giziew.org

ለምን እንታመማለን?

የሰው ልጅ ከአካል፣ ከአእምሮ፣ ከመንፈስና ከማኅበራዊ በሽታ ፈውስ ያስፈልገዋል
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በርዕሱ ለተነሳው ጥያቄ “በሽተኞች ስለሆንን” የሚል ምላሽ ሊሰጠው ይችላል። ምላሹ ትክክል አይደለም ማለት አይቻልም፤ ግን ጥያቄውን አሟልቶ አይመልስም።ምክንያቱም  “ለምን በሽተኞች  ሆንን?”  የሚል ሌላ ጥያቄ ያስነሳል።

አዳም በፈጣሪው እጅ ተበጅቶ፤ ዕጹብ ድንቅ የሆነ የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስ ብቃት ተጎናጽፎ ህይወት ሲጀምር ከምድር አፈር ቢሰራም “የእግዚአብሔር ልጅ” ነበር (ሉቃስ 3፡38)። የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆኑ ደግሞ ከእርሱ በታች ባሉት ሁሉ ላይ የገዢነት ሥልጣን የተሰጠው የአምላኩ ተወካይ ነበር። ስለ ሰው ልጅ አፈጣጠር መዝሙረ ዳዊት ሲናገር “ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርንና የሞገስን ዘውድ አቀዳጀኸው። በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛህለት” ይላል (መዝሙር 8፡5፣6)።

በዚህ ሁኔታ በክብርና በሞገስ የተፈጠረው ሰው ፍጹም በሽታ የማያውቅ፤ የአካል፣ የአእምሮውና የመንፈሳዊ ክፍሎቹ እንከን በሌለው ፍጽምና የሚሠሩና ለእግዚአብሔር አምልኮና አገልግሎት የዋሉ ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን አፈጣጠር በተመለከተ እግዚአብሔር ራሱ የተናገረውን ሲጠቅስ፤ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንፈጠር” በማለት መናገሩን ይጠቁማል (ዘፍጥረት 1፡26)። ይህ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው ሰው፤ በምድር የአምላኩ ወኪል እንዲሆን ተጨማሪ ኃላፊነትም ነበረው። በዚህ ኃላፊነቱ መሠረት አዳም “በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን” ተሰጠው (ዘፍጥረት 1፡26)። ቀጥሎም እግዚአብሔር እነዚህን ፍጡራን በሙሉ “ለእያንዳንዳቸውም ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ። ስለዚህ አዳም ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው” (ዘፍጥረት 2፡19፣20)።

የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ይህንን ዓይነት ረቂቅና ምጡቅ ችሎታ ያለው ነበር። አስተሳሰቡ እጅግ ጥልቅ፣ አእምሮው መለኮታዊ የሆኑ ነገሮችን በጥንቃቄ ማስተዋል የሚችል፤ አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ችሎታው ወደር የማይገኝለት፤ ፍቅሩ ነቁጥ አልባ ፍጹም፤ ፍላጎቱና ምኞቱ ሁሉ በምክንያት ላይ የተመሠረተ፤ የእግዚአብሔርን አምሳያነት የተሸከመና ለእርሱ በፍቅር የሚታዘዝ ለፈቃዱም የሚገዛ ፍጹም ፍጡር ነበር። ነገርግን በዚሁ አልቀጠለም፤ኃጢአት የሚባል ጣልቃ ገብ በመከሰቱ የሰው ልጅ የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስ ክፍሎች በሙሉ ተመረዙ።

ኃጢአት የሰውን የአፈጣጠር መሠረት አናጋ፤ በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ ሁለንተና ኃጢአት በሚባል በሽታ ተበከለ። የአስተሳሰብ አድማሱ መጥበብ፤ አእምሮው ማደፍ፤ አካሉ መኮሰስ፤ መንፈሱ መርከስ ጀመረ። የሰው ልጅ ስሜቱንና ፍላጎቱን መቆጣጠር የማይችል በምኞት ፈረስ የሚጋልብ ልቅ ሆነ። ለአምላኩ ፈቃድ የማይታዘዝ፤ የራሴ መንገድ ያዋጣኛል የሚል ራስወዳድ ሆነ! ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን፤ አዳምና ሔዋን፤ የተወለደው የመጀመሪያ ልጅ ቃየን ዓመጸኛ፣ ለአምላኩ የማይገዛ፣ ለወንድሙ ግድ የሌለው ከመሆን አልፎ ነፍሰ ገዳይ ሆነ! (ዘፍጥረት 4፡8)።

የሰው ልጅ ቁጥር በምድር ላይ እየበዛ ሲሄድ አስተሳሰቡና አመለካከቱ ያለማቋረጥ ኃጢአትን መፈጸም ብቻ ሆነ። ሁኔታው ያሳዘነው እግዚአብሔር “አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር (ያለማቋረጥ) ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን” ተመልከቶ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ አመጣ (ዘፍጥረት 6፡5፤7፣17)።

ከጥፋት ውሃ መከሰት በፊት ለአንድ ሺህ ዓመታት ያህል መኖር ይችል የነበረው የሰው ልጅ ዕድሜው ወዲያውኑ አጥሮ ከመቶ ትንሽ ፈቅ ያለ ሆነ። አሁን በዘመናችን ደግሞ ከመቶም አንሶ ሰማኒያና ዘጠና ዓመታትን መኖር ዕድሜ ጠገብ አሰኘ። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ያለበትን ሁኔታ ሲገልጽ አያመቻምችም፤ በማያሻማ ቃል እንዲህ ይላል፤ “ራሳችሁ በሙሉ ታሞአል፤ ልባችሁ ሁሉ ታውኮአል። ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጒራችሁ ጤና የላችሁም፤ቍስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤ አልታጠበም፤ አልታሰረም፤ በዘይትም አልለዘበም” (ኢሳይያስ 1፡5፣6)። ይህ የአካል፣ የአእምሮ፣ የመንፈስና የማኅበራዊ በሽታ ፈውስ ያስፈልገዋል።

ኃጢአት ባለመታዘዝ የመጣ እንደመሆኑ በሽታም የኃጢአት ውጤት በመሆን በጠላት ሰይጣን አማካኝነት የሰው ልጆችን ሕይወት የረበሸ ነው። ማውደም፣ ማበላሸት፣ ማርከስ፣ መመረዝ የሰይጣን ነው። ወደነበረበት መመለስ፣ አዲስ ማድረግ፣ መፈወስ፣ መቀደስ ደግሞ የመድኃኒዓለም ነው። ሰውን መስሎ ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ የጌታችንን አስተዳደግ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ” ይላል (ሉቃስ 2፡52)። በአዳም አለመታዘዝ የሰው ልጅ ያጣውን በክርስቶስ የአእምሮ (ጥበብ)፣ የአካል (ቁመት)፣ የመንፈስ (በእግዚአብሔር ፊት) ዕድገት መልሶ አገኘው። በዚህ ብቻ አላበቃም፤ በማኅበራዊም መስክ (በሰው ፊት) በትክክል በማደግ ከቃየን ጀምሮ እርስበርስ ለተፈጠረው አለመግባባትና ጥላቻ ፈውስ ሰጠ። ይህም ለሰው ልጅ የተሰጠው የተናጠል (አካል ወይም የመንፈስ ወይም የአእምሮ) ፈውስ ሳይሆን ሁሉንም ያካተተ ምሉዕ ነው።

አካላችን ሲታመም፣ አእምሯችን ይታመማል፤ አእምሯችን ሲቃወስ መንፈሳችን ይረበሻል፣ ከአምላካችን ጋር ግንኙነት ለማድረግ ያለን ፍላጎት ይበላሻል፤ የመንፈሳችን መረበሽ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ያቃውሳል። እነዚህ እርስበርሳቸው የተሳሰሩና አንዱ ከሌላው ሊነጠል የማይችል ነው። ለአካላችን መታመም በርካታ ምክንያቶችን ብንሰጥም የምንበላው ምግብ፣ የምንጠጣው፣ የምንመለከተው፤ የምንሰማው፤ በአጠቃላይ ወደ አካላችን የምናስገባው ለጤናችን መታወክ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል። ስንታመም የምንወስደው መድኃኒት አስፈላጊ የመሆኑ ያህል የህክምና ዋናው ዓላማ መድኃኒት በመስጠት መፈወስ እንጂ በሽታ እንዳያገኘን መከላከል አይደለም። ስለዚህ ከዘመናዊ ሕክምና ጋር አምላካዊ የፈውስ መንገዶችን መከተል የግድ ይላል። ጠላታችን ግን የምንታመምበትን መንገዶች ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ በአፋችን የሚገባው (ምግብና መጠጥ)፣ በዓይናችን የምንመለከተው፣ በጆሮአችን የምንሰማው ወዘተ ከአካላዊ፣ ከአእምሯዊና ከመንፈሳዊ ህይወታችን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው አድርጎ ያቀርብልናል፤ እኛም አምነን እንቀበለዋለን።    

የእግዚአብሔር ፈውስ የመንፈስ ብቻ አይደለም፤ ሁሉን አቀፍ ነው። መዝሙረ ዳዊት ይህንን ይለናል፤ “ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ የውስጥ ሰውነቴም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ባርኪ። ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ፤ ኀጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፣ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፣ ሕይወትሽን ከጥፋት ጒድጓድ የሚያድን፣ ምሕረትንና ርኅራኄን የሚያቀዳጅሽ፣ ጐልማሳነትሽም እንደ ንስር ይታደስ ዘንድ፣ ምኞትሽን በበጎ ነገር የሚያረካ እርሱ ነው” (መዝሙር 103፡1-5)።

አምልኳችንም ሆነ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ምን መሆን እንዳለበት በተደጋጋሚ ተነግሮናል፤ ይህም የአካል፣ የአእምሮ፣ የመንፈስና የማኅበራዊ እሴቶች ውጤት መሆን አለበት። “አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።… ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” (ማርቆስ 12፡31፣32)። ይህንን በሙላት ተግባራዊ ለማድረግ በአካል፣ በአእምሮ፣ በመንፈስና በማኅበራዊ ክፍሎች መካከል ያለውን ትሥሥር ማወቅና በተግባር ማዋል የመንፈስና የአካል በሽታን ለመፈወስ ብቻ ሳይሆን ለመከላከል ዓይነተኛ መንገድ ነው። “አምላክህን እግዚአብሔርን አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ”(ዘጸ. 23፡25)።

ስለዚህ “ለምን እንታመማለን?” ለሚለው ጥያቄ ኃጢአት አካላችንን፣ አእምሯችንን እና መንፈሳችንን በሽተኛ ስላደረገው ነው የሚለው አግባብነት ያለው ምላሽ ነው። ለመፍትሔው ደግሞ እነዚህን እንደገና ማደስ፣ ወደቀድሞው መመለስ፣ ደዌያችንን መፈወስ፤ እኛን መቀደስ የሚችል አምላክ አለ። ታላቁ ሐኪም መድኃኒዓለም ለማንኛውም ዓይነት በሽታችን ፈውስ ሊሰጠን ዝግጁ ነው። ለበሽታችን ፈውስ የሚሆን መድኃኒት አዞልናል፤ መድኃኒቱና አወሳሰዱ በማቴዎስ 11፡28፣29 ላይ በግልጽ ተቀምጧል። እንዲህ ይላል፤ “እናንት (የአእምሮ፣ የአካልና የመንፈስ በሽተኛ ሆናችሁ) ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። … ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ”።

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *