“በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ ‘እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ፤ ደግሞም፣ ‘ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ’ አለ።” (ራዕይ 21:5-6)
አዲስ ዓመት ሲጀምር ሁሉን ነገራችንን አዲስ ማድረግ እንፈልጋለን። ያለፈውን ዓመት “አሮጌ” በማለት የፈጸምናቸውን መጥፎ ተግባራት ለመርሳት፤ የበደልነውን ለመካስ፤ ይቅር ለማለት፤ አዲሱን ዓመት በደስታና በሰላም ለማሳለፍ እንመኛለን፤ አዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ ሰንቆ መጥቷል ብለን በማሰብ አዳዲስ ነገሮችን እንመኛለን። ነገር ግን አሮጌ ያልናቸው ዓመታት በተጀመሩ ቁጥር “የአዲስ ዓመት ውሳኔዎች” በማለት የዘረዘርናቸውን መለስ ብለን ብናይ፣ ወደ ሃሳብ ጓዳችን ዘልቀን የጻፍናቸውንም ሆነ ያልጻፍናቸውን ውሳኔዎች ብናጤን በራሳችን እናፍራለን። አፍረን ብቻ ግን አናቆምም፤ አሁንም “የአዲስ ዓመት ውሳኔዎችን” እናስተላልፋለን።
“የአዲስ ዓመት ውሳኔዎች” ተብሎ የሚጠቀሰውን የጀመሩት ባቢሎናውያን ናቸው ይባላል። የዛሬ አራት ሺህ ዓመት ገደማ ባቢሎናውያን አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ለአማልክታቸው (ለጣዖታቸው) በዓለ ንግሥ በማድረግ በአዲሱ ዓመት ታዛዦችና ታማኞች ለመሆን ቃል ይገቡ ነበር። ጥሩ ሰው ለመሆን፣ ዕዳቸውን ሁሉ ለመክፈል፣ የተዋሱትን ሁሉ ለመመለስ፣ ወዘተ ቃል በመግባት አማልክታቸውን ማስደሰት የአዲሱ ዓመት ውሳኔያቸው መሆኑን ያሳውቃሉ። ይህንን በትክክል ከፈጸሙ አምላከ-ጣዖታቸው በአዲሱ ዓመት መልካምን ሁሉ እንደሚያደርግላቸው፤ ሰብላቸውን እንደሚባርክ፤ ምድራቸውን እንደሚያበለጽግ፤ ይህንን ካላደረጉ ግን ተቃራኒው እንደሚሆንባቸው ያምኑ ነበር።

ይኸው እምነት ወደ ሮማውያን ዘልቆ እነርሱም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “የአዲስ ዓመት ውሳኔዎችን” በማድረግ አማልክቶቻቸውን ለማስደሰት ቃል መግባታቸውን እንደቀጠሉ ይነገራል። በተለይ ሮማውያን የመጀመሪያውን ወር “ጃንዩወሪ”ን የሁሉ ነገር መጀመሪያ ነው ለሚባለውና ሁለት የፊት ገጽታ ላለው “ጃኑስ” ተብሎ ለሚጠራው አምላካቸው ቃልኪዳን በመግባት፣ መስዋዕትን በማቅረብ አዲስ ዓመትን ይጀምሩ እንደነበር ይነገራል። ሁኔታው በዘመናችን መልኩን ቀይሮ የአዲስ ዓመት ውሳኔዎች የምንላቸው ለጣዖታት የሚደረጉ ውሳኔዎች መሆናቸው ቀርቶ ለራስ የሚደረጉ የውሳኔ ቃልኪዳኖች ሆነው ሲተገበሩ እናያለን። ለመሆኑ እኛ ሁሉን አዲስ ማድረግ እንችላለን?
አምላካችን እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን በፈጠረ ጊዜ ሁሉንም ውብ አድርጎ ነበር የሠራው (ዘፍ. 1፡1-31)። በእያንዳንዱ ቀን አዳዲስ ነገሮችን ከፈጠረ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እግዚአብሔርም … መልካም እንደሆነ አየ” ይላል (ዘፍ.1፡4፣10፣13፣19፣21፣25)። በመጨረሻም ሁሉን ፈጥሮ ከጨረሰና የፍጥረቱ ቁንጮ የሆነውን አዳምን አሳምሮ ከሠራው በኋላ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም እጅግ መልካም ነበር” ይላል (ዘፍ. 1፡31)። ስድስት ጊዜ “መልካም” ነው ካለ በኋላ በሰባተኛው ግን እንደ ስድስቱ በ“መልካም” ብቻ ሳይሆን የገለጸው “እጅግ መልካም” በማለት ነበር። ከዚያም የሰው ልጅ በአዲስ ሰማይና ምድር፣ ሁሉም ነገር አዲስ በሆነበት፣ ሁሉም “እጅግ መልካም” ተደርጎ በተፈጠረበት ውስጥ ህይወት እንዲጀምር፤ ምድርን ከማስተዳደር በስተቀር አንዳች ነገር እንዳይሰራ፤ ሁሉንም በምስጋናና በጸጋ እንዲቀበል የሰንበት እረፍት ተሰጠው።
እግዚአብሔር ሁሉን አዲስና “እጅግ መልካም” አድርጎ የመፍጠሩን ጉዳይ መጽሐፈ መክብብ ሲያብራራ “እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ በእርሱ ላይ ምንም አይጨመርም፤ ከእርሱም ምንም አይቀነስም፤ ሰዎች ያከብሩት ዘንድ ይህን አደረገ” ይላል (መክ. 3፡14)።
በዚህ ዓይነት ፍጽምና እና ውበት ለተሠራችው ፍጥረት አስተዳዳሪዋ እንዲሆን የተሾመው አዳም በአምላኩ ባለመታመኑ ምክንያት ሲበድል ታዛዥነቱን ላታለለው ለዲያቢሎስ አሳልፎ ሰጠ። ምስጋና በእርግማን፤ ፍቅር በራስወዳድነት፤ ህይወት በሞት ተተካ። ዘላለማዊነት የጊዜ ገደብ ተደረገለት፤ አዲስ የነበረው ሁሉ አሮጌ መሆን ጀመረ። ሞትም በሰው ሁሉ ላይ ነገሠ!

ከዚህ በኋላ የሰው ልጅ አዲስ ነገሮችን መመኘት እንጂ ማግኘት ተስኖት መኖር ጀመረ። ከምንም ውስጥ አንዳች የመፍጠር ኃይልና ሥልጣን ያለው አምላካችን ለሰው ልጅ ነገሮችን አዲስ ለማድረግ ዕቅድ አወጣ። የመጀመሪያውን ታላቅ የወንጌል ተስፋ አወጀ። “በአንተ (በእባብ ለተመሰለው ሰይጣን) እና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” በማለት እግዚአብሔር ለሔዋን የአዲስ ዘመን ውሳኔውን አሳወቃት፤ አዲስ ተስፋ ሰጣት (ዘፍ. 3፡15)። በዚህ ጥቅስ ላይ “ዘር” ተብሎ በተጠቀሰው በክርስቶስ አማካኝነት ሁሉን አዲስ እንደሚያደርግ ቃል ገባ፤ ቃሉንም ጊዜውን ጠብቆ ፈጸመ።
አዲስ የማድረግ፤ የመፍጠር ብቃት ያለው አምላካችን እግዚአብሔር ብቻ ነው። በኢሳ. 42፡9 ላይ “እነሆ፤ የቀድሞው ነገር ተፈጽሞአል፤ እኔም አዲስ ነገር እናገራለሁ” ይላል። እንዲሁም በዚሁ በትንቢተ ኢሳይያስ “እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ” ይላል (43፡19)። ኃጢአት ከገባ በኋላ የተበላሸውን ዓለም፤ ሰማይና ምድር አዲስ ማድረግ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው፤ “እነሆ፤ እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም። ነገር ግን በምፈጥረው፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ” (ኢሳ. 65፡17)።
ይህ ሁሉንም አዲስ የማድረግ ብቃትና ፍጹም ችሎታ ያለው አምላክ እኛ ነገሮችን አዲስ የማድረግ ድክመታችንን ስለሚያውቅ ጥሪ ያቀርብልናል። “በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?” (ህዝ18፡31)። ርግጥ ነው ለምን እንሞታለን? ለምንስ የማንችለውን ነገር ለማድረግ ግትር እንሆናለን? እስከመቼስ በማይሳካ ውሳኔ ራሳችንን እየሸነገልን እንኖራለን?
የአዲስ ዓመት ውሳኔዎችን የሚያጠኑ እንደሚሉት ከመቶ ሰዎች 8-10 የሚሆኑት ብቻ ናቸው የአዲስ ዓመት ውሳኔዎቻቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉት። እነርሱም በቀጣይ ዓመታት እነዚህን ውሳኔዎች ይዘው ለመቆየት እጅግ እንደሚቸገሩ ይነገራል። ለዚህም ይመስላል ኦስካር ዋይልድ ይህንን ያለው፤ “መልካም (የአዲስ ዓመት) ውሳኔዎች ዝርዝር ማውጣት ማለት ባንክ ቤት ሒሳብ ሳይኖረን ገንዘብ ለማውጣት ደረቅ ቼክ እንደመጻፍ ነው”። የሰው ልጅ ነገሮችን አዲስ የማድረግ አንዳች ብቃት የለውም። ነገሮችን አዲስ ለማድረግ በቅድሚያ ራሳችን መለወጥ፤ አዲስ መሆን አለብን። እንዴት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳችን ምላሽ ይሰጣል።
“ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ፣ እኛም እንዲሁ በአዲስ ሕይወት እንድንኖር በጥምቀት ሞተን ከእርሱ ጋር ተቀብረናል” (ሮሜ 6፡4)። በሥጋ ከአባትና እናታችን የመወለዳችን ጉዳይ ከአሮጌው ህይወት ጋር የተቆራኘ ነው። አዲስ ለመሆን አዲስ አባትና እናት ያስፈልጉናል – ውሃና መንፈስ። “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” (ዮሐ. 3፡5፣6)። ይህንን ቃል የአይሁድ መምህር ለነበረው ኒቆዲሞስ የተናገረው መድኃኒዓለም ነበር። አዲስ ውሳኔ ለመወሰን በቅድሚያ አዲስ መሆን ያስፈልጋል! አምላክን በፍጹም ሁለንተናችን ልንወደውና ልንታዘዘው በቅድሚያ ይገባል። የዚያን ጊዜ አዲስ ፍጥረት እንሆናለን።
“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ አዲስ ሆኖአል” (2ቆሮ5፡17)። አዲስ ፍጥረት አዲስ ዕቅድ ማውጣት ይችላል፤ አዲስ ውሳኔዎችን መወሰን ይችላል። ምክንያቱም በዓላማው ሁሉ በቅድሚያ ማሳካት የሚፈልገው የራሱን ፍላጎት ሳይሆን “ሁሉን አዲስ” ማድረግ የሚችለውን የአምላኩን በመሆኑ ነው።
በትክክል አስተውለነው ከሆነ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ዕድሜያችን እያለቀ ሞት ወደ እኛ እየቀረበ ነው ያለው። ለመሆኑ የሰው ህይወት ስድስትና ሰባት ዓሥርተ ዓመታትን ኖሮ መሞት ነው? በቃ ይኸው ነው? አዳም የተፈጠረው ለዘላለም ነበር፤ አዳም የተፈጠረው “አሮጌ” ዓመት እየቆጠረ የ“አዲስ ዓመት ውሳኔዎች” እያስተላለፈ መሞቻውን እንዲጠብቅ አልነበረም። በዘላለማዊ አምላክ ውብ ተደርጎ የተሠራው አዳም አፈጣጠሩ ዘላለማዊ ነበር፤ በእርሱ አማካኝነት የእኛም እንዲሁ። ይህንን ዘላለማዊነት መልሰን እስካላገኘን ድረስ ዓመት ባለፈ ቁጥር “አዲስ” እያልን የምንቆጥረው ሞት ወደ እኛ ምን ያህል እየቀረበ እንደመጣ ብቻ ነው። “የአዲስ ዓመት ውሳኔዎችን” ከማስተላለፍ በፊት በቅድሚያ አዲስ መሆን ያስፈልጋል። ይህንን አዲስነት የሚያጎናጽፈን ደግሞ መድኃኒዓለም ብቻ ነው። እርሱ እኛን ብቻ ሳይሆን ሰማይንና ምድርን ጭምር ነው አዲስ የሚያደርገው። ይህ ሊሆን ጊዜው ደርሷል ይለናል። ይህንን ቃል የመስሚያው ጊዜም አሁን ነው።
“በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ ‘እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ፤ ደግሞም፣ ‘ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ’ አለ።” (ራዕይ 21:5-6)
መልካም አዲስ ዓመት!
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ
(ለዚህ ጽሁፍ ግብዓት እንደምንጭ የተጠቀምነው ይህንን ነው፤ History Channel, The History of New Year’s Resolutions December 30, 2015)










