giziew.org

በልሳን መናገር: ትርጉምና አጠቃቀሙ

በልሳን ስለተናገሩ ሰዎች በሐዋርያት ሥራ ላይ ሶስት ቦታዎች ላይ ተፅፏል። (ሐዋ. ሥራ 2፣ 10፣ 19) እነዚህን ታሪኮች መመልከት ስለ ልሳን ጠቃሚ ግንዛቤ ይሰጠናል።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ልሳን ምን ማለት ነው?

አዲስ ኪዳን የተፃፈው በግሪክ ቋንቋ ነው። በግሪክኛ ግሎሳ (γλῶσσα) የሚለው ቃል ነው በአማርኛ “ልሳን” ተብሎ የተተረጎመው። ግሎሳ ቀጥተኛ ትርጉሙ ምላስ ሲሆን፤ ሁለተኛ ትርጉሙ ደግሞ ቋንቋ ነው።

ልሳን ለቤተክርስቲያን የተሰጠው ለምንድነው? 

ጌታ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “‘ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’” (ማቴ. 28:19)። 

ጌታ ይህን በተናገረበት ጊዜ፤ ደቀመዛሙርቱ የዓለምን ሕዝብ ለማስተማር የሚያስችል የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች አልነበሩም። በዚህ ምክንያት ነው ጌታ “የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል … በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ” ያለው (ማር. 16:17)።    

በአዲስ ቋንቋ/ልሳን መናገርን በተመለከተ በጥቅሱ “እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል …” የተባለው ደቀመዛሙርቱ በፊት ባልተናገሯቸው ቋንቋዎች በተዓምራዊ መንገድ (ያለ ጥናት) መናገር ስለጀመሩ ነው።   

ቃሉ በልሳን ስለተናገሩ ሰዎች ምን ይላል?

በልሳን ስለተናገሩ ሰዎች በሐዋርያት ሥራ ላይ ሶስት ቦታዎች ላይ ተፅፏል። (ሐዋ. ሥራ 2፣ 10፣ 19) እነዚህን ታሪኮች መመልከት ስለ ልሳን ጠቃሚ ግንዛቤ ይሰጠናል።   

“የበዓለ ኀምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር፤ ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው። የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር” (ሐዋ. ሥራ 2:1-4)። 

ወንጌልን ማሰራጨት ቋንቋን በመናገር ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው መንፈስ ቅዱስ በእሳት ምላሶች አምሳያ የተገለጠው። እሳቱ የወንጌልን ኃይል የሚያመላክት ሲሆን ምላሶቹ ደግሞ የንግግር ወይም የቋንቋ ብቃትን ያመላክታሉ።  

ይህ በተከሰተበት በበዓለ ኀምሳ ቀን፤ “ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡና እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይሁድ በኢየሩሳሌም ነበሩ። ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ፤ በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ ‘እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድንበት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው? እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጶዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣ በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብፅ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!’” (ሐዋ. ሥራ 2:5-11)።  

በዓለ ኃምሳ ከፋሲካ በኋላ ኃምሳ ቀናት ተቆጥረው በኃምሳኛው ቀን ላይ የሚከበር ከአይሁዳውያን ሰባት በዓላት መካከል አራተኛው ነው። ይህንን በዓል ለማክበር አይሁዳውያን ከተለያዩ ቦታ ተሰባስበው በነበረበት ጊዜ ነው ደቀመዛሙርት በተሰበሰቡት ሰዎች ቋንቋ ሲናገሩ የነበረው።

ከላይ የተጻፈው ጥቅስ በግልፅ እንደሚናገረው ለበዓሉ የተሰበሰቡት ብዙ ሰዎች ወንጌልን በተወለዱበት ቋንቋ እንደሰሙ ነው። ሐዋርያት የተጠቀሟቸውን ቋንቋዎችም ዘርዝሮልናል። በልሳን የመናገሩም ዋና ዓላማ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ ለማሰማት መሆኑም ይታያል።  

የልሳን ስጦታ የታየበት ሁለተኛ ክስተት ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስ ቤተሰብ ወንጌልን በሰበከበት ጊዜ ነው።  

“ጴጥሮስ ይህን እየተናገረ ሳለ፣ ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። ከጴጥሮስ ጋር የመጡት፣ ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ ተገረሙ፤ ይኸውም በልሳን ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ስለ ሰሟቸው ነው” (ሐዋ. ሥራ 10:44-46)።    

ቆርኔሌዎስ የኢጣሊያ ሰው ነበር (ሐዋ. ሥራ 10:1)። ጴጥሮስ ደግሞ አይሁድ ስለነበር በቋንቋ ላይግባቡ ይችል ነበር። መንፈስ ቅዱስ ሲፈስባቸው ግን አሕዛብ የሆኑት ኢጣሊያውያን እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ አይሁዶቹ ሰሟቸው።  

ይህ የሆነበትን ምክንያት ጴጥሮስ ሲገልፅ እንዲህ ብሏል፤ “መንፈስ ቅዱስ፣ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ በእነርሱም ላይ ወረደ” (ሐዋ. ሥራ 11:15)። በመጀመሪያ መንፈስ ቅዱስ በነጴጥሮስ ላይ በበዓለ ኃምሳ ቀን ሲወርድ በሚስተዋል የሰው ቋንቋዎች ደቀመዛሙርት እንደተናገሩ ተመልክተናል። በነቆርኔሌዎስ የወረደው መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኃምሳ ከወረደው የተለየ ለመሆኑ ምንም የቀረበ መረጃ የለም። አሕዛብ ወደ ክርስትና መምጣታቸውን ለመቀበል ይጠራጠሩ ለነበሩት አይሁዶች ይህንን ክስተት በነቆርኔሌዎስ ላይ ሲወርድ መመስከራቸው ጥርጥራቸው ያቀለለላቸው እንደሆነ እንረዳለን።

በቀጣይ ሐዋርያው ጴጥሮስ የአሕዛብን ጉዳይ አንስቶ ሲናገር “ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም” ብሎ ነበር (ሐዋ. ሥራ 15፡8-9)። የነቆርኔሌዎስና የዘመዶቹም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም።   

ሶስተኛው ልሳንን አስመልክቶ ቃሉ ላይ የምናየው ታሪክ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ከአስራ ሁለት የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ጋር ባደረገው ቆይታ ወቅት የተከሰተ ነው።    

“ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ” (ሐዋ. ሥራ 19:6)።

በኤፌሶን የሆነውም ነገር አዲስ ክስተት አለመሆኑ በቃሉ በግልፅ ተጽፎ እናነባለን። 

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ስለ ልሳን ምን መክሯቸው ነበር?  

የቆሮንቶስ ከተማ በልቅነትና በፍትወት የታወቀች ነበር። ይህ ልቅነት ደግሞ ከተራ ሕይወት አልፎ በባዕድ አምልኮ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ስለነበረው ብዙ የከተማይቱ ዜጎች በርኩሰት ተተብትበው ነበር። በከተማይቱ በስፋት የነበረው ምግባረብልሹነት በአንዳንድ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን አባላትም ሕይወት ላይ ይታይ እንደነበር የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ያሳያል (1 ቆሮ. 5:1-2)።    

የቆሮንቶስ ከተማ ከልዩ ልዩ አገራት የመጡ ሰዎች የሚኖሩባት በርካታ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድባት ታዋቂ የወደብ ከተማ ነበረች። ስለሆነም የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን የቋንቋዎች ወይም የልሳን ስጦታ ያስፈልጋት ነበር። ሆኖም የቆሮንቶስ ሰዎች የተቀበሉትን የልሳን ስጦታ ስርዓት በሌለው መንገድ ይጠቀሙ እንደነበር ጳውሎስ ይናገራል።  

“እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ በመግለጥ ወይም በዕውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ በልሳን ብናገር ምን እጠቅማችኋለሁ? እንደ ዋሽንትና እንደ በገና ያሉ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች እንኳ የድምፃቸው ቃና ልዩነት ከሌለው ዜማቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል? ደግሞም መለከት ትክክል ያልሆነ የጥሪ ድምፅ ካሰማ፣ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ ከአንደበታችሁ ትርጒም ያለው ቃል ካልወጣ፣ የምትናገሩትን ማን ሊያስተውለው ይችላል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ”(1 ቆሮ. 14:6-9)። 

የቆሮንቶስ አማኞች የልሳን ስጦታ ዋና ዓላማ የወንጌልን ደስታ ለሌሎች ማሳወቅ መሆኑን ረስተው ራሳቸውን ብቻ ወደማስደሰት አዘንብለው ነበር። ይህ ግን ትክክል እንዳልሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገራል። ትርጉሙ የማይስተዋል ነገር ማውራት ለነፋስ ከመናገር አይለይም፤ በዚህ መንገድ ተናግሮ ጉባዔውን ከማወክ ዝም ማለት እንደሚሻልም ይመክራል።  

“ነገር ግን በቤተክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፣ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፣ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል” (1 ቆሮ. 14:19)።  

የቆሮንቶስ ሰዎች ከስነሥርዓት ውጪ፣ ሳይጠባበቁ፣ በመንጋጋት ይናገሩ ነበር። ሁሉም ተናጋሪ በሆነበት ጉባዔ ውስጥ ብዙ ትምህርት መቅሰም አይቻልም። ስለሆነም ቅዱስ ጳውሎስ የሚከተለውን፣ ለዘመናችንም ፍቱን የሆነ ምክር ሰጠ። 

“በልሳን የሚናገር ቢኖር፣ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ ሌላው ደግሞ ይተርጒም፤ የሚተረጒም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና፤ ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር” (1 ቆሮ. 14:27-28)።

በአንዳንድ ቤተክርስቲያናት ውስጥ ዛሬ የሚታየው ልሳን 1 ቆሮንቶስ 14 ላይ የተጠቀሰው ነው?

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ እንዲህ ይላል፤ “በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ ምስጢር የሆነውን በመንፈስ ስለ ሚናገር የሚረዳው የለም” (1 ቆሮ. 14፡2)።

በዚህና በሌሎቹም ምክሮቹ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ስለ ልሳን ሲናገር የተጠቀመው ቃል “ግሎሳ” (γλῶσσα) የሚለውን ነው። ይህ ቃል “ቋንቋ” ማለት ስለሆነ፤ አንድ ሰው በመንፈስ ሆኖ ምስጢር ሲናገር የሚረዳው ባይኖርም በቋንቋ እየተናገረ ነው ማለት ነው። ምሥጢር ቢሆንም ግን ልሳኑ በባሕርዩ የሥነቋንቋ፣ የቃላት ትርጉም፣ አጠቃቀምና የሰዋሰው ሕጎችን የሚከተል መግባቢያ ነው እንጂ ከዚያ የተለየ አይደለም።

በኮንጎ አንዲት ሴት “በልሳን” ስትናገር፤ the New York Times Nov. 7, 2006

ቋንቋዎች ሁሉ የሚከተሏቸው መሠረታዊ ሕግጋት አንድ አይነት እንደሆኑ የሥነቋንቋ ተመራማሪዎች ይመሰክራሉ። ሌሎች ቋንቋዎችን ለመማር የሚያስችለው ጥበብ ያለንም፤ የምንናገራቸው ቋንቋዎችና የማንናገራቸው ቋንቋዎች የሚጋሩት የሰዋሰው መሠረት ስላለ ነው። ስለሆነም በስመ “ልሳን” ሌሎች የማይረዷቸውን ጥቂት ቃላት በመደጋገም የጠለቀ ምሥጢራዊ መልዕክት ማስተላለፍ እንደማይቻል አምላክ እንድናገናዝብ የቸረን አእምሮ ሊያስተውል ይገባል። ይህ ከሆነ በየቤተክርስቲያናቱ “ልሳን” እየተባለ የሚሰማው የተጠና የሚመስለው ድግግሞሽ በየትኛው የቋንቋ ህግ ነው መንፈሳዊ ምሥጢር የሚያስተላልፈው? ትርጉም አልባ የማይገባና የማይስተዋል ተደጋጋሚ የቃላት ናዳ በአምልኮ ውስጥ አላስፈላጊ መደናቆር የሚፈጥር አሳዛኝ ክስተት ነው።

“እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው” (1 ቆሮ. 14:33)።

ብዙ ጊዜ ሰዎች በልሳን እንናገራለን የሚሉባቸው ቦታዎች ላይ ሥነ ሥርዓት የለቀቀ መደናገርና ሁከት ይታያል። በሐዋርያት ሥራ ላይ የልሳን ስጦታ በጌታ ክርስቶስ የማያምኑትን ወደ ወንጌል እውነት እንደሳበ ከላይ ተመልክተናል። የዘመኑ ልሳን ግን በማያምኑት ዘንድ ቤተክርስቲያንን ትዝብት ላይ የጣላት ለምንድነው? የሰላም አምላክ ሦስትና አራት እንግዳ ቃላት እየደጋገሙ በሁከት ከሚፈነጩ ግለሰቦች ጋር ኅብረት አለው? የእግዚአብሔር ቤትና አምልኮስ በእንዲህ ዓይነት ሁከት በተቀላቀለበት ሁኔታ መመራት አለበት?

“በልሳን የሚናገር ቢኖር፣ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ ሌላው ደግሞ ይተርጒም፤ የሚተረጒም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና፤ ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር (1 ቆሮ. 14፡27-28)።

ሕጻናት ተራ ጠብቆ መናገር ይከብዳቸዋል፤ ስለዚህ ተራ ጠብቀው እንዲናገሩ ትምህርት እንሰጣቸዋለን። አዋቂዎች ግን በእግዚአብሔር ቤት ተንጋግተው ሲጮሁ መስማትና ማየት ፍጹም ሊስተዋል የሚችል ጉዳይ አይደለም። ጥንት ቤተክርስቲያን የምትታወቀው ለጸሎትና ጽሞና በምትሰጠው ከፍተኛ ዋጋ ነበር። ጳውሎስ “ቢበዛ ሦስት” ሰዎች ብቻ በልሳን እንዲናገሩ የመከረው ለዚህ ነው። የሚተረጉም ከሌለ ደግሞ ዝም ማለት ይሻላል ብሏል። ይህን የተናገረው ቅዱስ ጳውሎስ በድምጽ ማጉያ የሚሰማውን የማያቋርጥ ጉራማይሌ ቢሰማና፤ የጦርነት ብጥብጥ የሚመስለውን ጉባዔያዊ ነውጥ ቢያይ ምን ይል ይሆን?

“በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን” (1 ቆሮ. 14፡26)።

ዛሬ ቤተክርስቲያን የሚያንጽ መዝሙር፣ ትምህርት፣ መግለጥና ልሳን ትፈልጋለች። በኢትዮጵያ ልሳን የሚባለው ሥጦታና ሌሎች መንፈሣዊ ርኩሰቶች በተመሳሳይ ፍጥነት እየተስፋፉ ነው። የሚያንጽ ልሳን ካለ መረን የለቀቀ ግፍ፣ ብልግና፣ ሌብነትና ሥርዓት አልበኝነት ለምን ምድራችንን ወረሱብን? መንፈስ ቅዱስ የቋንቋን ስጦታ አበርክቶ የልብ ንጽህና ስለነፈገን ነው? መቅደም ያለበት ስጦታ የቋንቋ ጥበብ ነው ወይስ ለጌታ የሚታዘዝ ትሁት ልብ?

እግዚአብሔርን እናምናለን ካልን፤ ሁከት በማያውቀው መንፈስ ቅዱስ ምሪት ወደሚያንጽ እውነትና ሕይወት መድረስ አለብን።

ስለዚህ በ1ኛ ቆሮንቶስ 14 ላይ የተጠቀሰው በተመለከተ የሚከተለው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን፤

1ኛ ይህ “ልሳን” ተብሎ የተጠቀሰው በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተጻፈው “ግሎሳ” ወይም የሥነቋንቋ እና የሰዋሰውን ሕግ የተከተለ ቋንቋ ነው፤

2ኛ በጉባዔ መካከል “ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ” ሊናገሩ ይገባቸዋል፤

3ኛ የሚነገረው ልሳን መተርጎም አለበት፤

4ኛ “የሚተረጒም ሰው ከሌለ” ልሳን ተናጋሪው “በጉባዔ መካከል ዝም ይበል”፤

5ኛ ልሳን ይነገራል በሚል ሁከት ሊፈጠር አይገባም፤ እግዚአብሔር የሁከት ሳይሆን የሰላም አምላክ ስለሆነ አምልኮውም እንዲሁ በሰላምና በሥርዓት መካሄድ ይገባዋል። 

ስለ ዘመናችን ልሳን ታሪካዊ አመጣጥ ምን ማለት ይቻላል? 

ባለንበት ዘመን በልሳን እንናገራለን የሚሉ ሰዎች በሚስተዋል ቋንቋ ሲያወሩ አይደመጡም፤ በቆሮንቶስ እንደታየው ሁሉም ሰው ሊባል በሚችል ሁኔታ በአገልግሎት ጊዜ ሳይጠባበቁ፣ ያለ ተራ ሲናገር ይሰማል ። እንዲህ ያለውን ትርጉም ዓልባ ቃላት ድግግሞሽና ጩኸት ከአምላክ የመጣ ስጦታ ነው ብሎ መቀበል ያዳግታል።  

ልክ እንደ ዛሬዎቹ የልሳን ተናጋሪዎች በአምልኮ ፈንጠዝያ ሰክረው በሚያደናግር ቋንቋ የሚያወሩ ሰዎች ጥንትም ነበሩ። ክርስቶስ ከመወለዱ ስድስት መቶ ዓመታት በፊት ሜዲቴራኒያን ዙሪያ ባሉት አገራት በፓርናሱስ ተራራ ሥር ዴልፊ በተባለው አምላክ ስም ለተራ ሰው በማይገባ ቋንቋ ምስጢር ይናገራሉ የሚባልላቸው ካህናት ነበሩ። ይህ አምላክ ከስካር፣ ከሚያነቃቃ ሙዚቃና ከብልግና ጋር ትሥሥር ነበረው።       

በዴልፊ አምልኮ ሥርዓት ላይ አስደሳች ሙዚቃ ከቀረበ በኋላ ሊቀካህኗ በመጠጥና በአምልኮ ስካር ተንቀጥቅጣ፣ ራሷን መቆጣጠር ይከብዳትና “በመንፈስ” መናገር ትጀምራለች። ንግግሯን የሰሙ ካህናት ትርጉሙን በግጥም መልክ ለተሰበሰቡት ሰዎች ያሳውቃሉ። መልዕክቱ ደግሞ አፖሎ ከተባለው አምላክ እንደመጣ ተደርጎ ይቆጠራል። 

እንዲህ ዓይነቱ ከአምልኮ ጋር የተያያዘ ጩኸትና ትርጉም የለሽ ንግግር በብዙ የባዕድ አምልኮ ውስጥ ዛሬም ይታያል። በአፍሪቃዊው የቩዱ አምልኮ ሥርዓትና በአንዳንድ የኢትዮጵያ ልማዳዊ የጥንቆላ ዕምነቶችም ውስጥ በ“መንፈስ” ተይዞ የመጮህ ልማድ እንዳለ ይታወቃል። በተለምዶ ዛር ወረደ፣ ውቃቢው ተነሳ፣ ወዘተ በመባል የሚጠቀሱት ከዚህ ጋር ተያያዥነት አላቸው።

ይህ ዓይነቱ ልምምድ ወደ ፕሮቴስታንት ዕምነት የገባው በሃያኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አካባቢ ነው። ከጀማሪዎቹ ዋና የሚባለው የሎሳንጅለስ ከተማ ነዋሪ የነበረው ዊልያም ሲሞር የተባለ ሰባኪ ነው (Azusa Street Revival)። ክርስቲያን ሁሉ በልሳን መናገር አለበት በሚል እሳቤ የተነሳው ዊሊያም፤ ወንጌል ከሚያዘው የቅድስና ሕይወት ወጣ ያሉ፣ በጥራዝ ነጠቅ ጩኸትና የእንግዳ ቃላት ጋጋታ ሰላም የሚነሱ ጉባዔዎች መብዛት ምክንያት ሆኗል። ይኸው ልምምድ እየተሻሻለና እየረቀቀ በመሄድ አሁን ድረስ የመንፈስ ቅዱስ መገለጫ ተደርጎ በተግባር ሲውል ይስተዋላል።

የወንጌል እውነት አንድ ናት። በሚያደናግር ቋንቋ መጮህና መዝለል፤ ሁከት የማያውቀውንና ሥርዓትን የሚወደውን እግዚአብሔርን አያስከብርም። አምላካችን የስነሥርዓት ጌታ ነው። ባለንበት ዘመን የሚያስፈልገው ራስን ወደመቆጣጠርና ፈተናን ማሸንፍ ወደሚያስችል ፅሞና ውስጥ መግባት ነው። ከሚያስጮኸው መንፈስ ይልቅ ኃጢአትን የማሸነፍ ኃይልና ትህትና የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ይሻለናል። 

ድርባ ፈቃዱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *