giziew.org

ነቢያት፤ ድሮና ዘንድሮ

ነቢይ የመሆን ጥሪ ወደ ግለሰቡ የሚመጣው በሁለት መልኩ ነበር። የመጀመሪያው ልክ እንደ ሙሴና ኤልያስ ቦታቸውን የሚተኩትን መርጠውና አሰልጥነው እጃቸውን በመጫን ጥሪውን በማስተላለፍ ነው። ሁለኛው ደግሞ ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የሰው ልጅ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ በሰብዓዊ ዘር እና በፈጣሪው መካከል ትልቅ የግንኙነት ችግር በመፈጠሩ የክህነትና የነቢያት አገልግሎቶች እንደ መፍትሔ መተግበር ጀመሩ። የክህነት አገልግሎት ማለት ኃጢአት ይቅር እንዲባል የሰው ልጅ መስዋዕት ይዞ ወደ አምላክ እንዲያቀርብ የተዘረጋ ሲሆን የነቢያት አገልግሎት ደግሞ ከአምላክ የሚመጣውን መልዕክት ወደ ሰብዓዊ ዘር የሚያደርስ መስመር ነበር። እነዚህ ሁለት አገልግሎቶች በሙሴና በአሮን አገልግሎት በግልጽ ተወክለው ይታያሉ። አሮን ኃጢአተኛውን ለይቅርታ ወደ አምላክ የሚያቀርበውን የክህነት አገልግሎት ሲወክል፤ ሙሴ ደግሞ ከአምላክ ወደ ሰው መልዕክት የሚያደርሰውን የነቢያት አገልግሎት ይወክላል። እንግዲህ ነቢይ ብለን የምንጠራው ሰውየውን ሲሆን፤ የሚናገረውን መልዕክት ደግሞ ትንቢት ብለን እንጠራዋለን። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የድሮውንና የዘንድሮውን የነቢያት አገልግሎት ማነፃፀር ይሆናል።

ነቢይ ማነው?

“ነቢይ” የሚለው ቃል መሰረታዊ መነሻው “ናቡ” ከሚለው የአካዳውያን ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙ “ማስታወቅ”፣ “ማወጅ”፣ “አዋጅ መንገር” ማለት ነው። በዕብራይስጥ ደግሞ “ነቢይ” የሚለው ቃል “ነቢ” ከሚለው የተገኘ ነው። በተጨማሪ በብሉይ ኪዳን ውስጥ “ሮኤህ” እና “ሆዜህ” የተባሉ ሁለት ቃላት የነቢይን አገልግሎት ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውለዋል።

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የነዚህ ሁለት ቃላት ትርጉም በቅደም ተከተል “ተመልካች” እና “ባለራዕይ” የሚል ነው። እነዚህ ሦስቱም የዕብራይስጥ ቃላት ሁሉም በ1ዜና 29፡29 ላይ ተጠቅሰው እናነባለን። በብሉይ ኪዳን “ነቢይ” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት “ተመልካች” የሚለው ቃል አገልግሎት ላይ እንደዋለ ይነገራል። እየቆየ ግን ይህ ቃል “ነቢይ” በሚለው ተተካ። ከዚህ ሌላ “ነቢያት” ባብዛኛው “የእግዚአብሔር ሰው” በሚል ይጠሩ የነበረ ሲሆን በቡድን ደግሞ “የነቢያት ልጆች” በመባል ይጠሩ ነበር (1ነገ. 17-2፤ነገ. 10)። ስለዚህ በዕብራይስጥ “ነቢይ” ማለት የተገለጠለትን፣ የታየውን ወይም የተመለከተውን የአምላክ ሃሳብ ለሰው ልጆች የሚያውጅ ወይም የሚያሳውቅ ሰው ማለት ነው።

ወደ ግሪኩ ስንመጣ “ነቢ” (נָבִיא) የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል “ፕሮፌተስ” (προφήτης) በሚል ቃል ተርጉሞታል። የዚህም ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “ሌላውን ወክሎ የሚናገር” ማለት ሲሆን “የአምላክ ቃል አቀባይ” ወይም “በአምላክ ፈንታ ሆኖ የሚናገር” ወይም “የአምላክን ሃሳብ ለሰዎች የሚተረጉም” ማለት ነው። በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የዚህ የግሪክ ቃል ወደ እንግሊዝኛ ተወስዶ “ፕሮፌሲ” (ትንቢት) ተብሏል። ይህም “የወደፊቱን የሚናገር” የሚል ሃሳብ የያዘውን “ፕሪዲክሽን” ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሲሆን የቃሉ ትርጉም ግን በዚህ ብቻ ሳይገደብ “ኢንተርፕሪቴሽን” (ትርጉም፤ ፍቺ) የሚለውንም ያካተተ ነው። ወደ አማርኛ ስንመልሰው “መተርጎም” ማለት ሲሆን ይህም ነቢዩ ከአምላክ የተቀበለውን ቃል (ሃሳብ) ሰዎች በሚገባቸው መልኩ ማስተላለፍ የሚለውን ሃሳብ ያካተተ ነው።

ስለዚህ በሌላ አባባል “ፕሮፌሲ” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ሙሉ ሃሳቡን ለመረዳት “ፕሪዲክሽን” እና “ኢንተርፕሪቴሽን” የተባሉት ሁለት ቃላት ማገናኘት የግድ ይላል። የእነዚህ ቃላት ትርጉምም ነቢይ ማለት የወደፊቱን የሚተነብይና ተጨማሪ ከአምላክ የተገለጸውን ፈቃድ ተርጉሞ የሚያስተምር፣ የሚያውጅ ወይም የሚያብራራ ማለት ነው።

የነብያት አገልግሎት ታሪካዊ ዳራ

መጽሐፍ ቅዱስ በሦስት ዓይነት መንገድ እግዚአብሔር ራሱን ለነቢያት እንደሚገልጽ ያስረዳል። እነርሱም 1ኛ በሕልም፣ 2ኛ በራዕይ ሲሆን፣ 3ኛው ደግሞ በቀጥታ በድምጽ ወይም በፊት ለፊት ንግግር መሆኑን በዘኍልቁ ላይ እንረዳለን (ዘኍ. 12:5–8)። ሦስተኛው የግንኙነት መንገድ ከፍተኛው የመገለጥ ደረጃ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚያስረዳን በጥንት ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ለሙሴ ብቻ ነበረ።

ከኢያሱ እስከ ካህኑ ኤሊ ዘመን ድረስ እግዚአብሔር እንደ ሙሴ ዘመን በራዕይ አልተናገረም። በተለይም በመሳፍንት ዘመን የክህነት አገልግሎቱ እየተዳከመ በመምጣቱ፣ ከካህናቱ የብቃት ሞራል ከፍ ያለ የክህነት አገልግሎት ሕዝቡ ማግኘት አልቻለም ነበር። ስለዚህ ይህንን ክፍተት የሚሞላ ሌላ ተጨማሪ አገልግሎት አስፈለገ። በዚህም ምክንያት ለሕዝቡ እግዚአብሔርን መፍራት የሚስተምርና ወደ ንስሐ የሚጠራ የነቢያት አገልግሎት በካህኑ ሳሙኤል ተጀመረ። በመጀመሪያ በሙሴ አገልግሎት ይታወቅ የነበረው ይህ የነቢይ አገልግሎት ሳሙኤል እንደገና አነቃቃው። ቀደም ሲል ሙሴ “ጌታ እንደኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል” ብሎ ስለተነበየ፤ ይህ የነቢይ አገልግሎት በጣም ሲጠበቅ ቆይቷል (ዘዳ.13:1፣ 18:18፣ 20–22)። ይህ አገልግሎት ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ሕግ እንዲመለሱ የሚጠራና ወደ ትልቅ የሞራል ከፍታ እንዲደርሱ የሚያደርግ አገልግሎት ነው።

ሳሙኤልም የነቢያትን አገልግሎት ለማጠናከርና ለማስፋፋት በተለያዩ ቦታዎች የነቢያት ትምህርት ቤት ከፈተ። እነዚህም በራማህ (1ሳሙ. 19:19–20)፣ በቤቴል (2ነገ. 2:3)፣ በኢያሪኮ (2:5)፣ በጊልጌል (4:38) እና በሌሎች ቦታዎች (6:1) ነበሩ። እጩ ነቢያቱ በዋነኛነት ይማሩ የነበረው አምስቱን የሙሴ መጽሐፍት (ዘፍጥረት፣ ዘጸዓት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኍልቁና ዘዳግም) እና ትርጓሜያቸው (ፍቺያቸው) እንደሚሆን አያጠራጥርም። በተጨማሪም ሙዚቃና ቅኔ ወይም ሥነጽሁፍ ይማሩ ነበር (ዘጸ. 15:20፣ መሳ. 4:4-5)። ካህን ለመሆን የግድ ከሌዊ ዘር መወለድን የሚጠይቅ ሲሆን ነቢይ ለመሆን ወይም ወደ ነቢያት ት/ቤት ለመግባት ግን እስራኤላዊ መሆን ብቻ በቂ ነበር።

ነቢይነትና አገልግሎቱ

ነቢይ የመሆን ጥሪ ወደ ግለሰቡ የሚመጣው በሁለት መልኩ ነበር። የመጀመሪያው ልክ እንደ ሙሴና ኤልያስ ቦታቸውን የሚተኩትን መርጠውና አሰልጥነው እጃቸውን በመጫን ጥሪውን በማስተላለፍ ነው። ሁለኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ በቀጥታ ጥሪው በግል ደርሷቸው ወደ አገልግሎቱ እንደ ሳሙኤል የሚገቡ ናቸው። የነቢይነት ጥሪ ለወንዶች ብቻ የሚመጣ ሳይሆን በርካታ ሴቶችም በዚህ አገልግሎት ውስጥ የታቀፉ ነበሩ። እንደ ማስረጃም የሙሴ እህት ሚርያምንና ዲቦራን መጥቀስ ይቻላል (ዘጸ. 15:20-21፤ መሳ. 4:4-10፤ 6:1-10)።

ልክ በጽዮን ቅጥር ላይ የተመደቡ ጠባቂዎች አደጋ ሲመጣ መለከታቸውን በመንፋት ሕዝቡን እንደሚያስጠነቅቁ ነቢያትም አደጋን ሲመለከቱ ሕዝቡን ማስጠንቀቅ ይጠበቅባቸው ነበር። ዋና አገልግሎታቸው ሰዎችን ስለ ኃጢአታቸው መዝለፍ፣ መገሰጽ፣ መውቀስ፣ ሊመጣ ስላለው መለኮታዊ ቅጣት ማስጠንቀቅና ወደ ንስሐ መጥራት ነው። ሌላው ደግሞ ሕዝቡን ማጽናናትና ስለ እግዚአብሔር ይቅርታ ማወጅ ተጨማሪው የነቢያት ሥራ ነበር።

“በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር” (ኢሳ. 58:1፤ ሕዝ. 22:2፤ 43:10፤ ሚክ. 3:8)። “አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ። ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፤ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ” (ኢሳ. 40:1–2)።

እነዚህ ነቢያት በሚናገሩት ትንቢት እግዚአብሔር በጸጋው ለእስራኤል ልዩ ፍቅርና ዓላማ እንዳለው እየገለጹ፤ የእርሱን ፈቃድ፣ ፍርዱንና፣ ጽድቁን እያወጁ፤ ለእውነት በጥብቅና ከመቆማቸው ባሻገር፤ ከመስዋዕት ሥርዓት ይልቅ የሞራል ልዕልና እንደሚበልጥ ከፍ ባለድምጽ መስክረዋል። በአገልግሎታቸው ስለወደፊት ከመተንበይ ባሻገር በሙሴ መጻሕፍት ላይ ተመርኩዘው ሕዝቡ በየቀን ኑሮው እንዴት ህጉን በሥራ መተርጎም እንዳለበት በማሰብ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የአምላክን ፈቃድ ማወጅ ነበር። ስለዚህ አገልግሎታቸው የሞራል ትምህርትን ያቀፈና የወደፊቱን የሚተነብይ ነበር ለማለት እንችላለን።

ነቢያት እንደሚገጥማቸው ሁኔታ የአኗኗር ዘይቤያቸውም የተለያየ ነበር። አንዳንዶቹ ያገቡ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ያላገቡ ነበሩ። ለእግዚአብሔር ቃል ካላቸው ታማኝነት የተነሳ በሕይወታቸው አብዛኞቹ ሀብት ለማፍራት ሳይችሉ ሳያገቡ፣ በድህነትና በስደት ተንገላተዋል። ከኤልያስና ከመጥምቁ ዮሐንስ የአለባበስ መመሳሰል በስተቀር ሌሎቹ ሕዝቡ የሚለብሰውን ለብሰው፤ የሚበላውን በልተው ያገለግሉ ነበር።

ነብያት በአዲስ ኪዳን

በአዲስ ኪዳን ውስጥም ይህ የነብያት አገልግሎት ከመንፈስ ስጦታዎች ውስጥ ተዘርዝሮ የሚገኝ ሲሆን ከሐዋርያነትን ስጦታ ጋር ተወራራሽነት ያለው የአገልግሎት ዘርፍ ነበር (1ቆሮ. 12፡ 28-30)። በአዲስ ኪዳን አንዳንድ የሐዋርያነት ስጦታ ያላቸው ሰዎች የነቢይነት ስጦታም ነበራቸው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የነቢይነት ስጦታ ያላቸውን ሰዎች አገልግሎት በማጥናት ፍራንክ ቢ ሆልብሩክ (Frank B. Holbrook) የተባሉ የሥነመለኮት ምሁር የነቢያትን አገልግሎት በስድስት የተለያዩ ዘርፎች ያጠቃልሉታል።

በአዲስ ኪዳን የነበሩ ነቢያት፤

  1. ነገሮች ከመሆናቸው በፊት ሊመጡ ያሉ አስቸጋሪ ወቅቶችን አስቀድመው አስጠንቅቀዋል (የሐዋ. ሥራ 11፡27-30፤ 20፡23፤ 21፡10-14)፤
  2. በወቅቱ በነበረችው ቤተክርስቲያን አማካኝነት ወደ አህዛብ ወንጌል የማድረስ ጥሪ ተለኩሷል (የሐዋ. 13፡1-2) እንዲያውም የመጀመሪያዎቹ የወንጌል ሰባኪዎች የአገልግሎት ምሪትን ይቀበሉ የነበረው በዚህ ስጦታ አማካኝነት ነበር (የሐዋ. 16፡6-10)። በጳውሎስ ሁለተኛ ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት እንኳ ሲላስ የተባለ ነቢይ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ወንጌልን ለመሥራት ወጥቷል፤
  3. በሐዋርያት ዘመን የአስተምህሮ ጭቅጭቅ በተነሳ ጊዜ አባላትን በእውነተኛው ትምህርት ለማጽናትና ለማደፋፈር ተግተዋል (የሐዋ. ሥራ 15፡32)፤
  4. የቤተክርስቲያን አባላትን ያደፋፍሩ፣ ያጽናኑ እና ያንጹ ነበር (1 ቆሮ. 14፡3)፤
  5. ከሌሎች የመንፈስ ስጦታ ካላቸው ጋር በመሆን የቤተክርስቲያን አባላትን ከስህተት ትምህርት ታድገዋል። የቤተክርስቲያን አንድነት በእውነተኛ እምነት ላይ ለመጠበቅ ተግተዋል (ኤፌሶን 4፡11-15)፤
  6. ከሐዋርያት ጋር በመሆን ቤተክርስቲያናትን መሥርተዋል፤ “ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን” ተገልጧል (ኤፌ. 2፡20፤ 3፡5፤ 4፡11)።

እስካሁን ነብይ የሚለውን ቃል ትርጉም፣ የአገልግሎቱ ታሪካዊ ዳራና ዋና ትኩረት ምን እንደሆነ አይተናል፤ በአዲስ ኪዳን ደግሞ እንዴት በወንጌል ስርጭት ዙሪያ ነብያት ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተመልክተናል፤ በመቀጠል ደግሞ በዘመናችን ከሚገኙ ራሳቸውን “ነብይ” ብለው ከሚጠሩ ጋር ያለውን ንጽጽር እንመልከት።

በድሮና በዘመናችን የሚገኙ “ነቢያት” ልዩነቶች

በዘመናችን ራሳቸውን “ነቢያት” ብለው በሚጠሩና መጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት በማለት በሚጠራቸው መካከል የሚታዩ ሰፊ ልዩነቶች አሉ። በሞራል ልዕልና፣ በመልዕክት አቀባበል፣ በገንዘብ መውደድ (ፍቅረንዋይ)፣ በተጠያቂነት፣ ራስን ከፍ ከፍ በማድረግ፣ በአደረጃጀት እና በሌሎች ጉዳዮች ስንመለከተው ልዩነታቸው በጣም ሰፊ ነው።

ፍቅረንዋይ

ለምሳሌ ነቢዩ ኤልሳዕ ጄኔራል ንዕማንን ሂድና በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ታጠብ አለው። እርሱም ታጠበ ከለምጹም ነጻ። መፈወሱን ከተመለከተ በኋላም ብዙ ስጦታ ለነቢዩ አመጣ፤ በዚህን ጊዜ ነቢዩ ስጦታውን እንደማይቀበል ነግሮት ያመጣውን ስጦታ ንዕማን ይዞ ተመለሰ። ሆኖም ግን ግያዝ የተባለው የነቢዩ አገልጋይ ለዚህ ትልቅ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ፈውስ የገንዘብ ክፍያ መቀበል እንዳለባቸው ተሰማው። ይህንን ያስተዋለው ነቢዩ ኤልሳዕ ግን ግያዝን ከለከለው (2ነገ. 5፡15-27)።

የዘንድሮው “ነቢያት” ቢሆኑ ኖሮ ገንዘብ ከመውደዳቸው የተነሳ ዘይት በብልቃጥ እንደሚቸረችሩት ሁሉ እያንዳንዱን የዮርዳኖስ ውሃ በሃይላድ ላስቲክ እየሞሉ አሽገው ይቸረችሩት ነበር። ግያዝ፣ ኤልሳዕ የተባለ የሥራ አለቃውን “ይሄ ቢዝነስ የማይገባው ነቢይ” ብሎ፤ መንገዱን አሳብሮና አቆራርጦ፣ ንዕማንን በማጭበርበር ምርጥ የሆኑ ልብሶችና ጥሬ ገንዘብ ተቀብሎ እንደመጣ የዘመኑ “ነቢያትም” በሌላቸው የነቢይነት ስጦታ ልክ እንደ ግያዝ ኪስ ያወልቃሉ፣ ይዘርፋሉ።

እነዚህ “ነቢያት” ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር መሆኑን ዘንግተውታል። “በነጻ እንደተቀበላችሁ በነጻ ስጡ” የሚለውን ምክር ረስተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን ስለወደዱ “የበልዓምን መንገድ መርጠዋል” በማለት ይነግረናል። “ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ፥ ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ” (2ኛ ጴጥ. 2፡15-16)።

ተጠያቂነት

ብዙዎች የነቢይነትንና የሐዋርያነትን ማዕረግ የሚመኙትና “ነኝ” ብለው ራሳቸውን አታለው ሌላውንም ወደ ማታለል የሚገቡት ይህ የአገልግሎት ዘርፍ ተጠያቂነት የለውም ብለው ስለሚያምኑ ነው። በርግጥ ነቢይን ደፍሮ “ይህን ለምን ታደርጋለህ” ብሎ ማን ይጠይቃል? በተጨማሪም ራሳቸውን በሰው ዘንድ እንደ አምላክ ለመኮፈስም ስለሚፈልጉ ነው። ሰው መሆናቸውን ረስተው እንደ አምላክ ሆኖ መታየት እንዴት ያለ ታላቅ የገቢ ምንጭ መሆኑን አስበዋል።

ይህንን “ነቢያቱ” የሚያስገቡትን ገቢ የተገነዘበ አንድ ሰው ከፓስተሩ ጋር ስለ አገልግሎት እየተጫወቱ ሳለ፤ ፓስተሩ “ወንድሜ አንተን ስመለከትህ “የትዳር አማካሪነት” ስጦታ ያለህ ይመስለኛል” ቢሉት፤ ሰውየውም “የለም! የለም! ፓስተር እኔን ከወደዱኝ እንዲጸልዩልኝ የምፈልገው የትዳር አማካሪ እንድሆን ሳይሆን “ነቢይ” እንድሆን ነው” በማለት ተናገረ። ሰውዬው ይህንን ያለው በዘመናችን ከትዳር አማካሪነት ይልቅ ራሳቸውን “ነቢይ” ብለው የሚጠሩ ሰዎች እጅግ የናጠጡ ሀብታም ሆነው ስለተመለከተ ነበር። “የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ” (ማር. 12፡40)።

የነቢይነት አገልግሎት ዘርፉ ግን “ፈትኑ”፣ “መርምሩ” በሚሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዞች የታጀበ ስለሆነ ተጠያቂነት የሌለበት አይደለም። ከተጠያቂነትም የሚያመልጥም የለም። ራስን ከተጠያቂነት በላይ እንደ ጳጳስ ማድረግ ያውም በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መሃል የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብም ነው። “ወዮላችሁ! እናንት …. ከገሃነም ፍርድ አታመልጡም” (ማቴ. 23፡33)።

እንደሚታወቀው እነዚህ ራሳቸውን “ነቢያት” ብለው የሚጠሩ ሰዎች ቀድመው የነበሩበት ቤተክርስቲያን የተጠያቂነት አሠራር መኖሩ ስለማይመቻቸው ያንን ጥለው በመውጣት አዲስ ላቋቋሙት ድርጅት ራሳቸውን ሥራ አስኪያጅ በማድረግና በራሳቸው ስም የባንክ አካውንት በመክፈት የግላቸው የሆነ ቤተክርስቲያናትን የመሠረቱ ሲሆን በውስጣቸውም ከፍተኛ የሆነ የአደረጃጀትና የተጠያቂነት ችግር ያለባቸው ናቸው።

በመገለጥ ሳይሆን በመረጃ ማገልገል

ድሮ ድሮ የመጽሐፍ ቅዱሶቹ ነቢያት “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚለውን ትንቢትም ሆነ ዕውቀት የሚቀበሉት ከእግዚአብሔር ዘንድ በመጣ ድምፅ፣ ራዕይ ወይም ሕልም ነበር። የዘንድሮዎቹ ግን በተለያየ ድብቅ በሆኑ መንገዶች የሚያገኙትን መረጃዎች “ልዩ መገለጥ” በማስመሰል በማጭበርበር ላይ ናቸው።

አንዳንዶቹ መረጃቸውን የሚያገኙት ከግለሰቡ አጠገብ ተደብቆ ባለ መቅረጸ ድምጽ፣ ሰው መጽሐፍ ቅዱሱ ወይም ቦርሳው ውስጥ ጽፎ እንዲያስቀምጥ የተደረገውን የጸሎት አደራ ዝርዝር በድብቅ በማንበብ፣ ወይም ዝርዝሩን ፎቶ አንስቶ ለ“ነቢዩ” በማቀበል፣ የግለሰቦቹን የፌስቡክ አካውንት በማጥናት ወይም በመሰለልና መረጃዎችን ለዚሁ በተመደበ ግለሰብ አማካኝነት ወደ “ነቢዩ” በመላክ ነው። መረጃዎቹን ከተቀበሉ በኋላ የግለሰቡ ስም፣ ሞባይል ቁጥር፣ የህመም ዓይነት፣ የትዳር ሁኔታ ምን እንደሚመስልና ተመሳሳይ ነገሮች በመድረክ ላይ ይጠራሉ። “በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፤ እኔም አልላክኋቸውም” (ኤር. 29፡9)። “እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ ሐፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው” (ራዕይ 16፡15)።

“ተስማምተው … ምን ያሉት አይሸትም” እንደሚባለው የአገራችን አባባል ሐሰተኛ ነቢያት በአገራችን ሥራቸውን እየሰሩ ያለው በቡድንና እርስበርስ በመደጋገፍ ነው። “ነቢይ” ነን ባዮቹ እርስበርሳቸው መረጃ ይለዋወጣሉ፤ የተለያየ የሥራ ድርሻ በተሰጣቸው ሰዎች ይደገፋሉ። እየሆነ ያለው ሁሉም ባለድርሻ የገንዘብ ተከፋይ ስለሆነ ምሥጢሩን ለማውጣት የተቸገረ መሆኑን ነው። በድብቅ ሲለማመዱ የቆዩትን ድራማዊ የአጋንንት ማስወጣትና የተለያዩ መገለጥ የሚመስሉ ድርጊቶችን በየስብሰባዎቻቸው በቲያትር መልክ በማቅረብ የሚደረግ የተደራጀ ማጭበርበርና ሌብነት ነው።

በቅርቡ አንዲት “ራዕይ ታይቶኛል ባይ” በወለንጪቲ ከተማ መቃብር ተቆፍሮ እንዲከፈት በማድረግ ከሞተ ሁለት ሳምንት የሆነውን የሁለት ወር ህጻን ልጅ አስከሬን “ከሞት እንዳስነሳ ራዕይ ታይቶኛል” በማለት መቃብር አስቆፍራ ነበር። በመቀጠልም እየጸለየችና “ተነስ!” እያለች ለበርካታ ሰዓታት ድምጽዋን በጩኸት ብታሰማም፤ አስከሬኑ ምንም አልሰማትም፣ አልነቃም፣ አልተንቀሳቀሰምም። “ነቢይቱም” በፈጸመችው ድርጊት ስታፍር ሁኔታውን ለፖሊስ ሪፖርት ያደረጉ በመኖራቸው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውላ ተገቢውን ቅጣት እንዳገኘች ቢቢሲ አማርኛ 14 ጥር 2020 ዘግቧል

ከዚህ ድርጊት እነዚህ ራሳቸውን “ነቢይ” ብለው የሚጠሩ ሰዎች ሁለት ዓይነት መሆናቸውን እንማራለን። አንዳንዶቹ በርግጥ ራሳቸው ለዚህ አገልግሎት የተጠሩ መስሏቸው የሳቱና የተታለሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሆን ብለው ለማጭበርበር የሚሠሩና ድርጊታቸው የሐሰት መሆኑን የሚያውቁ ነገር ግን ገንዘብ ስለሚያስገኝላቸው ብቻ ሆን ብለው ብዙዎችን በማሳት ሥራቸው የተጠመዱ መሆናቸውን ነው።

አብዛኞዎቹ የዘንድሮ ነቢያት ራሳቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ ይታይባቸዋል። እውነተኛ ነቢይ ከፍ የሚያደርገው ራሱን ሳይሆን እግዚአብሔርንና ቃሉን ብቻ ነው። በዘመናችን የምናያቸው “ነቢያት” ግን ራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ ትላልቅ ፎቶዎቻቸውን በየመንገዱና በየአደባባዩ ይሰቅላሉ። በየቴሌቪዥኖቻቸው “ስለ ነቢዩ ምን ታስባለህ?” እያሉ ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ። ነገርግን እንደ ዮሐንስ መጥምቁ ያለ እውነተኛ ነቢይ የሚለው “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” ነው (ዮሐ. 3፡30)።

ሌላው እነዚህ ራሳቸውን “ነቢይ” ብለው የሚጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልዕክት የሌላቸው መሆኑ ነው፤ አብዛኛው የመልዕክታቸው ትኩረት ስለ ድንቅና ስለ ተዓምር በመናገር ስሜትን መቀስቀስ፣ ማስደነቅ፣ ማስለቀስ ብቻ ነው። ምዕመኖቻቸው መረጋጋት ያልቻሉ በትምህርት ነፋስ ወዲህና ወዲያ የሚፍገመገም የውሃ ላይ ኩበት፣ ተንከራታች ሆነዋል። የነቢይነት ስጦታ የሚሰጠው ግን ምዕመናንን ለማነፅና ለማጽናት ነበር። “እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም” (ኤፌ. 4፡14)።

በርካታ የሚባሉት ቅድስና የጎደላቸው፣ ተሳዳቢዎች፣ ከሴቶች ጋር የሚሴስኑ፣ ዝሙትን በአካባቢያቸውና በዙሪያቸው ያነገሡ አጭበርባሪዎችና ፈሪኃ እግዚአብሔር የጎደላቸው ነፍሰ ገዳይ መሆናቸው በስፋት ይወራል፤ የጉዳቱ ሰለባዎችም ይህንኑ ይመሰክራሉ። እነዚህ ሆን ብለው በእግዚአብሔር ስም አቅደውና ተዘጋጅተው ለማጭበርበር የመጡ ናቸው። “ዳሩ ግን፦ ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ” (ራዕይ 2፡20)።

በኢየሱስ አገልግሎት የተፈወሱ ሰዎች ከተፈወሱ በኋላ ኢየሱስ “ሂድና ራስህን ለካህን አሳይ” በማለት መፈወሳቸውን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት ከካህኑ እንዲያገኙ ይነግራቸው ነበር። የዘንድሮ ሐሰተኛ ነቢያት ግን “ተፈውሳችኋል” ያሏቸውን ሰዎች መድኃኒታቸውን መውሰድ እንዲያቆሙ በማድረግ ሕመም እየተሰማቸው እንኳን መድኃኒት አትውሰዱ የሚሉ ናቸው። ራሳቸውን ወደ ሐኪም ሄደው መፈወሳቸውን እንዲያረጋግጡ ምክር እንኳ አይሰጧቸውም። የታመሙት ሰዎችም ሐኪም ጋር ሳይሄዱ፣ “ተፈውሰሃል” የሚለውን “የነቢዩን” ቃል በመስማት ብቻ መድኃኒታቸውን መውሰድ እርግፍ አድርገው ትተው ለሞት የተዳረጉት ጥቂት አይደሉም።

አንድ ለቤተሰቤ ቅርብ የሆነ ሰው በጠና ይታመምና በባለቤቱ እየተረዳ “ነቢይ” ብሎ ራሱን የሚጠራ ሰው ስብሰባ ቦታ ይወሰዳል። በአምልኮ መሃል ይህ የታመመ ሰው በ“ነብዩ” ተጠርቶ በሰዎች መሃል እንዲቆም ተደረገ። ነቢዩ “ሞት አይሆንም!” “የሞት ቀንበር ተሰበረ!” ብሎ አስጨበጨበ፤ ተዘመረ፤ ታማሚውም ተጠየቀ፤ “አዎን፤ ሃኪም ሁለቱም ኩላሊቶችህ አይሠሩም ብሎኛል” አለ። “አዲስ ኩላሊት ይታየኛል”፣ “የሞት ቀጠሮ ተሻረ” “ዛሬ ቀኑ ነው ክብሩን ልታይ፣ ተፈውሰሃል፣ ነጋቲ ቡላ!” ብሎ አሰናበተው። ቤተሰቡም አምላክን አመሰገነ። ሆኖም ግን ሰውዬው ከበሽታው አልዳነም ነበረና ይህ የሃሰት ትንቢት በተነገረ በሁለተኛው ወር ሕይወቱ አለፈች።

የሚገርመውና የሚያሳዝነው ግን ይህንን “የሞት ቀጠሮ ተሻረ” የሚለውን ፊልም “ነቢዩ” እስከ ዛሬ ድረስ ከዩቲዩቡ ላይ አፍሮ እንኳን አለማንሳቱ ነው። ምክንያቱም በተጨማሪ ገና ሌሎችን ያጭበረብርበታል፤ ከዩቲዩቡ የሚያገኘው ክፍያ እንዲቀንስበትም አይፈልግም። ይህ ምን ዓይነት የሞራል ዝቅጠት ነው!? የቀድሞ ነቢያት ጋር ይታይ የነበረው የሞራል ልዕልና የት ሄደ!? “የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፥ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ምንም ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው!” እግዚአብሔር ሳይልካቸው፦እግዚአብሔር ይላል የሚሉ ሰዎች ከንቱ ነገርንና ውሸተኛ ምዋርትን አይተዋል፤ ቃሉም ይጠና ዘንድ ተስፋ አስደርገዋል። እኔም ሳልናገር፦እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል ስትሉ፥ ከንቱ ራእይን ያያችሁ ውሸተኛንም ምዋርት የተናገራችሁ አይደላችሁምን? ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ ውሸተኛ ራእይንም ስላያችሁ፥ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር” (ሕዝ. 13፡2-8)።

ከሶስት ወይም ከአራት ዓመት በፊት ነው፤ ሌላው ደግሞ በቴሌቭዥኑ “ትንቢት” ይናገራል፤ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ችግር ነበር “የሚተነብየው”። እንዲህ አለ “በኦሮምያ ያለው የጸጥታ ችግር በቅርቡ ጸጥ ይላል”፤ እንዳነጋገሩ በሁለት በሶስት ሳምንት ውስጥ ችግሩ የሚፈታ ይመስል ነበር። ነገሩ ግን “ነቢዩ” እንደተናገረው ሳይሆን ቀርቶ የጸጥታው ችግር በየቀኑ እየጨመረ፣ እየጨመረ! ሄዶ መንግሥት ተለወጠ። አገሪቱ እንኳን ያኔ አሁን ድረስ የጸጥታ ማጣት ቆፈን አለቀቃትም። “ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው” (ዘዳ. 18፡22)።

የማጠቃለያ ሦስት ማሳሰቢያዎች

ራሱን እያታለለ ለሚገኝ ሐሰተኛ ነብይ፡- “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል” (ገላ. 6፡3) እንደሚለው ቃሉ፤ መጀመሪያ ተረጋግተህ የእግዚአብሔርን ድምፅ እና ከገዛ ልብህ ወይም ከስሜትህ የሚመነጨውን ድምፅ መለየት ብትለማመድ ይበጃል። ነገር ግን ነብይ ሳትሆን ነብይ እንደሆንህ ከተሰማህ እጅግ ስተሃል፣ እጅግ ተታለሃል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስህን ጠንቅቀህ አጥና። እንደ “አኪማኣስ” መልክትም ሳትቀበል፣ እንድትሄድም ሳትላክ አትሩጥ። “ትሮጥ ዘንድ ለምን ትወድዳለህ?” (2 ሳሙ. 18፡19-33) “ወዮላችሁ!” የሚለው ማስጠንቀቂያ ወደ ነፍስህ ደርሶ ከሆነ ንስሐ ግባ!

ሆን ብለው ለሚያጭበረብሩ “ነብያት” ደግሞ፡- የተናገራችሁት ትንቢት ስላልተፈጸመ ጴጥሮስ እና ይሁዳ በየተራ “ውኃ የሌለባቸው ምንጮች” (2 ጴጥ.2፡17) እና “በነፋስ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች” ናችሁ በማለት ገልጸዋችኋል። በሌላ አነጋገር ባዶ ተስፋ ሰጪዎች ናችሁ ማለታቸው ነው። “እነዚህ ሰዎች በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ያለ አንዳች ኃፍረት ከናንተ ጋር ቀርበው የሚበሉ ነውረኞች ናቸው” ይለናል (ይሁዳ 12)። ያዘጋጃችሁት የነጻ መውጣት ዝግጅት ማጭበርበር ነው፤ “ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው፦ አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል” (2 ጴጥ. 2፡19)፤ ስለዚህ ንስሐ ግቡ! ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ!

በመጨረሻም ለምዕመን፡- እነዚህን ሐሰተኛ ነቢያት “አትፍራው” (አትፍራቸው) በማለት አምላክ እንዳንፈራቸው ያደፋፍረናል። “ከሐሰተኞች ነብያት ተጠንቀቁ” በማለትም ያሳስበናል (ማቴ. 7፡15)። መረጃ ከፌስቡክ እየለቃቀመ በሚተነብይ ሐሰተኛ በቀላሉ ከተታለልን፤ እሳትን ከሰማይ የሚያወርደው ሐሰተኛው ነብይ ሲመጣ እንዴት ልንሆን ነው? “ከእግረኞች ጋር ሮጠህ እነርሱ ካደክሙህ፣ ከፈረሰኞች ጋር እንዴት ልትወዳደር ትችላለህ?” (ኤር. 12፡5)። አምላክ በዘመናችን ሰይጣን በዘረጋው ወጥመድ ውስጥ ወድቀን እንዳንጠፋ ሁላችንንም ይጠብቅ! “ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ”(1 ቆሮ. 10፡12)።

ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ

ዋቢ መጻሕፍት

Achtemeier, Paul J. Publishers Harper & Row and Society of Biblical Literature, Harper’s Bible Dictionary, Includes Index., 1st ed. (San Francisco: Harper & Row, 1985), 826.

Arndt, William. Frederick W. Danker and Walter Bauer, A Greek-English Lexicon of the New Testament and Other Early Christian Literature, “Based on Walter Bauer’s Griechisch-Deutsches Wr̲terbuch Zu Den Schriften Des Neuen Testaments Und Der Frhchristlichen [Sic] Literatur, Sixth Edition, Ed. Kurt Aland and Barbara Aland, With Viktor Reichmann and on Previous English Editions by W.F. Arndt, F.W. Gingrich, and F.W. Danker.”, 3rd ed. (Chicago: University of Chicago Press, 2000), 122.

Bromiley, Geoffrey W. The International Standard Bible Encyclopedia, Revised (Wm. B. Eerdmans, 1988; 2002), 1:192-195, 3:986-1004.

Brown, Colin.The New International Dictionary of New Testament Theology. Edited by Colin Brown. Grand Rapids: Zondervan, 1976. 1:126-137.

Chantry, Walter J. Signs of the Apostles: Observations on Pentecostalism Old and New. Pennsylvania: The Banner of Truth Trust. 1973, 1976.

Elwell, Walter A. and Walter A. Elwell. Evangelical Dictionary of Biblical Theology. electronic ed. Baker reference library; Logos Library System. Grand Rapids: Baker Book House, 1997, c1996.

Enns, Paul P. The Moody Handbook of Theology. Chicago, Ill.: Moody Press, 1997, c1989.

Holbrook, F. B. (n.d.). The Biblical Basis for a Modern Prophet. Retrieved from  https://adventistbiblicalresearch.org/materials/adventist-heritage-bible-prophecy/biblical basis-modern-prophet

Horn, Siegfried H. Seventh-day Adventist Bible Dictionary. Revised edition. Commentary Reference Series. Washington, D.C.: Review and Herald Publishing Association, 1979.

Ryrie, Charles Caldwell. Basic Theology: A Popular Systemic Guide to Understanding Biblical Truth.      Chicago, Ill.: Moody Press, 1999.

Unger, M. F., Harrison, R. K., Vos, H. F., Barber, C. J., & Unger, M. F. (1988). The new Unger’s Bible dictionary. Revision of: Unger’s Bible dictionary. 3rd ed. c1966. (Rev. and updated ed.). Chicago: Moody Press.

Wood, D. R. W. New Bible Dictionary. InterVarsity Press, 1996, c1982, c1962


1 thought on “ነቢያት፤ ድሮና ዘንድሮ”

  1. ስለ ነቢያት : ድሮና ዘንድሮ የሚለውን ልዩ ዕትም አነበብኩት። እጅግ የተዋጣለት የመረጃና የዕውቀት ጥርቅም መሆኑን ተረድቻለሁ። አዘጋጁን ከልብ አመሠግናለሁ። ተባረኩ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *