giziew.org

የክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርት የትውልድ መንደር ተገኝቶ ይሆን?

ለዘመናት የሥነቅርስ ተመራማሪዎች ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ እንድርያስና ፊሊፕ የሚኖሩበትን መንደር ለማግኘት ፍለጋ ላይ ነበሩ
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የሥነቅርስ (አርኪዎሎጂ) ተመራማሪዎች በሰሜናዊ እስራኤል በቤተሳይዳ ከተማ የክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርት የትውልድ መንደር ሊሆን ይችላል የተባለ ቦታ በቁፋሮ ማግኘታቸው ተነገረ። ቦታው ጴጥሮስ፣ እንድርያስ እና ፊሊጶስ የኖሩበት መንደር ሊሆን ይችላል የሚለውን ግምት ከፍ አድርጎታል።

የሃይማኖት ዜና አገልግሎት (Religion News Service) ነሐሴ 1፤2009 ዓም እንደዘገበው ከሆነ ባለፈው ዓመት የሰኔና ሐምሌ ወራት ውስጥ ከእስራኤልና ከኒው ዮርክ ኮሌጆች የመጡ የሥነቅርስ ተመራማሪዎች ያሉበት ቡድን ከአንደኛው እስከ ሦስተኛው ክፍለዘመን ድረስ እንደነበር የሚገመት የመታጠቢያ ቤትና የሸክላ ስብርባሪዎች እንዲሁም ሳንቲሞችን በገሊላ ባህር አካባቢ በምትገኘው ቤተሳይዳ ከተማ አግኝተዋል።

እነዚህ ግኝቶች በአንደኛው ክ/ዘ የነበረው ፍላቪየስ ጆሲፈስ የተባለው የታሪክ ጸሐፊ ባሰፈረው መልኩ በቤተሳይዳ መገኘታቸው ለታሪኩ ተዓማኒነት እንደ ማስረጃ ቀርቧል፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ በኅብር የተሠሩ ወርቃማ ብርጭቆዎች፣ “ጠቃሚ” እና “ትልቅ” ቤ/ክ በቦታው ላይ እንደነበር የሚጠቁም መረጃ ከዚህ በፊት መገኘቱን በወቅቱ ከኮሌጆቹ የተሰጠው መረጃ አስታውቆ ነበር፡፡ የተመራማሪዎቹ ቡድን መሪ የሆኑት መርዶክዮስ አቫይም እንደሚሉት ይህ ግኝት በስምንተኛው ክ/ዘ የነበረ መናኝ ክርስቲያን በ“ቤተ-ጻይዳ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለነበሩት ለጴጥሮስና እንድርያስ ክብር” የተሠራ ቤ/ክ አለ ብሎ ከተናገረው ጋር የሚስማማ መሆኑን ለዜና አገልግሎቱ ተናግረዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሦስቱ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ከቤተሳይዳ ከተማ ይኖሩ ነበር፤ “ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ” (ዮሐንስ 1፡44)። እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ አሁን በቁፋሮ የተገኘው ቦታ የቤተሳይዳ ክፍል ከመሆኑ ባሻገር ሦስቱ ደቀመዛሙርት የኖሩበት ቦታ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።

በእብራይስጥ የቤተሳይዳ ትርጓሜ የምህረት ቤት ማለት ነው። የተማራማሪዎቹ ቡድን መሪ አቫይም ቡድናቸው በቀጣይ በሚያደርገው ቁፋሮ “ካሁኑ የላቁ ማስረጃዎች” እንደሚያገኝ ዕምነት እንዳላቸው መናገራቸውን የዜና አገልግሎቱ ዘግቧል።

“አንባቢው ያስተውል”!


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *