giziew.org

በእግር እንሂድ

የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግ ጂም መሄድ ወይም እጅግ ውድ የሆኑ ማሽኖችን መግዛት አስፈላጊ አይደለም የሚሉት ተመራማሪዎች ቀላሉና ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለው በእግር መጓዝ ነው
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በቅርቡ በአሜሪካ አገር ዕድሜያቸው ከ45 እስከ 75 በሆኑ 400 ሴቶች ላይ ጥናት ተካሂዶ ነበር። ሁሉም ሴቶች ከሚገባው በላይ ክብደት ያላቸው ወይም በጣም የወፈሩ፣ በአብዛኛው ቁጭ ብለው የሚሠሩና ከፍተኛ የደም ግፊት ያላቸው ነበሩ። ተመራማሪዎቹ እነዚህን ሴቶች በአራት ቡድን ከፈሏቸው። ሦስቱ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ በተለያየ የጊዜ ርዝማኔ የሚያደርጉና ቀሪው አንድ ቡድን ውስጥ ያሉትን ግን የተለመደውን ተቀምጦ የመሥራት ልምዳቸው እንዲቀጥሉ አደረጉ።

ከስድስት ወር በኋላ በሦስቱ ቡድኖች ውስጥ የሚገኙት በሙሉ የደም ግፊታቸው ተሻሽሎ ተገኘ። ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ከበድ ያለ የአካል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት በመጠኑ የተሻሻለ የደም ግፊት እንዳላቸው ተመዝግቧል። በአጠቃላይ ሴቶቹ በአብዛኛው የክብደት መቀነስ ባያሳዩም የደም ግፊታቸውና ጤናቸው ግን የተሻሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ለከፍተኛ የደም ግፊት የሚያጋልጠውን ጭንቀት ለመቀነስ ዓይነተኛ ስልት ነው። በተለይ የስኳር በሽተኞች፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ያላቸው፣ የልብ ሕሙማን በሳምንት ሁለት ሰዓት ተኩል ያህል የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው። ይህ ደግሞ መሆን ያለበት በአንድ ቀን ሳይሆን ቢቻል በየቀኑ ነው ይላሉ ተማራማሪዎቹ። ቢያንስ በቀን 30 ደቂቃ እንቅስቃሴ በማድረግ መሞከር፤ ነገርግን የፈለገው ቢሆን ሁለት ተከታታይ ቀናትን ያለ እንቅስቃሴ አለማሳለፍ ወሳኝነት አለው በማለት ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ይሰጣሉ።   

የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግ ጂም መሄድ ወይም እጅግ ውድ የሆኑ ማሽኖችን መግዛት አስፈላጊ አይደለም የሚሉት ተመራማሪዎች ቀላሉና ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለው በእግር መጓዝ ነው ይላሉ። ረጅም ርቀት መጓዝ ካልተቻለ ለአምስት ደቂቃ ያህል በቀን ሦስት ጊዜ ከተጓዝን ትልቅ ጥቅም እናገኛለን። ቀስ እያልንም ደቂቃዋን ማሳደግ ይቻላል።

ሌሎች ቀላል ምክሮችንም ይለግሳሉ ተመራማሪዎቹ፤ አዘውትረን በመኪና የምንጓዝ ከሆነ የመኪና ማቆሚያችንን ልንገባበት ካሰብንበት ህንፃ በማራቅ በእግር የምንሄድበትን መንገድ ማስረዘም፤ ፎቅ ስንወጣ ሊፍት (አሳንሰር) ከመጠቀም ይልቅ ፎቁ ደረጃ ካለው ያንን ማስቀደም፤ ሌሎች በእግር ልንጓዝ የምንችልባቸውን ነገሮች ከመቀነስ ይልቅ መጨመር። ልምድ እንዲሆን በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ዓላማ ማውጣት፣ ዕቅድ መንደፍ – ከፍተኛ የደም ግፊት ካለን ያንን ለመቀነስ ግብ በማድረግ መነሳትና በየጊዜው ግፊታችንን እየለካን ለውጡን መከታተል ጠቃሚ ተግባር ነው። በምንችለው መጠን ጫማችንና አለባበሳችን በእግር ለመሄድ የሚያመች ቢሆን ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም አጋጣሚውን ባገኘን ቁጥር እንቅስቃሴ ለማድረግ ይረዳናል።

ከዚህ ሁሉ ዋንኛው ነገር ይህንን የአካል እንቅስቃሴ የምንጀምረው ነገ ወይም የዛሬ ሳምንት ወይም በአዲሱ ዓመት ወይም ሌላ ቀን ሳይሆን ዛሬ ነው! አሁን! ወዲያውኑ ቀጠሮ ሳይሰጡ መጀመር!

(ምንጭ፤ Pennington Biomedical Research Center ድረገጽ)

ቅንብር፤ ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *