በኃይለኛ ንፋስ በመታገዝ የወረደ ከባድ ዝናብ (ሃሪኬይን ሃርቪ) በአሜሪካ በቴክሳስና ሉዊዚያና ጠቅላይ ግዛቶች ባደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ ለተጎዱ ጸሎት እንዲደረግ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በፈረሙት ትዕዛዝ መሠረት እሁድ ነሐሴ 28፤ 2009ዓም በመላው አሜሪካ የጸሎት ቀን ሆኖ ውሏል።

አርብ ነሐሴ 26፤2009ዓም በጽ/ቤታቸው በሃይማኖት መሪዎችና የአደጋ ጊዜ ፈጥኖ ደራሾች ታጅበው ፕሬዚዳንታዊውን ሰነድ በፈረሙ ጊዜ “ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት (የጸሎት ቀን) መቼ በተግባር እንደተፈጸመ አላስታውስም፤ ግን (ይህ ያሁኑ) በጣም ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሚሆን” እገምታለሁ ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። ሲቀጥሉም “አገራችን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ችግር በሚደርስብን ጊዜ ሁሉ አሜሪካውያን በጸሎት ስንተባበር ኖረናል” በማለት በአጠቃላይ የአሜሪካ ጠቅላይ ግዛቶች በሚገኙ ቤተ እምነቶች ሁሉም እንደ እምነቱ ነሐሴ 28፤2009ዓም ጸሎት እንዲያደርስ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ከፊርማው ሥነስርዓት በኋላም እዚያው ጽ/ቤታቸው ጸሎት ተደርጓል።
ሃይማኖትና መንግሥት መለያየት አለባቸው፤ ጸሎት በመንግሥት ትዕዛዝ መደረግ የለበትም የሚሉ ወገኖች ይህንን የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ ናቡከደነጾር ሁሉም ሰው የሠልስቱ ደቂቃንን አምላክ ያምልክ በማለት ካወጣው ንጉሣዊ ትዕዛዝ ጋር ያገናኙታል (ዳንኤል 3፡28-30)። የዳንኤል ሦስት ጓደኞች(አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ)ንጉሡ ላቆመው ምስል አንሰግድም በማለታቸው ወደ እቶን ቢጣሉም እግዚአብሔር በተዓምራዊ መንገድ አድኗቸው ነበር።
ተዓምሩን የተመለከተው ናቢከደነጾርም ይህንን ትዕዛዝ አስተላለፈ፤ “ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማናቸውንም (የስድብ)ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቈራረጣሉ፤ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣለሁ።”
“አንባቢው ያስተውል”