giziew.org

የሽንት ቤት አሠራርና ንጽህና አጠባበቅ በቀላሉ

ይህንን መፀዳጃ ቤት መገንባት ብዙ ወጪ አያስወጣም፤ ነገርግን ከብዙ በሽታ ሊከላከል ይችላል
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በያዝነው ዓመት ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ Water Aid የተሰኘ ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሠረት 93 በመቶ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ቦታ መሠረታዊ የንጽህና መጠበቂያ እንደሌላቸው ተናግሯል። በሌላ አነጋገር 110 ሚሊዮን ይሆናል ከሚባለው የአገራችን ሕዝብ 100 ሚሊዮን ያህሉ በቂ መጸዳጃ ቤት አገልግሎት አያገኝም ማለት ነው። እንደዘገባው ከሆነ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን በተከታታይ ለሁለት ዓመታት የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል። በአፍሪካ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቻድ፣ ማደጋስካርና ደቡብ ሱዳን ሲሆኑ እነርሱም ከኢትዮጵያ በትንሹ በተሻለ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት፤ ከኢትዮጵያ 93 በመቶ ጋር ሲነጻጸር የእነርሱ 90በመቶ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት 340 ሚሊዮን ህጻናት ተገቢ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ስለማያገኙ በተቅማጥ በመጠቃት ለሞት እንደሚዳረጉ Water Aid ጨምሮ ተናግሯል።

ከዚህ በፊት የዓለም የጤና ድርጅት እኤአ በ2015 ባወጣው መረጃ ከዓለም ሕዝብ 39በመቶው ወይም 2.9 ቢሊዮን የሚሆነው ብቻ ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አገልግሎት እንደሚያገኝ ዘግቦ ነበር። ይህም ማለት የተሻሻለ የመጸዳጃ ቤት፤ አንድ ቤተሰብ ለራሱ ብቻ የሚጠቀምበት ከሌሎች ጋር የማይጋራውና በመጸዳጃው የሚያልፈው ፍሳሽ በተገቢው ሁኔታ የሚወገድ ማለት ነው። ከዚህ አንጻር ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋው የዓለማችን ሕዝብ የሚጠቀምበት ሽንት ቤት ውጋጅ በተገቢው ቦታ (በሴፕቲክ ታንክ) ተጠራቅሞ የሚመጠጥ ሳይሆን በየቦታው ፈስሶ የሚቀር ነው። ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ሕዝብ (1 ቢሊዮን) ደግሞ ሽንት ቤት ብሎ የሚጠቀመው በየሰርጡ፣ በየመንገዱ ዳር፣ በዛፉ ሥር ወይም በውሃው ዳርቻ ነው።

ከዓለም ህዝብ 10በመቶ ለሚሆነው የሚመገበው ምግብ የሚመረተው ደግሞ በመስኖ ነው። ኮሌራ፣ ተቅማጥ (አተት)፣ የወፍ (የጉበት) በሽታ፣ ታይፎድና መሰል ተላላፊ በሽታዎች የሚተላለፉት ንጽህናን በትክክል ባለመጠበቅ ሲሆን በዚህም ምክንያት 1.5ሚሊዮን የሚጠጉ ልጆች ከተቅማጥ ጋር ግንኙነት ባላቸው በሽታዎች ምክንያት ይሞታሉ።

ባለፈው ቁጥር ሁለት ዕትማችን ንፅህና መጠበቅ ከቅድስና ጋር እንዴት የተገናኘ እንደሆነ ተመልክተን ነበር። ይህ አሠራር በተለይ ጥንት እስራኤላውያን ከአምላካቸው ጋር በሚገናኙበት ጊዜ ንፅህናቸውን መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው በዘፀዐት 19፡10-11 ላይ ያለውን ሃሳብ በመውሰድ ዝርዝር ትንተና ተሰጥቶበት ነበር። ንፅህናን መጠበቅ አምላክ አንዱ በእኛ የሚደሰትበትና አስፈላጊ የሆነ ተግባር እንደሆነ ተመልክተናል። የንፅህና ጉዳይ ይህንን ያህል ሕዝብ የሚጨርስና ከመንፈሳዊው አኳያም ትልቅ ቦታ የተሰጠው ከሆነ በዚህኛው ዕትም ርዕሳችን ደግሞ ባለፈው ካነሣነው ሃሣብ ጋር ተያያዥነት ያለው በቀላሉ እንዴት የመፀዳጃ ቤት መሥራት እና ንፅህናውን መጠበቅ እንዳለብን እንመለከታለን።

በውጭ አገር የኢትዮጵያ ምግብ ቤት

እንዳለመታደል ሆኖ በአገራችን የመፀዳጃ ቤት ጉዳይ እንደ ትርፍ (ተጨማሪ) ነገር የሚቆጠር እንጂ እንደ ዋና አስፈላጊ ጉዳይ ሆኖ አይታሰብም። እንዲያውም በገጠር አካባቢ የመፀዳጃ ቤት ማግኘት የሚከብድበት ሁኔታ አለ። በአብዛኛው ጊዜ በጫካ፣ በሜዳ መፀዳዳቱና በቅጠልና መሰል ነገሮች መጠቀሙ የተለመደ ነው። ከዚህም የአኗኗር ዘይቤ የተነሳ ይመስላል በከተማም ስንመጣ በየሆቴሉ፣ በየትምህርት ቤቱ፣ በየመስሪያ ቤቱ ያለው የመጸዳጃ ቤት አያያዝ እጅግ ደካማ፣ ሽታ የበዛበት፣ በሽታ የሚሸመትበት ቦታ የሆነው።

የሚገርመው ነገር ይህ ሽንት ቤትን እንደ ትርፍ የመውሰዱ አስተሳሰብ ተከትሎን ወደ አደጉት ሀገር ስንሄድ እንኳ የለቀቀን አይመስልም። በውጭ አገር ያሉ የኢትጵያውያን ምግብ ቤቶች ከአገርቤት ባልተናነሰ ሁኔታ የንፅህና አጠባበቃቸው ደካማ የሆነ፣ ተገቢው የእጅ ሳሙና፣ እጅ ማድረቂያ፣ ወዘተ ያልተሟላባቸውና አንዳንዶቹም መጥፎ ጠረን ያላቸው ናቸው። ይህ ጉዳይ የፋይናንስን አቅም የሚፈትን በመሆኑ ችላ ለመባሉ እንደ ምክንያት ቢጠቀስም፤ ከገንዘብ አለመኖር ጋር በተጓዳኝ ግን የአስተሳሰብም ችግር እንዳለ አመላካች ነው።

በከተሞች አካባቢ የሚታየውን የመፀዳጃ ችግር ጉዳይ ከገጠሩ ጋር ስናነጻጽረው ከገጠር ይልቅ በከተሞች ውስጥ ብዙ ሰዎች በጠባብ ሥፍራ የሚከማቹ ስለሆነ ችግሩ ይባባሳል። በአማራጭ ደረጃ ግን በከተሞች የተሻሉ የመፀዳጃ ቤቶች እንደሚገኙ እሙን ነው። ሆኖም ግን በከተማችን አዲስ አበባ ብዙ ጊዜ ሰው በጉንፋን እና መሰል በሽታዎች በብዛት የሚሠቃየው ከመፀዳጃ ቤት ንጽህና አጠባበቃችን ጋር በተያያዘ በሚመጣ ችግር ነው። ስለዚህ ጉዳዩን አጥብቀን ልናስብበት የባህርይም ለውጥ ልናመጣበት የሚገባ ነው። ፈጣሪ አምላካችን የምናስብበት እእምሮ የምንሠራበት ጉልበት ሰጥቷል። መንገዱን መከተል ለምንፈልግ በሁሉም የህይወት ክፍላችን ልዩ፣ ንፁህ፣ መልካም እንድንሆን ይፈልግብናል።

መጀመሪያ በገጠር አካባቢ እንዴት በቀላሉ የመፀዳጃ ቤት መሥራት እንደምንችል ሃሣቦችን እናቅርብ። በስዕሉ ላይ እንደሚታየው ጉድጓድ እንቆፍራለን። ጉድጓዱን በእንጨት ርብራብ ወይም ከቻልን በአርማታ አንድ ቀዳዳ በማስቀረት እንዘጋዋለን። ግድግዳውን በጭቃ ወይም በቆርቆሮ መሥራት ይቻላል። ነገርግን ግድግዳውን የምንሠራው በምንቆፍረው ጉድጓድ ልክ ሙሉ በሙሉ እንዲሸፍን ሳይሆን በስዕሉ እንደተመለከተው ወደ ውስጥ ገባ በማለት ነው። የጉድጓዱ የተወሰነ ክፍል ከግድግዳው አልፎ ወደ ውጭ ወጣ ማለት አለበት። ይህም ከጉድጓዱ በስተጀርባ በኩል ንፋስ ማስወጫ መሥራት እንድንችል ነው። በስዕሉ እንደሚታየው ቱቦ ከሽንት ቤቱ ጀርባ በማስገባት ንፋስ ከላይ በቱቦው አማካኝነት ከመፀዳጃ ቤቱ እንዲወጣ ማድረግ አለብን። የምንሠራውን ቱቦ አናቱ ላይ ጥቅጥቅ ባለ ወንፊት እንዘጋዋለን። ይህም የሚደረግበት ምክንያት በቱቦው አናት ከውጭ ሽታ ተከትለው ዝንብና ሌሎች ጥቃቅን ነፍሳት እንዳይገቡ ለመከላከል ነው። እንዲሁም ውስጥ ያሉት ዝንቦች የብርሃን ጭላንጭል በማየት በቱቦው አናት ለመውጣት ከፈለጉ ከወንፊቱ ጋር ተጋጭተው ወደ ጉድጓዱ እንዲወድቁ ስለሚረዳ ነው። በሽንት ቤቱ ውስጥ የምንጠቀምበት የመፀዳጃ ቀዳዳ ሁልጊዜ ክዳን ሊኖረው ይገባል። ይህም ዝንቦቹ ከጉድጓዱ ወደ ሽንትቤቱ ክፍል ውስጥ እንዳይወጡ ይረዳል።

ይህንን መፀዳጃ ቤት መገንባት ብዙ ወጪ አያስወጣም፤ ነገርግን ከብዙ በሽታ ሊከላከል ይችላል። ምናልባትም ከታሰበበት ለሽንትቤት ማሠሪያ ሲሆን ገንዘብ የለም ተብሎ ግን በሽታ ሲመጣ የሚወጣው ወጪ በትክክለኛው ጥቅም ላይ ቢውል ከማሠሪያው በእጅጉ የላቀ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ሽንትቤት በመሥራት የሚወጣው ገንዘብ ጥቅሙ ንፅህና ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ራስን ከአላስፈላጊ በሽታ አስቀድሞ ለመከላከልና በጤና ለመኖር ስለሚረዳም ነው። 

የገጠሩ መፀዳጃ ቤት በራሱ ሁኔታ በንፅህና መያዝ እንዳለበት ሁሉ በከተማ ያለውም እንዲሁ ሁልጊዜ በንፅህና መያዝ አለበት። በከተሞች ውስጥ በአብዛኛው ያለው የመፀዳጃ መጠቀሚያ WC (Water Closet) የሚባለው ወይም ሙሉ ለሙሉ ቁጭ ብለን የምንጠቀምበት ዓይነት ነው። ይህም በውስጡ የተወሰነ ውሃ አጠራቅሞ የሚይዝ s-trap የሚባል ልክ እንደ እንግሊዘኛው ፊደል “ኤስ” የሚመስል ባንቧ አለው። እዚህ ውስጥ የተቋተው ውሃ እንደ ክዳን ወይም እንደ ማፈኛ በመሆን ያገለግላል። ሽታ ማስወጫው (vent pipe) ከሴፕቲክ ታንኩ ጋር ወይም በግድግዳው በኩል በአንዱ ወገን ይሠራል። በs-trap ውስጥ የተቋተው ውሃ ሽታ ወደ ሽንትቤቱ እንዳይመጣ ስለሚከለክል ሽታው በተዘጋጀለት ማስወጫ (vent pipe) ብቻ እንዲወጣ ይገደዳል።

ነገር ግን ከመቀመጫው ጋር የተያያዘውና ከተጠቀምን በኋላ እዳሪውን አጥቦ እንዲወስድ የምንለቀው ውሃ በተለያየ ምክንያት የማይሠራ ከሆነ በs-trap ውስጥ የተቋተው ውሃ ሠገራ ወይም ሽንት ስለሚጠራቀምበት ሽታ ማፈኛ ክዳን መሆኑ ይቀራል። በዚህም ምክንያት የተቋው ውሃ ራሱ ሽታ ፈጣሪ በመሆን የመፀዳጃ ቤቱን ጠረን ይቀይረዋል። ስለዚህ ውሃው ሁልጊዜ ሽታ የሌለው መሆን አለበት። በአብዛኛው ውሃ በሚጠፋበት ጊዜ ሽንትና ሠገራውን አጥቦ እንዲወርድ የሚጠራቀመው ውሃ ስለማይኖር ከውጪ ውሃ በደንብ መድፋት ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ለውሃ ቁጠባ በሚል ጥቂት ውሃ ብቻ በሚደፋበት ጊዜ ሠገራውና ሽንቱ ታጥቦ ከመሄድ ይልቅ በs-trap ውስጥ ተደበላልቆ በመቀመጥ ከፍተኛ ሽታ የሚያመጣ ይሆናል። በተለይ በከተማ ያሉ ቤቶች ውስጥ የመፀዳጃ ቤት ከሌሎቹ ክፍሎች ጋር ተያይዞ የሚሠራ በመሆኑ ሽታው የቤቱን ጠረን የሚያውድና ለበርካታ በሽታ በቀላሉ የሚያጋልጥ ይሆናል። ስለዚህ እዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል። በተለይም መጀመሪያ ላይ በቂ ውሃ ከተደፋ ቀጣይ ተጠቃሚዎች ተመሳሳይ መጠን ያለው ውሃ መድፋት አያስፈልጋቸው ይሆናል። ከተጠራቀመ ግን ያንን ለማስወገድ ብዙ ውሃ ማፍሰስና ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ ይሆናል።

ውሃ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ቦታ እጅ የምንታጠብበትን ውሃ በማጠራቀም ለዚሁ ዓላማ መጠቀም እንችላለን። በግለሰብ ደረጃ የትም ሽንት ቤት ስንጠቀም ውሃ ደፍተንና በተገቢው ሁኔታ አፅድተን ብንወጣ ከዚህ ጋር በተያያዥነት የሚመጡ በርካታ ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንችላለን። ሽንት ቤቱን የሚያስተዳድሩ ሰዎች ደግሞ ሁልጊዜ ውሃ እንዲኖር መከታተል ያስፈልጋቸዋል።

ቁጢጥ ብለን የምንጠቀምበት ዓይነት (Turkish Style) የሚባሉት የሽንትቤት አሠራር ዓይነቶች እንዲሁ ውሃ ማቆሪያ ያላቸው አሉ። ለእነዚህ ዓይነት መፀዳጃ ቤቶች ልክ ከላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት የንጽህና አጠባበቅ ልናደርግላቸው ይገባል። ቁጢጥ ብለን የምንጠቀምባቸውና ውሃ ማቆሪያ የሌላቸው አሉ። ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ልክ እንደማንኛውም የጉድጓድ መፀዳጃቤት ክዳን ልናበጅለት ይገባል። የመቀመጫ አካባቢውን ግን በንጽህና ልንጠብቅ ስለሚያስፈልግ ተጠቅሞ ከጨረሱ በኋላ በቂ ውሃ በማፍሰስ ማጠብ ከጉድጓጉ ቀዳዳ አካባቢ የሚነሳ ሽታንና በአካባቢው ሊገኙ የሚችሉ ዝንቦችን ለመከላከል ይረዳል። ነገርግን ይህ ቁጢጥ ብለን የምንጠቀምበት መፀዳጃ በሌላ በኩል ማስተንፈሻ ወይም አየር ማስወጫ ከሌለው በቀዳዳው ላይ የሚደረገው ክዳን ምን የሚሰጠው ጥቅም አይኖርም። ምክንያቱም ክዳኑ ሲከፈት ጉድጓዱ ውስጥ የተጠራቀመውና ያልተነፈሰው ሽታ ሁሉ ወደ ክፍሉ በቀጥታ ስለሚገባ ነው።

በገጠር የሠራነውን ሽንት ቤት ንፅህናውን ለመጠበቅ፤ ከተጠቀምን በኋላ ሁልጊዜ ክዳኑን መክደን አስፈላጊ ነው። ያለበለዚያ ሽታው እንዲሁም ዝንቦች በቀዳዳው ይወጣሉ። ቆሻሻው (ዓይነምድሩ) ሊያርፍበት የሚችለው አካባቢ ቢቻል በሲሚንቶ ቢለሠን (ሊሾ) ቢሆን ጥሩ ነው። ይህ ከሆነ በቀላሉ ለማፅዳት ይመቻል። ተጠቃሚውም ደግሞ በተቻለ መጠን በቀዳዳው መሃል ምንም ዳርቻ ሣይነካ ቢጠቀም ብዙ ችግሮችን ማቃለል የሚያስችል ይሆናል።

የትም ቦታ ቢሆን መጸዳጃ ቤት ከተጠቀምን በኋላ እጃችንን በሣሙና ከተገኘ በሙቅ ውሃ መታጠብ አለብን። ይህ ከብዙ በሽታ ይጠብቀናል። ባለፈው ዕትም እንደተመለከትነውና እግዚአብሔር እንደነገረን ከተጠቀምን በኋላ አፅድተን መሄድ የክርስትና ኃላፊነታችን መሆኑን አንዘንጋ። “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” (ፊል. 2፡4) ይላል ቃሉ።

“ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ። ከትጥቅህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቈፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት። አምላክህ እግዚአብሔር ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን” (ዘዳ. 23፡12-14)።

ዘውዱ ሰብለወርቅ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *