giziew.org

“ታህሳስ 19 ሁለት ጊዜ ተወለድኩ” ናሆም ይትባረክ!

የክርስትና መንገድ ሁሉ አልጋ በአልጋ አለመሆኑንና ጌታ በፀጋውና በጥበቡ እንዴት እንደሚመራን አይቻለሁ
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጅማሬና ዕድገት

ናሆም ይትባረክ እባላለሁ፤ በ1982 ዓም ነው የተወለድኩት። ቤተሰቦቼ ሁለት ሴቶችንና ሦስት ወንዶች እኔን ጨምሮ ያላቸው ሲሆን እድገቴ በአክሱም ከተማ ቀበሌ 05 በተለምዶ “አዳጋ ሐሙስ” እየተባለ የሚጠራ ሰፈር ነው። የመጀመሪያ ትምህርቴን መከታተል ስጀምር የነበረኝ ባህርይ ጥሩ ቢሆንም ግን ከነበሩኝ ጓደኞች የተነሳ በጣም አስቸጋሪ ልጅ ነበርኩኝ። ከበርካታ ጓደኞቼ ጥቂቶቹ መርሃዊ ተስፋይ፣ ከዋኒ ገ/መድህን፣ ናቢ ግዑሽ፣ ሃፍቶም መኩሪያ እና አሕመዳይ መሐመድ ይባላሉ። በጣም ብዙ ጓደኞች ቢኖሩኝም እነኚህ ግን በጣም የምወዳቸውና ብዙ ታሪኬን የሚጋሩኝ ነበሩ።

ከጓደኞቼ ጋር በዚያ የህፃንነትና የወጣትነት ጊዜያችን ከትንሹ መጥፎ ነገር ጀምሮ እስከ አላስፈላጊ ሱስና መጥፎ ተግባራትን ስንፈጽም የነበረ ሲሆን እውነት ለመናገር ሁሉንም ነገር በልበሙሉነት ነበር ስናደርግ የኖርነው። እንደዚህ እያልን አላስፈላጊ ነገሮች በሕይወታችን እያስተናገድን እስከ 8ኛ ክፍል አብረን ኖርን። ከዚያም የሚኒስትሪ (8ኛ ክፍል) ፈተና ለመዘጋጀት ሁለት ሁለት ሆነን ተከፋፍለን ማጥናት ጀመርን። በዚህ ጊዜ እኔና ሃፍቶም አንድ ላይ ሆነን ማጥናት ጀመርን። ያኔ ነበር ከጓደኛዬ ከሃፍቶም ጋር ልዩ ቅርርብ ወይም ትስስር እንዲኖረን ምክንያት የተፈጠረው።

በጓደኝነት ጎዳና

የሃፍቶም ታሪክ እጅግ አስደናቂና የተለየ ሲሆን ያኔ አብረን ስናጠና ነበር ስለ ሕይወቱ፣ አስተዳደጉ እና ፍላጎቶቹ የሚያጫውተኝ የነበረው። በዚያም በልቤ ትልቅ ቦታ እያገኘ ነበር። እናም ልክ እንደ ወንድሜ አየው ስለነበር፤ ከቤተሰቦቼና አዝማዶቼ ጋር እርሱን ለማስተዋወቅ እጥር ነበር። እንደዚያ ሆነን አብረን ስናጠና ብዙ ነገሮቻችን እየተዋሃደ መጣና እግዚአብሔርም ፈቅዶት ሁለታችን ወደ ቀጣዩ የትምህርት ደረጃ ወደ 9ኛ ክፍል አለፍን።

ይሁን እንጂ እንደከዚህ ቀደም አብረን አንድ ክፍል ውስጥ መሆን አልቻልንም፤ እንደውም ይባስ ብሎ እርሱ የጧት ሲሆን እኔ የከሰዓት ክፍለ ጊዜ በመሆን ተለያየን። እንደአለመታደል ሆኖ ሎሎቹ ሦስት ጓደኞቻችን ወደ 9ኛ ክፍል በዚያን ጊዜ ባለማለፋቸው ጓደኝነታችን ቢቀጥልም ነገር ግን በክፍል ደረጃ ልንገናኝ ባለመቻላችን ቀስ በቀስ የመገናኘታችን ሁኔታ እየደበዘዘ መጣ። ይሁን እንጂ እነሱን የምናገኝበት ቦታ ለየንና እዚያ ቦታ ላይ ዘወትር እንገናኝ ነበር። የምንገናኝባቸው ቦታዎች ብዙ ጊዜ ቪዲዮ ቤቶች ሲሆኑ አልፎ አልፎ ደግሞ ጓደኛችን ሃፍቶም በትርፍ ጊዜው የሚሠራበት ፎቶ ቤትም እንገናኝ ነበር።

ለውጥ ሲጀምር

ከዕለታት አንድ ቀን ከቤቴ ወጥቼ ጓደኛዬ ሃፍቶም ወደሚሰራበት ፎቶ ቤት ከሰዓት በኋላ 10፡00 ላይ ሄድኩኝ። እናም ጓደኛዬ ሃፍቶም በታላቅ አግራሞት ሆኖ ነበር የጠበቀኝ። አሁን በቃላት ልገልፀው የማልችለው ፈገግታና መደነቅ በተሞላበት አነጋገር እንደዚህ አለኝ። “ታውቃለህ ናሆማ ትላንት የሄድኩት ቦታ በጣም የሚገርም አስቂኝና አዳዲስ ነገሮች የሞሉበት ቦታ ነበር” አለኝ። እኔም ይሄ ሃፍቶምን ያስደነቀው ነገር ለማወቅና ለማየት ጓጓሁኝ ግን በጣም አስጊና አስፈሪ ነበር ቀጥሎ የነገረኝ። እንዲህ አለኝ “የሄድኩት የሆኑ ሰዎች ጋብዘውኝ ወደ ጴንጤዎች ቤተጸሎት ነበር” አለኝ። እውነት ለመናገር በጣም ነበር የገረመኝና ያስደነገጠኝ። ምክንያቱም በአክሱም ከተማ እድገታችን ከህፃንነታችን ጀምሮ በክርስትና ሥነምግባር የታነጽን በመሆኑ ነው፤ እናም ከዚህ እምነታችን ውጪ ወደ ሌላ መሄድ ሰማያዊ በረከት ብቻ ሳይሆን ምድራዊውን ሕይወታችንንም ጥሩ የማያደርግ መስሎ ነበር የሚሰማኝ።

እናም ጓደኛዬ ስለነበረው ጊዜ ሲነግረኝ ባደረገውና ባያቸው ሁኔታዎች በመገረም ብስቅም ውስጤን ግን ታላቅ ፍርሃት ጨምድዶት ነበረ። ይሁንና በቀጣይ ጊዜ ለመሄድም ቀጠሮ ይዞ ስለ መጣ እኔንም ጭምር ጋበዘኝና እኔም ከነዚያ ፍርሃቶቼ ለመሄድ ወስንሁ። በቦታው በተገኘሁ ጊዜ ያረጋገጥኩት አንድ ነገር ቢኖር በብዙዎች ዘንድ “ጴንጤዎች የማርያምን ስዕል በፀሎት ቤታቸው በር ረግጠው ነው የሚገቡት” ይባል የነበረው አሉባልታ መሆኑን ነው። በወቅቱ በመፅሐፍ ቅዱስ የጥናት ጊዜያቸው ተካፈልን፤ ሌሎችንም ፕሮግራማቸውን እንዲሁ ተመለከትን።

በዕለቱ ለተወሰኑ ጊዜያት ከተካፈልን በኋላ በውስጤ ትልቅ ጥያቄ የፈጠረ አንድ ትዕይንት አየሁኝ፤ አርሱም በልሳን መናገር የሚሉት ነገር ነው። ይህ አዲስ ነገር ነበር የሆነብኝ። እናም በይበልጥ በቤቴ ያለውን መፅሐፍ ቅዱሴን ማጥናት ጀመርኩኝ። ከነበረው ውጫዊ የህዝብ ፍርሃት የተነሳ ደግሜ ወደ ጴንጤዎቹ የፀሎት ቤት ላለመሄድ ወሰንኩ። እናም በልቤ ወደ ማርያም ጽዮን ቤተክርስቲያን ሄጄ ወደ ጴንጤ ቤተ ፀሎት መሔዴንና ዳግመኛ እንደማልሄድ ንስሐ ገባሁ። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት አድርጌው በማላውቀው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩኝ። በዚህ መልኩ ነበር የ9ኛ ክፍል ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ 10ኛ ክፍል የተሸጋገርኩት።

ለውጥ ሲሰርጽ

እንዲህ ከቆየሁኝ በኋላ አሁንም ጓደኛዬ ሃፍቶም ሌሎችን ሰዎችን ተዋወቀ። በዚህ ጊዜ ግን ከእነዚህ ከተዋወቃቸው ሰዎች የጠለቀ ጓደኝነት መስርቶ ነበር። እናም ጊዜው ክረምት ነበር፤ እኔም ከረንቦላ ቤት እየተጫወትኩኝ ጓደኛዬ ሃፍቶም በዚያ ሲያልፍ አገኘኝና አብሬው እንድሄድ ጋበዘኝ። እኔም ብዙ ሳላቅማማ አብሬው ለመሄድ ወሰንኩኝ። በመንገድ እየሄድን ሳለ ስለ አንድ (አድቬንቲስት) ወንድም ብዙ ማውራት ጀመረ። የዚህ ሰው ስም ሐዱሽ ተስፋይ ይባላል። እና ስለ እርሱ ጓደኛዬ ሃፍቶም ብዙ ጥሩ ጥሩ የሆኑ ነገሮችን ተረከልኝ። እኔም ከእንደዚህ ዓይነት ሰው ጋር ለመተዋወቅ ፈለግኩኝና ወደ ቤቱ አብረን ሄድን።

ቤቱ ስንደርስ አሁንም እንዲህ ብዬ ልገልፀው በማልችለው ፈገግታና ደስታ ነበር ሐዱሽ የተቀበለን። እንደ አጋጣሚም ሆኖ ቁርስ በሚበላበት ሰዓት ነበርና የሔድነው አብረነው እንድንበላ ግድ አለን፤ ሁላችንም አብረን በላን። ልክ ወደ ቤቱ ስንገባ የነበረው በደስታ የተሞላ ፈገግታ ስንወጣም ተከተለንና ተሰናብተነው ሄድን። ሆኖም ወደ ቤታችን እንሂድ እንጂ ልባችን ግን ከእርሱ ጋር ቀርቶ ነበር። ወሬው፣ እንክብካቤው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀቱና አሳቢነቱ በተገናኝን ቁጥር ደግመን ከእርሱ ጋር እንድንሆን ይጋብዘን ነበር። እናም አንድ ቀን አብረነው አንድ ወጥ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንድናጠና ጋበዘንና ጓደኛዬ ሃፍቶም እሺ ሲል እኔ ግን እምቢ አልኩኝ፤ ግን ከእነርሱ ጋር መሆን እንደምፈልግ ነገርኳቸው።

ሐዱሽ በዚህ ምንም ተስፋ ሳይቆርጥ ከእኔና ከጓደኞቼ እንዲሁም ከሌሎቹ ጋር መገናኘት ቀጠለና በመጨረሻ ጓደኛዬ ሃፍቶም ለመጠመቅ ወሰነ። እናም ለኔ ነገረኝ እኔም በነገሩ ደስ አለኝ፤ ምክንያቱም በድብቅ እውነትን ያስተምረው እንደ ነበር ተረድቼ ነበርና። እናም ሃፍቶም ከተጠመቀ በኋላ የ10ኛ ክፍል ውጤቴ ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚያስገባኝ ስለ ነበር የነበረኝ ሁሉ ግንኙነት፤ ከሐድሽም ሆነ ከሃፍቶም፤ በመተው ትምህርቴን ማጥናትና በቤቴ መፅሐፍ ቅዱስን በጣም ማንበብ ጀመርኩ። ነገር ግን መፅሐፍ ቅዱስን በግሌ ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ ብዙ ጥያቄ ስለነበረብኝ አልፎ አልፎ ወደ ሐዱሽ እየሄድኩኝ እጠይቀውና መልስ እየሰጠ ያስረዳኝ ነበር። በዚህም ያሉኝን ጥያቄዎቼን በመመለስ ሐዱሽ እጅግ በጣም ነበር የረዳኝ። ይሁን እንጂ አሁንም ሐዱሽ ከእርሱ ጋር መፅሐፍ ቅዱስ እንዳጠናና ጥምቀት እንድወስድ ሲጠይቀኝ ሁሌ አመነታ ነበር።

እንዲህ እያልኩኝ የቴክኒክና ሙያ ትምህርቴን በአክሱም ካጠናከኩኝ በኋላ ወንድም ሐዱሽ የሥነመለኮት (ቲዎሎጂ) ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ኮሌጅ ሲገባ እኔ ደግሞ ዲፕሎማዬን ለመቀጠል ወደ መቀሌ ሄድኩኝ። ግን እነዚያ ከጓደኞቼና ከወንድም ሐዱሽ ጋር የነበሩኝ ግሩም ትዝታዎቼ በልቤ ውስጥ ሁሌም ነበሩ። እናም ወደ መቀሌ አንደሄድኩኝ በመንገድ ላይ በልቤ ከእግዚአብሔር ጋር ቃልኪዳን ገባሁኝ፤ በፀሎት መንፈስ ሆኜ ያልኩትም እንዲህ ነበር፤ “እግዚአብሔር ሆይ! አድቬንቲስት መሆን እፈልጋለሁ፤ እንዴት ከእነርሱ ጋር መገናኘት እንዳለብኝ አላውቅም እርዳኝ …”።

ታህሳስ 19፡ ለውጥ በተግባር

ወደ መቀሌ ከገባሁኝ ከሦስት ወር በኋላ በወርኃ ታህሳስ 15 ማክሰኞ ዕለት ከቀኑ በ4 ሰዓት ላይ እኔ ወደምኖርበት ወደ አክስቴ ቤት ስልክ ተደወለና “ናሆምን ፈልጌ ነበር” ሲል በአማርኛ አክስቴን አዋራት። አክስቴ በተጠራጣሪ መንፈስ እኔን አስጠራችኝና ስልኩን ማነጋገር ጀመርኩ። ደዋዩ የነበረው ሐዱሽ ወደ ኮሌጅ ሲሄድ እርሱን ተክቶ በአክሱም ያገለግለግ የነበረው፤ በተደጋጋሚ በአክሱም ላይ እያለሁ ሲያገኘኝና ያሉኝን ጥያቄዎችም ሆነ የምፈልገውን ሲያደርግልኝ የነበረ አገልጋይ ወንድም በየነ ኦቶሬ ነበር። እናም ወንድም በየነ ከሰላምታ በኋላ እንዲህ አለኝ፤ “ናሆም መጪው ሰንበት የጥምቀት ስነስርዓት ስላለ በመቀሌ የምትጠመቅ ከሆነ ልምጣ ወይ?” አለኝ። እኔም ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ለመጠመቅ ያመነታሁ ብሆንም አሁን ግን በድፍረት በመወሰን “መምጣት ትችላለህ፤ ና!” አልኩት። ይህንን ስል ግን የነበረኝ ፍርሃት ልገልፀው አልችልም፤ ሆኖም በቃላት ደረጃ ቢሆንም ወሰንኩኝ። ከሁሉ የገረመኝ ግን የእኔ ሳይሆን የወንድም በየነ ሁኔታ ነበር። ከነገርኩት እና መጠመቅ እፈልጋለሁ ካልኩት በኋላ ሊያምነኝ አልቻለም ነበር። ደጋግሞ ነበር ስልኩን ከመዝጋቱ በፊት ስለ እርግጠኛነቴ የጠየቀኝ፤ እኔም በሀሳቤ የፀናሁኝ መሆኔን ሲረዳ “እግዚአብሔር ይባርክህ አርብ እመጣለሁ 6፡00 ሰዓት ላይ መናሃሪያ ጠብቀኝ” ብሎ ስልኩን ዘጋው።

በዚህ ጊዜ የነበሩኝን ስሜቶች አሁን በቃላት ለመግለፅ እቸገራለሁ። ሆኖም ከማክሰኞ እስከ ዓርብ የነበረኝ ውስጣዊ ትግል ይህ ነው ብዬ የማልገልፀውና ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ በፍርሃት የተሞላ ነበር። ዓርብ ሲደርስሰ ጠዋት ከክፍል ተመልሼ ምሳ ለመብላት እንደተቀመጥኩኝ ስልክ ጮኸ፤ በታላቅ ፍርሃት ለአክስቴ “ናሆምን ፈልጌ ነው ካለሽ ናሆም ቤት አልገባም” በይልኝ አልኳት። እርሷም የነገርኳትን ብላ ስልኩን ዘጋችው። ሆኖም ስለሁኔታው ጥርጣሬ ገባትና “እነማን ናቸው?” አለችኝ። እኔም “ጓደኞቼ ናቸው” ብዬ ምሳዬን ለመብላት ስሞክር በፍጹም አልቻልኩም። እናም ለአክስቴ “መጣሁ” ብያት ወደ መናሃሪያ በፍጥነት ሄድኩኝ።

እዚያ ስደርስ ወንድሜ በየነ አስፋልቱ መሐል ላይ ምናልባት እንዳንጠፋፋ ወይም እንዳንተላለፍ በሚል ቆሞ ሳየው በዚያ በጠራራ ፀሐይ ልቤ ስብር ነበር ያለው። ወደ እርሱ እየቀረብኩ በውስጤ ግን እንዲህ ብዬ ራሴን ስወቅስ ነበር፤ “ለራሴ ደህንነት እንዲረዳኝ ጠርቼ እርሱ እኔ እንዳልጠፋባት በመሐል አስፋልት ላይ ሆኖ ሲጠብቀኝ፤ እኔ ግን በቤቴ እርሱን ላለማግኘት በስልክ የለም በሉት አስባልኩ፤ ጌታ ሆይ ለኔ መዳን አስቦ ባይሆን ይህ ሰው ዛሬ እዚህ ጠራራ ፀሐይ ምን ሊሰራ ይቆም ነበር? ይቅር በለኝ ይቅር በለኝ” እያልኩ “በየነ!” ብዬ ስጠራው የተሰማው ደስታ እና ፈገግታው ልዩ ነበር። በጣም ደክሞትና ከፀሐዩም የተነሳ ፊቱ አልቦት ነበር።

ቀጥሎም ምሳ አብረን በላንና ወደ ቤተክርስቲያን ሄድን። በወቅቱ የትግራይ ሚሽን ፊልድ ፕሬዚዳንት (መሪ) የነበሩት ፓስተር አብርሃም ተካን አገኘናቸው። እርሳቸውም በመምጣታችን ደስ ብሏቸው ሞቅ ባለ አቀባበል ተቀበሉንና አብረን ከተጫወትን በኋላ እኔ ወደ ቤት ተመለስኩ። ከዚያ ሰዓት ወዲህ ግን የነበረኝ ውስጣዊ ችግር ፀጥ አለ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገንኩ ይቅርም እንዲለኝ እየጠየቅኩ ወደ ቤቴ ደረስኩ። በነጋታው ቅዳሜ ታህሳስ 19 በተወለድኩባት ቀን እንደገና በክርስቶስ ተወለድኩኝ (ተጠመቅኩኝ)። ይህ በሕይወቴ የተከሰተ የሚገርም አጋጣሚ ነበር።

ድህረ አዲስ ልደት

ከዚህ በኋላ በመቀሌ የ7ተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን የቀሩኝን ወራቶች ስገለገልም ሆነ ሳገለግል ከቆየሁኝ በኋላ የኮሌጅ ቆይታዬን አጠናቅቄ ዲፕሎማዬን ይዤ ወደ አክሱም ወላጆቼ ቤት ተመለስኩኝ። ልክ እኔ ወደ አክሱም እንደተመለስኩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ወንድም ሓዱሽ ዳግመኛ ወደ አክሱም እንዲያገለግል ተላከ። በዚያ ለአንድ ሙሉ ዓመት እያገለግን ሳለ ወላጆቼ አድቬንቲስት እንደሆንኩኝ አላወቁም ነበርና እያንዳንዷ እንቅስቃሴዬን በጥንቃቄ ነበር የማደርግ የነበርኩት። ሆኖም እኔ ሕይወት ያለው ለውጥ ያስደስታቸው እንደነበር ከሁኔታቸው ሁልጊዜ እረዳ ነበር። ይሁን እንጂ አድቬንቲስት መሆኔን በታወቀ ጊዜ ከቤት እንድወጣ በመደረጉ አክሱም 7ተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤትክርስቲያን አባል ወደነበረው ወንድም አበበ ከበደ ሳና ቤት በምሽት (3፡30 ይሆናል) ነበር ያመራሁት።  

በዚያን ጊዜ የደረሰብኝ ነገር ሁሉ ገና ከመከሰቱ በፊት እግዚአብሔር አንዳንዶቹን ገና ከመድረሳቸው በፊት በህልም ያሳየኝ ነበር። ያኔ አይገባኝም ነበር እንጂ በወቅቱ ልቤን ሲያዘጋጀው ነበር። በዚህም ጊዜ ነበር በህይወቴ በጣም ቦታ የምሰጣቸው ቤተሰቦቼን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በላይ እንዳላገኛቸው የሆነው። በዚያን ወቅት እናቴና ወንድሞቼ ሲናፍቁኝ እናቴ አስተማሪ ስለነበረች ወደምታስተምርበት ት/ቤት እየሄድኩኝ ከእርሷ ጋር እውል ነበር። ወንድሞቼን ግን የማገኝበት ብዙም ዕድል አልነበረኝም። አልፎ አልፎ ግን በከተማ ሲንቀሳቀሱ አገኛቸውና ደስም ይለኝ ነበር። እህቶቼ ግን ወደ ቤ/ክ ሲወጡ ብቻ እንጂ እነርሱን የማገኝበት ዕድል አልነበረኝም። በዚያን ጊዜ ተመልሶ ወደ አክሱም መጥቶ የነበረው ሓድሽ ወደ ኮሌጅ ዳግም እንዲሄድ ተወሰነና ብቻዬን ቀረሁ።

እኔ ከቤት መባረሬን ያወቁ አንዳንድ አድቬንቲስት መሆኔን የማይወዱ ወገኖች በወቅቱ ሊጎዱኝ ይፈልጉና ባገኙት አጋጣሚም ይዝቱብኝ ነበር። በጣም ከባድ ሁኔታ ውስጥ የነበርኩ ቢሆንም ውስጣዊ ስሜቴን ይዤ ግን ከውጭ ስታይ በፈገግታና ተስፋ በሚሰጡኝ ነገሮች ላይ አተኩር ነበር። በዚያን ጊዜ ምንም የገቢ ምንጭ አልነበረኝም፤ የምበላበት፣ ልብስ የምገዛበትም ሆነ ሌላ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች የማደርግበት ምንም ብር አልነበረኝም። ይሁን እንጂ የአክሱም ቤ/ክ ወንድሞች ወደቤታቸው እየወሰዱ እንደራሳቸው ቤተሰብ ያግዙኝ ነበር። ሁሉም ልብሶቼ ከቤት እንዳይሰጡኝ ስለተከለከልኩኝ የምለብሰው ልብስ አንድ ብቻ ነበር።

ይህን ሁሉ እየሆነብኝ የነበረው ለጌታዬ ነው፤ ይህም ለእርሱ ሲያንሰው ነው! የሚል ሃሳብ በውስጤ ስለነበር መብላት፣ መጠጣት፣ መልበስ በማልችልበት ጊዜ ሁሉ በጸሎትና በጾም ብዙ ጊዜዬን በተራራ እየሄድኩ አሳልፍ ነበር። ከዚያን ጊዜ በኋላ የትግራይ ሚሽን በየወሩ 300 ብር መላክ ጀመሩና በአክሱም ከተማ የተመደበው አገልጋይ ቶማስ ነምቻ ረዳት ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ኮሌጅ ገብቼ ሥነመለኮት (ቲዎሎጂ) ትምህርቴን በዲግሪ ፕሮግራም እንድከታተል ዕድል ተገኘልኝና ወደዚያ አቀናሁ። ከዚያም በ2ዓመት ከ6 ወር ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ መቀሌ አገልጋይ ሆኜ ወንጌልን ለሌሎች ለማድረስ ስመለስ በሚሽኑ አቀባበል ተደርጎልኝ ወደ አድዋ ከተማ ለመሄድ በመንገድ ላይ ሳለሁ ከቤተሰቦቼ ስልክ ተደወለና ወደ ቤት መግባት እንደምችል ተነገረኝ።

አሁን

ወደቤት እንደገባ ስለመፈቀዱ የሰማሁት ዜና ለማመን የሚከብድ ነበር። ግን እውነት ነበርና በቀጥታ አክሱም ሄድኩኝ። ቤተሰቦቼንና ሌሎች የምወዳቸውን ሁሉ በሰላም አገኘኋቸው። በልቤ እግዚአብሔር ያደረገው እየገረመኝ ከእነርሱ ጋር የተወሰነ ጊዜ ከቆየሁ በኋላ ወደ ተመደብኩበት ቦታ በሰላም የሚያስፈልገኝን አድርገውልኝ ሸኙኝ። ከዚያም ወዲህ በነዚያ በተለያየንባቸው ጊዜያት በጣም ናፍቄአቸው ስለነበር በየሳምንቱ እየተመላለስኩኝ አያቸው ነበር።

ከተወሰነ ወራት በኋላ እንደገና አክሱም አገልጋይ ሆኜ ተመደብኩኝና ከቤተሰቦቼ ጋር አብሬ መኖር ጀመርኩ። ከዚያ በኋላ ከሰኔ 24፣ 2005ዓም (ከጁላይ 1 ቀን 2013) ጀምሮ የትግራይ ሚሽን ፕሬዚዳንት እንድሆን ዩኒየን (ዋናው መ/ቤት) በመወሰኑ ሰበካጉባዔውን በመምራት አምላኬን እያገለገለኩኝ እገኛለሁ። ጥር 29፤2008 አግብቼ ከሕይወት አጋሬ ጋር እየኖርኩ ነው።

ውድ ወገኖቼ፤ በዚህች ባሳለፍኩት አጭር ህይወቴ፤ የክርስትና መንገድ ሁሉ አልጋ በአልጋ አለመሆኑንና ጌታ ግን ከተለያዩ እኛን ከሚጎዱ ጎዳናዎች በፀጋውና በጥበቡ አላቆ እንዴት እንደሚመራን አይቻለሁ። ስለዚህ አሁን በልዩ ልዩ ፈተና ያላችሁ ወገኖቼ እግዚአብሔር በጥበቡ እየመራችሁ እና እየሞረዳችሁ ስለሆነ በትዕግስት እርሱን እንድትጠብቁት ልባዊ ምክሬና ፀሎቴ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፤ “እግዚአብሔር፣ ለሚወዱትና እንደ ሃሳቡ ለተጠሩት፤ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን” (ሮሜ 8፡28 ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም በ1993 ዓም ከታተመው የተወሰደ)። እግዚአብሔር ቸርነቱን ያብዛልን።


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *