giziew.org

በፓርላማው ድጋፍ ስኮትላንድ ለማርያም ተቀድሳ ተሰጠች

“እኛነታችንን ሁሉ፣ ፍቅራችንን ሁሉ፣ ያለንን ሁሉ እና ስኮትላድንም ጭምር ላንቺ (ለማርያም) ቀድሰን እንሰጣለን። ለአንቺ አእምሯችንን፣ ልባችንን፣ አካላችንና ነፍሳችንን እንሰጣለን። ..."
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በስኮትላንድ ፓርላማ ሙሉ ድጋፍና ውሳኔ ስኮትላንድ ለማርያም ተቀድሳ ተሰጥታለች። በስኮትላንድ ታሪክ “ልዩ” በተባለ መልኩ በተከናወነው ሥነሥርዓት ላይ ማርያም በአገሪቱ ላይ የሰፈነውን “የዲያቢሎስ አረም” እንድትነቅል ጥሪና ፀሎት ተደርጎላታል።

መስከረም 5፤ 2017ዓም (እኤአ) ላይ የታተመው “ናሽናል ካቶሊክ ሬጂስተር” እንደዘገበው፤ ከመላው ስኮትላንድ የመጡ በርካታ ምዕመናን በተሳተፉበት በካርፊን ከተማ በሚገኘው የማርያም ቤ/ክ “በስኮትላንድ ታሪክ ልዩ” የተባለው ሥርዓት ተካሂዷል። በዕለቱ የካቶሊክ ቤ/ክ ጳጳሳት፣ ካህናትና ኃላፊዎች እንዲሁም የመንግሥት ተወካዮች  ተገኝተዋል።

ፓርላማው ውሳኔውን ባፀደቀበት ጊዜ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፤

“በስኮትላንድ የካቶሊክ ጳጳሳት መስከረም 3፤ 2017 (እኤአ) ይህችን አገር ለማርያም ቀድሰው እንዲሰጡ (ፓርላማው) ዕውቅና ሰጥቷል፤ … በዚህም ስኮትላንድ እውነትን ለማወቅ እንድትነሳሳ፣ ለፓርላማ አባላትና ለመንግሥት ባለሥልጣናት በሙሉ ጸሎት በማድረግ ሁሉም ሰዎች የሚከበሩበት፣ አናሳዎች የማይናቁበት እና ሰዎች እምነታቸውን በነጻነት የሚለማመዱበት እውነተኛ የፍቅር ሥልጣኔ እንዲገነባ (አገሪቷን ለማርያም ቀድሰው በመስጠት ጳጳሳቱ ፀሎት ሊያደርጉ ይገባቸዋል)።”

በዕለቱ በቀረበውና ሁሉም ሰው በተሳተፈበት ፀሎት ላይ፤ “እኛነታችንን ሁሉ፣ ፍቅራችንን ሁሉ፣ ያለንን ሁሉ እና ስኮትላድንም ጭምር ላንቺ (ለማርያም) ቀድሰን እንሰጣለን። ለአንቺ አእምሯችንን፣ ልባችንን፣ አካላችንና ነፍሳችንን እንሰጣለን። ቤታችንን፣ ቤተሰባችንን፣ ቤ/ክናችንና ት/ቤቶቻችንን ለአንቺ አገልግሎት በፈቃዳችን እናስረክባለን። ማርያም ሆይ! ለእኛ ያለንን እና ባካባቢያችን ያለውን ሁሉ ለአንቺ እንዲሆን እንመኛለን” የሚል ልመና በእያንዳንዱ ሰው ቀርቧል።

ግረሰዶማዊነትና ሌሎች የግብረገብ ጉዳዮች ስኮትላንድን እየናጧት ባለበት ባሁኑ ወቅት ማርያም የማኅበራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳውን እንድትቆጣጠር መደረጉ በትክክለኛ ጊዜ የተከሰተ ነው ተብሏል። በዕለቱ ከተገኙት ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት ኪናን ሲናገሩ፤ “መልካም ስንዴ ዘር በሆነው የክርስትና ዕምነታችን መካከል ሰይጣን የዘራውን አረም እንድትነቅል፤ የሃይማኖታችንን ጠላቶች እኩይ ዕቅድ እንድታከሽፍ … ወደ ማርያም መምጣት አለብን” ብለዋል።       

የማርያምን ከሞት በኋላ በህይወት መኖር በሚያምኑ የካቶሊክና ሌሎች እምነቶች ብቻ ሲባል በዚህ መልኩ መንግሥት የሚሳተፍበት ሃይማኖታዊ አሠራር ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል። በተለይ የመንግሥትንና የሃይማኖትን መለያየት የሚደግፉ፤ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር የበርካታ ሰዎችን የሃይማኖት ነጻነት የሚጻረር ነው በሚል አጥብቀው ይቃወሙታል። በስኮትላንድ የካቶሊክና አምሳያው የስኮትላንድ ቤ/ክ አማኞች ቁጥር ከአጠቃላዩ ሕዝብ ግማሹን ያህል ሲሆን ከቀሪው ግማሽ ሕዝብ ውስጥ 37በመቶ ያህሉ ሃይማኖት አልባ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው።

በ16ኛው ክ.ዘ. የነበረው ዮሐንስ ኖክስ የተባለው የተሃድሶ አራማጅ የካቶሊክ ቤ/ክ ሁሉንም የመቆጣጠር አካሄድና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆኑ ሌሎች አስተምህሮቶችን አጥብቆ በመቃወም በስኮትላንድ ለውጥ ማምጣቱ ይታወሳል። ከዚህ አኳያ አሁን አገሪቱ ወደዚህ ዓይነት አሠራር ውስጥ መግባቷ እርሱን ከሰማዕትነት ሞት ቀስቅሶ እንደገና የመግደል ያህል ተደርጎ ተወስዷ።

“አንባቢው ያስተውል”


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *