“በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፥ የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ … ላክ አለኝ” (ራዕይ 1፡10-11)። “እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ” (አሞጽ 7፡15)። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ” (ዘጸ 9፡1)። “የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦” (ሕዝ 21፡8)። “የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ”(ዳን 10፡9)። “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤” (አሞጽ 7፡1)። እነዚህን የመሳሰሉ አገላለጾች ነቢያት በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት የተገለጠላቸውን መልዕክት እንደመዘገቡልን የሚያስታውሱ ናቸው። በዚህ ክፍል ሦስት ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጻፍ ስላደረገው ስለ መንፈስ ምሪት በጥቂቱ እንነጋገራለን። በቀዳሚዎቹ የክፍል አንድና ሁለት ዝግጅታችን መጽሐፍ ቅዱስ ምንድነው? እንዴት ተጻፈ? ስሙን ከየት አገኘ? መገለጥ ምንድነው? ወዘተ በሚሉ ርዕሶች ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተን ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የመንፈስ ምሪት (Inspiration) አምላክ ለነቢያት ስብዕናቸውንና ማንነታቸውን ሳይጋፋ መለኮታዊ ሥልጣን ያለው ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ያደረገበት ምሥጢራዊ አሠራር ነው። የዚህ አሠራር ሒደት ውጤት መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ምንጭ መሆኑን ሲያስረዳ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእነዚህ መጻሕፍት መልእክት ውስጥ እንደሚገኝ ይጠቁመናል። መንፈስ ቅዱስ ነብዩ የተቀበለውን መልእክት እንዲያስተውልና በታመነ መንገድ ለሌሎች እንዲያስተላልፍ አቅም ይሆነዋል። ሮጀርስ ኩን የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ሲናገሩ በመንፈስ መመራት ማለት “በተለየ መንገድ አንድ ወንድ ወይም ሴት ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን መልእክት ተቀብለው፤ መልዕክቱን ሳያዛቡ፣ በትክክልና በሚያስተማምን መልኩ የማስተላለፍ ሒደት ነው” ይላሉ። እንግዲህ ከዚህ በፊት እንዳጠናነው መገለጥ የሚያተኩረው የመልእክቱ ምንጭና መሰጠት ላይ ሲሆን የመንፈስ ምሪት የሚያተኩረው ደግሞ መልእክቱ እንዴት እንደመጣና አመዘጋገቡ ላይ ነው።
እንግዲህ ዘፍ. 3፡8ን መሠረት በማድረግ ከውድቀት በፊት አዳምና ሔዋን ከፈጣሪያቸው ጋር የተቀራረበ የፊት ለፊት ግንኙነት እንደነበራቸው መረዳት ይቻላል። ሆኖም ኃጢኣት ከሠሩ በኋላ ይህ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው መልካም ግንኙነት መበላሸቱን እንዳወቁ በተሰማቸው ፍርሃት፣ ባደረጉት መደበቅና መሸሸግ በግልጽ ታይቷል። በአዳምና ሔዋን ኃጢያት ምክንያት የሰው ልጆች በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን የፊት ለፊት ግንኙነት በመቋረጡ፤ እግዚአብሔር በተለየ መገለጥ አማካኝነት ለተለዩ ሰዎች በተለየ ጊዜና ቦታ ራሱን በመግለጥ ከእርሱ ጋር የነበረንን የግንኙነት ክፍተት አጥብቦታል።
ስለዚህ ከእግዚአብሔር መልእክት ወይም መገለጥን የሚቀበል ሰው ነብይ ተብሎ ሲታወቅ፤ እርሱም/ሷም እንደማንኛችንም ኃጢአተኛ ሰው ቢሆንም እንኳ የእግዚአብሔር መንፈስ መልእክት ይሰጠዋል። መልዕክቱንም ለሰዎች በንግግር ሲያውጅም ሆነ በጽሑፍ ሲያስተላልፍ የእግዚአብሔር መንፈስ አብሮት ይሠራል። ይህ ዓይነቱ የመንፈስ ቅዱስ አሰራር በእንግሊዝኛ “Inspiration” ሲባል በአማርኛ ትክክለኛ ትርጉሙን መስጠት ቢያስቸግርም በመንፈስ ምሪት መልዕክት ተቀብሎ ማስተላለፍ ብለን ልንጠራው እንችላለን። ነቢያትም የተቀበሉትን መገለጥ በመጻሕፍት ላይ አስፍረው ለትውልድ ሁሉ እንዲተላለፍ አድርገዋል። በመሆኑም ይህ ታላቅና በመንፈስ ምሪት የተወለደው መጽሐፍ፤ በዘመናችን መጽሐፍ ቅዱስ በመባል ይታወቃል።
ቅዱሳት መጽሕፍትን የጻፉት ነብያት ከተለያየ የሕይወት ተሞክሮ የመጡ ናቸው። አንዳንዶቹ እንደ አሞጽ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ፣ እንደ ኤርምያስና ሕዝቅኤል በክህነት የሚያገለግሉ፣ እንደ ዳንኤል በከፍተኛ የመንግሥት ዕርከን ላይ የነበሩ፣ እንደ ጴጥሮስና ዮሐንስ በዓሣ አጥማጅነት የሚተዳደሩ፣ እንደ ኢሳይያስና ሚክያስ ለነብይነት የተጠሩ፣ እንደ ሉቃስ ሐኪም የነበሩና እንደ ማቴዎስ በግብር (ቀረጥ) ሰብሳቢነትና በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ነበሩ።

መጻሕፍቱ የተጻፉበት አገራት በእስራኤል፣ በባቢሎን፣ በግሪክ፣ በጣልያንና በመሳሰሉት የጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ ሲሆን በውስጣቸው የያዙት የሥነጽሑፍ ይዘት ደግሞ እንደ ታሪክ፣ ሕግ፣ ግጥም፣ ምሳሌ (ጥበባዊ አገላለጽ)፣ ወንጌል፣ ደብዳቤ ያሉ ናቸው። ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹ አምስት መጻህፍት (ዘፍጥረት፣ ዘጸዓት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቅ እና ዘዳግም) ሕግ ወይም ኦሪት በሚባለው ሲካተቱ መጽሐፈ ኢዮብ፣ መዝሙራተ ዳዊት፣ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መክብብ እና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በሥነግጥም ስልት የተጻፉ የጥበብ መጻሕፍት ናቸው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚናገሩ ከተለያየ ቦታ የተሰባሰቡ ስነ-ጽሑፎች ውጤት ብቻ ሳይሆን በውስጡ ልዩና አስደናቂ የሆነ፣ የማይጣረስ የዓላማና የሃሳብ አንድነት የሚገኝበት መጽሐፍ ነው። ለዚህም አስገራሚ የሃሳብ አንድነት ምክንያት ሁሉም መጻህፍት ሲጻፉ የመራው አንድ መንፈስ በመሆኑ ነው።
በመንፈስ ምሪት መልዕክት የመቀበል ዓላማ ነብዩ መልእክት ሲቀበልና ሲያውጅ ከስህተት የጸዳ እንዲሆን ማድረግ ነው። ስለዚህ መልዕክትን በመንፈስ ምሪት የመቀበል ዋነኛው ነገር ከእግዚአብሔር የተላከው መልእክት ሳይበረዝና ሳይደለዝ መጠበቁና ለሰዎች መድረሱ ነው። ታዲያ በነብዩ የሚተላለፈው መልእክት መጀመሪያ በእግዚአብሔር ሃሳብ ውስጥ የነበረ መሆኑን ልብ ይሏል።
ይህ የተለየ መገለጥ በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ቅዱሳችን ብሉይና አዲስ በመባል በሁለት ታላላቅ ኪዳኖች ይከፈላል። ብሉይ ኪዳን ከሙሴ ዘመን 1450 ዓዓ (ዓመተ ዓለም) ጀምሮ እስከ 400 ዓዓ ድረስ ተጽፎ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ አዲስ ኪዳን ደግሞ ከ40-100 ዓም ድረስ የተፃፈ ነው። እነዚህ የብሉይና የአዲስ ኪዳን 66 መጻሕፍት ወደ 40 በሚጠጉ ሰዎች የተፃፉ ሲሆኑ ለመፃፍ የወሰዱት አጠቃላይ ጊዜ ወደ 1500 ዓመታት የሚያክል ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክርነት
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ምሪት መጻፉን ራሱ ይመሰክርልናል፤ ይህንንም የሚገልጹ ሁለት ጥቅሶችን አሉ። የመጀመሪያው ጥቅስ እንዲህ ይላል፤ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው” (2ኛ ጢሞ.3፡16-17 አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አ.መ.ት.))። ይህ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው” በማለት የተገለፀው አባባል የግሪኩ “ቲዮፕኒዩስቶስ” የሚለውን ቃል ነው። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ከሁለት የግሪክ ቃላት ውህደት የተፈጠረ ነው። እነርሱም “ቲዮ” እና “ፕኒዩማ” ሲሆኑ ትርጉማቸውም እንደ ቅደም ተከተላቸው “አምላክ” ማለትና “መንፈስ” ወይም “እስትንፋስ” ማለት ነው። ቃላቱ ሲዋሐዱ የሚሰጡት ትርጉም ግን “የእግዚአብሔር እስትንፋስ” ወደ ህልውና ያመጣቸው የሚለውን ስሜት ነው። ይህ ማለት ልክ አዳም በአምላክ እስትንፋስ ወደ ኅልውና እንደመጣና (ዘፍ.2፡7) በተመሳሳይ መልኩ ዳዊት “በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ” (መዝ.33፡6) እንደሚለው ቅዱሳን መጻሕፍትም ወደ ኅልውና የመጡት በእግዚአብሔር እስትንፋስ ነው የሚል ትርጉም ያዘለ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለራሱ የሰጠው ሁለተኛ ምስክርነት በ2ኛ ጴጥ 1፡21 ላይ የሚገኝ ነው። ጥቅሱም እንደዚህ ይላል “ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም” (አ.መ.ት.)። በአማርኛ “ተመርተው” (የ1962 ዓም ትርጉም ደግሞ “ተነድተው”) የሚለው ቃል የግሪኩ “ፌሮሜኖይ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተተረጎመ ነው። በርግጥም “ፌሮ” ማለት መሸከም፣ ማንቀሳቀስ፣ መምራት፣ መንዳት፣ ማምጣት የሚሉ ትርጉሞችን የያዘ ነው። ስለዚህ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ቃሉን “በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው” በማለት በትክክል ተርጉመውታል። ይህ ቃል በሐዋርያት ሥራ 27፡15 ላይ በተመሳሳይ መልኩ ጥቅም ላይ ውሏል። “መርከቢቱ በማዕበሉ ስለተያዘች ወደ ነፋሱ ልትገፋ አልቻለችም፤ ስለዚህ … ለቀን በንፋሱ ተነዳን (ኢፌሮሜታ) …” (አ.መ.ት.) እንግዲህ ንፋሱ መርከቢቱን ወደ ራሱ አቅጣጫ እንደነዳት ሁሉ መንፈስ ቅዱስም “ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች”ን ወይም ነቢያቱን ጽሑፋቸውን በሚጽፉበት ጊዜ ወደራሱ አቅጣጫ መርቷቸዋል። ስለዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት የነብያት በመንፈስ ቅዱስ ተፅዕኖ ሥር መሆን የወለዳቸው ነው። በዚህ መሰረት ጴጥሮስ እንደተናገረው ትንቢት ወይም ቅዱሳን መጻሕፍት ምንጫቸው ሰብዓዊ ሳይሆን መለኮታዊ ነው። ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቆስቋሽነት ወይም ምሪት የጻፏቸው እንጂ ከሰብዓዊ ምንጭ አልተቀዱም።
ስለዚህ በጢሞቴዎስ እና በጴጥሮስ ላይ የተገለጸውን ሃሳብ ስናጠቃለል “ቲዮፕኒዩስቶስ” የሚለው የግሪክ ቃል የእግዚአብሔር እስትንፋስ (መንፈስ) የፈጠራቸው መጻሕፍት መኖራቸውን ሲገልጽ “ፌሮሜኖይ” የሚለው ቃል ደግሞ የመንፈስ ተፅዕኖ (ምሪት) በፀሐፊዎቹ (በነብያቱ) ላይ አርፎ እንደነበር የሚያስረዳ ነው። ይህ ሃሳብ በእንግሊዝኛ “ኢንስፓይሬሽን” ስንለው በአማርኛ “የመንፈስ ምሪት የወለዳቸው” የሚል ትርጉም ብንሰጠው ገጣሚ ይመስለኛል።
ከላይ የተመለከትናቸው ሁለት ጥቅሶች፤ ቅዱሳን መጻሕፍት በመለኮትና ሰብዓዊ ተሳትፎ የተጻፉ መሆናቸውን ቢናገሩም እነዚህ መለኮታዊና ሰብዓዊ ወኪሎች በእንዴት ዓይነት መንገድ ወደ ኅብረት መጥተው መገለጡ እንዲፈጸም እንዳስቻሉ ግን አያስረዱም። በዚህ ምክንያት የስነመለኮት ተመራማሪዎች የተለያየ የኢንስፓይሬሽን ንድፈ ሃሳቦችን (ቲዎሪዎችን) ያቀርባሉ። ሆኖም ግን እነዚህን ንድፈ ሃሳቦች በዝርዝር ለመመልከት ከዚህ ጽሑፍ ዓላማ ውጪ ስለሆነ ወደዚህ ሐሳብ ዳሰሳ ውስጥ አንገባም።
በመጨረሻም በነዚህ ሁለት ጥቅሶች (1ኛ ጢሞ.3፡15 እና 2ኛ ጴጥ.1፡21) ላይ በመመስረት ቢያንስ ወደ ሁለት ዋና ድምዳሜዎች ላይ ለመድረስ እንችላለን። እነርሱም አንደኛው እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ መሆኑን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የላከው መልእክት መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ምንና ማንን ማመን እንዳለብን የሚነግረን፤ በተጨማሪም እንዴት ሕይወታችንን መኖርና መምራት እንዳለብን የሚያሳስበን ታላቁ ሰበር ባለሥልጣን ነው።
ዋቢ መጻሐፍት
Coon, W. Roger. “Inspiration/Revelation: What It Is and How It Works. Part I: The Prophetic Gift in Operation.” The Journal of Adventist Education. Vol 44, No. I October-November, 1981.
Geisler, Norman L. and William E. Nix, A General Introduction to the Bible Revised and Expanded. Chicago, Ill.: Moody Press, 1968.
Reid, George W. ed. Understanding Scripture: An Adventist Approach. Biblical Research Institute, Silver Spring: Review Herald, 2005.
Song, Ho Kyung. Revelation, Inspiration, and Prophetic Guidance. Adventist International Institute of Advanced Studies, n.d.
Wegner, Paul D. The Journey from Texts to Translations. Grand Rapids, Michigan Baker Academic 2004
ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ