የሰው ልጅ መታደስን ይፈልጋል፤ መለወጥን ይመኛል፤ መነቃቃትን ተስፋ ያደርጋል። ይህንን ዕውን የማድረጊያውን መንገድ ግን ያገኘው አይመስልም። ምክንያቱም የተለያዩ ነገሮችን ከመሞከር ባለፈ ለነፍስ አንዳች የማይጠቅም ነገር ሲያደርግ ይገኛል። መታደስን ከመፈለጉ የተነሳ ሕይወትን ከእግዚአብሔር የሚለዩ ተግባራትን በመፈጸም የበለጠ የተሳሳተ ጎዳና ውስጥ ራሱ በተስፋ መቁረጥ ተከብቦ ነፍሱም እጅግ ተጠምታ ያገኛታል። ታዲያ መንፈሳችን የሚታደሰው እንዴት ነው? ምንስ ይሆን የሚያነቃቃን?
“መንፈሴን አድስልኝ” የሚሉት ቃላት ልመና ብቻ ሳይሆን እምነት፣ ተስፋና እርግጠኝነትን ያካተቱ ናቸው። “አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ” በማለት ባለመዝሙሩ ልመናውን ብቻ ሳይሆን የነፍሱንም ናፍቆት ያቀርባል (መዝ. 143፡11)። ይህንን ልመና ዳዊት ባቀረበበት ጊዜ ጥያቄው ከልመና የላቀ ነበር። እግዚአብሔር ሕያው ማድረግ እንደሚችል ሙሉ እምነት ያለው መሆኑን እየመሰከረ ሲሆን ከእምነት ጋር በተጓዳኝም ተስፋንም የሰነቀ ነው፤ ይህ ተስፋ ደግሞ የማይታየውን ዕውን አድርጎ የሚያስጨብጥ፤ ሩቁን ቅርብ፤ ያልነበረውን እንዳለ አድርጎ በገሃድ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሰልፍ ኃያል የሆነው፤ ለዘላለምም የማይሸነፈው፤ ሁልጊዜ ድል አድራጊ የሆነውንና “ድል እየነሣ ድል ለመንሣት” በሚወጣው የክርስቶስ የመከወን ችሎታ ላይ እርግጠኛ ስለሆነ ነው (ራዕይ 6፡2)።
በዚህ የመስከረም – ኀዳር 2012ዓም ጊዜው ዕትም መንፈሱ እንዲነቃቃለት ከተመኘውና ይህንንም ዕውን ካደረገው ዳዊት የሕይወት ተሞክሮ የምንማረው ይኖረናል። በጥሞና ጊዜ ዓምድ ሥር የቀረበው “ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብኝ” የሚለው መልዕክት የዳዊትን ልብ ምን እንዳቆሸሸው በማብራራት፤ ከመታደሱ በፊትና በኋላ ያለውን ሕይወት በመዳሰስ፤ እውነተኛ የመንፈስ መለወጥ እንዴት እንደምናገኝ ያስተምረናል። የዚህ ዕትም ገዢ ርዕስ የሆነው “መንፈሴን አድስልኝ” የሚለው ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዓምድ ሥር የቀረበ ሲሆን ይህም እውነተኛ ተሃድሶና መነቃቃት እንዴት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደሚገኝ ያብራራል።
ልጆች ትምህርት የሚጀምሩት የት ነው? ተብሎ ቢጠየቅ ምናልባት መልሳችን “ትምህርት ቤት ነው” የሚል ይሆናል። ነገርግን የቤተሰብ ዓምድ ልጆች ትምህርት የሚጀምሩት የት እንደሆነ የሚያብራራ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያ አስተማሪዎቻቸው እነማን እንደሆኑ ያስረዳል። ከመታደስ ጋር በተያያዘ በውሃ መታጠብ ሌላው አካላዊ ዕድሳት የሚሰጥ መሆኑን የሚተነትነው ለጤናችን ዓምድ እንደ ቀላል አድርገን ለምንወስደው እጅ መታጠብ እንዴት ትኩረት መስጠት እንደሚገባን በመረጃ የተደገፈ ሰፋ ያለ ሃተታ በመስጠት በመታጠብ “ራሳችንን እናንጻ” ይለናል።
“ብሞትም ባልሞትም ችግር የለም፤ ያመንኩትን አውቃለሁና” በሚል ርዕስ የሐኪም ተመስገንን አስደናቂ የሕይወት ምስክርነት ይህ ነው ታሪኬ ዓምድ ይዞ ቀርቧል። “ሦስት ጊዜ ያህል ሞቼ ነበር፤ አምላኬ ከሞት አድኖኛል ይህንንም እመሰክራለሁ” ይላል ሐኪም ተመስገን። ይህንን በቃለ ምልልስ መልክ የቀረበ ዘለግ ያለና መሳጭ ምስክርነት ማንበብ ብዙ በረከት የሚገኝበት ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም የሚያነቃቃ እንደሚሆን ተስፋችን ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል ነው? ሊታመንስ ይችላል? ምን ማረጋገጫ አለን? አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ስህተቶች ስላሉት የእግዚአብሔር ቃል ሊባል አይችልም ይላሉ፤ ምንድነው መልሱ? መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሱት ታሪካዊ ክስተቶችስ ትክክለኛ ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን ከነመልሳቸው በጥያቄና መልስ ዓምዳችን ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። ጥያቄ ካላችሁ በገጽ 3 ላይ ባለው አድራሻችን በአንዱ እንድትልኩልን አንባቢዎቻችንን ልናደፋፍር እንወዳለን።
እንደተለመደው በጽሁፎች መካከልና መጨረሻ በ“አንባቢው ያስተውል” ዓምዳችን የቀረቡትን ወቅታዊ የዜና ዘገባዎች አንባቢያን የጊዜውን ሁኔታ ከትንቢት አፈጻጸም ጋር በማገናኘት እንዲያጤኑ እንጋብዛለን።
ዘመኑን ለመዋጀት ጊዜውን ያንብቡ!
አዘጋጆቹ