በዓለምአቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈው ራፐር ካንዬ ዌስት “ዳግም ተወልጃለሁ” ካለ በኋላ ዝናው እየገነነ መምጣቱ ተነገረ። በተለይም በክርስቲያኖች ዘንድ እያገኘ የመጣው ዝና በቀጣይ ዓለምአቀፋዊ የክርስቲያን መነቃቃት ሊያስነሳ ይችላል የሚል ግምቶች እየተሰጡት ነው።
“Jesus Is King” የሚለው የዘፋኙ ዘጠነኛ አልበም ከዚህ በፊት ከሚያወጣቸው መስመር የለቀቁና ስብዕናን ከሚያዋርዱ ዘፈኖች በተለየ መልኩ ክርስቲያናዊ ቃላትን በመጠቀም የዘፈነው ነው። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ባዲሱ አልበም በመደፋፈር ወደ ቤተእምነት ለመሄድ እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ። አልበሙ ከወጣበት ጥቅምት ወር 2012 ዓም ጀምሮ ሽያጩ ሬከርድ ሰብሯል ተብሎለታል። ከአልበሙ ጋር እያንዳንዱን በ170 ዶላር የሚሸጠው ኮፍያ ያለው ሹራብ (ሁዲ) ለዘፋኙ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እንደሆነለት ተዘግቧል።

በአሜሪካ የቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት ሒውስተን ከተማ ግዙፍ ቤ/ክ በመምራት የሚታወቁትና የማኅበራዊና የብልጽግና ወንጌል አራማጁ ጆል ኦስቲን በዚሁ በያዝነው የኅዳር ወር ካንዬ ዌስትን በቤ/ክናቸው ጋብዘውት ነበር። በፕሮግራሙ ላይ “እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ሁሉ ታላቅ የሆነው አርቲስት አሁን ደግሞ ለአምላክ እየሠራ ይገኛል” በማለት ካንዬ ስለ ራሱ መናገሩን ዋሽንግተን ፖሰት ዘግቧል።
“ያለፈው ዓመት (2018) 115 ሚሊየን ዶላር ነበር የሠራሁት፤ ግን ዓመቱ ሲያልቅ 35ሚሊየን ዶላር ዕዳ ነበረብኝ፤ (ያለፈውን ዓመት ታክስ ከከፈልኩ በኋላ) አሁን በዚህ ዓመት ተሰልቶ 68 ሚሊየን ዶላር ተመላሽ ተደርጎልኛል” በማለት ካንዬ እንዴት “በብልጽግና እንደተባረከ” ተናግሯል።
ጌታ ሰዎችን በሃብት በመባረክ ያበለጽጋቸዋል፤ ይህንንም በማሳየትና በማድረግ ይገልጻል የሚለውን የብልጽግና ወንጌል ሃሳብ አራማጅ ለሆኑት ጆል ኦስቲን የካንዬ ዌስት ተመሳሳይ መልዕክት ተጨማሪ ማሳመኛና ደጋፊ ሆኖ እየቀረበ ይገኛል። ከሒውስተን ወጣ ብላ በምትገኝ ከተማ 10.5 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ቤት ገዝተው የሚኖሩት ጆል ኦስቲን በዕለቱ ካንዬ ዌስት በቤ/ክናቸው ተገኝቶ ከተናገረ በኋላ “ካንዬ ከተሟገተልህ ምን ትፈልጋለህ?” በማለት መናገራቸውን ተዘግቧል።
ካንዬ ዌስት ያደረገውን ለውጥ የሚቃወሙና የማይቀበሉ ቢኖሩም እርሱ ግን በየቦታው በሚያደርጋቸው የሙዚቃ ድግሶች ሁሉንም ዓይነት በሚባል መልኩ ሰዎችን እየሳበ ይገኛል። ወደ ቤ/ክ እግራቸው ረግጦ የማያውቁ ሰዎች በእርሱ የሙዚቃ ድግሶች ላይ ለመገኘት በሚል ወደ ቤ/ክ ለመሄድ እንደቻሉ የተናገሩ አሉ። በዋዮሚንግ ጠቅላይ ግዛት በጣም ጥቂት ሕዝብ በሚኖርባት መንደር በሁለት ቀን ውስጥ በተነገረ ማስታወቂያ 3,800 የሚያህል ሰው ከአጎራባች ጠቅላይ ግዛቶችና ራቅ ካሉ ከተሞች መገኘት መቻሉ ብዙዎችን ያስደነቀ ሆኗል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ የሞርሞን እምነት ተከታዮች በብዛት በሚገኙበት የሶልት ሌክ ሲቲ ካንዬ ባደረገው የሙዚቃ ድግስ ላይ በርካታ ሞርሞኖች የቤ/ክናቸውን 189ኛ አጠቃላይ ዓመታዊ ስብሰባ በመሰረዝ በድግሱ ላይ መገኘታቸው ታውቋል። ከሰዓት በኋላ ለጀመረው ፕሮግራም ብዙዎች ከሌሊቱ 10ሰዓት ጀምሮ ወረፋ ይዘው እንደነበር ታውቋል።

ይህ የካንዬ ዌስት “አዲስ መወለድ” ሕይወት እውነተኛ ይሁን አይሁን ማንም መፍረድ አይችልም ሆኖም የዘፋኙ “መለወጥ” እና አዲስ የጉዞ መስመር መጀመር የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ ምናልባትም መነቃቃትን ሊያመጣ ይችላል የሚል ግምቶች ካሁኑ እየተሰጡት ነው። ጥያቄው ግን ይህ መነቃቃት እውነተኛ ይሆን ወይስ ጌታችንና መድኃኒታችን “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ” በማለት በማቴዎስ 7፥15 ላይ የተናገረው ዓይነት ይሆን የሚለው መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው።
እውነተኛ መታደስ የሚመጣው የእግዚአብሔርን ቃል ከማንበብና ከማጥናት ሲሆን ይህም ጥናት የሰዎችን ኃጢአት በመውቀስ ንሰሐ እንዲገቡ ልባቸውን ያነሳሳል። ይህ ዓይነቱ በአምላክ ቃል ጥናት የተነሳሳ ህይወት በጸሎት ኃይል መነቃቃት የሚችልና ለፍሬ የሚበቃ ይሆናል።
“አንባቢው ያስተውል”