giziew.org

“ባልንጀራዬ ማነው?”

ይህንን ለዘመናት ሲጠየቅ የነበረ ጉዳይ ጌታችን ውብ አድርጎ ማንም በቀላሉ ሊረዳው የሚችልና እንደ ሕግ ዐዋቂው ላሉት ደግሞ ጥልቅ ትርጉም ያለውን ተግባራዊ ምሳሌ ሰጠ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የአዳምና ሔዋን የመጀመሪያ ልጆች ቃየንና አቤል ለእግዚአብሔር ስለሚቀርብ መስዋዕት የወሰዱት የራሳቸው ውሳኔና ያንንም ተከትሎ እግዚአብሔር ለመስዋዕታቸው የሰጠው ምላሽ በቃየን ላይ ቁጣን እንዳስከተለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ዘፍጥረት 4፡5)። ቃየንም ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ አልሰማም በማለት ወንድሙን በግፍ ገደለው። ይህንን ይመለከት የነበረው አምላክ ቃየንን “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” በማለት ሲጠይቀው “አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” በማለት ነበር የመለሰው። ወንድም ስለወንድሙ አያገባኝም፤ የኔ ጉዳይ አይደለም አለ።

ቃየን ወንድሙን ገድሎ “አይመለከተኝም” የሚል ምላሽ ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሌሎችም እንዲሁ ስለ ወንድማቸው “እኔን አያገባኝም” ዓይነት ምላሽ በመስጠት ምክንያት ሲሰጡ ኖረዋል። ዘመናት ባለፉ ቁጥር አይሁዳውያንም እግዚአብሔር ካስቀመጠው የህይወት መስመር እየለቀቁ ሲሄዱ “ወንድሜ ማነው?” የሚለውን ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ ከመመለስ ይልቅ ራሳቸውን ከሌሎች የተሻሉ አድርገው በማየት ራስወዳድነትንና ንቀትን እየተመገቡ ኖሩ። ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ያወቀው አምላክ እስራኤላውያን በአገራቸው ለሚገኙ ስደተኞችና እንግዶች ማድረግ ስለሚገባቸው እንክብካቤ መመሪያዎችን ሰጥቷቸው ነበር። “መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብፅ መጻተኛ ነበራችሁና” (ዘጸ. 22፡21)።

ይኸው ሃሳብ በሌሎች ጥቅሶች ላይ ተነግሯል። እግዚአብሔር በልጆቹ መካከል የማያዳላ መሆኑን ለማመላከት ሲል ሰንበትን አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆኑ በቤታቸው የሚገኝ እንግዳ ሁሉ ሥራ ባለመሥራት እንዲያከብር ተናግሮ ነበር፤ “(በሰንበት) … በግቢህ ያለ መጻተኛ (እንግዳ) ምንም ሥራ አትሠሩም” (ዘፀ. 20፡10)። “መጻተኛ በምድራችሁ ላይ አብሮአችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤ አብሮአችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና” (ዘሌ. 19፡33-34)።  

ይህንን ሁሉ ማስጠንቀቂያና ትምህርት ችላ በማለት ከኖሩ በኋላ በተፈጠረ ችግር ከአስራ ሁለቱ ነገዶች ይሁዳና ብንያም “አይሁድ” በመባል በአንድ በኩል፤ ዐሥሩ ደግሞ “ሳምራውያን” በመባል በሌላ ሆነው ለሁለት ተከፈሉ (1 ነገሥት 12)። አይሁድ የተባሉት ራሳቸውን እጅግ ከፍ አድርገው በማየታቸው ሳምራውያንን መጥላት ብቻ ሳይሆን ይንቋቸውና ይጸየፏቸውም ነበር። ሳምራውያንም ከእውነተኛው አምልኮ እየራቁ በመምጣታቸው ምክንያት የአይሁዳውያኑ ንቀት እየጨመረ መጥቶ ሳምራውያኑን የስድብና የውርደት መለኪያ አደረጓቸው።

በሳምራዊያን ላይ አብዛኛው ከሚነገረው ፀያፍ አባባል አንዱ “ሳምራዊ የሚሰጥህ አንዲት ቁራሽ ዳቦ ከአሳማ ሥጋ ይልቅ የረከሰ ነው” የሚል ነበር። አንድ አይሁድ ከሚሳደበው ስድብ ሁሉ የመጨረሻው አንድን ሰው ሳምራዊ ብሎ መጥራት እንደነበርም ይነገራል። ሳምራውያኑም የዋዛ አልነበሩም፤ በአጸፋው እነርሱም የጥቃት ክንዳቸውን ሲሰነዝሩ ኖረዋል። እግዚአብሔር ግን በዚህ መካከል “አይሁዳዊው ወንድምህ፤ ሳምራዊው ወንድምህ ወዴት ነው?” እያለ ሁለቱንም ሲጠይቅ ነበር።

ዘመናት ባለፉ ቁጥር በአይሁዳውያንና በሳምራውያን መካከል ያለው ጥላቻ እየጠነከረ ሄደ። ልክ በዘመናችን በቦስኒያ በሙስሊምና በሰርቦች መካከል፤ ወይም በሰሜን አየርላንድ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች፤ ወይም በአገራችንም ብሔር በሚለው አስተሳሰብ እንደተፈጠረው ዓይነት ጽንፈኛ ወገንተኛነትና ጥላቻ ነበር የአይሁዳውያኑና የሳምራውያኑም የንቀትና የጥላቻ ጥግ። የእነዚህን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ሁለቱም የአብርሃም ዘሮች መሆናቸው፤ ሁለቱም አብርሃምን አባታችን ብለው የሚጠሩ ወንድማማች መሆናቸው ነበር። ግን ለዘመናት “እኔ የወንድሜ ጠባቂ አይደለሁም” በሚል ቃየናዊ ምላሽ አጠገባቸውን ያለውን ወንድማቸውን ክደው “ባልንጀራዬ ማነው?” በማለት በከንቱ ሲጠይቁ ኖሩ።

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት አካባቢ ምድራችን በዚህ ዓይነት የከፋ ጥላቻና ሥር የሰደደ ወገንተኝነት በምትሰቃይበት ጊዜ ነበር መድኃኒዓለም የመጣው። በወቅቱ በእግዚአብሔር ልጆች መካከል የነበረው መናናቅ፣ መከፋፈል፣ የዘር ጥላቻ፣ ክፋት፣ ወዘተ መድረስ የሚችለው ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር። ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ አገልግሎታቸውና እምነታቸው እርስበርሱ እሰከሚቃረን ድረስ ዘረኝነታቸውና ወገንተኝነታቸው መስመር የለቀቀበት ዘመን ነበር። “ባልንጀራዬ ማለት ዘሬ፣ ወገኔ፣ ቋንቋዬን የሚናገር፣ የአካባቢዬ ልጅ፣ መልኩ እኔን የሚመስል፣ …” የሚል የጠነከረ አመለካከት በነበረበት ወቅት ጌታችንና መድኃኒታችን በሉቃስ 10፡25-37 ዘመን የማይሽረው ምሳሌ ተናገረ።

ከምሳሌው በፊት አንድ የሕግ ዐዋቂ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” በማለት ይጠይቀዋል። ጌታም “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነበዋለህ?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ይመልስለታል። ሕግ ዐዋቂ ስለነበር “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” በማለት መለሰ። ኢየሱስም “በትክክል መልሰሃል፤ አንተም እንደዚሁ አድርግ፤ በሕይወት ትኖራለህ” አለው። ሰውየውም ግን “ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” በማለት መድኃኒዓለምን ጠየቀ።

ይህንን ለዘመናት ሲጠየቅ የነበረ ጉዳይ ጌታችን ውብ አድርጎ ማንም በቀላሉ ሊረዳው የሚችልና እንደ ሕግ ዐዋቂው ላሉት ደግሞ ጥልቅ ትርጉም ያለውን ተግባራዊ ምሳሌ ሰጠ። ምሳሌውን ሲያስረዳም፤ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲጓዝ ወንበዴዎች አገኙትና ደበደቡት፣ ዘረፉትና ሊሞት ሲያጣጥር ጥለውት ሄዱ። በዚያ የሚያልፍ አንድ ካህን ሰውየውን አየውና እንዳላየ ሆኖ አለፈ፤ አንድ ሌዋዊም (ዲያቆን ልንለው እንችላለን) እንዲሁ አይቶ እንዳላየ ሆኖ ፊቱን አዙሮ ሄደ። መጨረሻ ላይ ግን አንድ ሳምራዊ አየውና ቀረብ ብሎ ሲመለከተው ሁኔታው አሳዘነው፤ ራራለት። ቁስሉን ጠራርጎና አክሞ በአህያው ጭኖ ወደ እንግዳ ማረፊያ ወሰደው።

እዚያ ተጨማሪ ሕክምና እንዲሁም እንክብካቤ እንዲያገኝ አድርጎ፤ ተመልሶ መጥቶ እንደሚጎበኘውና ቀሪውን ወጪ እንደሚከፍል ቃል ገብቶ ሄደ። ታዲያ ለዚህ ችግር ለደረሰበት ሰው ከሦስቱ ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል በማለት ኢየሱስ የሕግ ዐዋቂውን ሲጠይቅ “የራራለት ነዋ” በማለት መለሰ። ጌታም “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” ብሎ ምላሽ በመስጠት አሰናበተው።

በምሳሌው የተጠቀሰው ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ የሚጓዝ አይሁዳዊ ነበር። ግን ወድቆ ሲሰቃይ የራሱ የሆኑት ወገኖች ካህኑና ሌዋዊው እያዩት አልፈውት ሄዱ። እነዚህ ሁለት የሃይማኖት ሰዎች እግዚአብሔር ራሱ ባቋቋመው ቤተመቅደስ አገልጋዮች ናቸው። ስለዚህ ይመጻደቁበት ለነበረው ወገንተኝነታቸው ሲሉ እንኳን ዕርዳታ ሊሰጡት ሲገባቸው “ቤ/ክ ፕሮግራም አለን” በማለት ችላ ብለው አለፉ። ራሳቸውን “የተከበሩ” ብለው የሚጠሩ ስለነበር “የወንድሜ ጠባቂ አይደለሁም” በማለት አልፈው ሄዱ። በደህናው ጊዜ ሌላውን ለመናቅና ለማንቋሸሽ “ወገኔ” እያሉ የሚመጻደቁበትን በችግር ጊዜ ለመርዳት ፍላጎት የሌላቸው ራስወዳድና ግብዝ መሆናቸውን አስመስክረው አለፉ። ዘረኛነትና ወገንተኛነት የቁርጥ ቀን ሲመጣ “ወገኔ” ሲለው ለነበረው እንኳን መቆም የማይችል በራስወዳድነት ካባ የተሸፈነ ጭፍን አስተሳሰብ መሆኑን በገሃድ መሰከሩ።

በአይሁዳውያንና በሳምራዊያን መካከል ከፍተኛ ጠላትነት ስለነበር በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሳምራዊው ሰውየውን ይረዳዋል የሚል ግምት ማንም አልነበረውም። መልካሙ ሳምራዊ ግን የሰውየው ማንነት ሳይሆን መቸገሩና ዕርዳታ መፈለጉ ስለነበር ያስጨነቀው ቃሉ እንደሚለው ራራለትና ሄዶ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለዚያ አይሁድ አደረገለት። የወንድሙ ሥቃይ ከምድር እየጮኸ “ወንድምህ ወዴት ነው?”ተብሎ ሳይጠየቅ፤ እርሱም “ባልንጀራዬ ማነው?” ብሎ ሳይጠይቅ ምላሽ የሰጠ፤ ክርስቶሳዊ ባህርይ የተላበሰ መልካም ሳምራዊ!

ለእኛስ ባልንጀራችን ማነው? የእምነት ቤታችን አባል? የራሳችን በምንለው ጎሣ ወይም ክልል ውስጥ ያለውን ነው? ወይስ ባልንጀራችን የኔ የምንለውን ቋንቋ ተናጋሪ፤ በመልኩ ከኛ ጋር ተመሳሳይና የቆዳ ቀለሙ እንደኛ የሆነውን ይሆን? ባልንጀራችን ከቤተክርስቲያናችን ወይም ከእምነታችን አንዱ አባል የሆነ ብቻ እንዳይደለ ጌታችን በምሳሌው አሳውቋል። ባልንጀራ ማለት ከዘር፣ ከጎሣ፣ ከቀለም፣ ወይም ከብሔር ፍጹም በላይ ነው። ይህንንም ጌታችን ፈጽሞ በማይረሳና ግልጽ ምሳሌ ተናግሯል። ባልንጀራችን ዕርዳታችንን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ነው፤ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ ባልንጀራችን ነው። ባልንጀራችን ማለት በጠላት የተጎዳና የቆሰለ ማንኛውም ሰው ነው። ባልንጀራችን ማለት ማንኛውም የእግዚአብሔር ንብረት የሆነ ሁሉ ነው። 

ለዚህ የተጎዳ ሰው ባልንጀራው ዘሮቹ፣ ወይም ወገኖቹ፣ ወይም የክልሉ ነዋሪዎች፣ ወይም የብሔሩ አባላት አይደሉም። ጌታችንም ይህንን አስረግጦ ለህግ ዐዋቂው ሲናገር “(ለመሆኑ)፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” በማለት ጠይቆት ነበር። አይሁዳዊው የሕግ ዐዋቂ ግን ገና በብዙ ነገሮች ተጠርንፎ የተያዘ ስለነበር “ሳምራዊው ነው” ብሎ ለመመለስ ለአፉ እንኳን ስለከበደው “የራራለት ነዋ” ብሎ መለሰ።

በእግዚአብሔር ዘንድ ዜግነት፣ ዘር፣ ጎሣ፣ የኅብረተሰብ መደብ፣ ብሔር፣ ጎጥ፣ ምንም ቦታ የላቸውም። እርሱ የሰው ልጅ ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ “የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ”(ሐዋ. 17፡26)። ስለዚህ ሰው ሁሉ የአንድ ቤተሰብ አባል ነው፤ በክርስቶስ ደም በመዳንኑ ደግሞ እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ አንድ ቤተሰብ ሆኗል። በክርስቶስ ዘንድ አይሁዳዊ ወይም ግሪካዊ፣ ባሪያ ወይም ነጻ፣ የዚህ ጎሣ አባል፣ የዚያኛው ቤተሰብ የሚባል የለም። ሁሉም በከበረው ደሙ ወደ እርሱ መቅረብ ይችላሉ (ገላ. 3፡28፤ ኤፌ 2፡13)።

ዘረኛነት፣ ወገንተኛነት ክፉ የኃጢአት በሽታ ነው፤ እንጥላውና ከዚህ እንላቀቅ፤ የምሳሌውን ጥልቅ ትርጉም እናስተውል፤ ዘረኝነትን፣ ወገንተኝነትን፣ ቡድነኝነትን እንጸየፈው፤ ከቤታችን፣ ከት/ቤታችን፣ ከቤ/ክናችን፣ ከአካባቢችን እናስወግድ። “ወንድምህ ወዴት ነው?” ተብለን ሳንጠየቅ በፊት፤ እኛም “ባልንጀራዬ ማነው?” ብለን ሳንጠይቅ “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ” በማለት ለሰብዓዊ ዘር ሁሉ የዘላለሙን ወንጌል በቃልና በሕይወት እንመስክር።

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *