giziew.org

“የማመልከው አምላክ ከሚገጥሙኝ ችግሮች ሁሉ በላይ ነው”

መቼም በዚህች ምድር ላይ ከጌታ ጋር ጉዞ ሁልጊዜ አልጋ ባልጋ አይደለም፤ በክርስትና ሕይወቴ ያሳለፍኳቸው ብዙ ተግዳሮቶችም አሉ።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ስሜ አፈወርቅ መርሻ ደስታ ይባላል፣ ተወልጄ ያደግሁት በአሰበ ተፈሪ ከተማ ነው። በአሁኑ ጊዜ የምኖረው በጀርመን አገር፣ ኑርንበርግ በምትባል ከተማ ውስጥ ነው። ወደ እምነት በሙላት የመጣሁት በጀርመን አገር በኑርንበርግ ከተማ ውስጥ ነው።

ወቅቱ እ.ኤ.አ. 1996 እስከ 1999 ባለሉት ዓመታት ነበር። በዚያን ጊዜ በኑርንበርግ ከተማ ውስጥ በጣም ሞቅ ያለ የክርስቲያኖች ጉባዔ ነበር። በዚያን ጊዜ ነበር በተለይ ቀዳሚት ሰንበትን በመጠበቅ የጌታችንና የመድኃኒታችንን ዳግም መገለጥ በናፍቆት ስለሚጠባበቁ ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት።

በወቅቱ ተዘጋጅቶ በነበረው የሁለት ሳምንት መንፈሳዊ ኮንፈረንስ ላይ አንድም ቀን ሳልቀር ተሳተፍኩኝ። ከኢትዮጵያ ተጋብዞ ሲያገለግል በነበረው ወንጌላዊ በኩል ይሰጥ የነበረው ትምህርት በጣም ልብ የሚነካና ጠቃሚ ነበር። እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቷ አባላት የሆኑት ወንድሞችና እህቶች ያሳዩት የነበረው ፍቅር በጣም ማራኪ ነበር። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው ሕይወቴን ለማስረከብና በጥልቀት ለመጠመቅ የወሰንኩበት።

እንግዲህ አሁን በዚህ የእምነት መስመር ላይ ስጓዝ እነሆ 20 ዓመት ሆኖኛል። ይህንን ጉዞዬን ከጀመርኩ ወዲህ በሕይወቴ ብዙ ለውጥ አስተውያለሁ። በቀድሞ ሕይወቴና አሁን ከጌታ ጋር በምኖረው ሕይወት መካከል ስላለው ትልቅ ለውጥ እኔ ከምናገር ይልቅ እኔን የሚያውቁ ቤተሰቦቼ፣ ዘመዶቼ እና የቅርብ ጓደኞቼ ቢናገሩ ይሻላል። ቢሆንም ግን ጌታ ክርስቶስን አዳኜና የሕይወቴ መሪ እንዲሆን ወስኜ ዳግም ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ ከዚያን ጊዜ በፊት ተለማምጄው የማላውቀውን ዓይነት ታላቅ ዕረፍት፣ ሰላምና ርካታን አግኝቻለሁ።

የአምላክን መንገድ ከመከተሌ በፊት አዘወትራቸው የነበሩ ብዙ ጎጂ ልማዶችን እርግፍ አድርጌ በመተዌ በሥጋዬም፣ በመንፈሴም እንዲሁም በነፍሴ ጤንነት ላይ ትልቅ ለውጥ አይቻለሁ። እግዚአብሔር በደስተኛ ቤተሰብ እጅግ ባርኮኛል። የሁለት ዓመለወርቅ ወንዶችና የሁለት ዓመለሽጋ ሴቶች ልጆች አባት ለመሆን አብቅቶኛል። በርግጥ ቃሉን በአደባባይ ላይ ሆኜ የመስበክ ስጦታ ባይኖረኝም ባገኘሁት አጋጣሚ አምላኬ ያደረገልኝን በጎነትና እንዴት እንደለወጠኝ ለሌሎች እመሰክራለሁ።

መቼም በዚህች ምድር ላይ ከጌታ ጋር ጉዞ ሁልጊዜ አልጋ ባልጋ አይደለም፤ በክርስትና ሕይወቴ ያሳለፍኳቸው ብዙ ተግዳሮቶችም አሉ። ነገር ግን ክርስትና ለእኔ ከሁሉ ነገር በላይ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ተለማምጄአለሁ። በርግጥ ክርስቲያን በመሆኔ ከችግሮችና ከፈተናዎች የተጠበቅሁ ነኝ ብዬ አላስብም። በማንም ሰው ላይ የሚደርሰው ፈተና በእኔም ላይ ደርሷል፣ ልዩነቱ ግን እኔ የማመልከው አምላክ ከሚገጥሙኝ ችግሮች ሁሉ በላይ መሆኑን ማመኔ ነው።

ስለዚህ እስከዛሬ ድረስ የገጠሙኝን ችግሮችና ፈተናዎች ሁሉ እየወደቅሁም ሆነ እየተነሳሁ ተጋፍጬ እነሆ በጌታ ፀጋ አሸንፌአቸዋለሁ። ወደፊትም በእርሱ ኃይል እንደምወጣቸው አምናለሁ፣ ምክንያቱም አምላኬ ይህንን የተስፋ ቃል ሰጥቶኛልና፡- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴዎስ 11፡28-30)።

የክርስትና ሕይወት በአውሮፓ ውስጥ ተግዳሮቶች አሉት። የክርስትናን ኑሮ በአውሮፓ የምመለከተው በሁለት መንገድ ነው፤ በአንድ በኩል በአውሮፓ ውስጥ የሃይማኖት ነጻነት በመኖሩ እግዚአብሔርን በነጻነት ማምለክ መቻሉ ትልቅ ዕድል ነው። እኔና ቤተሰቤም ያለምንም አካባቢያዊ ተጽእኖ መድኃኒዓለምን በነጻነት በቤታችንም ሆነ በቤተክርስቲያን እናመልካለን።

በሌላ በኩል ግን፣ በአውሮፓ ውስጥ እምነትን ጠብቆ መኖር ብዙ ተግዳሮቶች አሉት፣ ከእነርሱ መካከል አንዱ የሰንበትን ቀን ከመጠበቅ ጋር የተያያዙ ፈተናዎች ናቸው። ይህ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪና ፈታኝ ቢሆንም፣ በጌታ ፀጋ እየተወጣሁ እገኛሁ። አምላኬም የሚያበረታቱኝን ወገኖች ሁልጊዜ በአስፈላጊው ወቅት ይልክልኛል።

በርግጥ እነዚህና የመሳሰሉ ሌሎች ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ በአንጻሩ ደግሞ ብዙ በረከቶችን እየተለማመድኩ እገኛለሁ። በተለይ ደግሞ ዘወትር የማነበው የእግዚአብሔር ቃል እና በተለያዩ ሚዲያ መስመሮች የማዳምጣቸውና የምመለከታቸው መልዕክቶች “መንፈሳዊ ጡንቻዬን” አጠንክረውልኛል። ከሁሉም በበለጠ ግን እኔም ሆንኩ መላ ቤተሰቤ በጌታችንና በመድኃኒታችን ክርስቶስ ዳግም ምጻት ተስፋ የምድር ሕይወታችንን በመኖር ላይ እንገኛለን። በታላቅ ጉጉት የምንጠብቀውም አዳኝ በቅርቡ እንደሚመለስና ወዳዘጋጀልን መኖሪያ እንደሚወስደን ሙሉ በሙሉ እምነት አለኝ። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!

አቅራቢ፤ ዳዊት መሐሪ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *