የፖላንድ ፓርላማ እኤአ በ2020 ቀስ በቀስ የእሁድን ግብይት የሚከለክል ሕግ አጸደቀ። ውሳኔው ሦስት መሠረታዊ ምንያቶች እንዳሉት አስተያየት ተሰጥቶበታል። ይህ ዓይነቱ በመንግሥት ድጋፍ የሚካሄድ የእምነት ውሳኔ የሃይማኖት ነጻነትን የሚጋፋ ነው ተብሏል።
የካቶሊክ እምነት እሴቶችን በሚያራምደው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ድጋፍ የተሰጠው የሕግ ረቂቅ በሠራተኛ ማኅበራት ተቀናብሮ ነበር ለውሳኔ የቀረበው። በሕግ እንዲጸድቅ የተሰጠው ምክንያትም የሱቅ ሠራተኞች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ በማሰብ እንደሆነ ዴይሊ ሜይል እኤአ ኅዳር 24፤ 2017 በድረገጹ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል።
ለሕጉ አስፈላጊነት የተሰጡት ሌሎች ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፤
ነጻነት፤ እኤአ በ2012ዓም የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ እሁድ የዕረፍት ቀን እንዲሆን መሟገት “ለሰዎች ነጻነት መከበር” መታገል እንደሆነ ተናግረው ነበር። እንዲህ ነበር ያሉት፤ “እሁድ ለሰዎች የተሰጠ የጌታ ቀን ነው፤ በዚህ ቀን ሁሉም ሰው ነጻ መሆን አለበት፣ ይህ ነጻነት ለቤተሰብና ለእግዚአብሔር መሆን አለበት።”
እኩልነት፤ የፖላንድ ሠራተኛ ማኅበር እሁድ (ለአምልኮ) የዕፍት ቀን ከሆነ በሁሉም ሠራተኞች ዘንድ እኩልነት እንደሚሰፍን በእርግጠኝነት ይናገራል።
የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ፤ በ2013ዓም የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ በዋርሶው፤ ፖላንድ ተካሂዶ ነበር። በዚያው ዓመት ካርዲናል ኾርኼ በርጎግሊዮ የመጀመሪያው ኢየሱሳዊ ርዕሳነ ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ ሆነው ተመረጡ። ከመመረጣቸው ቀጥሎ ስለ አካባቢ ጥበቃ ባወጡት ጥብቅ ጳጳሳዊ መመሪያ እሁድን የዕረፍት ቀን በማድረግ “ምድራችንን ልንከባከብ” እና ልናድናት ይገባናል ብለው ነበር።
በገዢው የቀኝ ክንፍ ፓርቲ አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርላማ ውሳኔውን በ254 ለ156 ሲያስተላልፍ 23 ድምጸ ተዓቅቦ ነበር።
ውሳኔው በሕግ መወሰኛ ምክርቤት (ሴኔት) መጽደቅና በፕሬዚዳንቱ መፈረም የሚገባው ሲሆን ከፋሲካ እና ከገና በዓላት በፊት በሚኖሩት እሁዶች የእሁድ ገበያን ይፈቅዳል። ከዚህ ሌላ ዳቦ መጋገሪያ ቤቶችና በድረገጾች ላይ የሚከናወን ግብይት ዕገዳው እንደማይመለከታቸው በሕጉ ላይ ሰፍሯል።
በውሳኔው መሠረት እስከ 2018 (እኤአ) መጨረሻ ከትንንሽ ሱቆች በስተቀር ሁሉም በወር ሁለት እሁዶች እንዲዘጉ ያስገድዳል። ከ2019 ጀምሮ ትልልቅ የገበያ አዳራሾች (ሞል) በወር አንድ ጊዜ ብቻ እንዲከፈቱ ይፈቀዳል። በመጨረሻም ከ2020 ጀምሮ ትልልቅ የገበያ አዳራሾች (ሞል) ከዋና ዋና በዓላት በፊት በዓመት ለሰባት እሁዶች ብቻ እንዲከፈቱ ይፈቅዳል።
የፓርላማውን ውሳኔ በተመለከተ የሕዝብ አስተያየትን የሚጠይቅ የአሰሳ ጥናት ተካሂዶ ነበር። በመንግሥት በተካሄደው ጥናት 58በመቶ ፖላንዳዊያን ዕገዳውን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። በግል ድርጅት በተካሄደው ጥናት ደግሞ 76 በመቶ የሚሆኑ ፖላንዳዊያን በግብይት ላይ ምንም ዕገዳ ሳይደረግ በወር ሁለት ነጻ እሁዶችን በችርቻሮ ክፍለኢኮኖሚ ለሚሠሩ የሚፈቅድ ሕግ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
በፖላንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ውሳኔውን የደገፉ ሲሆን የሃይማኖት አስተምህሮቶችን በመንግሥት በመደገፍ በሕግ ማጽደቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አካሄድ እንዳልሆነና የእምነት ነጻነትን እንደሚጋፋ አስተያየት ይሰጥበታል። በቀድሞው ዘመናት በባቢሎናውያን ሲደረግ እንደነበረው ዓይነት ሕጉን በተግባር አናውልም የሚሉ ቅጣት ይበየንባቸዋል።
ሠልስቱ ደቂቃን (የዳንኤል ሦስት ጓደኞች) የናቡከደነጾር አገዛዝ ላቆመው ምስል አንሰግድም በማለታቸው ወደ እቶን እሳት እንዲጣሉ ተደርገው ነበር (ዳንኤል 3)። መድኃኒዓለም ግን በተዓምራቱ ታደጋቸው። በኋለኛው ዘመንም ተመሳሳይ የሞት ቅጣት የሚያስበይኑ ሕግጋት እንደሚወጡና አንታዘዝም በሚሉ ላይ የሞት ፍርድ እንደሚበየንባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ራእይ 13፡15-18)።
“አንባቢው ያስተውል”