giziew.org

ግር አለህ እንዴ ስለ ሰንበት?

Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ሰንበት ምንድነው?

የሰንበት ምንነት ለመጀመሪያ ጊዜ በመፅሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ የምናየው በዘፍጥረት ላይ ነው። “እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና” (ዘፍ 2:2-3)።

ቃሉ እንደሚለው አምላክ ሥራውን በስድስት ቀናት አጠናቆ በሰባተኛው ቀን በማረፉ ሰባተኛውን ቀን ባርኮ ለይቶታል (ቀድሶታል)። በዕብራይስጥ ሰንበት የሚለው ስርወቃል ትርጉም ዕረፍት ወይም ማቆም ማለት ነው። ከዚህም የተነሳ 7ኛው ቀን ሰንበት ወይም ዕረፍት የሚደረግበት ሥራ የሚቆምበት ቀን የሚል ስያሜ አግኝቷል።

ሰባተኛው ቀን የትኛው ነው?  

ሰባተኛው ቀን ቅዳሜ ነው። በአይሁዶች ዘንድ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሰንበት ሰባተኛ ቀን ተብሎ ወይም በሳምንቱ ቀናት አጠራር ቅዳሜ ተብሎ ሲከበር ቆይቷል (ዘፍ. 1፡5፣8፣13)። በአማርኛ የቀናት ስሞች የግዕዝ ስርወቃላት በሳምንቱ ውስጥ ያላቸውን ቅደምተከተል የሚጠቁሙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል እሁድ አሀድ ከሚለው የግዕዝ ቃል የመነጨ ሲሆን ትርጉሙም አንድ ማለት ነው። ሰኞ እስከ ዓርብ ያሉትም ቀናት ትርጉም በሳምንቱ ውስጥ ያላቸውን ተራ ይጠቁማሉ። (ሉቃስ 23፡56 እና 24፡1 ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል።)

የሳምንቱ ቀናት ቅደም ተከተል ተቀይሮ ያውቃሉ?

የሰባቱ ቀናት ቅደም ተከተል ተቀይሮ አያውቅም። በተለያዩ ክፍለዓለሞች የሚገኙ የታሪክ መረጃዎች የሚያሳዩት ሳምንቱ የሚጀምረው በእሁድ የሚያበቃው ደግሞ በቅዳሜ መሆኑን ነው። (አብዛኛዎቹ የቀን መቁጠሪያዎች ላይ የምንመለከተው ይህንኑ ነው)

በተጨማሪ ክርስቶስ በምድር ሳለ ወደ ምኩራብ ሄዶ በማምለክ ሰንበትን የማክበር ልምድ ነበረው (ሉቃ 4:16)። የሳምንቱ ቀናት ተዛብተው ቢሆን ኖሮ ራሱን የሰንበት ጌታ ብሎ የጠራው ክርስቶስ ያኔውኑ ይናገር ነበር (ማር 2:27))። ክርስቶስ ካረገ በኋላም አይሁዶች በቅዳሜ ሰንበት በምኩራቦቻቸው ያለማቋረጥ መሰብሰቡን እስከ ዛሬ አልተውም።

ሰንበት ለአይሁድ ብቻ የተሰጠ በዓል ነው?

ጌታ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ ብሏል: “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም” (ማር 2:27)። ሰንበት ለአይሁዶች ብቻ ቢሆን ጌታ እንዲህ ባላለ ነበር።

ሰንበት የተፈጠረው ለሰው ነው። ሰንበት ገና ምድር ስትፈጠር አዳም እና ሔዋን ባሉበት የተፈጠረ ቀን ነው (ዘፍ 2:2-3)። ያኔ አይሁድና አሕዛብ የሚባል አልነበረም። የነበረው ሰው ብቻ ነው። በተጨማሪ አራተኛው ትእዛዝ ሰንበት መከበር እንዳለበት ያሳስባል (ዘፀ 20:8-11)። አትግደልና አትስረቅ የሚሉት ትእዛዛት ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም የተሰጡ ናቸው ብለን ካመንን፣ የሰንበትን ትእዛዝ ከአሥርቱ ቃላት ነጥለን ለአይሁድ ብቻ ማድረጉ ፍፁም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰንበት ተሽሯል/ተቀይሯል ይላል?

አይልም፤ ሰንበት በፍጹም አልተሻረም፤ አልተቀየረም። እንዲያውም ክርስቶስ ስለ ከዳግም ምፅዓቱ በፊት ስለሚኖረው ስደት ለደቀመዛሙርቱ ሲናገር የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፤ “እንግዲህ ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ” (ማቴ 24:20)። የክርስቶስ ቃላት የሚጠቁሙት በመጨረሻው ዘመን እንኳን ሰንበትን አክባሪ ክርስቲያኖች በስደት ጊዜም ሰንበት እንደሚያከብሩ ነው።   

እሁድ ሰንበት የሆነው መቼ ነው?

መፅሐፍ ቅዱስ ስለ እሁድ ሰንበትነት የሚናገርበት ቦታ የለም። የክርስቶስ ደቀመዛሙርት እስከ መጨረሻው የቅዳሜ ሰንበት አክባሪዎች ነበሩ (የሐዋ. ሥራ 16:13፣ ራዕ. 1:10)።

ከቅዳሜ ይልቅ እሁድ እንዲከበር ከፍተኛ ተፅዕኖ የነበረው በ321 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.) ሲሆን እሁድ በሰንበትነት እንዲከበር ትዕዛዝ የወጣው በሮም መንግሥት አዋጅ ነበር። አዋጁን ያወጣው ቆስጠንጢኖስ ቄሳር ባዕድ አምልኮውን ትቶ የክርስትናን ኃይማኖት ከተቀበለ በኋላ ነው። በፀሐይ አምልኮ ምክንያት እሁድ (ሳንዴይ – የተከበረው የፀሐይ ቀን) እንዲከበር የፈለገው ደግሞ የባዕድ አምልኮና ክርስትናን ለማዋሃድ ነበር።

ይህን ተከትሎ የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእሁድን ሰንበትነት አጥብቃ ማስተማር ቀጠለች። የሰንበትን ቀን የሮም ቤተክርስቲያን በስልጣኗ እንደቀየረች በማስተማር ይህንን የሚቃወሙትን ሁሉ ከአውሮጳ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በተለያዩ ስልቶች በመዝመት ለብዙ መቶ ዓመታት አሳዳቸዋለች። የሮም ቤተክርስቲያን ለዚህ ተግባሯ ከመፅሐፍ ቅዱስ የሰጠችው ምክንያት እስከ አሁን የለም። ነገርግን ሥልጣን አለኝ ስለምትል የጌታን ቀዳሚት ሰንበት ወደ እሁድ ለመለወጧ በማስረጃ በተደገፈ ሁኔታ በግልፅ ትናገራለች። ቀሪው የእሁድ አክባሪ ሕዝበ ክርስቲያን ግን የሮም ቤ/ክ በሥልጣኗ የቀየረችውን ቀን በአሁኑ ዘመን ሲያከብር “ጌታ ከሞት የተነሳበት ቀን ስለሆነ ነው” የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የሌለው ምክንያት ይሰጣል።

ሰንበትን ለመጠበቅ ምን ላድርግ?

በሰንበት ቀን ማድረግ ያለብንን ነገር አስመልክቶ ቃሉ እንዲህ ይላል፤ “ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ ሥራህንም ሁሉ አከናውን። ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዕለቱ አንተም ሆንህ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህ ወይም ሴት አገልጋይህ፣ ወይም እንስሳትህ፣ ወይም በግቢህ ያለ መጻተኛ ምንም ሥራ አትሠሩም” (ዘፀ. 20:9-10; እንዲሁም ዘፀ. 16፡23 ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል)።

የሰንበት በዓል የሳምንቱን ሥራችንን ተወት አድርገን የፈጣሪን ደግነት በማሰብ በአምልኮ የምናሳልፍበት ቀን ነው። በዓላት ሁሉ ዝግጅት እንደሚጠይቁት ሰንበትም ዝግጅት ያስፈልገዋል። ቀኑ በሥርዓት እንዲከበር የመንፈስ፣ የአካልና የቤት ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ካደረግን አምላክ በባረከው ቀን እንባረካለን። አምላካችን “እባርክሃለሁ” ሲል “አንተ በእኔ ታምነህ ዕረፍ እኔ ሥራውን እሠራለሁ፤ ትንሹን አበዛለሁ፤ ባዶውን እሞላለሁ፤ አትረፈርፋለሁ” ማለቱ እንደሆነ እናስተውል። ስለዚህ የትኛው ይሻላል? ያለዕረፍት መድከምና በጎዶሎ መኖር? ወይስ በአምላክ ተማምኖ በዕረፍት የእርሱን ሙላት መቀበል? ምርጫው የእያንዳንዳችን ነው።

ድርባ ፈቃዱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *