ጉዳዩ “ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል” የካንተርበሪው ሊቀጳጳስ
ባለፈው የሰኔ ወር አካባቢ በስኮትላንድ የሚገኘው የኤጲስቆጶሳውያን ቤ/ክ ሲኖድ የግብረሰዶማውያንን “ጋብቻ” ካጸደቀ በኋላ በዚያው በስኮትላንድ የሚገኘው የአንገሊካን ቤ/ክ የመጀመሪያውን የሰዶማውያን “ጋብቻ” መፈጸሙ ተሰማ። የአንገሊካኑ ሊቀጳጳስ ጉዳዩ “ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል” ብለዋል። በሎንዶን ከተማ የግብረሰዶማውያንና የግብረገሞራውያንን (ሌዝቢያን) የህይወት መሥመር በትምህርት ቤት ደረጃ ለተማሪዎች አናስተምርም የሚሉ የግል ት/ቤቶች የመዘጋት አደጋ ላይ እንደሚገኙ ተነገረ።
በአውሮጳና አሜሪካ የተመሳሳይ ጾታ “ጋብቻ” በመንግሥት/በሕግ ደረጃ እየተፈቀደ መምጣት ከጀመረ ወዲህ ሥርዓቱን የሚፈጽሙ ቁጥር የዚያኑ ያህል እየጨመረ ሄዷል። ሆኖም በአብዛኛው በማዘጋጃ ቤቶች የሚካሄደው ሥነሥርዓት በአምልኮ ስፍራዎች በካህናት ቡራኬ ሲፈጸም እስካሁን እምብዛም የተለመደ አልነበር። ነገርግን ባለፈው ዓመት የሰኔ ወር የስኮትላንድ ኤጲስቆጶሳዊ ቤ/ክ አጠቃላይ ሲኖድ የተመሳሳይ ጾታ “ጋብቻ” በቤ/ክ እንዲካሄድ ሲፈቅድ ካህናቱም “ጋብቻውን” በሥርዓቱ መሠረት እንዲባርኩ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህም ማለት ማንኛውም የአንገሊካን ቤ/ክ አባል የሆነ በስኮትላንዱ ኤጲስቆጶሳዊ ቤ/ክ በፈለገው መልኩ “ጋብቻ” መፈጸም ይችላል።
በዚህ ውሳኔ ምክንያት ከቤ/ክኗ ቀኖና (አስተምህሮ/ዶክትሪን) ውስጥ ጋብቻ “በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መካከል ይካሄዳል” የሚለው ዓርፍተነገር እንዲሰረዝ አብሮ ውሳኔ ተላልፏል። በብራዚል፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በደቡብ ሕንድ፣ በኒው ዚላንድ እና በካናዳ የሚገኙ የአንገሊካን አያብተ ክርስቲያናት የሰዶማውያንን ጋብቻ ያጸደቁ ሲሆን በሌሎች አገራት የሚገኙ ግን አሁንም ውሳኔውን እየተቃወሙ ይገኛሉ። የአሜሪካው አንገሊካን ቤ/ክ ዋና ጉባዔ ከሁለት ዓመት በፊት የሰዶማውያንን “ጋብቻ” ማጽደቁ ይታወሳል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሁኔታውን አሳሳቢነት በተመለከተ የተጠየቁት 80 ሚሊዮን ምዕመናን ያሉት የአንገሊካን ቤ/ክ ሊቀጳጳስ ጀሰቲን ዌልቢ ሲናገሩ “ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል፤ በቀላሉ ይፈታል ከሚል አቋም ባለፈ መልኩ በጣም የተወሳሰበ ነው፤ ሆኖም በየአገረ ስብከቱ ያሉት ኤጲስቆጶሳት አብረው እንደሚሰሩ ቃላቸውን ሰጥተውናል” ማለታቸውን የሃይማኖት ዜና አገልግሎት (Religion News Service) ዘግቧል።
ቤ/ክኗ የተመሳሳይ ጾታ “ጋብቻ” ከፈቀደችበት ወር ጀምሮ በተለያዩ አጥቢያ ቤ/ክናት “የጋብቻ” ስነሥርዓታቸውን መፈጸም ለሚፈልጉ ምዝገባ መጀመሩን ማስታወቂያ ሲነገር ቆይቷል። ግላስጎው በተባለችው የስኮትላንድ ከተማ የቅድስት ማርያም ቤ/ክ አስተዳዳሪ ማስታወቂያውን በተናገሩ ጊዜ “የምዕመናኑ ጉባዔ ከፍተኛ አድናቆት በመስጠት በጭብጨባና በአሜን ድጋፍ” እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ይህ በስኮትላንድ በቤ/ክ ደረጃ የተጀመረው የ“ጋብቻ” ፈቃድ በተለያዩ የእንግሊዝ አብያተ ክርስቲያናትም ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ወደ ተመሳሳይ ውሳኔ እንዲመጡ የሚስገድድ እንደሚሆን በሰፊው እየተነገረ ይገኛል።
በተያያዘ ዜና የግብረሰዶማውያንና የግብረገሞራውያንን (ሌዝቢያን) የህይወት መሥመር በትምህርት ቤት ደረጃ ለተማሪዎች አናስተምርም የሚሉ በሎንዶን የሚገኙ የግል ት/ቤቶች የመዘጋት አደጋ ላይ እንደሚገኙ ተነገረ።
ዕድሜያቸው ከ3 – 8 ዓመት የሚሆኑ የሚማሩበት በሰሜን ሎንዶን የሚገኘውና ቪሽኒትዝ ተብሎ የሚጠራው የአይሁድ ሴት ህጻናት ት/ቤት፤ “ተማሪዎቹን ስለግብረሰዶማውንና ስለ ጾታ መቀየር” አያስተምርም በሚል በእንግሊዝ የትምህርት፣ የልጆች አገልግሎትና ክህሎት ደረጃ መዳቢ ቢሮ (Ofsted) በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በምርመራ (ኢንስፔክሽን) ተገቢውን ነጥብ ሳይሰጠው በመቅረት ውድቅ አድርጎታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ 212 ተማሪዎች ያሉት ት/ቤት “መሠረታዊ የብሪታኒያ እሴቶችን ለተማሪዎቹ አያስተምርም፤ ተማሪዎች መንፈሣዊ፣ ግብረገባዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ዕድገቶች እንዳያገኙ ገድቧቸዋል” በሚል ነጥብ ተይዞበታል። እንደ ቴሌግራፍ የሰኔ ወር መገባደጃ የዜና ዘገባ ከሆነ ይህ የምርመራ ውጤት የት/ቤቱን ደረጃ ዝቅ የሚያደርገው ይሆናል።

ከዚህ ት/ቤት በተጨማሪ ይህ መሰሉ የደረጃ ምድባ በሌሎች ሦስት የግል ት/ቤቶችም ላይ በተመሳሳይ ተደርጎባቸው ደረጃቸው ውድቅ መደረጉ ተነግሯል። በብሪታኒያ የትምህርት ሕግ መሠረት የግል ት/ቤቶች የደረጃ መዳቢውን ቢሮ ተገቢ ነጥብ ካላገኙ መዘጋት አለባቸው። ይህንን በመቃወም ክፍት ሆነው ከቀጠሉ ግን በወንጀል ተከስሰው ፍርድቤት እንዲቀርቡ ሕጉ ያዛል።
ከመጽሐፍ ቅዱስ የጋብቻና ሌሎች የጾታ መመሪዎች አንጻር ግብረሰዶማዊነት ኃጢአት ነው የሚሉ ወገኖች፤ “ስንወለድ ሰዶማዊ ሆነን ነው የተወለድነው…” ለሚለው መከራከሪያ “ሁላችንም ከአባትና ከእናታችን በኃጢአት እንደተወለድን ሁሉ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ በአዲስ ህይወት በምርጫችን መወለድ እንችላለን፤ ለሰዶማዊነት ችግር ዳግም መወለድ ከበቂ በላይ መፍትሔ ነው” በማለት ሃሳብ ያቀርባሉ። የሰዶምና ገሞራ ኃጢአት ከተመሳሳይ ጾታ ጋር በተደረገ ግንኙነትና በተያያዥ ኃጢአቶች እንደሆነ የሚሞግቱ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በይሁዳ 7 ላይ የተጻፈውን በአስረጂነት ያቀርባሉ። “እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ፣ በዙሪያቸውም ያሉ ከተሞች ለሴሰኛነትና ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ለሆነ ሩካቤ ሥጋ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት በመቀጣት ለሚሠቃዩት ምሳሌ ሆነዋል”። የዘመኑን ልቅነት ከሎጥ ዘመን ጋር በማመሳሰል ጊዜው መድረሱን፤ የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ከመቼውም ይልቅ መቅረቡን ደጋፊ ማስረጃ አድርገውም ያቀርባሉ።
በዓለማችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣው የግብረሰዶማውን ጉዳይ ከበስተጀርባ ሆኖ የሚገፋው ኃይል እንዳለ የሚነገር ቢሆንም በአብዛኛው የማኅበራዊና የሃይማኖት መሠረቶችን እያናጋ ይገኛል። በዚህ ዓይነት የህይወት መስመር ላይ የሚገኙቱ “ስንወለድ ሰዶማዊ ሆነን ነው የተወለድነው፤ ተለወጡ ከምትሉን እንዳለን ተቀበሉን” በማለት መከራከሪያ ያቀርባሉ። ከዚህም ሌላ ሰዶምና ገሞራ የጠፉት እንደሚባለው በነበራቸው ከተመሳሳይ ጾታ ጋር በተደረገ ግንኙነት ሳይሆን በሌሎች ኃጢአቶች ነው በማለት ይከራከራሉ።
“አንባቢው ያስተውል”!