ከትውልድ አገሩ ወጥቶ ወደ አሜሪካ ከመጣ አራት ዐሥርተ ዓመታት አልፈዋል። አሜሪካ አገር በሕክምና ሙያ ተመርቆ በሐኪምነት ሙያው የሚገባውን ተግባር የሚፈጽም ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባለፈው ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን ከሥራ ሰዓቱ ውጭ ያክማል፤ ይረዳል። በሚኖርበት ካንሳስ ሲቲ “አመመኝ” ብሎ ቤቱ የማይመጣ ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት ይቸግራል። በዘር፣ በጎጥ፣ በሃይማኖት፣ በመንደር፣ ወዘተ ሳይገደብ አምላክ በሙያው የሰጠውን መክሊትና ዕውቀት ያካፍላል። ከዚህም በተጨማሪ ከባለቤቱ ጋር በመሆን በአገር ውስጥና በውጭ የሚካሄዱ የወንጌል አገልግሎቶችን በሚችለው ይደግፋል፤ ዶ/ር ተመስገን ዋቅወያ ይባላል።
ከአንድ ዓመት በፊት በተለምዶ የአንጀት ካንሰር በሚባለው ክፉ በሽታ ተይዞ በአምላክ ኃይልና በወገኖች ጸሎት ከሐኪሞች ዕርዳታ ጋር ተዳምሮ ተፈውሷል። በታመመበት ወቅት እጅግ በርካታዎች በጸሎት አምላክን ሲማጸኑለት ነበር። ከተፈወሰም በኋላ በካንሳስ ሲቲ ዙሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤ/ክ የምስጋና ፕሮግራም ተዘጋጅቶለት አምላኩን፣ ቤተሰቡንና የጸለዩለትን ሁሉ አመስግኗል። ይህ ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተገኙ አማኞች በተሳተፉበት መርሃግብር የእርሱ ምስጋና እና ምስክርነት ብቻ ሳይሆን የተሳታፊዎችም ተሰምቷል።
ሐኪም ተመስገን ዋቅወያ ከባለቤቱ ወ/ሮ ዕጸገነት ፍቅሩ ጋር በመሠረቱት ትዳር ሦስት ልጆች (ካሌብ፣ ኅሊና እና ዮሴፍ) አፍርተዋል። ሁለቱ የአባታቸውን ፈለግ በመከተል በሕክምና ሙያ ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ። ጊዜው መጽሔት የዚህ ዕትም “ይህ ነው ታሪኬ” ዓምድ ሐኪም ተመስገንን እንግዳ አድርጎ አቅርቦታል። ስለፈቃደኝነቱ በቅድሚያ እያመሰገንን “አንተ” ብለን መጥራታችን ከቀረቤታ አኳያ መሆኑን አንባቢያን እንዲረዱልን እንፈልጋለን።
ጊዜው፤ ባለፈው ምስክርነትና ምስጋና በሰጠህበት ጊዜ “ሲዖል (መቃብር) ደጃፍ ደርሼ ነበር የተመለስኩት” ብለህ ነበር፤ ምን ማለት ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ በቀላል አማርኛ ሞቼ ነበር፤ አልቆ ነበር፤ ሕይወቴ ልታልፍ ትንሽ ነበር የቀራት ማለቴ ነበር።
ጊዜው፤ “ትንሽ” ሲባል ምን ያህል ነበር ማለት ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ በሕክምናው አጠራር resuscitate ነው የሚባለው፤ ይህም ኅሊናውን የሳተና ወደ ሞት የሚሄድን ሰው ማንቃት ማለት ነው፤ ለኔ ሦስት ጊዜ ተደርጎልኛል፤ ይህ ሲሆን ምንም አላውቅም፣ አላስታውስም ነበር። ምክንያቱም የማሰብ ችሎታዬ ድራሹ ጠፍቶ ነበር… ።
ጊዜው፤ እንደ ሞተ ሰው ሆነህ ነበር ማለት ይቻላል?
ሐኪም ተመስገን፤ አዎ፤ ሦስት ጊዜ ሞቼ ነበር ማለት ይቻላል።
ጊዜው፤ ሦስት የተለያዩ ጊዜያት ናቸው ወይስ ባንዴ በተከታታይ ነው የሆኑት?
ሐኪም ተመስገን፤ ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ የሆነ ነው፤ ብዙም አይራራቅም፤ ሐኪሞቹ እንደ ሕልም ይታዩኝ ነበር ግን ምንም አላስታውስም፤ ባለቤቴ ዕጸገነትም ልጆቼም አብረውኝ ነበሩ፤ ስለዚህ ሞቼ ነበር ማለት ይቻላል፤ እሱን ነው የሲዖል ደጃፍ ደርሼ ነበር በማለት የተናገርኩት።
ጊዜው፤ ወደ ሕመሙ እንመለስና በተለምዶ የአንጀት ካንሰር ነው የምንለው፤ ግን ሕመሙ ከሕክምና አኳያ ምንድነው የሚባለው?
ሐኪም ተመስገን፤ በእንግሊዝኛው የ“ኮለን ካንሠር” ነው የሚባለው፤ ይህም እንግዲህ የትልቁ አንጀት ካንሠር ሊባል ይችላል፤ አንጀት እንግዲህ ትንሹ አንጀት የምንለው አለ፤ ትልቁ አንጀትም አለ፤ የኔ የትልቁ አንጀት ካንሠር ነበር።
ጊዜው፤ በሽታው እንዴት ነው የሚይዘው? ማለት በዘር የሚተላለፍ ነው? ከአመጋገብ ችግር የሚመጣ ነው? ምንድነው መንስዔው?
ሐኪም ተመስገን፤ (ዘለግ ያለ ሳቅ) እሱን ባውቅማ ኖሮ በጣም ደስ ባለኝና ራሴን እከላከልና እንዳይዘኝ አደርግ ነበር፤ ግን በካንሠር ለመያዝ በአንደኛ ደረጃ ወደ ሰውነታችን የምናስገባው ነገር አስተዋጽዖ አለው፤ ለምሳሌ የሚያጨሱ ሰዎች፤ እኔ ግን ሕይወቴን ሙሉ አንድ ጊዜ እንኳን አላጨስኩም፤ መጠጥም የሚጠጡ ሰዎች በካንሠር ሊጠቁ ይችላሉ፤ እኔ ግን አልኮል ከንፈሬን ነክቶት አያውቅም፤ ነገርግን በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎች በዓለም ከሚደርሰው ችግር ነጻ ይሆናሉ ተብሎ የተጻፈ ነገር የለም፤ በኃጢአት በተበላሸች ዓለም ውስጥ ስለምንኖር እኔም የዚያ ዕጣ ፋንታ ደርሶኛል።
ጊዜው፤ ለነገሩ አመጋገብህም ጥሩ ነው።
ሐኪም ተመስገን፤ አዎ እንዲያውም አሁንማ ቪጋን ነኝ (ከአትክልትና ፍራፍሬ በስተቀር ምንም አልበላም)፤ ሥጋም ከበላሁ ዘመናት ተቆጥረዋል።
ጊዜው፤ ይህንን ሁሉ አልፎ ነው ካንሠር የያዘህ?
ሐኪም ተመስገን፤ አዎ፤ ኃጢአት በሞላበት ዓለም እስካለን የበሽታ ተጠቂ ነን፤ ቅድም ደግሞ እንዳልከው ጄኔቲክስ (ዘር) አስተዋጽዖ ሊያደርግ ይችላል፤ ቀጥታ ከወላጆቻችን ይተላለፋል ማለት ሳይሆን በበሽታው የመጠቃት ዝንባሌ ሊኖር ይችላል።
ጊዜው፤ እንግዲህ በሙያህ ሐኪም ነህና “ሐኪምም ይታመማል ወይ?” ብሎ አንድ ሰው ቢጠይቅ ምን ትላለህ?
ሐኪም ተመስገን፤ ሐኪም መታመም ብቻ ሳይሆን ባይገርምህ ይሞታል (ዘለግ ያለ ሳቅ)፤ ስለዚህ ነበር ሲዖል ደጃፍ ደርሼ የተመለስኩት፤ ልሞት ነበር።
ጊዜው፤ ሕመሙ እንዴት ታወቀ? እንዲሁም የታወቀ ጊዜ ምን አደረግህ?
ሐኪም ተመስገን፤ ሕመሙን እኔው ራሴ ነኝ ዳያግኖስ (ምርመራ) ያደረግሁት፤ እንደ እውነቱ መንገዱን የመራኝ እግዚአብሔር ነበር፤ እዚህ ቤቴ ጀርባ አንድ የአትክልት ቦታ አለኝ፤ ወሩ ግንቦት መጀመሪያ ነበር፤ ለቁፋሮ፣ አትክልት ለመትከል ወጥቼ ነበር፤ እና ከልክ በላይ በጣም ደከመኝ፤ ያልተለመደና የማላውቀው ነው፤ ጎንበስ ስል ደግሞ ዥው ይልብኝ ነበር፤ መንቀሳቀስም አቃተኝ፤ የምሠራውን እዚያው ትቼ ወደቤት ገባሁና ዕጸገነትን “ምን እንደሆነ አላውቅም” ብዬ ነገርኳት፤ ይህ ሲሆን እንግዲህ እሁድ ነበር፤ በሚቀጥለው ቀን ሰኞ ወደ ሥራ ሄጄ ደም እንድቀዳ አዘዝኩና ደሜን ተመረመርኩ፤ ማክሰኞ ውጤቱ ሲመጣ ሂሞግሎቢንህ (በደም ውስጥ ደም የሚያዘዋውረው ፕሮቲን) 7 ነው አሉኝ፤ መሆን የሚገባው 14 ነበር፤ በዕጥፍ ወርዷል፤ እንደዚህ የሆነበት ምክንያት ደም ወደ ውጭ ሳይፈስ ግን ውስጥ እየፈሰሰኝ ነበር ማለት ነው፤ በውስጤ እየደማሁ ነበር፤ በእኔ ዕድሜ እንዲህ ዓይነት የደም ማለቅ (ማነስ) የሚመጣባቸው ምክንቶች አንዱ ኮለን ካንሠር ሲይዝ ነው፤ ስለዚህ ወዲያውኑ ኮለን ካንሠር ይዞኛል አልኩ፤ ከዚያ በሚቀጥለው ቀን ረቡዕ ሆስፒታል ሄድኩና ኮሎኖስኮፒ ሲያደርጉ እዚያ ደሙን ይረጭ እንደነበር ተገኘ።
ጊዜው፤ ኮሎኖስኮፒ ማለት አንጀትን የሚያዩበት ምርመራ ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ አይደለም፤ አንጀትማ ላይ ነው፤ ይሄ የታችኛውን ክፍል ነው የሚመረምሩት፤ አንተ ኮሎኖስኮፒ አልተደረግህም እንዴ? አርባ ዓመት አልሞላህም?
ጊዜው፤ (ሳቅ) ኧረ አልፎኛል!
ሐኪም ተመስገን፤ (ዘለግ ያለ ሳቅ) that is a must (ይህ የግድ ነው) በተለይ አንድ ሰው ዕድሜው 45 ዓመት ካለፈ በኋላ የግድ ኮሎኖስኮፒ መታየት አለበት፤ ምክንያቱም በጊዜ ከተያዘ ቶሎ ይድናል፤ ቶሎ ይድናል ብቻ ሳይሆን ጨርሶም ይድናል፤ በጊዜ ካልተያዘ ደግሞ ይገድላል፤ ባሁኑ ጊዜ የኮለን ካንሠር ዋና ገዳይ በሽታ ሆኗል፤ ስለዚህ ኮሎኖስኮፒ በየጊዜው ማድረግ የግድ ነው።
ጊዜው፤ የኮሎኖስኮፒው ውጤት ከታወቀ በኋላ ምን ሆነ?
ሐኪም ተመስገን፤ ከዚያማ በሦስት ባራት ቀን ወዲያው ቀዶጥገና ይደረግ ተባለ።
ጊዜው፤ ይህ እንግዲህ ካንሠሩን ለማውጣት ነው አይደል?
ሐኪም ተመስገን፤ በትክክል፤ ከዚያ ወደ 12 ኢንች (30 ሴሚ) የሚሆን ሄሚኮለክቶሚ (hemicolectomy) ተደረገ፤ ማለትም የትልቁ አንጀቴ በቀኝ በኩል ያለው ከነካንሠሩ ተቆርጦ ወጣ፤ ይህ ማለት እንግዲህ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።
ጊዜው፤ ስታወራው ቀላል ይመስላል፤ ይህ ማለት ቀላል ቀዶ ጥገና የሚባል ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ አይደለም፤ እንዲውም ሜጀር ሰርጀሪ (ዋና ቀዶጥገና) ነው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ቀዶ ጥገናው ያለ ምንም ችግር ነበር የተጠናቀቀው፤ ከዚያ በኋላ ግን ከሆስፒታል ለመውጣት ዐሥር ቀን ያህል ፈጀብኝ።
ጊዜው፤ ቀዶጥገናው ስንት ሰዓት ነበር የወሰደው?
ሐኪም ተመስገን፤ ወደ ስድስት ሰዓት ያህል ነው የፈጀው፤ ምሽት 12 ስዓት (6pm) ላይ ገብቼ እኩለ ሌሊት ላይ ነው ያለቀው ያሉኝ፤ ከዚያ በደንብ አገግሜ ከዐሥር ቀን በኋላ በደህና ወጣሁ። እኔ ቀዶጥገና ከመግባቴ በፊት ጀምሮ እስከምወጣ ድረስ እስከ እኩለሌሊት ማለት ነው፤ ሆስፒታሉ ድረስ መጥተው በርካታ ወገኖች ሲጸልዩልኝ እንደነበር ከቤተሰቤ ሰምቻለሁ።
ጊዜው፤ ከዚያ በኋላ የተከሰተው ምንድነው?
ሐኪም ተመስገን፤ በሰላም ከወጣሁ በኋላ ሊገድለኝ የነበረውና ወደ ሲዖል ደጃፍ ያደረሰኝ ኪሞቴራፒው ነበር፤ ቀዶጥገናው ከተደረገ ከስድስት ሳምንት በኋላ ኪሞቴራፒ ጀመርኩ፤ ይህም በሚዋጥ ኪኒን ነበር የምወስደው፤ ኪሞውን ከጀመርኩ አራት ቀን በኋላ አምስተኛው ቀን ላይ ሊገድለኝ ነበር፤ ምክንያቱም ከሚገባው በላይ በጣም ኃይለኛ ነበር፤ መርዝም ሆኖብኛል መሰለኝ፤ እና አምቡላንስ መጥቶ ወሰደኝ፤ ሆስፒታል ገባሁ፤ ያኔ ነበር ሦስት ጊዜ ራሴን ስለሳትኩ ለማንቃት ሲሞክሩ የነበረው፤ እና ይህ ህክምና ነው ትልቁን ችግር ያመጣብኝ።
ጊዜው፤ ቀዶጥገና ከተደረገልህ በኋላ ኪሞቴራፒው ለምን አስፈለገ?
ሐኪም ተመስገን፤ እሱ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ካንሠሩ ትልቁ አንጀት ውስጥ ብቻ ተወስኖ ነው ያለው ወይስ ወደሌሎች ቦታዎችም ተሰራጭቷል? የሚለውን ለማወቅ ባደረጉት ምርመራ ከአርባ ሊምፍ ኖድ (lymph node፤ ፍርንትሩ) አንዱ ብቻ ነበር ካንሠር የተገኘበት፤ ይህ በራሱ በጣም ጥሩ ነገር ነው፤ ግን አንዱም ባይኖር በጣም የተሻለ ነው፤ ቢሆንም ያቺ አንዷ በኪሞቴራፒ መጥፋት ነበረባት፤ ቀዶጥገናው ሊፈውሰኝ ይችል ነበር ግን ያቺ አንድ ሊምፍ ኖድ መኖሯ ኪሞ እንድወስድ አስደረገኝ።
ጊዜው፤ ለስንት ጊዜ ነበር ኪሞቴራፒው የሚወሰደው?
ሐኪም ተመስገን፤ ለስድስት ወር በየሁለት ሳምንት፤ ብዙ ሰዎች ይህንን ሕክምና ሲወስዱ ምግብ ፍላጎታቸው ይቀንሳል፤ ያስመልሳቸዋል፤ ዓቅም ያጣሉ፤ እኔ ግን በደንብ እበላ ነበር፤ ሥራም እሠራ ነበር፤ ምንም ችግር አልነበረብኝም፤ እግዚአብሔር በማይገባኝ ፍቅር ስለወደደኝ እንዲህ ዓይነቱን ነገር አደረገልኝ እላለሁ።
ጊዜው፤ አሁን የኪሞውን ሕክምና ጨርሰሃል፤ ውጤቱስ ምን ይመስላል?
ሐኪም ተመስገን፤ እስካሁን አምስት ጊዜ ካት-ስካን ተደርጌአለሁ ምንም የካንሠር ነገር የለም፤ ነጻ ነህ ተብያለሁ፤ ኮሎኖስኮፒም ተደርጌ ምንም የለብህም ተብያለሁ፤ ለዚህ እግዚአብሔርን በጣም አመሰግናለሁ፤ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ጤንነት ይሰማኛል።
ጊዜው፤ ወደኋላ እንመለስና እንግዲህ ከቀዶጥገናው በኋላ ኪሞቴራፒ ጀመርህና ታመምህ ከዚያ በኋላ ነው እንደገና ኪሞ የወሰድከው?
ሐኪም ተመስገን፤ ከቀዶጥገናው በኋላ ኪሞውን ጀምሬ ለሞት በሚደርስ ሁኔታ ወይም የሲዖል ደጃፍ አደረሰኝ ባልኩት ሁኔታ ታምሜ ከሞት ከተረፍኩ በኋላ ለሦስት ሳምንት ሐኪምቤት ቆየሁ።
ጊዜው፤ ከዚያ በኋላ ነው እንደገና ኪሞ የጀመርከው?
ሐኪም ተመስገን፤ ወዲያው አልጀመርኩም፤ ምክንያቱም በጣም ታምሜ ዓቅም አጥቼ ስለነበር ወዲያው አልሆነም፤ ድጋሚ ከመጀመሬ በፊት “ዊማር” የሚባል የአድቬንቲስት የጤና ማዕከል ሄድኩ (Weimar Institute)፤ ካሊፎርኒያ ጠቅላይ ግዛት የሚገኝ ነው፤ እዚያ ሔጄ ነው ነፍስ የዘራሁት።
ጊዜው፤ ምንድነው እዚያ የተፈጠረው? ምን አደረጉልህ?
ሐኪም ተመስገን፤ እዚያ ምንም መድኃኒት የለም፤ ሕክምናው በምግብ ነው፤ ማለትም አመጋገብን በማስተካከል ነው ሕክምናው፤ የአካል እንቅስቃሴ ታደርጋለህ፤ ሌሎችም ነገሮች አሉ፤ እዚያ ለሦስት ሳምንት ቆየሁ።
ጊዜው፤ ሦስት ሳምንት ቀላል ጊዜ አይደለም፤ የቀኑ ውሏችሁ ምን ይመስላል? በየቀኑ ምን ታደርጉ ነበር?
ሐኪም ተመስገን፤ በየቀኑ የውሃ ሕክምና አለ (ሃይድሮ ቴራፒ)፤ ምግብ በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የሚያበሉት፤ ጠዋት ሁለት ሰዓት (8am) ላይ ከሰዓት ደግሞ ስምንት ሰዓት (2pm) ላይ ነው የምንመገበው፤ ማታ ምግብ የለም።
ጊዜው፤ ምን ዓይነት ምግብ ነበር የምትበሉት?
ሐኪም ተመስገን፤ መቶ በመቶ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የኦቾሎኒ ዘሮች (ቪጋን ብቻ)፤ አኩሪ አተር አለ፤ የአትክልት በርገር አለ፤ ፕሮቲን ለማግኘት ስለሚያስፈልግ፤ ይህ እንግዲህ በኬሚካል ያልተበረዘ፣ ያላረረ ነው፤ እዚያው ራሳቸው የሚያመርቱት ነው፤ ምንም ከእንሳስት የሚመረት ነገር የለም፤ እና ደግሞ የኦቾሎኒ ዘሮች ማለትም አልመንድ፣ ካሺው፣ የመሳሰሉት፣ መቼም የሌለ ዓይነት የኦቾሎኒ ዘር የለም፤ እና እነዚህን በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር የምንበላው፤ አበሳሰሉንም ያስተምሩሃል፤ የምግብ አሠራርም ተምረናል።
ጊዜው፤ ይህ እንግዲህ ከሕክምናው ጋር በተያያዘ ምን የጠቀመህ ነገር አለ?
ሐኪም ተመስገን፤ እጅግ በጣም ነው የጠቀመኝ፤ ዓቅም አገኘሁ፤ ጉልበት ሰጠኝ፤ ከዚያ በኋላ ነው የሚዋጠውን ኪሞቴራፒ መውሰድ ትቼ በደም ሥር የሚሰጠውን ለመውሰድ የቻልኩት፤ እዚህ ደረቴ ላይ (እያሳየ) ተቀድዶ የተዘጋጀ ቧንቧ አለ፤ በዚህ በኩል ነበር ሲሰጡኝ የነበረው፤ ይህ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይቆያል፤ ምክንያቱም ተመልሶ ካንሠሩ ከመጣ እንደገና መቅደድና ቧንቧ ማስገባት የለባቸውም።
ጊዜው፤ ስለዚህ ዊማር ተቋም መቆየትህ እጅግ በጣም ረድቶሃል ማለት ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ በጣምንጂ፤ ምንም ጥርጥር የለውም፤ እዚያ ባልሄድ ድጋሚ ኪሞውን ለመውሰድ ያቅተኝ ነበር፤ ዊማር ስለ ምግብና አመጋገብ ብቻ ሳይሆን ያለ ግዴታ መንፈሣዊ ነገርንም በደንብ ይሰጣሉ፤ እና በየጊዜው የምግብ አሠራሩንም ሆነ ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ደምበኛ ትምህርት ይሰጣል፤ ወደቤታችን ስንመለስ ራሳችንን እንድንቀይር፤ በራሳችን አብስለን መመገብ እንድንችል ለማብቃት የሚሰጥ ትምህርት አለ።
ጊዜው፤ ባለሙያ ሆነህ ነው የመጣኸው ማለት ነዋ? ማለትም ከእንስሳት ተዋጽዖ ከሥጋ፣ ከዶሮ፣ ከእንቁላል፣ ከወተት በስተቀር የአትክልትና ፍራፍሬ አሠራር ኤክስፐርት ሆነህ ነዋ የመጣኸው?
ሐኪም ተመስገን፤ የእንስሳት ተዋጽዖ ስሙም አይነሳም እንኳን ሊኖር፤ በጣም የዱሮ ዓይነትና ሰላማዊ የአኗኗር መርኽ የሚከተሉ ናቸው፤ አለባበስ እንኳን በተመለከተ ሴቶቹ ረጃጅም ቀሚስ እግራቸው የሚደርስ ነው የሚያደርጉት።
ጊዜው፤ እና እዚያ በምግብ ብቻ ሰው ታክሞ መዳን ይችላል ብለው ነው የሚያምኑት ማለት ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ ወደ ዊማር ስሄድ የኔ ሒሞግሎቢን ወደ ስምንት አካባቢ ነበር፤ እዚያ ሦስት ሳምንት ቆይቼ እንደገና ስለካ 12 ደርሷል፤ ይህ ማለት ወደ ትክክለኛ ደረጃ ደርሷል ማለት ነው፤ ይህ እንግዲህ በሦስት ሳምንት ውስጥ ማለት ነው። በአመጋገብ ለውጥ መፈወስ ማለት ይህ ይመስለኛል።
ጊዜው፤ በደም ሥር የሚሰጠው ኪሞቴራፒ ስንት ጊዜ ወሰደ?
ሐኪም ተመስገን፤ ስድስት ወር፤ በየሁለት ሳምንቱ ለአራት ሰዓት ነበር የሚሰጠኝ፤ ያለፈው ዓመት የካቲት ወር አካባቢ ነበር ያቆምኩት፤ በየጊዜው እመረመር ነበር፤ በመጨረሻም ካንሠር እንደሌለኝ ተረጋገጠ።
ጊዜው፤ መቼም በሕክምና ብቻ አይደለም በጸሎትም ነው የዳንከውና ምን ትላለህ?
ሐኪም ተመስገን፤ ምን ጥያቄ አለው!? እኔ በእውነቱ ያልጸለየልኝ ሰው የለም፤ በአሜሪካ ከጥግ እስከ ጥግ በጣም ብዙዎች፣ በአውሮጳና ሌሎች አገራት እስከ ኢትዮጵያ ድረስ፤ እዚህ ካንሳስ ሲቲ እንኳን የኦርቶዶክስ ካህናትና ምዕመናን፣ ሙስሊሞች፣ የፕሮቴስታንት አማኞች፣ በዚሁ ከተማ (ካንሳስ ሲቲ) ያሉ የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ቤ/ክ አማኞች በጾም በጸሎት፤ ሳይበር ሚኒስትሪና ሻሎም ቴሌኮንፍራንስ፣ ህጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ቆጥሬ የማልጨርሰው ብዙ ሰው፣ ብቻ ያልጸለየልኝ የለም፤ ይህ ዋንኛና ቀዳሚው ነው፤ ሐኪሞቹ አይደሉም ያዳኑኝ፤ መድኃኒቴም አይደለም የፈወሰኝ፤ በእርግጥ እግዚአብሔር በእነዚህ ነገሮች ይጠቀማል፤ ነገርግን እኔ እግዚአብሔር ራሱ ነው የፈወሰኝ ብዬ ነው የማምነው፤ ደግሞ አልተሳሳትኩም።
ጊዜው፤ በሕመም በነበርክ ጊዜ በውስጥ ይመላለስ የነበረ ነገር ምን ነበር? ሰው ሲታመም ተስፋ ይቆርጣልና ከዚያ አኳያ ማለቴ ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ እውነቱን ለመናገር እኔ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተስፋ አልቆረጥኩም፤ እሞታለሁ ብዬም በፍጹም አልፈራሁም፤ ገና ካንሠር መሆኑን ሳውቅ ጀምሮ ሞት ምንም አላሳሰበኝም ነበር፤ መቼም ደስ አለኝ አልልህም፤ ነገርግን እሞታለሁ ብዬ የፈራሁበት ሁኔታ የለም፤ ምክንያቱም ሞት ዕንቅልፍ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ልጆቼ ጥሩ ደረጃ ደርሰዋል፤ ባለቤቴ ግን ብቻዋን ትሆናለች ብዬ አስባለሁ፤ ዕንቅልፍ እንደማይፈራው ሁሉ ሞትንም እንዲሁ አልፈራሁም ነበር።
ጊዜው፤ ስለዚህ ስለ ሞት ያለህ አመለካከት ነው እንዳትፈራ ያደረገህ ማለት ይቻላል?
ሐኪም ተመስገን፤ በትክክል፤ አንድ ሰው መልካም ዕንቅልፍ ከተኛ ጠዋት ሲነቃ ምን ያህል ሰዓት እንደተኛ አያውቅም አይደል? ስለዚህ ስንሞት ገነት የለም ገሃነም የለም፤ ዕንቅልፍ ነው የሚለው መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ነው፤ ክርስቶስ ሲመጣ ነው በትንሣኤ የምንነሳው፤ የትንሣኤ ማለዳ ጠዋት ላይ ነው የምንነቃው።
ጊዜው፤ ረጅም ዕንቅልፍ የመተኛት ያህል ነው ማለት ይቻላል?
ሐኪም ተመስገን፤ የተኛኸው ምን ያህል እንደሆነ የት ታውቃለህ? ትንሣኤም እንደዚያው ነው፤ ክርስቶስ ሲመጣና “ተነስ” ሲል ያኔ እንነሳለን።
ጊዜው፤ በዚህ ሕመም ወቅት ባልድን ወይም ባልፈወስ ብለህ አስበህ ነበር? እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ምን ተሰማህ?
ሐኪም ተመስገን፤ ባልድን ምን ይሆን ነበር ማለት የቤተሰቤ ነገር ካልከኝ፤ አሱን ካዘጋጀሁ ሃያ ዓመት አልፎኛል፤ ልጆች ሲኖሩህ ለምሳሌ “እኔ የሞትኩ እንደሆን ልጆቼ፣ ቤተሰቤ ምን ይሆናል? እኔና ባለቤቴ ብንሞትስ ልጆቼ ምን ይሆናሉ? ለማነው የምሰጣቸው?” የሚለውን ከሰው ጀምሮ ማዘጋጀት አለብህ፤ እና ይህንን አስቀድሜ ተዘጋጅቼበት ነበር፤ አሁንማ ልጆቹም አድገዋል፤ ግን ቢሆንም እንደገና ተከልሶ ተዘጋጅቷል፤ እናም ደግሞ በተለይ ልጆች ያላቸው እንደዚህ አስቀድመው ሊያስቡ ይገባል፤ ቤተሰብን፣ ልጆችን እንዲሁ በትኖ መሄድ ጥሩ አይደለም፤ ቅጥ ያጣ ጭንቀትና ዝግጅት ሳይሆን ተገቢውን የሆነ ዝግጅት።
ጊዜው፤ ወደ ሕክምናው ብንመለስና ኪሞውን ከወሰድክ በኋላ ካንሠሩ አልዳነም ብትባልስ ኖሮ?
ሐኪም ተመስገን፤ ሌላ ደግሞ ሕክምና አለ፤ ወደሱ እቀጥላለሁ።
ጊዜው፤ እንደሱ ማለት ሳይሆን በእምነትህ ላይ ለማለት ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ እምነቴን ያናጋዋል ወይ ማለትህ ነው? ፈጽሞ፤ በጭራሽ፤ ብሞትም ባልሞትም ችግር የለም፤ ያመንኩትን አውቃለሁና።
ጊዜው፤ መፈወስህ አስደናቂ ነገር ነው፤ ለዚያ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ዕድሜ እንደተጨመረልህ አድርገው የሚወስዱ ጥቂቶች አይደሉምና በዚህ በተጨመረልህ ዕድሜ ምን ለማድረግ ያሰብከው ነገር አለ? ማለትም በመንፈሣዊ አገልግሎትም ቢሆን በሌላ ማለት ነው?
ሐኪም ተመስገን፤ እውነት ነው ተጨምሮልኛል፤ አሜን ይመስገን፤ ቢያንስ እስካሁን አንድ ዓመት ተኩል ተጨምሮልኛል (ዘለግ ያለ ሳቅ)፤ ስለ አምላኬ፣ ስለ ጌታዬ ድንቅ መሆን ሳልናገር አንድም ቀን አልፎኝ አላውቅም፤ ፈዋሽ መሆኑን በየቀኑ ከበሽተኞቼ ጋር አወራለሁ፤ እመሰክርላቸኋለሁ፤ አንዳንዶቹ “አንተ ቄስ ነህንዴ?” ይሉኛል፤ ሥራዬን እወደዋለሁ፤ በዚያ ሥራ እግዚአብሔር እየተጠቀመብኝ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ሌላም ደግሞ ብዙም ዝርዝር ውስጥ መግባት ባልፈልግም የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ዓቅሜ በሚፈቅደው በፋይናንስም ቢሆን በሚቻለኝ አግዛለሁ፤ ማለት እንግዲህ ሚሽነሪ ሆኜ አልሄድኩም (ሳቅ)።
ጊዜው፤ በተለይ ግን ዕድሜ ተጨምሮልኛልና ይህንን አደርጋለሁ ብለህ ያሰብከው እንዳለ?
ሐኪም ተመስገን፤ በተለየ ከህመሙ በኋላ ያሰብኩት ነገር የለም፤ ግን የበለጠ እቀጥላለሁ ነው የምለው፤ አዲስ ሃሳብ ግን የለኝም።
ጊዜው፤ በመጨረሻም በህመም እየተሰቃዩ ለሚገኙ ሰዎች ምን ምክር ትሰጣቸዋለህ?
ሐኪም ተመስገን፤ ጌታችን ያደርግ የነበረው፤ በተለይ ሲፈውስ የሚናገረው ነገር “እምነትህ/ሽ አዳነህ/ሽ” ነበር የሚለው፤ አንዳንድ ጊዜ የተፈወሱት “መጥተን እንከተልህ” ይሉት ነበር፤ ታዲያ እርሱም ለአንዳንዶቹ ሲመልስ፤ ሂድና ለቤተሰቦችህ፣ በአካባቢህ ላሉት ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ ንገር፣ መስክር ይላቸው ነበር፤ የኔ ሥራ እርሱ ነው! ጌታ ምን ዓይነት ትልቅ ነገር እንዳደረገልኝ፤ ህይወቴን እንደቀጠለልኝ መመስከር ነው፤ ስለዚህ በህመም ላሉ የምለው ይህንኑ ነው፤ “እምነታችሁ ያድናችኋል፤ ተስፋ አትቁረጡ፤ ተስፋ መቁረጥ የሰይጣን ዋና መሣሪያ ነው”፤ እንዲያውም ተስፋ የሚቆርጡ ሰዎች በሽታ የመከላከል አቅማቸው (ኢሚውን ሲስተማቸው) ይቀንሳል፤ በሽታን መዋጋት ያቅታቸዋል፤ መዝሙረ ዳዊት ላይ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው” ይላል (መዝ. 139፡14)፤ ስለዚህ ይህንን ድንቅ አድርጎ የሠራቸውን ጌታ አምላክ እንዲያምኑት፤ በእርሱ ተስፋ እንዳይቆርጡ ነው የምመክራቸው፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔርን ካመን ተስፋ ልንቆርጥ አንችልም፤ እምነት ካለን ሞትን እንኳን ቢሆን አንፈራም፤ ምክንያቱም ላመነ ሰው ሞት እንቅልፍ ነው፤ ክርስቶስ ሲመጣ ደግሞ በትንሣኤ ህይወት ይነሳል።