ጥያቄ፤ በ1954ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ዘፍጥረት 2፡7 ላይ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።” በአዲሱ መደበኛ ትርጉም (አመት) ደግሞ “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ይላል። የዚህ ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም የትኛው ነው?
መልስ፤ ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ጠቅለል ባለመልኩ ስለ ሰማይና ምድር፣ በውስጣቸው ስለሚገኙ ሕይወት ያላቸው ነገሮች አፈጣጠር ከተረከልን በኋላ፣ በተለይ የፍጠረት ቁንጮ ሆኖ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለተፈጠረው ሰው ይገልጽልናል። በምዕራፉ መጨረሻ እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት ተመልክቶ “እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” አለ:: በዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ደግሞ የሰው አፈጣጠር ሒደቱን ዘርዘር ባለመልኩ ከቁጥር 7 ጀምሮ እንዲህ በማለት ይገልጻል።
“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።” 2፡7 (1954 ትርጉም)
“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” 2፡7 (አመት)
“እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ፈጠረ መሬት ከምድር። ባፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።” (1879 ትርጉም)
በዘፍጥረት አንድ ላይ አምላክ ብርሃንን ከጨለማ እንዳወጣ፤ በተመሳሳይ አገላለጽ በምዕራፍ ሁለት ሰውን ከምድር አፈር እንዴት እንዳበጀው ዘርዝሮ ይናገራል።
በዚህ ጽሁፍ ላይ በዘፍጥረት 2፡7 ላይ የተጠቀሱትን “ሰውን አበጀ”፣ “የህይወት እስትንፋስ” እና “ሕያው ነፍስ ሆነ” የሚሉትን ሶስት አባባሎች ትኩረት በመስጠት እንመለከታለን። “ሰውን አበጀ” የሚለውና “የሕይወት እስትንፋስ” የሚሉት አባባሎች እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሲፈጥር የወሰደው እርምጃ ከፍጥረት ሁሉ ይልቅ ለሰው ልዩ ትኩረት መስጠቱን የሚያሳዩ ናቸው።
“ሰውን አበጀ” የሚለውን ቃል ከዕብራይስጡ “ዋይሴር” ከሚለው ግስ የተገኘ ትርጉም ሲሆን፤ ይህም ቃል ስለ እግዚአብሔር ሰውን የመፍጠር ሁኔታ የሚነግረን ስዕላዊ የሆነ አገላለጽን የያዘ ነው። ይኸውም፤
1ኛ፤ አበጀው የሚለው ቃል እግዚአብሔር ሰውን እንደሸክላ ሠሪ እንደቀረጸው (ኤር. 18፡2) የሚገልጥ ሲሆን፤ ይህም ከፍጥረታት ሁሉ ይልቅ ለሰው ልዩ የፍቅር ትኩረት መሰጠቱን የሚያሳይ ነው።
2ኛ፤ እግዚአብሔር ሰውን በገዛ እጆቹ ሲፈጥር ሌሎች ፍጥረታት ግን ቃል በተናገረ ጊዜ ተፈጥረዋል፤ ይህ የሚጠቁመን አምላክ በሰው አፈጣጠር ላይ ልዩ የሆነ መጠበብን እንዳደረገ ነው። (ኢሳ. 44፡9-10)
3ኛ ይህ በእግዚአብሔር የተበጀው ሰው ያለ አምላክ ድጋፍና ዕርዳታ ለመኖር እንደማይችል የሚጠቁም ነው። (ኢሳ. 2፡16)
“የሕይወት እስትንፋስ” የሚለው አገላለጽ ሌሎች ፍጥረታት በአየር ላይ የሚበሩ፣ በውሃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በምድር ላይ የሚርመሰመሱ ሕይወትን ያገኙት እግዚአብሔር ከተናገረው መለኮታዊ የሥልጣን ቃል ሲሆን፤ ሰው ግን ሕይወትን ያገኘው በአምላኩ እጅ ተበጅቶ ብቻ ሳይሆን የሕይወት እስትንፋስ በአፍንጫው እፍ ተብሎበት፤ ለልዩ ዓላማና በልዩ ትኩረት መፈጠሩን የሚያስረዳ አገላለጽ ነው። ሰው በልዩ ትኩረት የመፈጠሩን መልካም ዜና ዘፍጥረት 2፡7 ሲያበስር፤ “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ይላል።
ሆኖም ለብዙ ሰዎች አነጋጋሪ የሆነው “ሕያው ነፍስ ሆነ” የሚለው አባባል (አጻጻፍ) ነው። በዚህ ጥቅስ ምክንያት ሰው የተለየ ነፍስ የምትባልና ከአካል ተለይታ የምትገኝ ነገር እንዳለችው ተደርጎ ይታሰባል። ነገርግን ይህንን ጥቅስ መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጡ እና በተለያዩ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በማነጻጸር ስናየው አንዳንድ ልዩነቶችን እንመለከታለን።
በመጀመሪያ የ1879ኙን፣ የ1954ቱንና የአዲሱ መደበኛ ትርጉም በማነጻጸር እንመልከት፤
1879 ትርጉም | 1954 ትርጉም | አዲሱ መደበኛ ትርጉም |
ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ | ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ | ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ |
ከእነዚህ ሶስት የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል ዘፍ. 2፡7ትን በተመለከተ የዕብራይስጡን አባባል በትክክል “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” በማለት የገለጸው የአዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው።
በዕብራይስጥ “ነፌሽ ሃያ” በአማርኛ “ሕያው ነፍስ” በማለት የተገለጸው በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሌላ ቦታዎች ወደ ስምንት ጊዜ ያህል የተደገመ ሲሆን፣ ከአዲሱ መደበኛው ትርጉም ይልቅ “ሕያው ነፍስ” የሚለውን ትርጉም ሳይቀያይሩ በዘላቂነት በተደጋጋሚ የተረጎሙት የ1879ኙና የ1954ቱ ትርጉሞች ናቸው። (ዘፍጥረት 1፡21፣24፣30፤ 2፡7፣19፤ 9፡12፣15፣16 እና ሕዝቅኤል 47፡9ን ይመልከቱ።) በ1879ኙና በ1954ቱ ትርጉሞች ላይ የሚታየው ችግር በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን የማይገኙ “ያለበት” ና “ያለው” የሚሉ ቃላቶችን የአማርኛውን ተነባቢነት ለማሳለጥ ሲሉ ከመጨመራቸው የተነሳ ነው፤ ይህም ትርጉማቸውን በስህተት እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው “ነፍስ” የምትባል ልዩ ነገር በውስጡ ይዟል ብለን እንድናስተውል ወይም እንድናስብ አድርጎናል። በተጨማሪም ይህ አስተሳሰብ በማኅበረሰባችን ውስጥ የሚገኝ ተለምዷዊ አስተሳሰብ በመሆን ተስፋፍቶ ይገኛል።
በዘፍጥረት 2፡7 ላይ የሚገኘው የዕብራይስጡ አገላለጽ ግን ሰው “ነፍስ” የምትባል ልዩ ነገር በውስጡ ይዟል ለማለት የሚፈልግ ሳይሆን፤ ሰው ከግዑዝ ፍጥረት ተለይቶ “ሕያው ፍጡር” ሆነ የሚል ነው። በሌላ አገላለጽ በዘፍጥረት 2፡7 መሠረት “ነፍስ” ማለት “ሕያው ፍጡር” ማለት ነው። ስለዚህ ሰው “ሕያው ፍጡር” ሆነ ማለት ከአፈር የተበጀው አካል ሕይወትን አገኘ፣ መንቀሳቀስ፣ ማሽተት፣ ማየት፣ መናገር፣ መስማት፣ ማሰብ፣ ሃሳቡን መግለጽ፣ መቆፈርና መንከባከብ ጀመረ ማለት ነው።
በበለጠ እርግጠኛ ለመሆን እንዲረዳዎት በ1954ቱ የአማርኛ ትርጉም በዕብራይስጡ “ነፌሽ ሃያ” የሚለው አገላለጽ ከዘፍጥረት 2፡7 ውጪ በሚገኙ ቦታዎች እንዴት በአማርኛ እንደተተረጎመ የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበብ ለማስተዋል ይሞክሩ። እነዚህን ጥቅሶች መመልከት በቀላሉ “ነፌሽ ሃያ” ማለት ሕያው ፍጥረት መሆኑን ለመረዳት ይቀልዎታል። በዕብራይስጥ “ነፌሽ” ማለት ፍጥረት፣ “ሃያ” ማለት ደግሞ ሕያው ማለት መሆኑን እነዚህን ጥቅሶች መመልከት በራሱ እንኳ ያረጋግጣል።
ይህ “ነፌሽ ሃያ” የተባለ የዕብራይስጥ ቃል በ1954ቱ የአማርኛ ትርጉም በዘፍ 1፡21 “ሕያዋን ፍጥረታት”፣ 1፡24 “ሕያዋን ፍጥረታትን”፣ 1፡30 “ሕያው ነፍስ”፣ 2፡19 “ሕያው ነፍስ”፣ 9፡12 “በሕያው ነፍስ”፣ 9፡15 “ሕያው ነፍስ”፣ 9፡16 “በሕያው ነፍስ”፣ በመጨረሻ ሕዝ 47፡9 ላይ “ሕያው ነፍስ” በመባል ተተርጉሟል። በእነዚህ ጥቅሶች መሰረት “ነፌሽ ሃያ” ማለት ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ፍጥረት ማለት እንጂ ነፍስ ማለት ሌላ ከአካል ተለይታ መኖር የምትችል ረቂቅና ድብቅ ነገር አይደለችም። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ጥቅሶች እንስሳቶችም ሆኑ ሰዎች በሕይወት እያሉ ራሳቸው ነፍስ እንደሚባሉ ያስረዳሉ።
በአዲሱ መደበኛ ትርጉም “ነፌሽ ሃያ” እንዴት ከዘፍጥረት 2፡7 ውጪ እንደተተረጎመ ስንመለከት ደግሞ፤ በዘፍ 1፡21 “ሕይወት ያላቸው ነገሮች”፣ 1፡24 “ሕያዋን ፍጡራንን”፣ 1፡30 “ሕያዋን ፍጡራን”፣ 2፡19 “ሕያዋን ላላቸው ፍጡራን”፣ 9፡12 “ሕያዋን ፍጡራን”፣ 9፡15ና 16 “ሕያዋን ፍጡራን” ሕዝ 47፡9 “ሕያዋን ፍጡራን” በሚል ተተርጉሟል። በነዚህ ጥቅሶች መሠረት የ“ነፌሽ ሃያ” ጠቅለል ያለ ትርጉም ሕይወት ያላቸው ነገሮች፣ ሕያዋን ፍጡራንና ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ማለት እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም። ስለዚህ ይህ አባባል ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት ጥቅም ላይ በመዋሉ ሕይወት ያለው ነገር ወይም ሕይወት ያለው ፍጡር የሚል ትርጉምን የያዘ እንጂ ነፍስ ከአካል ተለይታ በሰው ውስጥ ተሰንቅራ የምትገኝ ነገር መሆኗን የሚያስረዳ አይደለም።
በተጨማሪ በ1879ኙ ትርጉምና በ1954ቱ ትርጉም ላይ የሚገኙት በዘፍጥረት 2፡7 ላይ የአማርኛውን አነባብ ለማሳለጥ በሚል የገቡት “ያለበት” ና “ያለው” የሚሉት ቃላት በእርግጠኝነት በዕብራይስጡ ላይ እንደማይገኙ ከዚህ በታች ከቀኝ ወደ ግራ የተጻፈውን የዕብራይስጥ ጥቅስና ከስሩ የሚገኙትን የአማርኛ ጥሬ ትርጉም ይመልከቱ።
ይህንን የዕብራይስጥ ዓረፍተ ነገር በግርድፉ ወይም በቀጥታ ወደ አማርኛ ስንመልሰው እንደሚከተለው ሆኖ ሊተረጎም ይችላል።
“እና ኤሎሂም ያህዌ ሰውን ከምድር አፈር አበጀው። እና በአፍንጫው የህይወት እስትንፋስ ተነፈሰበት። እና ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።”
ስለዚህ ይህንን ጽሑፍ የሚያነብ ማንኛውም ሰው እነዚህን መረጃዎች በመመልከት “ሕያው ነፍስ ሆነ” የሚለውን የዘፍጥረት 2፡7 አባባል ሰው ሕይወት ያለው ፍጡር ሆነ ማለት እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ይችላል ማለት ነው።
ዋቢ መጻህፍት፤
HALOT – The Hebrew and Aramaic Lexicon of the Old Testament by Ludwig Koehler And Walter Baumgartner, © 1994-2000 Koninklijke Brill NV, Leiden, The Netherlands. All rights reserved.
Doukhan, Jacques B. Seventh Day Adventist International Bible Commentary: Genesis. Pacific Press, 2016.
Computer Assisted Concordance
(ማሳሰቢያ፤ ይህ እንደ ናሙና በራሳቸውን ያቀረብነው ነው እንጂ ጥያቄው ለዝግጅት ክፍላችን ተልኮልን አይደለም። በቀጣይ ዕትሞች ግን የእናንተን ጥያቄዎች የምናስተናግድ ስለሆነ በአድራሻችን ጥያቄዎቻችሁን እንድትልኩልን ልናሳስብ እንወዳለን።)
ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ