መድኃኒዓለም ሁለት ልጆች ስለነበሩት ሃብታም አባት በሉቃስ ወንጌል ላይ ይናገራል። ከልጆቹ ታናሹ “ነፃነት” እና ልቅ ኑሮ ተመኘ። ምኞቱን ለማድረስ ደግሞ ብዙ ገንዘብና ከአባቱ ቤት ርቆ መሄድ እንደሚያስፈልገው ተረዳ። የምኞቱ ከልካይ የአባቱ በሕይወት መኖር ነበር። አባቱ ቢሞት ንብረቱ ለልጆቹ ሲከፋፈል በተገኘው ሀብት እንደፍላጎቱ መኖር ይችላል። ይህን ቢያውቅም የአባቱን ሞት መጠበቅ አቃተው። አንድ ቀን ደፍሮ “አባቴ ሆይ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ” አለ (ሉቃስ 15:12)።
አባቱ ምን ተሰምቶት ይሆን? የልጁን አስተዳደግ በልቡ መቃኘት ጀመረ። ልጄ ምን ጎደለው? ምን ከልክየው ይህን ለመጠየቅ በቃ? ጥያቄዎቹ ሳይመለሱለትና የልቡ ህመም ሳይድን “ሃብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው” (ሉቃ. 15:12)።
ያ ልጅ ገንዘቡን እንዳገኘ ሕልሙን ኑሮው ለማድረግ ተጣደፈ። “ብዙም ቀን ሳይቆይ … ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ” ወደ ሩቅ አገር ሄደ። የገባበት ከተማ እንደ ተናፋቂ ባለሀብት ተቀበለው። ምሽቱ ደመቀ። ምርጥ ምግብ ቀረበለት። በውድ ዋንጫዎች የተቀዳለትን መጠጥ ቀምሶ ሞቀው። በተስፋ ሲፈትነው የነበረው ፍትወት ድንገት ሥጋ ለብሶ ፊቱ ከተፍ አለለት። ሳያመነታ በእርኩሰት ትኩሳት ውስጥ ተዘፈቀ። ጓደኞች አፈራ፤ ጋበዛቸው። የአባቱ ደምና ወዝ የሆነው ገንዘብ በየመሸታ ቤቱ እንደ ርካሽ ውሃ ፈሰሰ።
ወሬ አይደበቅም። የልጁን ሁኔታ ያ አባት ሲሰማ ምን ብሎ ይሆን? በቁስል ላይ ቁስል ያመጣበትን ልጅ እያሰበ ሃዘን ፀጉሩን ሽበት አለበሰው። በምሳ ሰዓት አብሮት ይበላ የነበረውን ታናሽ ልጁን እያስታወሰ ሰውነቱ በፍርሃት ቀዘቀዘ። መብላት አቃተው። ልጁ ይተኛበት የነበረውን ቦታ በምሽት እየጎበኘ ያለቅሳል። በጧት ተነስቶ “ልጄ ዛሬ ይመለስ ይሆናል” ብሎ አውራ ጎዳና አጠገብ ይቆማል፤ ያለመታከት ይጠብቃል።
ልጁ ግን አባቱን አላስታወሰም። በአዳዲስ ሱሶች መርቅኖ ፈጣን “ደስታ” አገኘ። የልጅነት ትዕቢት ከኅሊና ፍርሃት አራቀው። የበላይነት ተሰማው። ተስማማው። ገንዘብ ዘላቂ ደኅንነት እንደማያመጣ ማስተዋል አልቻለም። መጨነቅ አልፈለገም። ዕድሜውን ሁሉ በዘፈን ግፊትና በእርኩስ ጥጋብ መኖር ፈለገ።
አንድ ቀን ገንዘቡ አለቀ። አባቱ በብዙ ጊዜና ልፋት ያገኘውን ሀብት በጥቂት ቀናት ልቅነት አወደመው። ነገር ብሶ “በአገሩ ሁሉ ፅኑ ራብ ሆነ” (ሉቃ. 15:14)። ልጁ ተቸገረ። ከቦርሳው ገንዘብ መምዘዝ ብቻ የሚያውቀው ወጣት ገንዘብ የሚያስገኝ ሙያ እንደሌለው በጭንቅ ተረዳ። ምን ያድርግ? ሰው የሚፀየፈውን ሥራ ለመስራት ተገደደ። አሳማዎች የመቀለብ ኃላፊነት ተሰጠው።
ሆዱ በረሃብ ተይዞ ሳያቋርጥ ይጮሃል። ምን ያድርግ? አሳማዎቹ እያነፈነፉ የሚበሉትን ዐሰር ተመልክቶ ምራቁን ይውጣል። ምግባቸውን ቢመኝም መብላት አልተፈቀደለትም። ራብ ወደ መቃብር ሊወስደው እንደሚችል ተገንዝቦ ልቡ በፍርሃት መምታት ጀመረ።
አባቱን አስታወሰ። የአባቱ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሠራተኞች ተርበው አያውቁም። የአሳማ ምግብ ለመብላት የተመኘ ሰው ባደገበት አካባቢ መኖሩን አያስታውስም። ትምክህትና ውድቀቱ ፊቱ ተደቀኑ። እውን መስሎት የነበረው ድንቅ ሕልም አደገኛ ቅዥት መሆኑን አይቶ አዘነ። ለካስ ነፃነት ያለው በአባቱ ቤት ነው። በአባቱ ቤት ተጨንቆ የማያውቀው አባቱ ለርሱ ይጨነቅ ስለነበረ ነው። በልቅ ኑሮ ያበላሸው ገንዘብ የአባቱ የጭንቀት ውጤት ነው። ያለፈበት ደስታ ሁሉ የአባቱ ልፋትና መስዋዕትነት ውጤት ነው። በጭካኔውና አባቱን በማቁሰሉ የተሰማው ሐዘን ራቡን አስረሳው። አሁን ግን ከአባቱ ርቋል። ምን ያድርግ?
ልጁ ያለበት አገር በፅኑ ራብ መያዙን አባቱ ሲሰማ ልቡ ተሰበረ። የክት ልብስ የለበሰበትን ቤት ልጁ ሸሽቶ በድህነት፣ በእርዛትና በረሃብ እንደሚሰቃይ ሲያስብ እንባው ፈሰሰ። ሞት ልጁን ለመንጠቅ እያጠላ መሆኑን ማወቁ እንቅልፍ ነሳው።
አንድ ቀን ይህ አባት እንደለመደው መንገድ ዳር ቆሞ አላፊዎቹን በተስፋ ሲቃኝ አንድ ክሳት ያገረጣው ወጣት ከሩቅ ብቅ ሲል አየ። የሽማግሌው አባት ልብ መምታት ጀመረ። የከሳውን ወጣት እርምጃ አጠና። ልጁ ወደ ቤት እየተመለሰ መሆኑን አባትየው ተገንዝቦ እየጮሀ ዕድሜው በሚፈቅደው ፍጥነት ወደ ልጁ ሮጠ። ውሃ ገላውን ባለመንካቱ ጠረኑ የተቀየረውንና ለብዙ ወራት ከሰው ርቆ ከአሳማዎች ጋር በመኖር እነርሱኑ ይሸት የነበረውን ልጁን አቀፈው። እያለቀሰ ተጠምጥሞበት ደጋግሞ ሳመው።
ልጁ የተደረገለት አቀባበል እንደማይገባው ተረድቶ “‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው። አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤ የሰባውንም ፍሪዳ አምጡና ዕረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአል።’ ከዚያም ይደሰቱ ጀመር።” (ሉቃ. 15:21-24)
ይህ አባት የሰማዩ አምላካችን ነው። የአባቱን ንብረት በድፍረት ወስዶ ወደ ልቅ ኑሮ የሄደው ልጅ ደግሞ እኛን — ሰዎችን — ያመላክታል። በአመፃችን የፈጣሪ ልብ ላይ የተውነውን ጠባሳ መቼም ልናስተውለው አንችልም። ተበድሎ ማፍቀር ያላቆመውን አባት ርኅራሄስ ማን ሊረዳው ይችላል?
እግዚአብሔር ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር ለሰዎች ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣል። ውሏችን ከሚሸቱ አሳሞች ጋር ቢሆን፣ በርካሽ ሕይወት ብንበላሽ፣ እርኩሰት ባህርያችንን እንደ ከሰል ቢያጠለሸውም አባታችን የልጅነት ቦታችንን መልሰን እንድንወስድ ይፈልጋል። ለዚህ ግብዣ ጊዜ ሳያልፍ ፈጣን ምላሽ መስጠት አለብን።
ከአባቱ ቤት የጠፋው ልጅ ተስፋ ቆርጦ ከአሳማዎች ጋር መኖሩን ቀጥሎ ቢሆንስ? ወደ አባቱ ቤት እንዲመለስ የጋበዘውን ፀፀት ንቆ በረሃብ እየማቀቀ መኖርን ቢመርጥስ?
ዛሬ በፅኑ ክፋት ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች አምላክ የልጅነት ማዕረግ የማይሰጣቸው መስሏቸው በክፉ ሥራቸው መቀጠሉን ይመርጣሉ። ሌሎች ደግሞ በምድር አታላይ ደስታዎችና በሰዎች ከንቱ ውዳሴ ስለተማረኩ የአምላክን አባታዊ ፍቅር ለማሰብ ጊዜ የላቸውም። ያመለጣቸውን እውነተኛ ደስታና ሀብት የሚያውቀው ሰማያዊ አባት ግን እያለቀሰ የሚመለሱበትን ቀን በናፍቆት ይጠብቃል።
ምድራችን እንደ ፈቃዷ ሰዎችን ከፍ ዝቅ ታደርጋለች። በአንድ ወቅት ድህነት ሊነካቸው አይችልም የተባሉ ሰዎች ዘመን ሲቀየር ለማኞች ይሆናሉ። በጡንቻቸው የፈለጉትን ሁሉ ያገኙ የነበሩ ደግሞ እርጅናና በሽታ አድክሟቸው የመከነው ጡንቻቸው የምኞታቸው ዋና ከልካይ ይሆናል። ዓለም እንዳሻት ትሾምና ወረቷ ሲያልቅ ማቅ ታለብሳለች። የወረቷ ተረኞች ግን ካለፈው ክፋቷ መማር ያቅታቸዋል። ሽልማቷን ተንሰፍስፈው የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር ዕለት በዕለት እየጨመረ ነው።
ዓለም ለፍቅሯ የምታስከፍለው ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ሰዎች የዓለምን ደስታ ለማግኘት የመስገብገባችን አሳዛኝ ትዕይንት ሰው ሆኖ ያየው የሰማይ አምላክ እንዲህ ብሏል — “ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው?” (ማር. 8:36)
እርግጥ ነው። ሲያሰኛት ዓለም የሚወዷትን ትወዳለች። ሲላት ደግሞ የሚወዷትንም ትጠላለች። አምላክ ግን ሁላችንንም እንዲሁ፣ ያለ ምክንያት ይወደናል (ዮሐ. 3:16)። የሰማይ አባት ፍቅር በወረት ነፋስ አይንገዳገድም። የእርሱ ፍቅር የተጠሙትን ሁሉ አርክቶ ሌሎችን ማረስረስ ይችላል። በደልን እየቆጠረ በቂም አይበሳጭም። ይቅርታው በምስራቅና ምዕራብ መሃል ካለው ርቀት በላይ ነው። ፍቅሩ ይፈውሳል። ዓለማዊ እብደታችንን አብርዶ በንፅህና ሰላም ውስጥ ሊያቆየንና ሊያኖረን ይችላል። ይህ ፍቅር ከእናትና ከአባት ፍቅር ድምር በላይ ነው። በሰማይ አባት የደስታ ቤት ውስጥ ለዘላለም ያኖረናል።
ድርባ ፈቃዱ