giziew.org

“ነብይ ኢያሱ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ነው” – ተከታዮቹ

“የተዓምር አገልግሎት አለኝ፤ ሰዎች እየመጡ ይፈወሳሉ፤ ከዚህም ሌላ የሃብት (የብልጽግና) ቅብዓት አገልግሎትም አለኝ ..."
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በአለባበሱ ሽቅርቅር የሆነውን የቴክሳሱን ነብይ ጆሹዋ (ኢያሱ) ሆምስን የማያውቅ ካለ ክርስቶስን አያውቅም ማለት ነው፤ ምክንያቱም “ነብይ ኢያሱ ክርስቶስ ራሱ በሥጋ ነው” ይላሉ ተከታዮቹ። እርሱን የሚጠሉና የሚነቅፉ መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ናቸው፤ በማለት ሌሎቹ ጨምረው ይከራከራሉ። እርሱ የሰዎችን ህይወት በየቀኑ የሚለውጥ ነው፤ … የእግዚአብሔር ኃይል በእርሱ ላይ ነው በማለት ተከታዮቹ ይመሰክሩለታል።

በውድ ልብሶች በማሸብረቅ የሚታወቀው ወጣቱ ኢያሱ ብዙዎች የሚተቹት ቢሆንም በቅርብ ወራት በማኅበራዊ ድረገጾች ፈውስ በማድረግና “የገንዘብ ተዓምራትን” በመፈጸም በርካታዎች የሚከታተሉት ታዋቂ እየሆነ መጥቷል። አገልግሎቱን በተመለከተ የለቀቀው የአንድ ደቂቃ ቪዲዮ ከሦስት ሚሊዮን ጊዜ በላይ የፌስቡክ ተመልካች አግኝቷል።

የዚህን “ነቢይ” ማንነትን በተመለከተ የጠራ መረጃ እስካሁን የለም። ስለትንቢታዊ ምሥጢራት የሚገልጽ መጽሐፍ በአንድ መቶ ዶላር በሚሸጥበት የራሱ ድረገጽ ላይም “በጌታ የተጠራ ነቢይ … ብዙዎችን ወደ ደኅንነት የመራ … በአምስት ዓመቱ ለአገልግሎት የተጠራ … በ6 እና በ14 ዓመቱ ጌታ የተገለጠለትና ለነቢይነት የተጠራ ነው” ከማለት በስተቀር ስለ ማንነቱ ግልጽ የሆነ መረጃ የለም።

ከጥቂት ወራት በፊት በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ሲጠየቅ “የተዓምር አገልግሎት አለኝ፤ ሰዎች እየመጡ ይፈወሳሉ፤ ከዚህም ሌላ የሃብት (የብልጽግና) ቅብዓት አገልግሎትም አለኝ፤ ብዙ ሰዎች ስለዚህ አያውቁም፤ ባለፈው ዓመት እግዚአብሔር እኔንም ዘር እንድዘራ (ገንዘብ እንድሠጥ) ተግዳሮት ሰጠኝ፤ ያንን ተግዳሮት ስፈጽምና ያንን ዐቢይ ዘር ስዘራ በወቅቱ ከምኖርባት ቦታ አውጥቶ በ48 ሰዓት ውስጥ በጣም ትልቅ ቪላ ቤት ውስጥ አስገባኝ” በማለት መልሷል።

ሲቀጥልም “እኔ በፋይናንስ በኩል የሰማይ መስኮቶች ተከፍተውልኛል … ብዙዎች ግን በህይወታቸው የገንዘብ ተዓምራት ሲያገኙ ታማኝ ስለማይሆኑ የሃብት፣ የብልጽግና ቅብዓታቸውን ያጡታል” ብሏል።

እጅግ ውድ የሆኑ ልብሶችንና ጌጣጌጦችን በማድረግ የሚታወቀውን ኢያሱ የሚቃወሙት ጥቂቶች አይደሉም፤ ሃሰተኛ ነቢይ ይሉታል። በንግግሩ (በስብከቱ) ውስጥ እጅግ ፀያፍ ቃላትን ከመጠቀሙ ጀምሮ በበርካታ ጉዳዮች ተቃውሟቸውን ያነሳሉ።

የአዘጋጆቹ ማስታወሻ፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ስለኋለኛው ዘመን በማቴዎስ 24፡23-27 ሲናገር ይህንን ብሏል፤ “በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘ይኸውላችሁ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ። እነሆ፤ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። … በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ።” በአገራችንም ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ እንደ ቴክሳሱ ኢያሱ “ሐዋሪያ”፣ “ነቢይ”፣ “ነቢይት” ወዘተ የሚሉ ማዕረጎችን ለራሳቸው እየሰጡና በብልጽግና ወንጌል ብዙዎችን ቀቢጸተስፋ እየሞሉ ለራሳቸው የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩ ጥቂቶች አይደሉም። ይህ በሃይማኖትና በመጽሐፍ ቅዱስ ስም የሚደረግ ውንብድና ለበርካታ አጭበርባሪዎች የገንዘብ ማካባቻ ቀላል መንገድ የከፈተ ሲሆን ብዙዎችን ግን በሃሰት መንገድ ወደሞት እየመራ ነው። ሃሰተኛ ፈውሶች፣ ሃሰተኛ ተዓምራት፣ ወዘተ በሚደረግባቸውና ከውጭው ዓለም በተኮረጀ ስልት ሰዎችን በመሬት ላይ በመዘረር ክብራቸውን በሚነካ መልኩ የሚፈጸመው ተግባር የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጽሞ የማያደርገውና በመጽሐፍ ቅዱስም አንዳች ድጋፍ የሌለው ነው። ነቢይ ነኝ የሚሉትም በመጽሐፍ ቅዱስ ተመርምረው የነቢይነትን ፈተና ማለፍ ይገባቸዋል። ለህይወት ርካታ ደግሞ ሃብትና ገንዘብ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቃል የበለጠ አንዳችም ነገር የለም፤ “ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው” (መዝ.19፡103)። ስለዚህ አንታለል፤ በርካታዎች ስለተሰበሰቡ ጉባዔው ትክክለኛ ነው ብለን በሰፊው የስህተት መንገድ አንጓዝ፤ ከላይ በጥቅሱ እንደተመለከተው “በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ”። ራሳቸውን በፈለጉት ስም የሚጠሩት ታየኝ፣ ተመለከትሁ፣ በራዕይ ነበርሁ፣ … የሚሉት ሳይሆን የአምላካችን ቃል ብቻውን ለዘላለም ይኖራል፤ “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ኢሳ. 40፡8።

“አንባቢው ያስተውል”


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *