የሮም ካቶሊካዊት ቤ/ክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በመጪው ጥር ወር በፔሩ የሚደርጉት “ሐዋሪያዊ ጉዞ” ይፋ ተደረገ፤ ዓላማው “ትብብር ለተስፋ” በሚል መሪ መፈክር እንደሚሆን ተገለጸ፡፡ ሊቀጳጳሱ ለሁለት አብያተ ክርስቲያናት በላኩት መልዕክት ክርስቲያኖች ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው አሳሰቡ።
በ2010ዓም ከጥር 18 – 21 የሮም ካቶሊካዊት ቤ/ክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮ (ፍራንሲስ) በፔሩ የሚደርጉት ጉብኝት ይፋ መደረጉን የቫቲካን ሬዲዮ ነሐሴ 13፤ 2009ዓም በድረገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡ የጉብኝቱ ዋና መፈክር (ዓላማ) “ትብብር ለተስፋ” (“United for Hope” (Unidos por la esperanza) የሚል መሆኑን የገለጸ ሲሆን ከዚሁ ጋር የጉብኝቱን ዓርማ አብሮ ይፋ አድርጓል፡፡ ዓላማው “ታላቅ የተስፋ በዓል በአንድነት መቀበል” እንደሆነ በመጥቀስ በፔሩና በአካባቢው ላሉ አገራት “አዲስ የሚሲዮናዊ መነቃቃት” እንደሚያመጣ አብሮ ተዘግቧል፡፡ እስካሁን እርግጠኛ ለመሆን ባይቻልም በጉብኝቱ ላይ የሌሎች ፕሮቴስታንትና ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናትም በኅብረት እንደሚሳተፉ ተገምቷል።
በተመሳሳይ ዜና ሊቀጳጳስ ፍራንቼስኮ በጣሊያን ለሚገኙት የሥርዓታውያን (ሜቶዲስት) እና የውልድንሶች አብያተክርስቲያናት ሲኖዶች በእጃቸው ጽፈው በላኩት መልዕክት ከምንጊዜውም በላቀ መልኩ ክርስቲያኖች ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ሁለቱ ሲኖዶሶች ከነሐሴ 14 – 19፤ 2009ዓም የሚያካሂዱትን ስብሰባ አስመልክቶ ሊቀጳጳሱ “በኅብረት እንደጋገፍ፤ … ተስፋን ሰንቀን ወደ ሙሉ አንድነት ለመድረስ አብረን መጓዛችን ጠቃሚ ነው፤ … በተለይ በዚህ ክፍፍል፣ መለያየት እና ሁከት በሞላበት ምድር (አንድነት) አስፈላጊ ነገር ነው” ማለታቸውን CatholicPhilly ነሐሴ 15፤ 2009ዓም በድረገጹ ባተመው ዜና ላይ አስፍሮታል።
የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ከመነሳቱ በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በአውሮጳ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይጠፋ በመከላከል ያቆዩና የቅዳሜ ሰንበትነትን ጨምሮ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነታዎች ይጠብቁ የነበሩት ውልድንሶች በሮም ካቶሊክ ቤ/ክ ሊቃነ ጳጳሳት “መናፍቅ” እየተባሉ ተቃጥለዋል፤ ተሰድደዋል፤ ለመከራ ተዳርገዋል። ይህንን ግፍ አስመልክቶ ሊቀጳጳስ ፍራንቼስኮ ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወቃል።
ከዚሁ የኅብረት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ካቶሊካዊ የመንፈስ ቅዱስ ተሃድሶ እንቅስቃሴና ካቶሊካዊ ወንድማማችነት በጥምረት በጠሩት ጉባዔ ላይ የፕሮቴስታንት፣ የወንጌላውያንና የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በተገኙበት ታላቅ የአንድነት ስብሰባ መካሄዱን የቫቲካን ሬዲዮ በሚያዝያ 27፤2009ዓም ዕትሙ ገልጾዋል። ፖፕ ፍራንሲስ ባደረጉት ጥሪ መሠረት ወደ 30ሺህ የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የተገኙበት ይህ ጉባዔ ባለፈው ዓመት የግንቦት ወር የተካሄደ ሲሆን ዋናው ዓላማም በሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ድጋፍ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው ካቶሊካዊ የመንፈስ ቅዱስ ተሃድሶ (Catholic Charismatic Renewal) እንቅስቃሴ የተጀመረበትን 50ኛው ዓመት ምሥረታ ምክንያት በማድረግ ነበር።
የአብያተ ክርስቲያናትንና የሌሎች ሃይማኖቶች ኅብረትን በተመለከተ ሊቀጳጳስ ፍራንቼስኮ የሥልጣን መንበሩን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ አበርትተው የሚሠሩበት ጉዳይ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲስተዋል የቆየ ጉዳይ ነው። ላለፉት እጅግ በርካታ ዓመታት በሮም ካቶሊካዊት ጳጳሳዊ መንበር ላይ የሚቀመጡት ሁሉ በሐዋሪያው ጴጥሮስ ሥልጣን ቤ/ክኗን እንደሚያስተዳድሩ በግልጽ ይናገራሉ። ሟቹ ሊቀጳጳስ ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ ከዚህ በፊት ከምስራቃዊው ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ጋር ስለ አንድነት ሲነጋገሩ፤ አንድነት ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በጴጥሮሳዊ ሥልጣን የካቶሊክ ሊቀጳጳስ የኅብረቱ የበላይ ኃላፊ መሆን እንዳለበት መናገራቸው ይታወሳል። ለዚህም ምክንያታቸው የሮም ሊቃነ ጳጳሳት ከሐዋሪያው ጴጥሮስ ጀምሮ ሲወርድ የመጣ ሥልጣን ባለቤት በመሆናቸው መንበሩም እንደሚገባቸው አስረድተው ማሳመናቸው የሚታወስ ነው።
“አንባቢው ያስተውል”!