ብዙ አገሮች የተመሰረቱበትን ወይም ነፃ የወጡበትን ቀን በታላቅ ድምቀት በየዓመቱ ያከብራሉ። እነዚህ በዓላት ታሪክን የሚዘክሩ፤ ተከታዩ ትውልድ በማንነቱ እንዲኮራና የአሳዳጊ እናት አገሩን ጅማሬ እንዳይረሳ የሚረዱ ናቸው። የአገር ሥርዓት በአብዮት ወይም በሌላ መንገድ ካልተለወጠ በስተቀር ታሪካዊ በዓላት አይቀየሩም።
እንደዚያው የሰውንና የፈጣሪውን ማንነት ለማስታወስ አምላክ ቀድሞ ያዘጋጀው በዓል አለ። ይህ በዓል የአምላክ ድንቅ ሥራና ለሰው ዘር ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚዘክር ነው። በአፀፋው የፈጣሪን ልዩ ጥበብና ርኅራኄ በመጠኑ የተረዳ ሰው በዚህ በዓል የሰማይ አባቱን አያሰበ ምስጋናና ውዳሴ እንዲያቀርብ ፍቅር ግድ ይለዋል።
ጌታ በስድስት ተከታታይ ቀናት ምድርን በማይገለፅ ድንቅ ተፈጥሮ አስውቦ ሲያበቃ ሰውን ሰራው። አዳም መተንፈስ እንደጀመረ ያየው፣ የሰማው፣ የነካው፣ ያሸተተውና የቀመሰው ሁሉ ለፍላጎቶቹ አርኪ፣ ለጤናው ደግሞ በእጅጉ ተስማሚ ነበር። ስለሆነም ረቂቅ ምስጢሮችን ማገናዘብ የሚችለው የአዳም አእምሮ በአምላክ ፍፁም ሥራ ከመገረም ሌላ ምንም ጉድለት አላገኘም። በመሆኑም በፈጣሪ ሥራ ላይ ያለ ምንም ፍርሃትና ጭንቀት ማረፍ ቻለ።
ጌታ ለአዳም የትዳር ጓደኛ አድርጎ የሰጠው አብራው በተፈጥሮ ምርምር የምትደሰት፣ ስነልቦናዊ እኩያው የሆነች፣ ፍቅር መስጠትና መቀበል የምትችልና እጅግ ቆንጆ የሆነችውን ሔዋንን ነበር። ሁለቱም ተፈጥረው ባልና ሚስት የሆኑበት ቀን ስድስተኛው ቀን (ዓርብ) ነበር። በህይወት እና በጋብቻቸው ያሳለፉት የመጀመሪያው ሙሉ ቀን ደግሞ ከዓርብ ቀጥሎ ያለው፣ በቅዱሳት መፅሐፍት ሰባተኛው ቀን ወይም ሰንበት የተባለው ቅዳሜ ነው። “እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና” (ዘፍ 2:2-3)።
ሰባተኛው ቀን ወይም ቅዳሜ የፈጣሪን በጎነትና ግሩም ኃይል ያስታውሰናል። ምድርን የፈጠረው በቃሉ ብቻ ነው። ሰውን ደግሞ አክብሮ በመልኩና በአምሳያው ሠራው። ፍጥረት ሰውን ማዕከል ያደረገ፤ የአምላክ ፍቅርና የፈጠራ ጥበብ ጥምር ኃይል ውጤት ነው።
ምድር ከተፈጠረች በኋላ የተባረከውና የተቀደሰው ሰባተኛ ቀን በሰዎች ቢከበር አምላክ እንደሚደሰት ቃሉ ያስተምራል። “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብር። ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ ሥራህንም ሁሉ አከናውን። ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። … እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንና በውስጡም ያሉትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፤ በሰባተኛው ቀን አርፎአልና። ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም” (ዘፀ 20:8-10፣ 11)።
አሁን የምንኖርባት ምድር እንደ ጥንቱ አታምርም። በሽረሪት ድር ውስጥ የሚሰቃዩ ትንኞችና በረጋ ውሃ ላይ ተራብተው ሕፃናትን በበሽታ የሚያውኩ ተውሳኮች የቀድሞው ውበት ምስክሮች አይደሉም። ዓለማችን በሰማያዊ ዕረፍት ሳይሆን በክፋት ምጥ ተወጥራለች፤ የእርኩሰት ትዕይንቶች መድረክ ሆናለች። በአንድ በኩል ሰው ተራ መብቱን “ለማስከበር” ደም ያፈሳል። በሌላ በኩል ደግሞ ግፈኞች ከድሆች በብዝበዛ ባገኙት ገንዘብ እየሳቁ ዘግናኝ ቅንጦት ውስጥ ይንፈላሰሳሉ። የሰውን ማንነት የሚያዋርዱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ እንከኖች በቀኝና በግራ ጠፍረው ይዘውናል፤ “የተጣመመው ሊቃና አይችልም” (መክ 1:15)። ፍጥረት በመበስበስ ባርነት ውስጥ ነው (ሮሜ 8:21)። ታዲያ በዚህች ጨለማ ምድር ውስጥ የጥንቷን ገነት እያስታወስን ሰንበትን ማክበሩ ምን ጥቅም አለው?
የአምላካችን ኃይል ኃጢአት በጫነብን የባርነት እስራት አይወሰንም። ጌታ ክርስቶስ ሟች ስጋችንን ለብሶ ወደ ምድር የወረደው የርሱን ክብር ለብሰን በሰማይ ለዘላለም እንድንኖር ነው። “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ” (2 ቆሮ 8:9)።
ከዚህ የተነሳ ዘላለማዊ ድኽነት አያሰጋንም፤ አግዚአብሔር ፍቅር ነውና፤ በመልኩ የተፈጠርን ልጆቹ ነንና። የኃይል ሁሉ ኃይል የእግዚአብሔር ስለሆነ የተፈጥሮ ብልሽቶችና ሞት አያሰጉንም፤ ምድርን በቃሉ የሰራው አምላክ መቃብር ውስጥ በሚበሰብሱ አጥንቶች ላይ ስልጣን አለውና። ምንም አይሳነውም። ስለዚህ ቀን ቢከበርለት ያንሰዋል? የመታሰቢያ በዓል ይገባዋል። ቀኑ ደግሞ እርሱ የመረጠው ወይም የለየው (የቀደሰው) መሆን አለበት። ያ ቀን ቅዳሜ ነው።
ቀድሞ ወደታሰበልን ክብር እንድንመለስ ጌታ እጅግ ተሰቃይቷል። ሰው ሆኖ የተንገላታው መጀመሪያ ወደታቀደልን የማዕረግ ቦታ ተመልሰን እንከንና ምድራዊ እንግልት በሌለው የአምላክ ሥራ ላይ እንድናርፍ ብሎ ነው። ያዳነን እንድናርፍ ነው፤ ስለዚህ የሰንበት በዓል የመዳናችን መታሰቢያና ተስፋ ነው።
ፈጣሪ ይህችን ምድር በመለኮታዊ ውበቱ ዳግም ሊያለብሳት ይፈልጋል። ኃጢአት ያጠፋው ዕረፍትና ነፃነት ኢየሱስ ክርስቶስ ባዳናቸው ነፍሳት ወስጥ ዳግም ይነሳል። “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ ‘እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ፤ ደግሞም፣ ‘ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ’ አለ”(ራዕ. 21:5-6)።
ጌታ ምድርን ከክፋት አንጽቶ ዳግም ተፈጥሮን ወደ ቀድሞ የፍቅር ሥርዓት የሚመልስበት ጊዜ ቅርብ ነው። በመሆኑም በዘመናችን ሰንበትን አስበው የሚውሉ የዚህ ተስፋ ተጠባባቂዎች ናቸው። በየሳምንቱ የሚመጣው ቅዳሜ ሰንበት የምድርን አምባገነናዊ ደንቦች ይቃወማል። ሰው የበሽታ ሰለባ ሆኖ በሞት ጥላ መካከል ሲንገዳገድ ሰንበት የሚመጣውን ፈውስ በተስፋ ይጠቁማል። ሰዎች በክፉ ገዢዎች የጭቆና ቀንበር ስር ስብእናቸው ሲገፈፍ ሰንበት ደግሞ የፍጥረት ማዕረጋቸውን አስታውሶ ከአምላክ ጋር የሚወርሱትን ክብር በእምነት ብርሃን ያሳያል።
በዘመናችን የሰንበት በዓል ተረስቷል። በተስፋ ከማረፍ ይልቅ በጭንቀት መንፈራገጥ ብቸኛው ምርጫ መስሎ ይታያል። የአምላክ ልጅ ከመባል የገንዘብ ባሪያ መሆኑን ምድራዊው ሰው ይሻለኛል ብሏል። የማያርፈውም ሰይጣን ሰንበት አላስፈላጊ መሆኑን በማሳመን የቅዳሜን እውነተኛ ታሪክና ትርጉም በማጠልሸት የተፈጠርንበትን ዓላማ ረስተን የሚመጣውን አዲስ ምድር ተስፋ በጥልቀት እንዳናይ አድርጐአል። “እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም” (ዕብ. 10:39)።
ሰንበት የአምላክን ፍቅር በጽኑ የሚያሳይ ለሰው የተሰጠ ድንቅ ስጦታ ነው። “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም” (ማር 2:27) ። የአምላክ የፍቅር ባህሪ ካልተለወጠ በስተቀር የሰንበት ምንነት ከቶውኑ ሊቀየር አይችልም። ከዚህ የተነሳ ጌታ ሰንበት “በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል” ይላል (ዘፀ 31:17)። የሰው ልጅ ይህን ማስተዋልና ማስታወስ የተሳነው ለምን ይሆን?
ታሪካችንን በማስታወስ ተስፋችን ወደሆነው ሰማያዊ ዕረፍት የሚያመላክተን የጌታ ቀን ስለሆነ ከየትኛውም ጊዜ የበለጠ የሰንበት ዕረፍት ዛሬ ያስፈልገናል። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ፍቅር ነው። ይህን አስደማሚ እውነት በየሳምንቱ ቅዳሜ በሚመጣ በዓል ከምድራዊ ስራዎቻችን አርፈን ማስታወሱ እጅግ ይጠቅመናል።
ዛሬውኑ በኃይሉ ተማምነን ያለ ፍርሃትና ጭንቀት እንድንኖር ፈጣሪ ይፈልጋል። ከዓለም ግዴታዎቻችን ዘወር ብለን የሰንበትን በዓል በተለየ የአምልኮ መንፈስ ስንጠብቀው በአምላክ ኃይልና ፍቅር ላይ ያለን ዕምነት ይታያል።
በሰንበት የግል ጉዳዮቻችንን ባናስፈፅም ትልቅ ጉዳት ላይ የምንወድቅ ቢመስለንም፣ ቀኑን ጠብቁ ያለው አምላክ ለጉዳዮቻችን ዕልፍ መፍትሄዎች እንዳሉት አንርሳ። ይልቅ አግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አለማረፍና አለመታዘዝ የሚያመጡብን አዕላፍ የኑሮ መጠላለፎች በጊዜ ብዛት ይባስ ይወሳሰባሉ እንጂ አይፈቱም። ስለዚህ ጊዜያችንን ሰጥተነው የጊዜ ጌታ ቋጠሮአችንን ቢፈታልንና ቢያሳርፈን ይሻላል። በኑሮ ላይ ጌትነቱን እንዲያሳየን እርሱ ባለው መሠረት ማረፉን እንምረጥ።ጌታን በአካል እስክናገኘው ድረስ የግኑኝነታችን ምስክርና መታሰቢያ የሆነውን በዓል በድምቀት መጠበቁ ደስታችን ሊሆን ይገባል። ዝንጉነት ቢፈትነንም የተዘረጋልንን ዘላለማዊ የፍቅር ዕቅድ አጥብቀን እንያዝ። የስጦታ ሁሉ መገኛ የሆነውን የሰንበት ጌታና ቅዱስ በዓሉን አንርሳ።
ድርባ ፈቃዱ