በዓለማችን በሚገኙ በርካታ ሃይማኖቶች ዘንድ ውሃ ከመንጻት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ይውላል። ውሃ ቆሻሻ ያስወግዳል፣ ያነጻል ተብሎ ስለሚታመን ከኃጢአት ለመንጻት የሚፈልግ ሁሉ የውሃ እጥበት ያካሂዳል። በውሃ እጥበት ምክንያት የቀደመው እድፍ ይወገዳል፤ መንፈስ ይታደሳል፤ አዲስ ተስፋ ያንሰራራል።
በተለይ አይሁዶች ከቤተመቅደሱ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ውሃን ለማንጻት በስፋት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። በውሃ አማካኝነት እጅን፣ እግርን እንዲሁም መላ አካልን በመታጠብ የመንጻት ሥርዓት ያከናውኑ ነበር። ካህናት ለቤተመቅደስ አገልግሎት የእጥበት ሥነሥርዓት ሲፈጽሙ ቆይተዋል። በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ፈሳሽ ነገር ከሰውነቱ የሚወጣ ማንኛው ሰው “ርኩስ” ተብሎ ስለሚቆጠር መንጻት እንደሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዘሌዋውያን 15)። ይህ ሰው ከርኩሰቱ ሲነጻም “ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል” (ዘሌ.15፡13)። ሌሎችም በርካታ ከውሃ ጋር የተገናኙ የመንጻት ሥነሥርዓቶች ይካሄዱ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል።
ምንም እንኳን እኛ ባለንበት ዘመን በዚህ ዓይነት ሥነሥርዓታዊ ጉዳዮች የተጠመድን ባንሆንም በውሃ መንጻት ግን መከናወን ከሚገቡ ቀዳሚውን የሚይዝ ነው። በውሃ አማካኝነት ከራሳችን ጀምሮ ቤታችንን እንዲሁም አካባቢያችን ማንጻት እንችላለን። ሆኖም የውሃ እጥረት ባለባቸውም ይሁን በሌለባቸው ቦታዎች ሰዎች የግል ንጽህናቸውን ሲጠብቁ አይታዩም። በተለይ የውሃ ዕጥረት በሌለባቸውና ያደጉ በሚባሉት አገራት ለግል ንጽህና መጓደል ዋንኛው ምክንያት ስንፍና እንደሆነ በተለያዩ ጥናቶች ይጠቀሳል።
የተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሽንትቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጃቸውን የሚታጠቡት አሜሪካውያንና አውሮጳውያን ቁጥር ከፍተኛ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። የውሃና የሳሙና ዕጥረት በሌለባቸው በእነዚህ አገራት በሚገርም ሁኔታ 40በመቶ ያህል ሰዎች ለማንኛውም ጉዳይ ሽንትቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጃቸውን እንደማይታጠቡ ተናግረዋል። አንድ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ የተደረገ ጥናት እንደጠቆመው ግማሽ ያህሉ የኔዘርላንድስ (ሆላንድ) ሰዎች ሽንት ቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጃቸውን እንደማይታጠቡ ተናግረዋል። ጣሊያናውያን፣ ፈረንሳውያን፣ ስፔናውያን ደግሞ 40በመቶ ያህሉ እጃቸውን አይታጠቡም። እስከ 35በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን በዚህ ውስጥ ይካተታሉ።
ይህንን መሰሉ ጥናት ሁሉን አካታችና በትክክል በየአገራቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ ነው ባይባልም በተወሰነ መልኩ ግን አቅጣጫ የሚጠቁም ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል። ውሃውም ሳሙናውም እጅ ማድረቂውም የተሟላ በሚባልባቸው አገራት ይህንን መሰል የንጽህና አጠባበቅ ጉድለት ካለ ጉዳዩ የመሰልጠን ወይም የአቅርቦት መጓደል (ውሃና ሳሙና የማጣት) ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጥ የሚሻ ነው የሚለውን እንድናስብ ያደርገናል። ከግል ንጽህና አጠባበቅ ጋር በተጓዳኝ ስንፍናንም መታገል እንዳለብን እንድናስብ የሚያደርግ ጠቋሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል።
የተለያዩ የጤና ምርምር ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በሽንት ቤት አካባቢ መድኃኒት የመቋቋም ብቃት ያዳበሩ የተለያዩ ባክቴሪያዎች ስለሚገኙ እጃችንን መታጠብ ወሳኝነት ያለው ነገር ነው። በሽንት ቤት የውጪ በር፣ የውስጥ ክፍል በሮች፣ ወዘተ እነዚህ ባክቴሪዎች ስለሚገኙ ሳናውቀው በእጃችን ነክተን በቀጣይ ወደ ውስጣችን እንዲገባ በምናደርገው ምግብም ይሁን መጠጥ ባክቴሪዎቹ በቀላሉ ወደሰውነታችን እንዲተላለፉ ማድረግ እንችላለን።
የተላላፊ በሽታዎችን የሚያጠናው አሜሪካዊው ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በታዳጊ አገራት በያመቱ 3.5 ሚሊዮን ልጆች ህይወታቸውን የሚያጡት በተቅማጥና በመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን መሆኑን ይናገራል። ከዚህ ጋር በተያያዘ እጅን መታጠብ ከእነዚህ በሽታዎች ጋር ያለውን ቁርኝት ለማወቅ ባደረገው ጥናት መሠረት በፓኪስታን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ዘንድ የእጅ መታጠብ ሥርዓትን መከተል ከጀመሩ በኋላ ከላይ በተጠቀሱት ተላላፊ በሽታዎች የመጠቃታቸው ሁኔታ በግማሽ እንደቀነሰ ለመረዳት ተችሏል። ማዕከሉ ጥናቱን ለአንድ ዓመት በሚያካሂድበት ጊዜ ለእነዚህ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ ሳሙና በማቅረብም ረድቷቸዋል። በውጤቱም ትምህርቱ ካልተሰጣቸውና አቅርቦት ካልተደረገላቸው ቤተሰቦች ጋር በንጽጽር ግማሽ ያህሉ በተቅማጥና በመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን ሳይጠቁ ቀርተዋል።
ከጥናቱ የተገኘው መረጃ የሚያሳየው ልጆቻችን በበሽታ ተጠቅተው ለሕክምና በርካታ ገንዘብ ከሚወጣ ይልቅ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረጉ በቀዳሚነት ሊሠራበት የሚገባ ተግባር እንደሆነ ነው። በእርግጥ አገራችንን ጨምሮ በታዳጊ አገራት የሚታየው ትልቅ ችግር የውሃ አቅርቦት ማነስና ሳሙና ለመግዛት ያለው የዓቅም ማነስ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም የመታጠቢያ ቦታ አለመኖር አብሮ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የአቅርቦት ችግር በሌለባቸው አገራትም ያለመታጠብ ችግር ስላለ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ሊሠራ የሚገባ ነገር እንዳለ ይጠቁማል።
ስለዚህ በቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በትምህርት ቤቶች አካባቢ ልጆች ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ እጃቸውን መታጠብ ወሳኝነት ያለው ነገር መሆኑን እንዲማሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን በትጋት ለሚፈጽሙ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ የትምህርት ቤቶቻችን እንዲሁም የትምህርትና የጤና ፖሊሲ አውጪዎች ትኩረት ሊሆን ያስፈልጋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልጆች ይህንኑ ትምህርት ለወላጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው እንዲያስተምሩ በማድረግ የተጽዕኖውን መጠን ማስፋት ይቻላል።
በገጠርና ከከተማ ወጣ ባሉ ቦታዎችም የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ትንሽ የሚባል ባለመሆኑ የውሃ አቅርቦት እጅግ ደካማ በሆነበት አገር ይህንን “ቅንጦት” ሊባል የሚችል ነገር እንዴት ተፈጻሚ ማድረግ ይቻላል የሚል ጥያቄ ቢነሳ አግባብነት አለው። ነገርግን በአገራችን የሚታየው አንዱና ዋንኛ ችግር የትኩረት ቅደም ተከተል መዛባት መሆኑን መረዳት የግድ ይላል። በመንግሥትና በባለሃብት ደረጃ እንደምናየው በብዙ ቦታዎች ህንጻ ለማስዋብ፣ ትልልቅ ፎቅ ለመገንባት፣ የተሳለጡ መንገዶች ለመሥራት፣ ወዘተ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ እጅግ ውድ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት፣ ዋጋቸው ውድ የሆኑ መኪናዎችና ለመንዳትና ልብሶችን ለመግዛት፣ ወዘተ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሲወጣ ይህንን ለመሰለ በርካታዎችን ሊታደግ የሚችል ፕሮጀክት በተመለከተ ግን ትኩረት የሚሠጠው አካል የለም ለማለት በሚያስችል መልኩ ነው ያለው።
ከዚህ በተጨማሪም እጅግ በርካታ ሊባል የሚችለው በውጭም ሆነ አገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ በርካታ ጊዜውን የሚያጠፋው ስፖርት በመከታተል፣ የስፖርተኞችንና “የአርቲስቶችን” የግል ህይወት በማጥናት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ፎቶ በመለጠፍ፣ “ላይክ” እና “ሼር” በማድረግ እንዲሁም የሰዎችን ህይወት የሚታደግ ሳይሆን የሚያጠፋ ፖለቲካ በመከታተል፣ በመነጋገር፣ በመተንተን፣ ወዘተ በመሆኑ ይህንን መሰሉ በቀላሉ ህይወትን የሚያድን ተግባር ቸል ተብሏል፤ ወይም አላስፈላጊ ተደርጎ ተወስዷል። እጅግ ብዙ ሃብት (የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የአስተሳብ) በዚህ ከላይ በጠቀስናቸው አላስፈላጊ ጉዳዮች እየወደመ ነው።
በአገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመመልከት እጅ በመታጠብ በቀላሉ በሽታን ለመከላከል የሚቻልበትን መንገድ የቀየሱና የተገበሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች አሉ። የውሃ አቅርቦት፣ የመታጠቢያ ቦታ መሠረተልማት በሌለባቸው አካባቢዎች፣ እንዲሁም በየቤቱ በቀላሉ ሊተገበር የሚችል የእጅ መታጠቢያ ስልት አበጅተው ተግባራዊ አድርገዋል። ከዚህ ውስጥ አንደኛ ተጠቃሹና በተለያዩ ታዳጊ አገራት እንደሚሠራ የተረጋገጠለት ውሃ ቆጣቢ የእጅ መታጠቢያ ወይም “tippy tap” ነው። ይህ በሥዕሉ ላይ እንደተመለከተው በቀላሉ መሥራትና ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል የእጅ መታጠቢያ ነው። በአንድ ወቅት በቦረና አካባቢ ተሞክሮ አጥጋቢ ውጤት እንዳመጣ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንዲሁም ከዚህ በታች በሚገኘው ምስል ላይ እንደተመለከተው ገላኔ ባዩ ለራሷ ለቤተሰቧ ያዘጋጀችውን ቀላል ውሃ ቆጣቢ የእጅ መታጠቢያ ሌላው ተጠቃሽ ነው። ይህ Growth through Nutrition Learning በሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ድረገጽ ላይ በቀላሉ በፎቶ ተደግፎ የወጣው መረጃ ማንም ሊከተለውና በየትኛውም ቦታ ሊተገበር የሚችል ቀላል ሥልት ነው። ሆኖም ግን የአገራችን ወጣቶች የትኩረት አቅጣጫቸውን ሕዝብንና ትውልድን በሚጠቅም ነገር በማተኮር ቢሠሩበት ከዚህ የተሻሉ በርካታ ሥልቶችን መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ አያጠራጥርም።
አንድ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የሚሰማ አባባል አለ “ንጽህና ከአምላካዊነት (ቅድስና) ቀጥሎ ያለ ነው” ይባላል። እግዚአብሔር አምላካችን ንጽህናን ይወዳል፤ እርሱን የሚያመልኩ ሁሉ ከኃጢአት ርኩሰት ብቻ ሳይሆን ከአካላዊም መቆሸሽ እንዲነጹ ይፈልጋል። እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሁሉ ራሳቸውን ዝቅ ማድረጋቸውን ወይም ትህትናቸውን የሚያሳዩት ንጽህናቸውን ባለመጠበቅ አይደለም፤ መሆንም የለበትም። አላስፈላጊ መብለጭለጭና ውድ ልብሶችንም በመልበስና የውስጥ ዕድፍን በውጪ “ውበት” ለመሸፈን በመሞከርም አይደለም። እርሱ እኛን የሚፈልገን እንዳለን ነው፤ ይህ ሲባል ግን ቆሽሸን፤ ማድረግ የምንችለውን በስንፍና እና በግዴለሽነት ዘንግተን ወደ አምላክ እንቅረብ ማለትም አይደለም። እግዚአብሔር ከኃጢአታችን በልጁ በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም አንጽቶናል። እኛ ደግሞ አካላችንን እንደ አምላክ ፍጡራን በንጽህና መጠበቅ ክርስቲያናዊ ተግባራችን እናድርገው።
“እንግዲህ፣ ወዳጆች ሆይ፤ ይህ የተስፋ ቃል ስላለን፣ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርገው” (2ቆሮ. 7፡1)።
ዘውዱ ሰብለወርቅና ጥበበሥላሴ መንግሥቱ