giziew.org

ቅድስና፤ የግል ንፅህናና መፀዳጃ ቤቶች

የግል ንፅህና በአካላዊ ቅድስና ውስጥ ይጠቃለላል። አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ለራሱ ሰውነት መጠንቀቅ የሚያስችል አእምሮና አካላዊ ብቃት ሰጥቶታል። ለመታጠብ የሚረዳውን ውሃ ሰጥቶ ሳሙናን መፍጠር የሚያስችል ብቃት አላብሶታል።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ አማኞች ምኞቱን ሲገልፅ እንዲህ ብሏል፤ “የሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና ሥጋችሁ (አካላችሁ) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ነቀፋ ይጠበቁ።” (1 ተሰ. 5:23)

“መቀደስ” ማለት “መለየት” ነው፤ ከ“ዓለም መለየት”። የጳውሎስ ምኞት የተሟላ ለውጥ በአንባቢዎቹ ሕይወት ውስጥ እንዲታይ ነው። የተሟላ ቅድስና ዓላማ ደግሞ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ነቀፋ ተጠብቆ መገኘት ነው።

ይህም መንፈስና ነፍስን ብቻ ሳይሆን አካልንም ያጠቃልላል።

ቅድስና የአስተሳሰብ ለውጥ ይፈጥራል። የአስተሳሰብ ለውጥ ደግሞ የአኗኗር ለውጥ ያመጣል። አካላችንን የተመለከቱ ጉዳዮች ቅድስና በፈጠረው የአስተሳሰብ ለውጥ ምክንያት ይቀየራሉ። በአምላክ የቅድስና ለውጥ ውስጥ መኖር የጀመረ ሰው እጅግ ጠንቃቃ የሆነውን የሰማይ አባት ለማስደስት ሲል ከነቀፋ ሁሉ ለመራቅ ይፈልጋል። በአምላክ ዕርዳታ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ሲል በጥንቃቄ ላይ የተመሠረቱ እርምጃዎችንም መውሰድ ይጀምራል።

የግል ንፅህና በአካላዊ ቅድስና ውስጥ ይጠቃለላል። አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ለራሱ ሰውነት መጠንቀቅ የሚያስችል አእምሮና አካላዊ ብቃት ሰጥቶታል። ለመታጠብ የሚረዳውን ውሃ ሰጥቶ ሳሙናን መፍጠር የሚያስችል ብቃት አላብሶታል። ሲቆሽሽና ጠረኑ ሲበላሽ እንዲያስተውል የማየትና የማሽተት ችሎታ አልነፈገውም። ስለዚህ አንዳንዶች ዘንድ የጎደለው ንፅህና የፈጣሪ ጥፋት ሳይሆን ሰዎች በራሳቸው ቸልተኝነት ወይም በሌላ ምክንያቶች ያመጡት ውጤት ነው።

ጥንት እስራኤላውያን አምላካቸውን ከመገናኘታቸው በፊት ንፅህናን አስመልክቶ ግድየለሾች እንዳይሆኑ በሙሴ አማካይነት ተመክረው ነበር። “እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ ‘ወደ ሕዝቡ ሂድና ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ ልብሳቸውን እንዲያጥቡ አድርግ፤ በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በዚያ ቀን በሕዝቡ ፊት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል።’” (ዘፀ. 19:10-11)

ቆሻሻና ክፉ ጠረን ያላቸውን ነገሮች እንድንፀየፍ አምላክ አእምሯችንን ቃኝቶታል። ሆኖም የንፅህና መጉደል ሲደጋገም ቀድሞ እንፀየፋቸው የነበሩትን ነገሮች ለምደን እንደ ተራ ዕለታዊ ክስተቶች እናያቸዋለን። አዳፋውን ሸሚዝ ደጋግሞ መልበስ ከነውር አይቆጠርም። ላብ በተደጋጋሚ ደርቆበት ለብዙ ቀናት ያልታጠበው ሰውነት ሸትቶ በታክሲ ውስጥ አብረው የተሳፈሩትን ግለሰቦች ጤና ሲነሳ የችግሩ ባለቤት ግን የለመደው ጠረን ሳይረብሸው ውሎ ያድራል። ይህ ደግሞ በታክሲ ውስጥ ብቻ ሳይወሰን በሥራ ቦታ፣ በቤተሰብ፣ በቤ/ክ እና በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታ ሲከሰት ይታያል። ታዲያ በእንዲህ ዓይነቱ ሰው አካባቢ የሚገኙቱ የመጥፎው ጠረን ምንጭ በቅድስና  እኖራለሁ ከሚል አማኝ የሚመጣ መሆኑን ሲረዱ ምን ያስቡ ይሆን?

የግል ንፅህና ከራሳችን አልፎ ለሌሎች ከአምላክ ጋር ስላለን ግንኙነት የሚመሰክር መሆኑን ማወቅ አለብን። ሁላችንም በንፅህና ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተናል። ንፅህናው በጥንቃቄ የተጠበቀ ቤትና መንደር ውስጥ መኖር የማይመርጥ ማነው? ይህ እውነት ከሆነ በንፅህናችን ሌሎችን ማስደሰቱ የቅድስና አንዱ ክፍል መሆኑን እንወቅ። ቃሉ እንደሚለው፤ “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” (ፊል. 2:4)። ከዚህ የምክር ቃል የተነሳ በቅድስና መኖር የሚፈልግ ሁሉ አርቆ በማሰብ ለሌሎች የሚጠቅመውን በግል ንፅህናው ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታው ነው።

በታዳጊው ዓለም የግል ንፅህና መጉደል ከሚታይባቸው ዋና ቦታዎች አንዱ የመፀዳጃ አካባቢዎች ላይ ነው። በምድራችን 2.5 ቢሊዮን ሰዎች በገላጣ ቦታዎች የሚፀዳዱ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። እነዚሁ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወደ 2 ቢሊዮን የሚሆኑ በከተማዎች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚጠቀሟቸው መፀዳጃ ቤቶች በትክክል አይመጠጡም፤ ንጽህናቸው አይጠበቅም። ከነዚህ ሽንት ቤቶች የሚያመልጠው ፍሳሽ በጎዳና ከሚፈስና በቱቦ ከሚተላለፍ የመጠጥ ውሃ ጋር ተቀላቅሎ የበሽታ መንስኤ ይሆናል። በዚህ ምክንያት የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በዓለም ዙሪያ የሚሞቱ ህጻናት ቁጥር 700 ሺህ ይጠጋል። ይህ የፈጣሪ ሃሳብ አለመሆኑ ግልፅ ነው።

ለመሆኑ አምላክ በመፀዳዳት ጉዳይ ዙሪያ በቃሉ የተናገረው ነገር አለ? እስራኤላውያን ልብሳቸውን እንዲያጥቡ የመከረው ቅዱሱ አምላክ እንዲህ ብሏል፤ “ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ። ከትጥቅህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቆፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት። አምላክህ እግዚአብሔር ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን” (ዘዳ. 23:12-14)።

ለእስራኤላውያን ጤንነት ሲል ፈጣሪ ከሠፈራቸው ርቀው እንዲፀዳዱ አዘዘ። ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው እስራኤላውያን በምድረበዳ እያሉ ነው። የሚበሉበት፣ የሚተኙበትና ጌታን የሚያመልኩበት ሰፈር በዐይነ ምድራቸው ነውር መርከስ እንደሌለበት ተነገራቸው።  ታዲያ ዛሬ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢና በመጫወቻ ሜዳዎች ላይ እየተፀዳዱ በሽታና ሞትን በሕፃናት ላይ የሚጠሩትን “አዋቂዎች” አምላክ እንዴት ያያቸው ይሆን? ለመጪው ትውልድ የሚሰጡትን መጥፎ ምሳሌስ ምን እንለዋለን?

አምላክ ከሰፈሩ ወጥተው እንዳሰኛቸው ተፀዳድተው እንዲመለሱ አላዘዘም። መቆፈሪያ ይዘው በዐይነ ምድራቸው ላይ የዛቁትን አፈር እንዲመልሱበት ነገራቸው። ሽታውን ከማፈንም በላይ በአፈር መሸፍኑ በነፍሳት እገዛ ዐይነ ምድሩ ቶሎ ከአፈር ጋር እንዲዋሃድ ያደርጋል። የአምላክ መፍትሄ ድንቅ ነው። “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ”(መዝ. 104:24)።

ምክሩን ከልብ ብንፈልግ አምላክ የኑሮን ሸክሞች ማቃለል የሚችሉ ብዙ ጠቃሚ ምክሮች ሊሰጠን ዝግጁ ነው። ለእስራኤል የተሰጠው ምክር እንደሚጠቁመው መፀዳጃ ቤቶችን ተጠቅመን ከመውጣታችን በፊት ተከትለውን ቦታውን ለሚጠቀሙ ሰዎች ማሰብ አለብን። ስለሆነም ቦታው በእኛ ምክንያት እንከን እንዳያገኘው የተቻለንን ማድረግ አለብን።

ፈጣሪንና ሌሎችን በመውደድ ለንፅህና የምናደርገው ጥንቃቄ የእውነተኛ ቅድስና ውጤት ነው። በፍቅር የተሰራ ሁሉ የአምላክ መንፈስ ስላለበት ሌሎችን ወደ ክርስቶስ ይስባቸዋል። በአንፃሩ በንዝላልነትና በተዝረከረከ ሕይወት መሰንበቱ ለራሳችንና ለአምላክ ስም ብዙ ምስጋና አያመጣም። አምላካችን ይህንን ዓይነት ትዕዛዝ ለእስራኤላውያን በዚያን ዘመን ከሰጠ፤ በቴክኖሎጂ በልጽገናል ለምንለው ለዚህ ዘመን ሰዎች ከዚህ ያነሰ አይጠብቅብንም። ይህንን ለመተግበር ከኢኮኖሚ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ካሉብንም እናዋየው፤ እርሱ የመፍትሔ አምላክ ነው።

ፈጣሪ በንፅህና ዙሪያ የሰጠው ምክር ለሰዎች ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጥ አምላክ መሆኑን ይነግረናል። ንፅህና ከቅድስና ጋር መያያዙ ደግሞ ጤናችንን አስፍቶ ብዙ ሳንናገር ለሌሎች የቅዱሱ አባታችን ምስክሮች እንድንሆን ምቹ አጋጣሚ ይሰጠናል። ስለዚህ ቅድስና ማለት የመንፈስ፣ የነፍስና የአካል ጭምር መሆኑን ተገንዝበን በፀሎት ኃይል ለመሻሻል እንበርታ።

ድርባ ፈቃዱ


1 thought on “ቅድስና፤ የግል ንፅህናና መፀዳጃ ቤቶች”

  1. Yetagesu H/Michael

    It is very interesting and clear message for all people of God. We have to be careful to be a model for others because we are stewards.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *