giziew.org

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገና ዛፍ ምን ይላል?

Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጥያቄ፤ በኤርምያስ 10፡3-4 ላይ ስናነብ የምናገኘው ክፍል ስለ ገና ዛፍ ይሆን የሚናገረው?

መልስ፤ በቅድሚያ ጥቅሱን እንመልከት፤ እንዲህ ይላል፤ “የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል። በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል።”

በርግጥ አንዳንድ ሰዎች ይህ ጥቅስ የሚናገረው በገና ወቅት አጊጦ ስለሚሠራውና በተለምዶ “የገና ዛፍ” ስለምንለው ነው በማለት እንደ ማስረጃ ጥቅስ ያቀርቡታል። ሆኖም ጉዳዩ ከዚያ ያለፈ እንደሆነ እዚያው ምዕራፉ ላይ እናነባለን።

መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ መከተል የሚገባን ሥርዓት አለ። በቅድሚያ ምዕራፉን በሙሉ ማንበብ፤ ከምዕራፉ በፊትና በኋላ ያሉትን ምዕራፎች ማንበብ፤ ጥቅሱ ወይም ምዕራፉ መቼ፣ ለምንና ለማን እንደተጻፈ መረዳት፤ ከተቻለ ደግሞ ምዕራፉ በተጻፈበት የመጀመሪያ ቋንቋ (ዕብራይስጥ ወይም ግሪክ ወይም አረማይክ) ሌሎች አጋዥ መተርጎሚያዎችን በመጠቀም ማጥናት ነው። ይህ መሠረታዊ መመሪያ ነው እንጂ ከዚህ የበለጡ መከተል የሚገባን ዝርዝር መመሪያዎች አሉ (ወደፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዓምዳችን የሚዳሰስ ይሆናል)። ይህንን መመሪያ ካልተከተልን ማንኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደፈለግን በመተርጎም እኛ አስቀድመን አቋም ለያዝንበት አመለካከት ደጋፊ አድርገን እናቀርበዋለን። ይህ አንድን ጥቅስ የመለጠጥ ወይም ቆርጦ ለፈለግነው አመለካከት የመለጠፍ አካሄድ ሃሰተኛ ትምህርት ውስጥ እንድንወድቅ ወይም ራሳችን የሃሰተኛ ትምህርት ተከታዮችና አስተማሪዎች እንድንሆን ሊያደርግ የሚችል መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

ዛፎችን ማምለክ “ከገና ዛፍ” በፊት የነበረ በጣዖት አምላኪያን ዘንድ ሲተገበር የኖረ ተግባር ቢሆንም ኤርምያስ ምዕራፍ 10 በቅድሚያ የሚያወራው ስለ ባዕድ አምልኮና ስለ እውነተኛው አምልኮ ልዩነት ነው። ባዕድ አምልኮ፤ ዛፍ በመቁረጥና የራስን አምላክ በመሥራት ወይም በብር አንጥረኛ በማሠራት (ቁጥር 9) ወይም በወርቅ አንጥረኛ በማስቀረጽ (ቁጥር 14) የሚከናወን መሆኑን፤ እውነተኛው አምልኮ ግን እውነተኛ፣ ኃያልና ታላቅ የሆነውን እግዚአብሔርን የሁሉም ፈጣሪ የሆነውን ጌታ በማምለክ (ቁ.6-7፤ 10፤ 12-13) የሚፈጸም መሆኑን በንጽጽር የሚያስረዳ ነው። ከዚህ ሌላ ምዕራፉ ጣዖታት በሙሉ የሰው ልጅ የእጅ ሥራ ውጤቶች መሆናቸውን፤ ሰው በራሱ የእጅ ሥራ ውጤት መዳን እንደማይችል ምክንያቱም የሰው ሥራ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የማይችል የሚቃጠል፤ የሚጠፋ መሆኑን የሚያሳይ ነው (ቁ. 11)።

ይህ በኤርምያስ ላይ የቀረበው ሃሳብ በኢሳይያስ 44፡12-28 በሌላ መልኩ ተዘርዝሮ እናነበዋለን። በዚሁ ምዕራፍ ላይ ሰው የራሱን እጅ ሥራ አምላክ ብሎ በማምለክ ከዚያው ከራስ እጅ ሥራ ደኅንነትን ለማግኘት መፈለጉ ከንቱነቱን የሚያሳይ እንደሆነ በአስረጂነት ቀርቧል። ከዚያ በተጻራሪው ግን ኃያሉ አምላክ ጌታ እግዚአብሔር ከምንም መፍጠር የሚችል ምሉዕ በኩለሄ የሆነ አምላክ እንደሆነ፤ ምስጋና፣ ውዳሴ፣ አምልኮና ስግደት ብቻውን የሚገባው አምላክ እርሱ እንደሆነ ለእስራኤላውያን ትምህርት እንዲሆን በማስጠንቀቂያ መልኩ የተጻፈ ሆኖ እናገኘዋለን።

ከላይ ስለ ኤር. 10 የሰጠነው ሃሳብ እንዳለ ሆኖ “የገና ዛፍ” ግን ያስፈልጋል ማለታችን እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። የገና ዛፍ ከጣዖት አምልኮ ወደ ክርስትና የገባ ሥርዓት ነው። በተለይ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዘመን (በ4ኛው ክፍለዘመን) ከጣዖት አምልኮ ወደ ክርስትና የመጡ ሰዎችን ለማስደሰት ሲባል ቤተክርስቲያን በሯን ከፍታ ካስገባቻቸውና “ክርስትና ከተነሱት” በርካታ የጣዖት አምላኪያን ልምምዶች የገና በዓል እንደ አንዱ ሊጠቀስ የሚችል ነው።

(ማሳሰቢያ፤ ይህ እንደ ናሙና በራሳቸውን ያቀረብነው ነው እንጂ ጥያቄው ለዝግጅት ክፍላችን ተልኮልን አይደለም። በቀጣይ ዕትሞች ግን የእናንተን ጥያቄዎች የምናስተናግድ ስለሆነ በአድራሻችን ጥያቄዎቻችሁን እንድትልኩልን ልናሳስብ እንወዳለን።)


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *