giziew.org

አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር

ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል”
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት በሚሆንበት ጊዜ የሚከሰተውን ከዚህ በፊት በነበረውና የጌታ ዳግም ምፅዓት በሚለው ርዕስ ሥር በሥፋት ተከታትለን ነበር። ጌታ ሲመለስ እግሩ ምድርን አይረግጥም፤ ነገርግን ጌታችንን አምነው የሞቱ አዲስ አካል ለብሰው ከመቃብር ይነሳሉ፤ በኃጢአታቸው የሞቱ እዚያው ባሉበት በመቃብር ይቆያሉ፤ በሕይወት ያለን ደግሞ አዲስ አካል በቅጽበት በመልበስ እንለወጣለን። በህይወት ያሉ ኃጥአን በጌታችን የክብር ብርሃን ይሞታሉ። ከሞት የተነሱትና በህይወት እያለን የተለወጥነው ጌታን ለመቀበል በአየር እንነጠቃለን፤ ከዚያም በመላዕክት ታጅበን ወደ ሰማይ ከጌታችንና መድኃኒታችን ጋር እንሄዳለን። በዚያም ለአንድ ሺህ ዓመት እንቆያለን።

በምድር ላይ ግን ኃጥአን በአምላክ ክብር ብርሃን ከሞቱ በኋላ የሚቀሩት ሰይጣንና አጋንንት ለአንድ ሺህ ዓመት በምድር ይታሰራሉ። ሺሁ ዓመት ሲፈጸም ሰይጣንና መላዕክቱ ከእስራታቸው ይፈታሉ፤ በመቃብር የሚገኙት ኃጥአን ይነሳሉ፤ አዲሲቷ የሩሳሌም ወደ ምድር ትወርዳለች፤ በውስጧም ለሺህ ዓመት ከጌታችን ጋር በሰማይ የነበሩት ጻድቃን ከአምላካቸው ጋር ሆነው ይመጣሉ። ሰይጣንና ሠራዊቱ ከሞት ከተነሱት ኃጥአን ጋር በመሆን አዲሲቱን የሩሳሌም ለመውረር ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እሣት ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ ትበላቸዋለች። ከዚያም ጌታችን ይችን ምድር በእሣት ያጸዳታል፤ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይፈጥራል፤ እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከዚያ ወዲያ ሞት አይኖርም፣ ጻድቃን ከአምላካቸው ጋር በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።

በዚህ ክፍል ስለ አስደናቂዋ አዲስ ከተማ ኢየሩሳሌም ስለ እንዲሁም አዲሲቷ ሰማይና አዲሲቷ ምድር ዘርዘር ያሉ ሃሳቦችን እንዳስሳለን፤

1. የዚህች አስደናቂ ከተማ ፕላን ነዳፊ ማነው? የገነባትስ?

“እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና” (ዕብ. 11፡16)።

2. ይህች ከተማ የት ነው ያለችው?

“ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ” (ራዕይ 21፡2)። ይህች ከተማ ተዘጋጅታ የምትመጣው ወደዚህች ምድር ነው። ይህች ምድር ከታደሰችና እንደገና ከተፈጠረች በኋላ የዚህ ምድር ዋናከተማ ቅድስቲቱ ከተማ ትሆናለች። 

3. የከተማዋ ስፋት፣ መጠንና አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ስሟ፤ “አዲሲቷ ኢየሩሳሌም” ነው (ራዕ.21፡2)፤ “ከተማዪቱም ርዝመቷና ስፋቷ እኩል ሆኖ አራት ማእዘን ነበረች። እርሱም ከተማዪቱን በዘንጉ ለካ፤ ርዝመቷም ዐሥራ ሁለት ሺህ ምዕራፍ ሆነ፤ ስፋቷና ከፍታዋም እንዲሁ ሆነ” (ራዕይ 21፡16)። ከተማዋ በአራቱም ጎኖቿ፤ እኩል መጠን ያላት (ስኩዌር) ስትሆን መጠነዙሪያዋ 12,000 ምዕራፍ የተባለው መለኪያ 2,414 ኪሜ አካባቢ ነው። ይህም ማለት የአንዱ ጎን ርዝመት በግምት 604 ኪሜ ነው።

ቅጥሯ፤ “ደግሞም የከተማዪቱን ቅጥር ለካ፤ ርዝመቱም የመልአክ መለኪያ በሆነው በሰው መለኪያ መቶ አርባ አራት ክንድ ነበር። ቅጥሩ የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበር” (ራዕይ 21፡17፣18)። የቅጥሯ ርዝመት 144 ክንድ የተባለው 66ሜትር ወይም 20 ፎቅ አካባቢ ነው፤ ይህም የከተማዋ ቅጥር (ግድግዳ) ርዝመት ሲሆን የተሰራውም ኢያስጲድ ከተባለ የከበረ ድንጋይ ነው።

በሮቿ፤ “ዐሥራ ሁለት በሮች የነበሩት ትልቅና ረጅም ቅጥርም ነበራት፤ … በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮች፣ በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ። ዐሥራ ሁለቱም በሮች ዐሥራ ሁለት ዕንቈች ነበሩ፤ እያንዳንዱም በር ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ” (ራዕይ 21፡12፣13፣21)።

መሠረቷ፤ “የከተማዪቱም ቅጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ … በሁሉም ዐይነት የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፣ 2ኛው ሰንፔር፣ 3ኛው ኬልቄዶን፣ 4ኛው መረግድ፣ 5ኛው ሰርዶንክስ፣ 6ኛው ሰርድዮን፣ 7ኛው ክርስቲሎቤ፣ 8ኛው ቢረሌ፣ 9ኛው ወራውሬ፣ 10ኛው ክርስጵራስስ፣ 11ኛው ያክንት፣ 12ኛው አሜቴስጢኖስ” (ራዕይ 21፡14፣19፣20)። እነዚህ 12 የከበሩ ድንጋዮች የሚፈጥሩት ቀለም ውኽደት ከተማዋ በቀስተዳመና ላይ የተቀመጠች ያስመስላታል።

መንገዶቿ፤ “የከተማዪቱም አውራ መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን የሚያስተላልፍ ንጹሕ ወርቅ ነበረ” (ራዕይ 21፡21)።

አጠቃላይ ገጽታ፤ “ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ … በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ፣ እንደ መስተዋት የጠራ ነበር። ከተማዪቱም ርዝመቷና ስፋቷ እኩል ሆኖ አራት ማእዘን ነበረች” (ራዕይ 21፡2፣11፣16)። ከተማዋን ከሚያበሩት የከበሩ ድንጋዮች ብርሃን በተጨማሪ በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር።

የሕይወት ወንዝና የሕይወት ዛፍ፤ “ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ መስተዋት የጠራውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤ ወንዙም በከተማዪቱ አውራ መንገድ መካከል ይፈስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ” (ራዕይ 22፡1፣2)።

4. ያልዳኑት ምን ይሆናሉ? ኃጢአትስ?

“… ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል፤ … እኔ በምሠራበት ቀን ክፉዎችን ትረግጣላችሁ፤ ከእግራችሁ ጫማ በታች ዐመድ ይሆናሉ” (ሚል.4፡1፣3)። “… በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል። … እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” (2ጴጥ.3፡10፣13)።

እግዚአብሔር ለኃጢአት መጨረሻ ያደርጋል። ይህ ሲሆን ከኃጢአት ጋር መላቀቅ ያልቻሉትን እጅግ በጣም እያዘነ፣ “እንዴት ልተዋችሁ?” እያለ ምርጫቸውን በማክበር ወደ መቃጠል እንዲሄዱ ይፈቅዳል። ኃጢአትና ይህች ምድር በእሣት ከፀዱ በኋላ አምላካችን ኃጢአትና የኃጢአት ውጤቶች ሁሉ የሌሉበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይፈጥራል። ከዚህ በኋላ ኃጢአት ደግሞ አይነሳም (ናሆም 1፡9)።

5. ወደዚህ አዲስ ምድር ለመግባትና ለመኖር ለሚፈልጉ እግዚአብሔር የገባው ቃል ምንድነው?

ሀ) ጌታ ራሱ በአካል ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ (ራዕይ 21፡3)።

ለ) መድከም፣ መሰልቸት የሚባል ነገር አይኖርም፤ በዘላለም ፍሰሐ ውስጥ ይኖራሉ፤ (መዝ.16፡11)።

ሐ) ሞት፣ ሕመም፣ እንባ፣ በሽታ፣ ሆስፒታል፣ ቀዶጥገና፣ መከራ፣ ሐዘን፣ ብስጭት፣ ረሃብ፣ ጥማት አይኖርም፤ (ራዕይ 21፡4፤ ኢሳ. 33፡24፤ ኢሳ. 65፡23፤ ራዕይ 7፡16)።

) ሁሉም ሰው በአካል ብቁ ይሆናል፤ መስማት የተሳነው ይሰማል፣ ዓይነስውሩ ያያል፤ ሽባው ይሮጣል፤ (ኢሳ. 35፡5፣6፤ ፊሊ. 3፡21)።

ሠ) ቅንዓት፣ ፍርሃት፣ ጥላቻ፣ ውሸት፣ ምቀኝነት፣ ርኩሰት፣ ጥርጥር፣ ጭንቀትና ማንኛውም ዓይነት ክፋት በእግዚአብሔር መንግሥት አይኖርም (ራዕይ 21፡8፣27፤ ራዕይ 22፡15)።

6. አዲሲቷ ምድር አሁን ካለንባት ምድር በምን ትለያለች?

ያለንባት ምድር ያላት የተዘበራረቀ የአየር ንብረትና መልከዓምድር በአዲሲቷ አይኖርም። ለምሳሌ የሚያቃጥል ፀሐይ፣ በረሃ (ኢሳ. 35፡1፣2)፣ በሙቀት መለብለብ፣ በብርድ መንሰፍሰፍ አይኖርም። አውሬ የምንላቸው የዱር እንስሳት ለማዳ ይሆናሉ፤ አሁን ከሚያድኗቸው ጋር ወደፊት አብረው በሰላም ይኖራሉ፤ አዳኝና ታዳኝ አይኖርም፤ አንድ ታናሽ ብላቴናም ሁሉንም በእረኝነት ይጠብቃል፤ (ኢሳ. 11፡6-9፤ ኢሳ. 65፡25)። በዘፍ. 3፡17-19 የተጠቀሰው ርግማን በዚህች አዲስ ምድር ላይ አይኖርም። ወንጀል፣ ዓመጽ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የተፈጥሮ ቁጣ፣ … አይኖርም (ኢሳ.60፡8)። ከተማዋን የሚያረክስ አንዳች ነገር አይኖርም (ራዕይ 21፡27)።

7. በእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ይኖራሉ ያድጋሉ?

“የከተማዪቱም አደባባዮች እዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ” (ዘካ.8፡5)። በቅድስቲቱ ከተማና በአዲሲቷ ምድር የሚያድጉ ወጣቶችና ልጆች ይኖራሉ። ከአዳም ውድቀት በኋላ ሁለንተናችን እየኮሰሰ፣ ኃይላችን እየተዳከመ ስለመጣ ጌታ በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአእምሮና በአካልም ያሳድገናል (ሐዋ. 3፡20፣21)።

8. የዳኑት በሰማይ ሲገናኙ ይተዋወቁ ይሆን? በሰማይ ሰዎች ሲኖሩ አካል ይኖራቸው ይሆን?

“አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው” (1ቆሮ. 13፡12)። በዚህ ምድር ላይ አሁን ሰዎች እንደሚተዋወቁት ሁሉ በአዲሱም ሰማይና ምድርም እንዲሁ የሚተዋወቁ ይሆናል (ኢሳ. 26፡19፤ ኤር 31፡15-17፤ 1ቆሮ. 15፡51-55፤ 1ተሰ. 4፡13-18)።

“ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና” (ሉቃ.24፡36-39)። እነዚህ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ ሁለት ደቀመዛሙርት ጌታችንን ከሞት ከተነሳ በኋላ ነው ያገኙት። እርሱ እንዳለው ሥጋና ደም ያለው እንጂ መንፈስ ብቻ እንዳልሆነ በመገለጥ መስክሮላቸዋል።

9. በአዲሱ ምድር የሚኖሩ ሰዎች ምን ያደርጋሉ?

“ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ … እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል” (ኢሳ. 65፡21፣22)።

10. የዳኑት ምን ሌሎች ነገሮችን ያደርጋሉ?

መዝሙር ይዘምራሉ፤ (ኢሳ.35፡10፤ 51፡11፤ መዝ. 87፡7)፤ እግዚአብሔርን በዙፋኑ ላይ በየሰንበቱ ያመልኩታል፤ (ኢሳ. 66፡22፣23)፤ በማይጠወልጉ አበቦችና በማያረጁ ዛፎች ሁልጊዜ ይረካሉ፤ (ሕዝ. 47፡12፤ ኢሳ. 35፡1፣2)፤ ስለ እንስሳት ያጠናሉ፤ (ኢሳ. 11፡6-9፤ 65፡25)፤ ይጓዛሉ፣ ይሮጣሉ፣ ያስሳሉ፣ ይመረምራሉ፣ ነገርግን አይደክሙም፤ (ኢሳ. 40፡31)፤ እግዚአብሔር ሲዘምር ያዳምጡታል፤ (ሰፎ. 3፡17)፤ ከሁሉ የሚበልጠው ደስታ የሚሆነው ከጌታችንና መድኃኒታችን ጋር ፊት ለፊት እያዩት ለዘላለም ይኖራሉ፤ (ራዕይ 14፡4፤ 22፡4)።

11. ስለ አዲሱ ምድርና አዲሱ ሰማይ መግለጽ ይቻል ይሆን?

“ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል” (1ቆሮ.2፡9)። በመጀመሪያው አዳም ያጣነውን ሁሉና ከዚያም የሚልቀውን በሁለተኛው አዳም በጌታችንና በመድኃኒታችን ክርስቶስ አማካኝነት መልሰን እናገኛለን። ደስታችን ፍጹምና ዘላለማዊ ይሆናል፤ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትና በጥቂቱ ለማብራራት የሞከርነው በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠኑ የተገለጸውን ነው። ሆኖም እግዚአብሔር ለልጆቹ ያዘጋጀው ምን እንደሆነ በምድራዊ ቃላት መገለጽና መብራራት የሚችል አይደለም።

12. ይህ ታላቅ የሥጦታ ጥሪ ለማን ነው የቀረበው?

“የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ” (ራዕይ 22፡17)። “በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን” (1ጴጥ.1፡4)። ጥሪው የቀረበው ለሁሉም ነው፤ ዘላለማዊ ሕይወት ለሚፈልግ ሁሉ በነጻ የቀረበ ሥጦታ ነው። ርስቱን እንድንወስድ ተጠርተናል፤ ጥሪውን መቀበል እያንዳንዱ ሰው በግሉ የሚያደርገው ውሳኔ ነው። “እነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ” እያለ ነው አምላካችን፤ “ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ” እገባለሁ ይላል (ራዕይ 3፡20)። ምናልባት በሩን ላለመክፈት የያዘን የተሸከምነው ኃጢአት ቢሆን፤ ወይም ያለፈውና በስህተት የተሞላው ሕይወታችን ቢሆን፤ ወይም ሌላ በልባችን የከበደ የኃጢአት ሸክም ቢሆን “የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል” ወደ እርሱ እንምጣ (1ዮሐ.1፡7)። ይጠራል፤ ይለምናል፤ “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። … ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ. 11፡28-30)።

የተወደዱ አንባቢ ሆይ፤ ለዚህ ጥሪ የሚሰጡት ምላሽ ምንድነው?

ቅንብር፤ ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *