giziew.org

ራስን መቆጣጠር፡ የክርስቲያን ኑሮ

የእግዚአብሔርን የጤና ሕግጋት በራሳችን ኃይል መጠበቅ ስለማንችል አምላካችን “ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል”። ከዚህም የተነሳ እንደ ጳውሎስ ራሳችንን መቆጣጠር፣ መግዛት፣ ማሸነፍ አለብን።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ ሲያበቃ የሆነውን መፅሐፍ ቅዱስ በሚከተለው መልክ ይገልፀዋል፤ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ …” (ዘፍ 1:31)። በተፈጠረች ጊዜ ዓለም ውብ ሰላም ነበራት። ይህ ማለት በምድር ላይ በጨጓራ በሽታ የሚቃጠል ወይም በአእምሮ መታወክ የሚቸገር ሰው አልነበረም ማለት ነው። በሽታ ሰው ሟች መሆኑን የሚያስታውስ ሸክምና የኃጢአት ውጤት ነው። ኃጢአት ደግሞ የፈጣሪን መልካም ፈቃድ መጣስ ወይም በተፈጥሮ ውስጥ ያለውን ሕጋዊ ስምምነትና ውኅደት ማቃወስ ማለት ነው (1 ዮሐ 3:4)።

ቅድስና ኃጢአት ያበላሸውን ሁለመናችንን የሚዳስስ መለኮታዊ የለውጥ ሂደት ነው። መንፈስ ቅዱስ እኛን ከጥፋት መልሶ ወደ ጥንቱ የፈጣሪ ፈቃድ ሲመልሰን የኑሮ ዘይቤያችንን ቀኝ ኋላ በማዞር ነው። ስለሆነም አሰተሳሰባችንንና አነጋገራችንን ብቻ ሳይሆኑ አበላል፣ አጠጣጣችንና አለባበሳችንም ይለወጣሉ። በውስጣችን የሚሠራው ቅዱሱ መንፈስ ውጫችንንም በመለወጥ አካላዊና ስነልቦናዊ ጤና እንድናገኝ ይረዳናል።

የዚህ ለውጥ ጥቅም ብዙ ነው። ጤናማ ክርስቲያን በሰከነ አእምሮ እግዚአብሔርን ማምለክ ይችላል (1 ቆሮ 11: 21-30)፣ በሽታ ካልተጠናወተው ባልንጀሮቹን ብዙ ማገልገል ይችላል። ቅንጦትና የጌጣጌጥ ፍቅር ጊዜና ጉልበቱን ካልፈጁት በመንፈስ መጥቆ መሄድ ይችላል። በዚህ ምክንያት ጤና ተኮር እውቀት ለቅድስና ወሳኝ ነው። ቃሉንም ስንፈትሽ የምናየው መንፈሳዊና አካላዊ ቅድስና ትልቅ ትስስር እንዳላቸው ነው፤ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኮአችሁ ነው” (ሮሜ 12:1)። ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ እንዴት ነው ሰውነታችን በቅድስና የምንጠብቀው? ከአፈጣጠራችን በመጀመር እንዴት በዚህ ዘመን እግዚአብሔር ራሳችንን መጠበቅ እንዳለብን የሚያስተምረንን እንመልከት፤

1. ፈጣሪ በገነት ውስጥ የጤና ሕጎች ሰጥቶ ነበር?

አምላክ አዳምና ሔዋንን ፈጥሮ በገነት ካኖራቸው በኋላ ያሻቸውን እንዲበሉ አልፈቀደም። ቃሉ እንደሚለው፤ “እግዚአብሔርም፣ እንዲህ አለ፤ ‘በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬያቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ’” (ዘፍ 1:29) ይህ ትዕዛዝ ነው። ስለሆነም ሰዎች እንደ ስንዴ፣ ዘር የሚሰጡና እንደ ብርቱካን ያሉ ዘር-አዘል ፍሬዎች ብቻ በመብላት ይኖሩ ነበር።

የእንስሶችን አመጋገብ አስመልክቶ ቃሉ እንዲህ ይላል፣ “እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ” (ዘፍ 1:30)። ይህ ትእዛዝ ሁሉንም የምድር አራዊትን ያካተተ ስለነበር የሌላ እንስሳ ሥጋ በልቶ የሚኖር አውሬ አልነበረም። ከዚህ ደግሞ የምንማረው በአምላክ የፍጥረት ሥራ ውስጥ ደም ማፍሰስ እንዳልነበረ ነው።

2. አዳምና ሔዋን ከኃጢአት በኋላ ምን ይበሉ ነበር?  

ቃሉ እንደሚለው፣ “ምድርም እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች፤ ከቡቃያዋም ትበላለህ” (ዘፍ 3:18)። ይህ ትእዛዝ እንደሚጠቁመው ኃጢአት ከገባ በኋላ እንኳን ሰዎች ምድር የምታበቅለውን ቡቃያ እንዲበሉ አምላክ እንደተናገረ ነው።

3. ታዲያ ሥጋ መብላት የተፈቀደው መቼና በምን ምክንያት ነው?

ከውሃ ጥፋት በኋላ ሰዎች ሥጋ እንዲበሉ ፈጣሪ ፈቀደ (ዘፍ 9:2-4)። ይህ የሆነው በውሃ ጥፋት ምክንያት የሚበላ ፍሬ ወይም ተክል ባልነበረበት ሁኔታ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል። ምክንያቱም ምድር ሁሉ በውሃ ከጠፋችና በምድር የሚገኝ ሰብል ሁሉ ከወደመ በኋላ ኖህና ቤተሰቡ ከመርከቧ ሲወጡ ነበር አምላክ ሥጋ እንዲበሉ የፈቀደው። ቀጥሎ ደግሞ የእስራእኤል ልጆች ሥጋ የመብላት ፍላጎት ካላቸው ምን ዓይነት እንስሶች ለመብል እንደሚሆኑና በምን አይነት መንገድ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጌታ በዝርዝር ተናግሯል (ዘሌ. 11)። ይህም ሆኖ ግን አምላክ ራሱ እስራኤላውያንን በምድረበዳ በነበሩበት ጊዜ ይመግባቸው የነበረው ከሰማይ መና አውርዶ ነበር (መዝ 78:24)። ከዚህ የምንረዳው ከቀድሞው ጀምሮ የአምላክ ፈቃድ አለመቀየሩንና ሰዎች ደግሞ ከፈጣሪ ፈቃድ የራቀ ሆድ (የምግብ ፍላጎት) እንዳላቸው ነው።

የሰዎች አመጋገብ በኃጢአት ምክንያት ተቀይሯል። ከብቶችን ለእርድ አደልቦ ማቅረብና የረጋ ደም ያለበት ሥጋ መብላት የማዕረግ ምልክት ሆኗል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በየዋህ እንስሶች ላይ፣ በስነልቦናችንና በጤናችን ላይ የሚያመጣውን ውጤት ቆም ብሎ ማሰብ ጠቃሚ ነው።

4. በሰማይ ሥጋ መብላት ይኖራል?

በሚመጣው ዓለም ቅዱሳን የሚበሉት የገነትን ፍሬ ነው (ራዕ 22:2)። በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ነፍስ አጥፊ አውሬም አይኖርም (ኢሳ 9:6-9)። ርኅራሄና ደግነት በነገሡበት ቦታ ወደ ቄራ ለዕርድ የሚነዳ ከብት ወይም የዶሮውን አንገት ለመቀንጠስ ቢላዋ ሲሳል የሚሰማ ድምጽ አይኖርም። ያንን ሰላም ለማየት ከዚሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል፤ “እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1 ቆሮ 10:31)።

5. ፈጣሪ ከምግብ ውጭ ሌሎች ጤና ተኮር ሕጎች አሉት?

ቃሉ አለባበስና ንፅህናን አስመልክቶ ምክሮች ይሰጣል። ከቅንጦት ርቀን ራሳችንን እንድንገዛም ያሳስበናል።

አለባበስ፤ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ገላቸውን በበለስ ቅጠሎች ሸፍነው ነበር (ዘፍ 3:7)። ፈጣሪ ይህን አይቶ ቆዳ እንዳለበሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዘፍ 3:21)። ይህ የሚያስተምረን ልብስ ዘላቂ ሽፋን መስጠት እንዳለበት፣ በአየር መለዋወጥ ምክንያት ሊመጣ ከሚችል መረበሽ መከላከል እንደሚገባው ነው። አዳም የተጎናፀፈው የቅጠል ልብስና ብዙ ዘመናዊ ጨርቆች ይህንን ወሳኝ የልብስ መስፈርት አያሟሉም። ፈሪኃ እግዚአብሔር እንዳለው ሰው አለባበሳችን ለሰውም ይሁን ለአምላክ ቅድስናችንን የሚያሳይ፣ ቁጥብነት የተሞላበትና ልታይ ልታይ ማለትን በምንም መልኩ የማያሳይ መሆን ይገባዋል። በአለባበሳችን አምላክ ግልፅ ያደረገውን ፆታዊ ሥርዓት ማወሳሰብና ማደናበር ስህተት ነው። በዚህ ረገድ ሰው ከፈጣሪ ዓላማ ምን ያህል እንደራቀ ያለንበት ዘመን ይመሰክራል።

አነጋገር፤ ከአፋችን የሚወጣው የሰዎችን ህይወት ይጠግናል ወይም ይሰብራል። “እኔ ልቤ ንፁህ ነው አፌ ነው ሰው የሚያስቀይመው” በማለት የፈለግነውን በሰዎች ላይ ለመናገር ለራሳችን የማረጋገጫ ሠርቲፊኬት መስጠት የለብንም፤ “አንደበቱን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፤ አፉ እንዳመጣለት የሚናገር ግን ይጠፋል” (ምሳ 13፡3)። መጽሐፍ ቅዱሳችን አንደበታችንን እንድንገራ አጥብቆ ይመክራል ምክንያቱም “አንደበት የሞትና የሕይወት ኀይል አላት” (ምሳ 18፡21)። “ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ፤ ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህ ሊሆን አይገባም” (ያዕ 3፡8-10)። ስለዚህ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁል ጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን” (ቆላ 4፡6)።

ውበት፤ ቃሉ ሰውነታችንን መነቀስ እንደሌለበትና (ዘሌ 19:28) ጌጣጌጥንም አስመልክቶ “በወርቅ በማጌጥ” መዋብ እንደማያስፈልገን ይናገራል፤ “ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል (1ጴጥ 3:3-5)። መልክን ለማሻሻል መቀባባት፣ የፀጉር ውበት ላይ ብዙ መመራመርና፣ ውድ አልባሳትን አጥንቶ መግዛት፣ ወርቅና ብር ተሸክሞ ለመዞር መበሳሳት፣ ወዘተ … ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የትህትና፣ የጤናና ራስን የማዋረድ ሕይወት ጋር የማይሄዱ ተግባሮች ናቸው። የክርስትና ውበት ገርነት የተላበሰ የልብ ቅድስና ነው (1ጢሞ 2:9-10)። በመቃብር ወድቆ የሚበሰብሰውን ሥጋ ለማስዋብ መልፋት ከንቱ ነው። ይልቅ ወደ ሰማይ የሚሻገሩትን ፍቅርና ይቅር ባይነትን የመሳሰሉ ባህርያትን ለመላበስ ብንተጋ፣ ቁጣ፣ ትዕቢትና ራስ ወዳድነት ለማሸነፍ ብንታጠቅ ይሻላል።

6. ስለ ንፅህና ቃለ እግዚአብሔር ምን ይላል?

ሰውነታችን፣ ቤትና አካባቢያችን ንፁህ መሆን እንዳለባቸው አምላክ ተናግሯል (ዘዳ 23: 9-14)። የግል ንፅህና ከአምልኮ ጋር በጥብቅ የተገናኘ ነው (ዘፀ 19:10-11)። ስለሆነም እግዚአብሔር ሁልጊዜ አብሮን እንዳለ በመገንዘብ የተጣለብንን የንፅህና አደራ መጠበቅ አለብን።

7. ሰውነታችንን በቅድስና ለመጠበቅ መከተል የሚያሻን አጠቃላይ መርህ አለ?

ዋናው መርህ ራስን መግዛት ነው። ቅጥ ያጣ ሕይወት አመጋገብ፣ አለባበስና ዕንቅልፍ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። ዘመኑ በፍጥነት የሚገሰግስ፣ ጊዜያዊ ጥቅምና ደስታ ላይ ያተኮረ እንደመሆኑ መጠን ለአማኞች አስጊ ነው (2ጢሞ 3፡1-5)። ዓለም ሰውነትን የሚያጠፉ ኃጢአቶች ማስተናገዱን አልተወችም። መዝናናት ለሚፈልጉ እንቅልፍ ከልካይ ከንቱ ፊልሞችን፤ በፍትወት መንደድ ለሚፈልግ እርኩስ የብልግና ትይንቶችና የረቀቁ ዝሙት ቀጠሮዎች፣ የመብልና መጠጥ ባሪያ ለሆኑ ደግሞ በጥጋብ ሆድ የሚወጥሩና የሚያሰክሩ ግብዣዎችን ማሰናዳት ትችላለች።

ክርስቲያኖች ግን ሰውነታቸውን ለሱሶች መሸጥ አይችሉም። የእግዚአብሔር ልጆች ከሻይና ቡና ጀምሮ የማንኛውም ነገር (የሲጋራ፣ የሺሻ፣ የመጠጥ፣ የምግብ፣ የለስላሳ መጠጦች፣ ከበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) ጋር በተያያዙ እንደፌስቡክ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ፣ ወዘተ) ሱሰኞች መሆን የለባቸውም፤ ምክንያቱም ቃሉ “በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” ይላል (1ቆሮ 6:20)። የፍትወት ሱሶችም በአምላክ ዘንድ እጅግ ጸያፍ በመሆናቸውን ከዚ እንድንሸሽ መፅሐፍ ቅዱስ አጥብቆ ያስተምራል፤ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤ ደግሞም እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤ ይህም እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወተ ሥጋ ምኞት አይሁን” (1ተሰ 4:3-5)።

ስለዚህ የእግዚአብሔርን የጤና ሕግጋት በራሳችን ኃይል መጠበቅ ስለማንችል አምላካችን “ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል” (ያዕ 4:6)። ከዚህም የተነሳ እንደ ጳውሎስ ራሳችንን መቆጣጠር፣ መግዛት፣ ማሸነፍ አለብን። “ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል፤ … ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጐሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” (1 ቆሮ 9:25-27)። የተወደዱ አንባቢ፤ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊሊ.4፡13) በማለት አምላካችን የሚጠብቅብዎትን በተቀደሰ የክርስቲያናዊ አኗኗር ለአምላክ ክብር ለመኖር ፈቃድዎ ነው?

ቅንብር፤ ድርባ ፈቃዱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *