አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው” እና “አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች” ዳን 7፡17፣23።
2. የሮም ጳጳሳዊ ሥርዓት መቼ (በስንት ዓም) ነበር ያከትማል የተባለው?
“በአርባ ሁለት (42) ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው” (ራዕይ 13፡5)።
በዓለም በተለይም በአውሮጳ ለዘመናት በሥልጣን መንበር ላይ የነበረው የሮም ጳጳሳዊ ኃይል ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው ጊዜው ሲደርስ ከመንበሩ ተነስቷል። ከዚህ በፊት ስለ ትንቢታዊ ቀናት ስናጠና እንደተማርነው የቀን-ለዓመት ስሌትን በመከተል አንድ የትንቢት ቀንን ወደ ዓመት በመቀየር ሒሳባዊ ቀመሩ እንዴት ከታሪክ ጋር በተሰናሰለ ሁኔታ ትንቢት ሲፈጸም እንደኖረ አጥንተናል። በዚህ መሠረት 42 የትንቢት ወራት ማለት 1,260 ቀናት ወይም የትንቢት ዓመታት መሆኑን እንረዳለን (ሕዝ 4፡6፤ ዘኍልቍ 14፡34)።

አንድ ዓመት 12 ወራት አሉት፤ በ3 ዓመታት ደግሞ 36 ወራት (3×12 = 36) አሉ። በትንቢቱ ከተሰጠው 42 ወራት 36 ስንቀንስ 6 ወራት ይቀሩናል። ስለዚህ 42 ወራት ማለት 3 ዓመት 1/2 ወይም 1260 የትንቢት ቀናት መሆኑን እንረዳለን። ይህም ጳጳሳዊ ሥርዓት በሥልጣን የቆየበት ዘመን ነው። ይህ ሥልጣን ደግሞ በወቅቱ የፈረንሣይ ንጉሥ የናፖሊዮን ጄኔራል የነበረው በርቲየር እኤአ በ1798ዓም በዚያን ጊዜ የነበሩትን ጳጳስ (ፖፕ) ከመንበራቸው ባወረደበት ጊዜ ትንቢት ተፈጸመ፤ አውሬውም ለሞት በሚያደርስ ቁስል ቆሰለ!

3. ጳጳሣዊ ሥርዓት ለሞት በሚያደርስ ቁስል ሲቆስል የትኛው መንግሥት ወደ ሥልጣን መጣ?
“ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር” (ራዕይ 13፡11)።
በራዕይ 13፡10 እንደተጠቀሰው ጳጳሣዊ ሥርዓት ለሞት በሚያደርስ ቁስል የቆሰለው በ1798 ዓም ነበር። ልክ በዚያው ዘመን አካባቢ ነበር (ቁጥር 11) አሜሪካ እንደ አገር ብቅ ማለት የጀመረችው። በ1776 ዓም አሜሪካ ነጻነቷን አወጀች፤ ሕገመንግሥቱ በ1787 ጸደቀ፤ የመብት ማስጠበቂያ ድንጋጌ (Bill of Rights) በ1791 ዓም በሥራ ላይ ዋለ፤ በ1798 አሜሪካ በገሃድና ሁሉ በሚያውቀው መንገድ የዓለም ኃያል የምትሆንበትም ፈር እየቀደደች መጣች። እነዚህና ከትንቢት ቃላት ጋር ስናነጻጽራቸው ይህንን ሁሉ መሥፈርት የምታሟላው ከአሜሪካ በስተቀር ማንም ሊሆን አይችልም።
4. “ከምድር ሲወጣ” የታየውን አውሬ ልዩ የሚያደርገው ምንድነው?
“ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ” ራዕይ 13፡11።
በዳንኤልና ራዕይ መጻሕፍት መንግሥታትን የሚወክሉት አራዊት ባብዛኛው ሲወጡ የሚታዩት ከባሕር ነው። አንድ አውሬ ወይም መንግሥት ከባሕር መውጣቱ የሚያመለክተው በርካታ ሕዝብ ካለበት ቦታ የሚነሳ መሆኑ ነው። “አለኝም፦ ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው” (ራዕይ 17፡15)። ጥቅሱ እንደሚያመለክተው ውኃዎች የተባሉት ባሕር ወይም ብዙ ውሃ ያለበትን ሲሆን ይህም “ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም” የሚሳይ ነው። ምድር ደግሞ የብዙ ውኃዎች ተቃራኒ ስለሆነ ይህ ከምድር ወጣ የተባለው መንግሥት የሚነሳው ብዙ ሰው ከሌለበት ቦታ ነው በሚለው ልንወስደው እንችላለን። ከዚህ አንጻር ከተመለከትነው አሜሪካ በምትነሳበት ወቅት “አዲሱ አገር” ወይም “New World” የሚባለው አሁን አሜሪካ ያለችበት ቦታ ሕዝብ ያልሰፈረበት ባዶ የሚባል ቦታ ነበር።
5. በበግ የተመሰለው አውሬ ላይ ያሉት ቀንዶች የሚያመለክቱት ምንድነው? ዘውድ የሌለውስ ለምንድነው?
“አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው” (ዳንኤል 7፡24)፤ “በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው” (ዳንኤል 8፡21)።
ቀንድ የሚያመለክተው መንግሥታትን ወይም ነገሥታትን ነው። አሜሪካ ንጉሥ አልባ አገር ነች፤ ነገርግን አሜሪካንን የሚገዛት ንጉሥ ሳይሆን ሁለት መሠረታዊ መመሪያዎች ናቸው። እነዚህም የሲቪልና የሃይማኖት ነጻነት ናቸው። እነዚህ መመሪያዎችም አንደኛው “ሪፓብሊካዊነት” (ንጉሥ አልባ መንግሥት ወይም “ሪፑብሊክ” ማለት ሕዝብ በሚመርጣቸው ተወካዮች ወይም እንደራሴዎች የሚመራ መንግሥት ማለት ነው)፤ ሁለተኛው ደግሞ “ፕሮቴስታንትነት” (ጳጳስ የማይመራው ቤ/ክን) ነው።

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሃይማኖትና መንግሥት የተሳሰሩ ሆነው ኖረዋል። የመንግሥት ሃይማኖት የሚባል ከመንግሥት ጋር በትሥሥር የሚሠራ ሃይማኖት ሲኖር የሃይማኖቱ መሪዎች ነገሥታትን በመሾምና በመቀባት የላቀውን ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል። መንግሥታትም በበኩላቸው የሃይማኖት ድርጅቱን ለመደጎም በሕዝብ ላይ ግብር ሲጭኑና ሲጨቁኑ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል።
አሜሪካ ከዚህ የተለየች ነች። እንደ ቀደምት መንግሥታት ሳይሆን አዲስ ሥርዓትን ነው የጀመረችው። ማንኛውም ሰው የፈለገውን እንዲያመልክ ወይም የፈለገውን ሃይማኖት እንዲከተል ነጻ የምትሰጥ አገር ብቻ ሳትሆን መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እንደማገባ በግልጽ በሕግ የደነገገች አገር ናት።
ስለዚህ በአውሬው ላይ ዘውድ አለመኖሩ የሚያመለክተው በሕዝብ የሚመረጥ መሪ እንጂ በንጉሥ የሚተዳደር መንግሥት እንዳልሆነ ነው። “የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶች” የሚያሳዩት ይህች አገር ሰላም ወዳድ፣ ነጻነት የሞላባት፣ ጭቆና የማትቀበል፤ መልካም አገር መሆኗን ነው። ጥያቄው ያለው በዚሁ ትቀጥላለች ወይ የሚለው ነው፤ መልሱን ጥናታችንን ስንቀጥል እናገኘዋለን።
6. በራይዕ 13፡11 ላይ ለምንድነው በጉ እንደ ዘንዶ ይናገራል የሚለው?
“… እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር” (ራዕይ 13፡11)።
ከዚህ በፊት እንደተማርነው ዘንዶው ሰይጣን ነው፤ ሰይጣን ደግሞ ዓላማውን የሚያሳካው በምድር በሚነሱ መንግሥታት አማካኝነት ነው። የራሱን መንግሥት በምድር ለመመሥረት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማጥፋት ይጥራል፤ ይሠራል፤ የጌታን ተከታዮች ያሳድዳል፣ ይገድላል።
ስለዚህ በጉ እንደ ዘንዶ መናገሩ የሚያመለክተው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ሆኖ የሚሠራ መሆኑን ነው። አሜሪካ እንደ አጀማመሯ ነጻነትን በመስጠትና የሃይማኖትን እኩልነት በማስፈን የምትቀጥል ሳትሆን በመጨረሻው ዘመን ሰዎች የማይፈልጉትን እንዲያመልኩ የምታስገድድ፤ እምቢ የሚሉትን ደግሞ የምትቀጣ አገር ትሆናለች።
7. ይህ ለማመን የሚከብድ ጉዳይ ነው፤ ለመሆኑ አሜሪካ እንደ ዘንዶ ስትናገር የሚከሰቱት ነገሮች ምንድናቸው?
ከዚህ በታች አራት ወሳኝ ነጥቦች ተጠቅሰዋል፤

- “በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል” (ራዕይ 13፡12)። በዚሁ የራዕይ መጽሐፍ 13ኛው ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ከባህር የወጣው አውሬ የሮም ጳጳሳዊ ሥርዓት ነበር፤ ይህ ኃይል በመካከለኛው ዘመን በርካታ ክርስቲያኖችን ያሳደደና የገደለ እንደነበር ታሪክ መስክሯል፤ ልክ እንደዚህ አሳዳጅ ኃይል አሜሪካም እንዲሁ ሰዎችን ወደ አስገዳጅ ሃማኖታዊ ሥርዓት ታስገባለች፤ እምቢ የሚሉትንም ታሳድዳለች።
- “ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል” ራዕይ 13፡12። አሜሪካ የዓለም መንግሥታትን በመምራት ሓሳዊ ክርስቶስ ለሆነው የጳጳሳዊ ኃይል እንዲሰግዱ ወደማስገደድ ሥራ ውስጥ ትገባለች። (ሓሳዊ ክርስቶስ ማለት ሐሰተኛ ክርስቶስ ወይም ጸረ ክርስቶስ ማለት ብቻ ሳይሆን የክርስቶስ ቦታ ለኔ ይገባኛል ማለትም ነው)። ከጥንት ጀምሮ የነበረው አንዱና ዋንኛ ጉዳይ አምልኮ ነበር። የሰው ልጅ ማንን ይታዘዛል፤ ለማን ይሰግዳል የሚለው ጥያቄ ባለንበት የመጨረሻ ዘመን የሰዎችን ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ጉዳይ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ሰዎች ለማን ይሰግዳሉ? ለሓሳዊው መሢሕ (ጳጳሳዊ ሥርዓት) ወይስ ለክርስቶስ እውነተኛው መሢሕ? የሚለው ለሰዎች በግልጽ የሚቀርብ ይሆናል። ሰይጣን በረቀቀ ስልት ድንቅንና ተዓምራትን በማድረግ (ራዕይ 13፡13-14)፤ እጅግ ብዙዎችን ያሳስታል፤ ያታልላል (ራዕይ 13፡3)። ይህንን እንቅስቃሴ አንቀላቀልም፤ አንቀበልም የሚሉ መናፍቃን፣ ጽንፈኛ፣ ተቃዋሚ፣ ጸረኅብረት፣ አመጸኛ፣ ወዘተ ተብለው ይኮነናሉ፤ ለሞት ተላልፈውም ይሰጣሉ። ይህ በራዕይ 13፡11 በበግ ተመስሎ የቀረበው የአሜሪካ መንግሥት በራዕይ 19፡20፤ 20፡10 “ሐሰተኛው ነቢይ” ተብሎ እንደተጠራ እናነባለን (ራዕይ 19፡20፤ 20፡10)። ምክንያቱም ብዙዎችን ለማሳሳት ሰይጣን የሚከተለው ቀላሉ መንገድ መንፈሳዊና የሚታመን ሆኖ በመቅረብ ነው። ምናልባት አሁን ላይ ሆነን ይህንን ስናነብ ይከሰታል ብለን ለማመን ይከብደን ይሆናል። በትንቢተ ዳንኤል 2 እንደምንመለከተው በምስሉ የተጠቀሱት መንግሥታት በእርግጠኝነት እንደሚነሱና እንደሚወድቁ፤ በመጨረሻም እኛ ያለንበት ዘመን እንደሚደርስ ይህንንም ልክ እንደተተነበየው ሲፈጸም ተመልክተናል። ጌታችን ኢየሱስ ይህንን ብሏል፤ “ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን ነግሬአችኋለሁ”(ዮሐ. 14፡29)።
- “የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል” (ራዕይ 13፡14)። አሜሪካ ከባህር ለወጣውና ቁስሉ ለተፈወሰለት አውሬ (ጳጳሳዊ ሥርዓት) ሃይማኖታዊ ሕግጋትን ትደነግጋለች። የጨለማው ዘመን በሚባለው ወቅት ዓለምን ሲቆጣጠር በነበረው ጳጳሳዊ ሥርዓተ ዘመን እንደነበረው አሁንም እንዲሁ ሃይማኖትን ከመንግሥት ጋር በማጋባት አሜሪካ ምስለ ጳጳሳዊ ሥርዓትን ትዘረጋለች። በተለይ በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ዋና ዐምድ የሆነው ፕሮቴስታንትነት ይህንን ሃማኖታዊ ሥርዓት ለመመሥረት ትልቅ ሚና ይጫወታል፤ ከጳጳሳዊ ሥርዓትም ጋር “ጋብቻ” በመፈጸም የዓለም ሕዝብ ለጳጳሱ እንዲገዛ በጥምረት ይሠራል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በናፖሊዮን ዘመን ቆስሎ የነበረው ጳጳሳዊ ኃይል ቁስሉ ተፈውሶ እንደ መካከለኛው ዘመን ዓለምን በቁጥጥሩ ሥር ያደርጋል።
- “ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ (ያስገድላቸዋል)” (ራዕይ 13፡15)። ዓለምን በኃያልነት የምትመራው አሜሪካ ለዚህ ለጳጳሳዊ ሥርዓት የሚቆመውን ምስል “አንቀበልም”፣ “አንሰግድም” የሚሉ ሁሉ እንዲገደሉ የዓለምን መንግሥታት ታስተባብራለች። የዓለም መንግሥታትም አንታዘዝም ባዮችን ለመግደል የሚያስችል የሞት አዋጅ ያውጃሉ። የእነዚህ አንታዘዝም ባዮች ዋንኛ ጥፋት የሚሆነው የምናመልከው ኃያሉን ፈጣሪ አምላክ እግዚአብሔርን ብቻ ነው ማለታቸው ይሆናል። ይህ ዓለምአቀፋዊ ኅብረት “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብሎ ይጠራል። ይህ ዓለምአቀፋዊ ኅብረት በአስገዳጅነት ለሚያወጣው ትዕዛዝና ሥርዓት አንታዘዝም የሚሉትን ሁሉ በቁጥጥር ሥር የሚያውልበትንና የሚያስገድድበትን፤ እምቢተኞችን የሚገድልበትን ሥርዓት ይዘረጋል።
8. ሞት የሚታወጅበት ዋናው ትዕዛዝ በምን ላይ ያተኮረ ነው?

“የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ” (ራዕይ 13፡15-17)።
የመጨረሻው ዘመን ትኩረት የሚያደርግበት ዋናው ጉዳይ አምልኮ ይሆናል። ይህም ደግሞ አውሬውንና ምልክቱ የሆነውን የእሁድ ሰንበትነት በመቀበል ለእርሱ መስገድ፤ ወይም የቅዳሜ ሰንበትነት በመቀበል ጌታ ኢየሱስን ማክበርና ለእርሱ መስገድ ይሆናል። ይህ የቀን ወይም አንድን ቀን ከሌላው አስበልጦ የማየት ጉዳይ ሳይሆን እግዚአብሔር ያዘዘውን ባይገባን እንኳን መታዘዝ አለብኝ ብሎ ከመቀበልና ለእርሱ ክብር ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው። የሰንበት ቀን የአምላካችንን ፈጣሪነት ብቻ ሳይሆን አዳኝነቱንም የምታሳይ ነች። በዚያች ቀን እርሱን በልዩ ሁኔታ የምናከብርበትና ከእርሱ ጋር የምንገናኝበት ነው። በሌሎቹም ቀናት ይኸው ግንኙነታችን አለ፤ አስፈላጊም ነው። የሰንበት ቀን ግን ከሥራ፣ ከሳምንታዊ ጉዳያችን፣ ከትምህርት፣ ወዘተ በመቆጠብ ሙሉውን 24 ሰዓት ባምላካችን በመታመን ስለ እርሱ ብቻ በማሰብ የምናሳልፈው ነው። ይህንን ግልጽ ትዕዛዝ አልቀበልም ብሎ የጳጳሳዊ ኃይል በራሱ ላቋቋመው የእሁድ ሰንበት መገዛትና ያንን ማክበር ከአምላክ ሕግ ይልቅ ለሰው መገዛት ነው፤ ለጌታ ከመስገድ ይልቅ ለአውሬው መስገድ ነው። የሮም ጳጳሳዊ ሥርዓት የእሁድ ሰንበትነት አስመልክቶ ሲናገር ይህንን ይላል፤ “ቤተክርስቲያኗ ሰንበትን (ከቅዳሜ) ወደ እሁድ ቀይራለች፤ በመሆኑም ዓለም ሁሉ አምልኮውን በዚያን ቀን በመፈጸም ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትዕዛዝ በጸጥታ በመታዘዝ ይሰግዳል” (ምንጭ፤ Hartford Weekly Call, February 22, 1884)።
9. በርግጥ መንግሥት መግዛትና መሸጥን መከልከል ይችላል?
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መግዛትን በተመለከተ በዜጎች ላይ ቁጥጥር ተደርጎ ነበር፤ ሰዎች ስኳር፣ ነዳጅ እና የመሳሰሉትን በራሽን እንዲገዙ የተደረገበት ወቅት ነበር። ዕቃዎችን በሚገዙበት ጊዜ ማኅተም የተመታባቸውን ኩፖኖች የያዙ ብቻ ነበሩ መግዛት የሚችሉት። ማኅተም ከተደረገባቸው ኩፖኖች ውጪ ጥሬ ብር እንኳን ምንም መግዛት የማይችል ዋጋ ቢስ ሆኖ ነበር።
ባለንበት ዘመን ነገሩ ሁሉ በኮምፒውተር ቁጥጥር የሚደረግበትና ሰዎች በጣት አሻራቸውና በሚሰጧቸው ልዩ ግላዊ የመለያ ቁጥሮች አማካኝነት ማንነታቸው የሚታወቅ በመሆኑ ቁጥጥር ለማድረግ ብዙም የሚከብድ አይሆንም። በዚህ መሠረት መንግሥት ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በመስማማት የሚያወጣውን ሕግ አንታዘዝም የሚሉ ሁሉ በቀላሉ በኮምፒውተር ቋት ውስጥ በእምቢተኝነት ተመዝግበው የትም ቦታ ምንም መግዛት እንዳይችሉ ማድረግ ይቻላል። ይህ አንድ መላምት ሲሆን ይህ መግዛትና መሸጥ የመከልከል ሥራ በእርግጠኝነት እንዴት እንደሚከናወን ማንም አሁን የሚያውቀው አይደለም። እርግጠኛ የምንሆንበት ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተናገረው የሚፈጸም መሆኑን ነው።
ሁለቱ ገናና ኃይላት
በራዕይ 13 ሁለት ዓለምአቀፋዊ ኃይላት እንዳሉ እናነባለን፤ አንዱ ከባህር የሚወጣ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከምድር የሚወጣ ነው። እነዚህ ልዕለኃያላን ባለንበት የመጨረሻ ዘመን የዓለማችንን አጠቃላይ የኃይል አሰላለፍ የሚቆጣጠሩና የሚወስኑ ናቸው። እነዚህም የሮም ቤተክርስቲያን (ቫቲካን) እና አሜሪካ ናቸው። አሜሪካ ቫቲካንን በመርዳት ዓለም የጳጳሳዊ ሥርዓትንና በእርሱ በኩል የሚወጡትን ሕግጋት አንዲፈጽም ታደርጋለች። በሌላ አነጋገር ለአውሬው እንዲሰግዱና ምልክቱንም እንዲቀበሉ ታደርጋለች። ይህንን አንቀበልም የሚሉትንም በሞት እንዲቀጡ የሚደነግግ ሕግ በማስወጣት በኩል አሜሪካ ቁልፍ ሚና ይኖራታል። ጳጳሳዊ ሥርዓት የጨለማው ዘመን በሚባለው ወቅት ኃይማኖታዊ ደንቦችን በመደንገግ ሰዎች እንዲታዘዙ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን የሮምንና የሌሎች መንግሥታትን ሥልጣን በመጠቀም ደግሞ እነዚህን ኃይማኖታዊ ድንጋጌዎችን አንቀበልም የሚሉትን ሲያስቀጣና ሲያስገድል እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። በዚህም ዘመን ተመሳሳይ ተግባር እንደሚፈጽም ይህ ጥናት ይነግረናል።

10. ባለንበት ዘመን ጳጳሳዊ ሥርዓት ምን ያህል ብርቱና እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው?
ቫቲካን የሚገኘው ጳጳሳዊ ኃይል በልዩ ሁኔታ የመንግሥትንና የኃይማኖትን ሥልጣን አጣምሮ የያዘ የዓለማችን ብቸኛ የሚባል ሥርዓት ነው። ይህም በዓለም ላይ በተለየ ሁኔታ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል ሥልጣንን አጎናጽፎታል። የቫቲካን የበላይ ኃላፊና መሪ ሊቀ ጳጳሱ ሲሆኑ እርሳቸው በዚያው ሥልጣናቸው “ቅዱስ አባት”፣ “ብፁዕ ወቅዱስ” እየተባሉ የሚጠሩ የኃይማኖት መሪም ናቸው። በዓለም የሚገኙ አገራት በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ አምባሳደሮቻቸው በቫቲካን ይገኛሉ። ቫቲካንም እንደ አገር አምባሳደሯን በየአገራቱ አስቀምጣለች። አንዳንድ ዕውነታዎችን አለፍ አለፍ እያልን ብንመለከት፤
- ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ እኤአ በ2015 በአሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት ፖለቲካዊም ሃይማኖታዊ እንዲያውም “ሐዋሪያዊ” ነበር። እንደ አንድ የአገር ፖለቲካ መሪ በአሜሪካ የእንደራሴዎች ምክርቤት በመገኘት በዓለም ማኅበረሰባዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ንግግር አድርገው ነበር። በተለያዩ ከተሞች ደግሞ ሥርዓተቅዳሴ በማካሄድ ልዩ ፕሮግራሞችንም መርተው ነበር። ካርዲናል ጢሞቴዎስ ዶላን ሲቢኤስ በተሰኘው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ በወቅቱ ይህንን ብለው ነበር፤ “እርሳቸው (ፖፕ ፍራንሲስ) ጳጳሳዊ ሥልጣንና ክብር ትኩረት እንዳይሰጣቸው ባደረጉ ቁጥር ብዙ ሰዎች እየሰሟቸውና ትኩረት እየሰጧቸው ይሄዳሉ” (ምንጭ፤ Cardinal Timothy Dolan፤ CBS This Morning, September 22, 2015)
- የቫቲካን ዋንኛ ሃሳብ የክርስቲያኑን ዓለም አንድ ማድረግ፣ ማዋኃድ ነው። እኤአ በ2014ዓም ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ በቅዱስ ጳውሎስ ባሲሊካ (ግዙፍ ቤ/ክ) ከኦርቶዶክስ፣ ከአንገሊካን፣ ከሉተራን፣ ከሜቶዲስትና ከሌሎች አብያተክርስቲያናት ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር እርሳቸው የመሩት የኅብረት ስብሰባ ተካሄዷል። በወቅቱ ክርስቲያናዊ ኅብረት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ሊቀጳጳስ ፍራንሲስም ይህንን ብለው ነበር፤ “በቤተክርስቲያናት መካከል ያለውን ልዩነት ተፈጥሮአዊና መሆን ያለበት አድርጎ መውሰድ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ ምክንያቱም መከፋፈል የክርስቶስን አካል የሚያቆስልና አማኙ የተጠራበትን ለዓለም ሊሰጥ የሚገባውን ምስክርነት የሚያንሸዋርር ነው” (ምንጭ፤ Catholic Herald, January 27, 2014)
- የዓለምን ሰላም በተመለከተ መሪዎች በቀዳሚነት የሚያማክሩትን ሊቀጳጳስ ፍራንሲስን ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ፖፕ ፍራንሲስ በቫቲካን ከእስራኤልና ፍልስጤም መሪዎች ጋር የጸሎት ጉባዔ አካሂደዋል። ከዚህ ሌላ በላቲን አሜሪካ ያላቸውን ከፍተኛ ተቀባይነት በመጠቀም (የተወለዱትም እዚያው ነው) በኩባና በአሜሪካ መካከል ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን ልዩነት በማጥበብ ወደ ስምምነት አንዲመጡ አድርገዋል። (ምንጭ፤ Sylvia Poggioli, National Public Radio, April 14, 2016 ዘገባ)
- የማንኛውም አገር መሪ ወደ አሜሪካ ለጉብኝት ሲመጣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአውሮጵላን ማረፊያ በመሄድ አቀባበል አያደርግም። ነገርግን በ2015 ዓም ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ ወደ አሜሪካ በመጡ ጊዜ በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኦባማ ጳጳሱ በመጡበት የአሜሪካ የአየር ኃይል በመሄድ ይፋዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ይህም በኋይት ሃውስ (ነጩ የአሜሪካ ቤተመንግሥት) አስደተዳደር የተወሰደ እርምጃ መንግሥትና የአሜሪካ ሕዝብ ለጳጳሱ ያላቸውን ታላቅ አክብሮት ያሳዩበት ተደርጎ ተወስዷል። ከዚህ ሌላ በአሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ በአሜሪካ ጣምራ ምክርቤት ፊት በመቅረብ ንግግር አድርገዋል። (ምንጭ፤ Irish Daily Mail, September 23, 2015)
11. ባሁኑ ዘመን አሜሪካ ምን ያህል ብርቱና ተጽዕኖ ፈጣሪ ነች?
ባለንበት ዘመን አሜሪካ ብቸኛዋ የዓለም ልዕለ ኃያል ነች። አንዳንድ ጠቋሚ መረጃዎችን እንመልከት፤
- “በቀጣይ ባሉት በርካታ ዓመታት በብዙ ዘርፎች አሜሪካ ቀዳሚ ኃያል አገር ሆና ትቀጥላለች”–Ian Bremmer, Time magazine, May 28, 2015
- “በጦርነትና በሰላም መካከል ያለው ወሳኝ ልዩነት … መልካም አስተሳሰብ፣ ከረር ያሉ ቃላት፣ ወይም የላቀ ትብብርና ስምምነት ሳይሆን አሜሪካ እስከ ምድር ጥግ ለመድረስ የምትዘረጋው ብቃት፣ ተዓማኒነትና ዓለምአቀፋዊነት ነው” – Senator John McCain, November 15, 2014
- “አሜሪካ በጣም አስፈላጊ ወይም ምትክ የሌላት አገር ናት እንደዚህ ሆናም ትቀጥላለች፤ ይህ ለበርካታ መቶ ዓመታት የኖረ ሐቅ ነው፤ ወደፊትም ለበርካታ መቶ ዓመታት ሐቅ ሆኖ ይቀጥላል” – President Barack Obama, May 28, 2014.
- የቀድሞው የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁበርት ቬርዲን በፓሪስ በተደረገ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ “አሜሪካ ማለት በሁሉም ዘርፍ የላቀ የበላይነት ያላት ልዕለኃያል (‘hyperpower’) አገር ነች” ብለዋል – The New York Times, February 5, 1999

ምንም እንኳን እንደ ሩሲያና ቻይና ያሉ አገራት የአሜሪካንን የበላይነት የሚገዳደሩ ኃይላት መሆናቸው ባይካድም አሜሪካ የሚቃጣባትን ማንኛውም ጥቃት ፈጥና ለመቋቋምና ለመመከት የመቻሏ ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። በመሆኑም በዓለማችን ላይ ከፍተኛ የበላይነት ኖሯት መቀጠሏ የማይቀር ነው። ስለሆነም በዓለም ሰላም ወይም በጸጥታና መረጋጋት ስም ዓለምን የሚያስተባብር ድንጋጌ ቢወጣ ወደፊት የሚነሱትም ሆነ አሁን በሥልጣን መንበር የሚገኙት ፕሬዚዳንት ሕጉን ከመደገፍና የአሜሪካንን ተፅዕኖ በመጠቀም ሕጉን ከማስፈጸም ወደኋላ አይሉም።
12. ዓለምን አንድ የማድረጊያና ይህንን የሚቃወሙትን ደግሞ ጸጥ የማሰኛ ምክንያቶች ምን ይሆናሉ?
ዓለምን አንድ ለማድረግ በጥቅም ላይ የሚውለው መንገድ አንድ ብቻ ነው ለማለት አይቻልም። በአንድ መንገድ ብቻ 8 ቢሊዮን የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ አንድ ለማድረግ አይቻልም። ነገር ግን በቅርቡ እንዳየነው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ዓለም በአንድ መንገድ እንዲጓዝ አድርጎታል፤ ከበርሊን እስከ ቤንሻንጉል፤ ከፓሪስ እስከ ቦረና፤ ዓለም በአንድ ቋንቋ ሲናገር፣ መረጃ ሲለዋወጥ፣ ሕግ ሲያወጣ፣ ሕግ ሲያስፈጽም፣ ወዘተ ታይቷል። ይህ በማንም ሰው ስሌት ይሆናል ተብሎ ያልተጠበቀ ክስተት ነው። ስለዚህ ወደፊት የሚሆኑትን ከወዲሁ ለመናገር ቢከብድም ከሚታዩት ሁኔታዎች ጥቂቶቹን እንዘርዝር፤

- አሸባሪነት
- ከወንጀል መበራከትና ያንን ተከትሎ የሚነሳው ብጥብጥ
- አደንዛዥ ዕፅ ዝውውርና በዚያ ላይ የሚታወጀው ጦርነት
- የኢኮኖሚ ቀውስ
- ወረርሽኝ (እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ)
- ከጽንፈኛ መንግሥታት የሚነዛው የኑክሊየር ዛቻ
- የፖለቲካ ሙስና
- የፍትህ መጨናገፍ (ኢፍትሐዊነት)
- የማኅበራዊና የፖለቲካ ውዝግብ
- የግብር መጨመር
- የግብረገብነት (የሞራል) መዝቀጥና መረን የለቀቀ ብልግና (በፍትወት መቃጠል)
- ዓለምአቀፋዊ የተፈጥሮ አደጋ
- የአካባቢ ብክለት
- አክራሪነትና ጽንፈኝነት
እነዚህንና የመሳሰሉትን ለመዋጋት በሚል የሚወጡ ሕግጋት በመብት ገፈፋ ላይ የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይሆንም። አሸባሪነትን፣ ሕገወጥነትን፣ ኢግብረገባዊነትን፣ ልቅነትን፣ ኢፍትሐዊነትን፣ ድህነትን፣ ሙስናን፣ ወዘተ ላይ የሚታወጀው ጦርነት አስፈላጊ ቢሆንም ይህንኑ ተከትሎ የሚወጡ አፋኝ ሕግጋት የመብት ጥሰት በማስከተል በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ሊደረግ ይችላል።
13. የዓለም ችግር እየተባባሰ ሲሄድ ሰይጣን ብዙሃኑን ለማሳሳት ምን ያደርጋል?
“እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል። በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል” (ራዕይ 13፡13-14)።
በዓለማችን እንደምናየው ሃይማኖት ትልቁ የሰዎችን ህይወት የሚነካ ጉዳይ ሆኗል። በየቦታው የሃይማኖት መነቃቃትና የተዓምራትና የፈውስ አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ። የብልጽግና ወንጌልም በድህነትና በመከራ የሚማቅቀውን ህዝብ የተስፋ ዳቦ እያበላ የእንቅስቃሴውን አራማጆች ኪስ እያደለበ ይገኛል።
ይህ በተለይ በአሜሪካ አገር በቀላሉ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን አሜሪካ ከአነሳሷ ጀምሮ ሃይማኖትን (በተለይ ፕሮቴስታንትነትን) መሠረት ያደረገች አገር በመሆኗ ለሃሰተኛ መነቃቃት በጣም ቅርብ የሆነች አገር ናት። ከላይ እንደተመለከትነው አሜሪካ ከምድር በወጣው በግ መሰል አውሬ ብቻ ሳትሆን በሐሰተኛ ነቢይ ጭምርም ትመሰላለች። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ወደ ስህተት ለመምራት ዓይነተኛ መንገድ የሚከፍት ይሆናል።
ሌላው አሜሪካ ባላት ሥልጣን በመጠቀም ዋናዋ ዓላማ ለጳጳሳዊ ሥርዓት ምስል ማቆም ስለሆነ የእሁድ ሰንበትነት በአዋጅ እንዲጸድቅ በማድረጉ ሒደት ቁልፍ ሚና ትጫወታለች። እሁድ ዓለምአቀፋዊ የዕረፍት ቀን ሆኖ እንዲከበር የሚወጣውን ሕግ የማይታዘዙ፤ እውነተኛውንና ሰባተኛውን ቀን ሰንበት የሚያከብሩ መግዛትና መሸጥ እንዳይችሉ የሚገደዱበት ሁኔታዎች እንዲመቻች በማድረግ በኩል አሜሪካ በቀዳሚነት ከሌሎች አገራት ጋር በመሆን የምትከውነው ይሆናል። የዓለም ችግር ሲፋፋም፤ ሰዎች ወደ “አምላካቸው” እንዲጮኹ ሲደረግ፤ በአንድነት እንዲያመልኩ ሁኔታዎች ሲመቻቹ፤ ከሌሎች ላለመለየትና ዒላማ ውስጥ ላለመግባት ይህንን ሃሰተኛ እንቅስቃሴ የሚቀላቀሉ ጥቂት አይሆኑም። አምነውበትም ይሁን ፈርተው አውሬውን ምልክት በግምባራቸው ወይም አቀኝ እጃቸው ይቀበላሉ።
14. ሃሰተኛው መነቃቃት ሲፋፋም እውነተኛውስ እንደተዳፈነ ይቀራል?
“ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች” (ራዕይ 18፡1)።
በማቴዎስ 24፡14 እንደምናነበው “ለአህዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን … ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል”። ይህ ወንጌል በሚሰበክበት ጊዜ ምድር በወንጌል ከሚመጣው ብርሃን የተነሣ ትበራለች። በተለይም እግዚአብሔር በራዕይ 14፡6-14 ላይ የተናገረው ሦስትዮሽ ይዘት ያለው መልዕክት የዓለም ሕዝብ ሁሉ የሚሰማውና ምርጫውን የሚያስተካክልበት ይሆናል።

ይህ ምድርን የሚያበራ ወንጌል በሚሰበክበት ጊዜ እጅግ ብዙዎች ከዚህ በፊት ሰምተውት የማያውቁትን እውነት በመስማት በደስታ ይቀበሉታል። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተከፈለውን መስዋዕትነት በመቀበል ራሳቸውን ለዳግም ምፅዓቱ ያዘጋጃሉ። አውሬውን አንሰማም፣ ለምስሉ አንሰግድም፣ ምልክቱንም አንቀበልም በማለት በገሃድ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት ይገልጻሉ። በዚህም የእግዚአብሔርን ማኅተም ይቀበላሉ፤ ለዘላለማዊ መንግሥቱም ይታተማሉ (ራዕይ 7፡2-3)።
ይህንን መልዕክት የሚቀበሉ እምነታቸው ሊፈተን፣ ሊሰደዱና ለመኖር እስኪያቅታቸው ድረስ መግዛትና መሸጥ እንዳይችሉ ሊገደዱ ይችላሉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ይህንን ተስፋ ሰጥቶናል፤ “እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች” (ኢሳይያስ 33፡16)፤ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” (መዝሙር 34፡7)።
15. ሁኔታው ሲፋፋም በራዕይ 13፡14-15 በተጠቀሰው መሠረት ሰዎችን ለማሳመን የሚተገበረገው ዋንኛ ስልት ምንድነው?
በእግዚአብሔር ያመኑትን ሳይቀር እምነታቸውን የሚፈትን ታላቅ ድንቅና ተዓምራት ይካሄዳል። በመጨረሻው ጊዜ ሰዎች እውነትን እያወቁ ለእውነት በመቆም ውሳኔያቸውን እያከረሩ ሲመጡ እነሱን ለማሳመን እጅግ አስደናቂ ተዓምራትና ድንቅ ይከናወናሉ (ማቴዎስ 24፡24)። ሰይጣን እና አጋንንቱ የሞቱ ወገኖቻችን እና ከመጽሐፍ ቅዱስ የታወቁ የእግዚአብሔር ነቢያትንና ሃዋርያትን በመምሰል ይገለጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ (ራዕይ 18፡23)። ይህንንም በሚያደርጉበት ጊዜ እነዚህ አሳሳች አጋንንትና የሰይጣን ተወካዮች እግዚአብሔር ልኮን ነው የመጣነው በማለት ነው ብዙዎችን በመዋሸት የሚያታልሉት (ዮሐ. 8፡44)።
ሰይጣን ክርስቶስን በመምሰል ይገለጣል፤ አጋንንቱም የክርስቲያን አገልጋይ ሆነው ይታያሉ፤ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ይገለጣል ይላል 2 ቆሮንቶስ 11፡13-15። ይህ ብቻ ሳይሆን ጌታችንን ኢየሱስ መስሎ በግልጽ በመታየት ብዙዎች እንዲሰግዱለት ያደርጋል (ማቴዎስ 24፡23-24)። ይህንን በሚደርግበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሰንበትንም ጨምሮ መቀየር በማስፈለጉ ምክንያት እንደተቀየረና ሰዎች በዚህ መልኩ እንዲታዘዙት የሚችለውን ማሳመኛ ሁሉ ይጠቀማል፤ ብዙዎችም ለውሸቱና ለቅጥፈቱ እጅ ይሰጣሉ።
በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዚህ ማታለያ ሰለባ ይሆናሉ፤ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዓለማችን ሰዎች ሰይጣንን በእውነት ኢየሱስ ነው ብለው ይቀበላሉ። ጌታችንን በምድረበዳ በፈተነው ጊዜ ሰይጣን ወድቀህ ስገድልኝ እንዳለው (ማቴዎስ 4፡9)፤ በዚህ ወቅትም ሰዎች እንዲሰግዱለት ያደርጋል፤ “ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ” (ራዕይ 13፡3)። አውሬውን የሚያንቀሳቅሰውና ትዕዛዝ እየሰጠ የሚመራው ዘንዶው የተባለው ሰይጣን ስለሆነ ለአውሬው የሚሰጥ ማንኛውም ስግደት ለዘንዶው እንደ ገጸበረከት የሚቀርብ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ግን አይታለሉም፤ ለሰይጣን ማሳሳቻ አይበገሩም፤ ማንኛውንም ነገር በቃሉ ይፈትናሉ (ኢሳይያስ 8፡19-20፤ 2ጢሞቴዎስ 2፡15)። የእግዚአብሔር ሕግ መቼም ቢሆን የማይለወጥ ነው (ማቴዎስ 5፡18)። ጌታችን ወደ ምድር ዳግም ሲመጣ ዓይን ሁሉ ያየዋል (ራዕይ 1፡7)፤ እንጂ በምድር እየተንጎራደደ ሕሙማንን አይፈውስም፤ እግሩም ምድርን አይረግጥም፤ ይኸው እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ ብሎ አዋጅ አያስነግርም፤ ሰበር ዜና አያሰማም (1ተሰሎንቄ 4፡16-17)።
16. ከመጨረሻው ዘመን አደገኛ ማታለያ እንዴት እንጠበቅ?
- ሁሉንም ትምህርት በእግዚአብሔር ቃል በመፈተን (2ጢሞቴዎስ 2፡15፤ የሐዋሪያት ሥራ 17፡11፤ ኢሳ. 8፡20)፤
- በጌታችን የተገለጸውን እውነት ከልብ በእምነት በመከተል (ዮሐንስ 7፡17)፤
- ከኢየሱስ ጋር በቅርብ በመኖር፤ ከእርሱ ባለመለየት (ዮሐንስ 15፡5)፤
ተጨማሪ ጥያቄዎች፤
1. ለዘመናት እውነትን ሳይሰሙ የቆዩ ሰዎች በመጨረሻው ሐሰተኛውን ትምህርት ተቀብለው መጥፋታቸው እንዴት ትክክል ይሆናል?
የመጨረሻውን ጊዜ በሚሆንበት ወቅት ማንም ሰው እውነቱን ሳይሰማ እና መወሰን ሳይችል የስህተትን መንገድ ሊመርጥ አይችልም። እግዚአብሔር አመጸኛ አምላክ አይደለም። ሁሉም ሰው እውነትን እንዲሰማ ያደርጋል፤ ቃሉም የሚመሰክረው ይህንኑ ነው (ማርቆስ 16፡15፤ ዮሐንስ 1፡9)። በራዕይ 14፡6-12 የተጻፈው ሦስትዮሹ መልዕክት ለሁሉም ሰው በግልጽና ምንም በማያሻማ ሁኔታ ይቀርባል። ከዚህ በኋላ ነው ሰዎች የአውሬውን ምልክት የሚቀበሉት እና ወደ ጥፋታቸው የሚሄዱት፤ ምክንያቱም ክርስቶስን መከተል ዋጋ ያስከፍላል፤ መስዋዕትነት አለው።
2. በራዕይ 16፡12-16 የተጠቀሰው የአርማጌዶን ጦርነት ምንድነው? የት፣ መቼና ከማን ጋር ይደረጋል?
የአርማጌዶን ጦርነት በክርስቶስና በሰይጣን መካከል የሚደረግ የመጨረሻው ጦርነት ነው። የሚካሄደውም በዚህች ምድር ላይ ሲሆን ልክ የመጨረሻው ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት የሚፈጸም ይሆናል። ነገርግን ጦርነቱ በጌታችን ዳግም ምፅዓት ምክንያት ይቋረጣል፤ ይጨናገፋል። ከዚያ 1,000 ዓመት ከተጠናቀቀ በኋላ በድጋሚ ይነሳል፤ ሆኖም በዚህ ወቅት ኃጥአን ከሰይጣንና መላዕክቱ ጋር በመሆን አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ለመውረር በሚያነሱት ጦርነት እሣት ከሰማይ ወርዶ ይበላቸዋል፤ ጦርነቱም ይጠናቀቃል።
“አርማጌዶን” ምን ማለት ነው?
ይህ አርማጌዶን የተባለው “ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን የሚሆነው ጦርነት” ነው፤ ይህም የሚካሄደው ሁሉም ሰው በሚሳተፍበት ሁኔታ በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ነው (ራዕይ 16፡12-16፣19)። “ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው” የተባለው ለእግዚአብሔር አብና ለልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “የፀሐይ መውጫ” የሚለው “ምስራቅ” ተብሎ የሚጠራው ሲሆን የሚያመለክተውም የእግዚአብሔርን የሰማይ መንግሥት ነው (ራዕይ 7፡2፤ ሕዝቅኤል 43፡2፤ ማቴዎስ 24፡27)። በዚህ ጦርነት ዓለም በሙሉ ይሳተፋል (ራዕይ 16፡14)፤ ጦርነቱም የሚከፈተው ጌታችን ኢየሱስንና እርሱን በሚከተሉ ላይ ነው (ራዕይ 17፡14፤ 19፡19)። የጦርነቱ ዋንኛ ዓላማም አውሬውን አናመልክም፣ ምልክቱንም አንቀበልም ያሉትን በማስወገድ ላይ ያነጣጠረ ነው (ራዕይ 13፡15-17)።
የስህተት አሠራርና እውነትን መርገጥ
የእግዚአብሔርን መልዕክት ለመቀበል አሻፈረን የሚሉና እውነትን ሲቃወሙ የኖሩ ሁሉ ውሸትን ለመቀበል ሁኔታው የተመቻቸ ይሆንላቸዋል (2 ተሰሎንቄ 2፡10-12)። ከዚህም የተነሳ በተዘፈቁበት የሃሰት አሠራር ውስጥ ሆነው የእግዚአብሔር ሥራ ነው ብለው በማሰብ እውነተኞቹን የእግዚአብሔር ልጆች ለማጥፋት በርትተው ይሠራሉ። ቅዱሳን የጌታ ሰዎችንም “አክራሪ፤ ጽንፈኛ” ብለው በመሰየም የዓለምን ጥፋት የሚያልሙና የሚመኙ እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን መነቃቃት (ሃሰተኛውን) የሚቃወሙ አድርገው በመውሰድ የጥቃት ዒላማ ያደርጓቸዋል። ይህ ለሁለት ጎራ ክፍፍል የአርማጌዶን ዋነኛ የጦርነት ሃሳብ ይሆናል።

የጌታችን ዳግም ምፅዓት ጦርነቱን ያስቆማል
የአርማጌዶን ጦርነት ዓለምአቀፋዊ ነው። መንግሥታት የእግዚአብሔርን ልጆች ለማጥፋት ይሞክራሉ፤ ጌታ አምላክ ግን ጣልቃ ገብቶ ይታደጋቸዋል። ከላይ በጥቅሱ እንዳነበብነው በምሳሌ የተጠቀሰው የኤፍራጥስ ወንዝ ይደርቃል (ራዕይ 16፡12)። ከዚህ በፊት እንዳጠናነው ውሃ በትንቢት ብዙ ሕዝብን ነው የሚያመለክተው (ራዕይ 17፡15)። የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ የሚያመለክተው አውሬውን ሲደግፉ የነበሩ እጅግ በርካታ ሰዎች ለአውሬው (ለሰይጣን) ይሰጡ የነበረውን ድጋፍ የሚያቆሙ መሆኑን ነው፤ ሁሉ ነገር ይደርቃል። የተመሠረተው ሃሰተኛ ጥምረት የእምቧይ ካብ ይሆናል (ራዕይ 16፡13-14 እና 19)፤ የክርስቶስ ዳግም መመለስ ጦርነቱን በማስቆም ለመከራ ተዳርገው የነበሩትን ልጆቹን ይታደጋል (ራዕይ 6፡14-17፤ 16፡18-21፤ 19፡11-20)።
ጦርነቱ ከ1,000 ዓመት በኋላ እንደገና ይደረጋል
ሺሁ ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ላይ በሚደረገው ጦርነት ዋና መሪ በመሆን ተከታዮቹን አስተባብሮ ለጦርነት ይነሳል። ከሺህ ዓመት በፊት ያቋረጠውን ጦርነት በማዘመን በልዩ ሁኔታ ኃይሉን አስተባብሮ የእግዚአብሔርን ከተማ ሊወርር ሲል እሣት ከሰማይ ወጥቶ እርሱንና ተከታዮቹን በሙሉ ያጠፋቸዋል።
3. ጌታችን ኢየሱስ “የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል” ብሎ ነበር (ዮሐንስ 16፡2)። በርግጥ ይህ በዚህ ዘመን ይፈጸም ይሆን?
አዎ፤ በመጨረሻው ጊዜ በመንግሥታትና በሃይማኖት ድርጅቶች መካከል በሚፈጠረው ኅብረት ለእግዚአብሔር ልጆች የሚሰጠው ርኅራኄ ያከትማል። ሃሰተኛውን መነቃቃት በመቀበል ለእግዚአብሔር እየሠሩ የሚመስላቸው በርካቶች የእሁድ ሰንበት አምልኮን ይቀበላሉ። ከመነቃቃቱ ጋር በተያያዥነት የሚከሰቱት ድንቆችና ተዓምራት ትክክለኛ ለመሆናቸው እንደ ማስረጃ ይቀርባሉ። ፈጽሞ ይድናሉ ተብለው የማይጠበቁ በሽታዎች ሊድኑ፣ ሙታንም ሳይቀሩ የተነሱ መስለው ሊታዩ ይችላሉ፤ ሃይማኖተኛ ይሆናሉ ተብለው የማይገመቱ ብዙዎች በዚህ መነቃቃት ምክንያት የእምነትን መስመር ተከትዬአለሁ እያሉ ሲናገሩ በየሚዲያው በስፋት የሚወራ ጉዳይ ይሆናል። ይህንን ዓይነቱን መነቃቃት የሚቃወሙ ፈጽሞ ተቀባይነት የማያገኙና ጸረ መነቃቃትና ተሃድሶ ተደርገው ይወሰዳሉ። በዚህ ሃሰተኛ መነቃቃት ውስጥ የሚገቡት ሰዎች እሁድን እንደ እውነተኛ ሰንበት ለመቀበል ብዙ የማይከብዳቸው ይሆናሉ። ይህንን ሃሰተኛ ትምህርት አንቀበልም የሚሉ በአሁኑ ዘመን “አክራሪ ትምህርት” ተከታዮች እንደሚባሉት በዚያም ጊዜ ከዚህ በበለጠ ይወነጀላሉ። ጸረ ሰላም፣ ጸረ አንድነት፣ ጸረ ወንድማማችነትና ጸረ ኅብረት ተብለው ይፈረጃሉ። ከዚህ ጽንፈኛ አቋማቸው በመላቀቅ ዓለምአቀፉን መነቃቃት እንዲቀላቀሉ ጥሪዎች ይቀርቡላቸዋል። አንዳንዶች እሺ ብለው ጥያቄውን የሚፈጽሙ ሲሆን እምቢ የሚሉትን ግን ከሃዲ፣ ጽንፈኛ፣ ግትር፣ አውቃለሁ ባይ፣ ትምክህተኛ፣ አደገኛ አክራሪ፣ ወዘተ ብለው በመፈረጅ እነዚህን ካላጠፋን ሰላም አናገኝም በሚል ሞት ይፈረድባቸዋል። በዚህ መልኩ እውነተኞቹን የእግዚአብሔር ልጆች በመግደልና በማሳደድ ተግባር የሚጠመዱት ራሳቸውን ለሃይማኖታቸው ቀናዒ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጻሚ አድርገው በመውሰድ በሙሉ ልብ ለሚፈጽሙት ግፍ ማጣፊያ ለማቅረብ ይሞክራሉ።
4. የዳንኤልን እና የራዕይ መጻሕፍትን ስናጠና ሁልጊዜ ዋንኛው ጠላት ዲያብሎስ መሆኑን ነው የምንረዳው፤ ትክክል ነው?
ምንም ጥርጥር የለውም፤ የሁልጊዜ ጠላታችን ሰይጣን ነው፤ እርሱ ደግሞ የሚሠራው የምድር ነገሥታትን፣ መሪዎችንና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን በመጠቀም ነው። ይህንንም በማድረግ የእግዚአብሔርን ልጆች ይጎዳል፤ እስከ መግደልም ይደርሳል። በዚህ ድርጊቱ እግዚአብሔር አምላክንና ልጁን ጌታችን ኢየሱስን እንደሚጎዳ ያውቃል። ለማንኛውም ክፋት ሁሉ ተጠያቂው ሠይጣን ነው። ከተኮነነም በቅድሚያ መኮነን ያለበት እርሱ ነው እንጂ ሰዎች ወይም የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች አይደሉም። በግለሰቦች፣ በመሪዎች (የሃይማኖትም ይሁን የፖለቲካ)፣ በመሳሰሉ ሰዎች ላይ ጣት ከመቀሰር ልንጠነቀቅ ይገባል። አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህም ድርጊታቸው ሰዎችን ሲጎዱ ላያውቁት ይችላሉ። ሰይጣንን በተመለከተ ግን እንደዚህ አይደለም፤ እርሱ የሚሠራውን ጠንቅቆ ያውቃል። እግዚአብሔርንና ሕዝቡን ሲጎዳ ሆን ብሎ አስቦና አቅዶ ነው።
5. የርዕሳነ ሊቀጳጳስ ሞት ይሁን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መቀየር በራዕይ 13፡11-18 ትንቢት አፈጻጸም ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖር ይሆን?

የመሪዎቹ መቀያየር በትንቢቱ አፈጻጸም ላይ የሚያመጣው ምንም ለውጥ የለም። ምናልባት የሰዎቹ ማንነት እና የግል ዕምነት ትንቢቱ እንዲፈጸም ሊያፋጥን ወይም ሊያዘገይ ይችላል። የትንቢቱ አፈጻጸም ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው ነው የሚሆነው።
6. በራዕይ 13፡11-18 በግ መሰል አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውና በራዕይ 16፡13 ሃሰተኛው ነቢይ የተባለው አንድ ናቸው?
አዎ አንድ ናቸው፤ በራዕይ 19፡20 አውሬው እና ሐሰተኛው ነቢይ ወደ እሣት ባሕር በመጣል እንደሚቃጠሉ ይናገራል። በዚሁ ምዕራፍ 19 ስለ ሃሰተኛው ነቢይ ሲናገር ተዓምራትን የሚያደርግ፣ ሰዎች የአውሬውን ምልክት እንዲቀበሉና ለምስሉም እንዲሰግዱ የሚያስታቸው እንደሆነ ይናገራል። በራዕይ 13፡11-18 በግ መሰል አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውም ይህንኑ ሥራ እንደሚያደርግ እናነባለን። ስለዚህ በራዕይ 19 ሐሰተኛው ነቢይ ተብሎ የተጠቀሰውና በራዕይ 13 በግ መሰል አውሬ የተባለው አንድና ተመሳሳይ ናቸው።
(ቅንብር፤ ጥበበሥላሴ መንግሥቱ)










