giziew.org

ሐዋርያነት፤ ዱሮና ዘንድሮ

የሐዋርያነት ሥጦታ መመዘኛ አለው። እነዚህን መመዘኛዎች በመጠቀም በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ላይ የነበረችው የኤፌሶን ቤተክርስቲያን በወቅቱ ራሳቸውን “ሐዋርያ” ብለው የሚጠሩ አገልጋዮችን መርምራ “ሐዋርያ” አለመሆናቸውን ስላረጋገጠች ከጌታ ኢየሱስ ምስጋናን ተቀብላለች።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በዘመናችን ሐዋርያ ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ መበራከት ስለዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ምንነት እንድንጠይቅ ይገፋፋናል። ሐዋርያ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ሐዋርያ የሚሆነው በምን መሥፈርት ነው? ሐሰተኛና እውነተኛ ሐዋርያ እንዴት መለየት እንችላለን? በቀድሞ ዘመንና በዚህ ዘመን ሐዋርያ መሆን ልዩነቱ ምንድን ነው? ይህ ጽሑፍ እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል።

የቃል ፍቺ

ሐዋርያ የሚለው ቃል “አፖስቶሎስ” ከሚል የግሪክ ቃል የተገኘ ነው። ይህንኑ ሃሳብ ሊገልጹ የሚችሉ ሌሎች ሦስት ተዛማጅ የግሪክ ቃላት አሉ። እነዚህም “አፖስቴሎ”፣ “ኤክሳፖስቴል” እና “ፔምፖ” የተባሉ ናቸው። ትርጓሜያቸውም እንደ ቅደም ተከተላቸው “መላክ”፣ “ወደ ውጪ መላክ” እና “መላክ” የሚል ሲሆን “አፖስቶሎስ” የሚለው የግሪክ ቃል ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ “ልዑክ፣ አምባሳደር ወይም ሐዋርያ” ማለት ነው።

ይህ “አፖስቶሎስ” የሚለው ቃል  የሚታወቀው ከክርስቶስ ልደት ቀደም ባሉ ጊዜያቶች በባህር ላይ ዕቃ ለማድረስ የተላከ (የሚያጓጉዝ) መርከብን በመወከል ነበር። በኋላ ላይ ግን ዕቃውን እንዲያደርስ የተላከው የመርከቧ ካፒቴን ወይም አዛዥ በዚህ ስም ይታወቅ ጀመረ። እየቆየ ደግሞ የቃሉ ትርጉም “ኃላፊነት ተሰጥቶት የተላከ ግለሰብን”፤ “ከላኪው ተልዕኮና ሥልጣን ተሰጥቶት የተላከና የተላከበትን ተልዕኮ በትክክል ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ” ሰውን የሚወክል ትርጉም እየያዘ መጣ። የእንግሊዝኛው “አምባሳደር” የሚለው ቃል በትክክል የዚህን ግሪክ ቃል ሃሳብ ሊገልጽ የሚችል ሲሆን፤ በመንግሥት ውስጥ በሚገኝ ከፍተኛ ባለሥልጣን አማካኝነት የተሰጠ ሹመት የሚወክልና መንግሥትን ወክሎ የላኪውን አገር ሥራ የሚያስፈጽም ኦፊሲያላዊ ከፍተኛ ልዑክ ማለት ነው።

ልክ እንደዚሁ በተመሳሳይ ትርጉም “ሐዋርያ” ማለት ግልጽ ለሆነ ተልዕኮ የተላከና ለላከው አካል መልስ መስጠት እንዳለበት ተረድቶ በሥልጣንና በተጠያቂነት ስሜት ሥራውን የሚሠራ ማለት ነው። አንዳንዶች ይህንን ቃል የቤ/ክ መሥራች፣ ባለራዕይ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣን ወይም የሥራ መሪ እና ሚሽነሪ ከሚሉ ስያሜዎች ጋር ያዛምዱታል። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ትርጉም ግን ከዚህ የዘለለ ነው።

ስለ ሐዋርያነት ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች

በዘመናችን ባሉ የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ሐዋርያነት ውዝግብን ከሚያስነሱ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ነው። ክርክሩም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ላይ ባሉ የተለያዩ ስነመለኮታዊ ትምህርት አመለካከቶች ምክንያት የመጣ ነው። እነዚህ አስተምሮዎችም ሦስት ዓይነት ናቸው። 1ኛው አመለካከት ሁሉም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ከአንደኛው ምዕተ ዓመት በኋላ መሥራት አቁመዋል ሲል፣ 2ኛው ደግሞ ያቆሙት የኃይል፣ የተዓምራትና ድንቅ የማድረግ ስጦታዎች እንጂ የተቀሩት በከፊልም ቢሆን አሉ የሚል ነው። 3ኛው ደግሞ  የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሁንም ቢሆን መሉ በሙሉ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ይገኛሉ የሚል ነው።

ስለዚህ በነዚህ አስተምሮዎች ላይ በመንተራስ የሐዋርያነትንና የነብይነትን ስጦታዎች በተመለከተ በተለያዩ ክርስቲያን ቤተ እምነቶች ውስጥ ያለውን አመለካከት ስናጠቃልለው ወደ ሁለት ማሳነስ ይቻላል። አንደኛው አስተምህሮ ሐዋርያነት እና ነብይነት በመጀመሪያው ምዕተ-ዓመት የነበሩ የመሥራችነት ስጦታዎች (ኤፌ 2፡20) ብቻ ሲሆኑ በተጨማሪም የመጨረሻው ሐዋርያ ሲሞት ስጦታነታቸው አቁሟል ይልና ከዚህም ጋር የመጀመሪያዎቹን ቤተክርስቲያናትን ለማቋቋም አብረው የተሰጡ ድንቅ የማድረግ ስጦታዎችም ሐዋርያ ከመሆን ጋር የዚያን ጊዜ አብረው አገልግሎታቸው እንዳከተመላቸው ይናገራሉ። ሁለተኛው አስተምህሮ ደግሞ እነዚህ ሐዋርያና ነብይ የመሆን ጥሪዎች አብሮአቸው ከሚሰጡ የምልክት፣ ተአምራት የማድረግና ድንቅ የመሥራት ስጦታዎች ጋር አሁንም በቤተክርስቲያን የቀጠሉና ያልተወሰዱ ናቸው የሚል ነው። ሁለቱንም አስተምህሮዎች የሚቀበሉ ክርስቲያን ቤተ እምነቶች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም።

አንደኛውን አመለካከት ለሚቀበሉ በዚህ ዘመን “ሐዋርያ” ወይም “ነብይ” ነኝ ብሎ የሚመጣ ማንኛውንም ሰው እንደ ሐሰተኛ የሚመለከቱት ሲሆን፤ ሁለተኛውን አመለካከት የያዙ ቤተ-እምነቶች ግን ሐዋርያነትም ሆነ የነብይነት ስጦታ አለ፤ ነገር ግን እውነተኛ መሆናቸው መፈተሸ አለበት ይላሉ (1ተሰ. 5፡21)።

ለሐዋርያነት የሚያበቁ መሥፈርቶች

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለሐዋርያነት የሚያስፈልጉ መሥፈርቶች አሉ። እንደሚታወቀው ይህ አገልግሎት እንደማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት በዋነኛነት የመንፈሳዊና የሞራል ብቃት መሥፈርት ያስፈልጉታል። እነዚህ ተፈላጊ የሞራል መሥፈርቶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቂቶቹ በ1ጢሞ. 3፡1-7፣ በሐዋ. 6፡ 3-6ና በቲቶ 1፡5-9 ተዘርዝረው ይገኛሉ። ልብ ማለት ያለብን ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ዲያቆን ወይም ኤጲስ ቆጶስ ሊኖራቸው ከሚገባ የባህርይ ዝርዝር ያነሰ የሞራል መሥፈርት ለሐዋርያነት ከተመረጡት ሊጠበቅ እንደማይችል ነው።

በተጨማሪ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ለመሆን አስቀድሞ በኢየሱስ መመረጥ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ በሰጠው አገልግሎት አብረውት መኖርና የትንሳኤው ምስክር መሆንን (ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ማየት) ይጠይቃል። ሐዋርያት ከአስራ ሁለቱ ደቀመዝሙር አንዱ የነበረውን የይሁዳን ቦታ ሊተካ የሚችል ሰው ሲመርጡ በሐዋ. 1፡21-22 “ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች፥ ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል” በማለት እንደ ተፈላጊ መሥፈርት ተጠቅመው ማትያስን ከአስራ ሁለቱ አንዱ እንዲሆን መርጠውታል።

በተጨማሪም “እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን” (የሐዋ. 10፡ 38-41)።

አስራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን መቋቋም መሠረት ናቸው (ኤፌ. 2፡20)። በሰማይ ለነርሱ የተለየ አስራሁለት ዙፋን ይኖራል (ማቴ. 19፡28)፤ በተጨማሪም አዲሲቱ ኢየሩሳሌም አስራ ሁለቱ መሠረቶቿ በስማቸው የተሰየሙ ናቸው (ራዕይ 21፡14)። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የአስራ ሁለቱ ሐዋርያነት ከሌሎቹ የተለየ መሆኑን ያሳያሉ።

በተጨማሪ ከአስራ ሁለቱ ውጪ ሐዋርያት ለሚሆኑ ደግሞ “ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል” (1ቆሮ. 12፡11) የሚለውን እንደ ሐዋርያ መመረጫ መሥፈርት ልብ ይሏል።

በርግጥ የጌታ ኢየሱስን ምድራዊ አገልግሎት በቅርበት ይከታተሉ የነበሩ 12ቱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ደቀመዛሙርትም ነበሩ። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ሁለት ሁለት አድርጎ የላካቸውን ወደ 70 የሚደርሱ ተከታዮቹን ልናስታውስ እንችላለን (ሉቃስ 10፡1፣ 17)። በተጨማሪ በዚያን ጊዜ ትንሳኤውንና ዕርገቱን የተመለከቱ ምስክሮች አምስት መቶ ይደርሱ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (1 ቆሮ. 15፡6)።

በሽተኛን የመፈወስ፣ አጋንንትን የማውጣትና ሌሎች ተዓምራትን የመፈጸም ልዩ ጸጋ፤ የሐዋርያነት ጥሪ ሲመጣ ወይም ሲሰጥ አብሮት እንደ ትጥቅ የሚሰጥ መሆኑን የአስራ ሁለቱን ሐዋርያት አገልግሎት መመልከት ብቻ በቂ ነው። በዚህ አንጻር ማንኛውም የአገልግሎት ስጦታ ሐዋርያነት፣ ነብይነት፣ ፓስተርነት፣ ካህንነትም ሆነ አገር መምራት ከአምላክ በኃላፊነትና በተጠያቂነት የተካፈልናቸው መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሐዋርያነት በተለያዩ ሶስት ገጽታዎች ታይቷል። የመጀመሪያው ኢየሱስ “ሐዋርያ” ተብሎ መጠራቱ ሲሆን (ዕብ. 3፡1) በሁለተኛ ደረጃ አስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት “ሐዋርያ” ተብለው መጠራታቸው ነው። በተጨማሪም ሌሎች ከአስራ ሁለቱ ውጪ የሆኑ አገልጋዮች “ሐዋርያ” ተብለው የተጠሩ አሉ።

“ሐዋርያ” የሚለው ቃል ትርጉሙ “የተላከ” ማለት ስለሆነና እግዚአብሔር አብ ደግሞ ኢየሱስን ወደዚህ ምድር ስለላከው፣ ኢየሱስ ራሱ “ሐዋርያ” ተብሏል (ዕብ 3፡1)፣ ኢየሱስ ደግሞ አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርቶቹን “ምስክሮቼ ናችሁ” ብሎ ስለላከ እነርሱም “ሐዋርያ” ተባሉ “አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ” (ዮሐ. 20፡21)፤ በመጨረሻም ቤተክርስቲያን ለተለያየ አገልግሎት የላከቻቸው አገልጋዮች ደግሞ “ሐዋርያት” ተብለዋል (2ቆሮ. 8፡23፤ ፊል. 2፡25)። ስለዚህ ይህንን የሐዋርያነት አገልግሎት በቀጥታ ከኢየሱስ ጥሪው የተሰጣቸውና በቤተክርስቲያን በኩል ጥሪው የደረሳቸው ብለን በሁለት ለመክፈል እንችላለን።

አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው አስራ ሁለቱ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ለሦስት አመት ተኩል አብረውት በምድር ላይ ያገለገሉ ናቸው። ከኢየሱስ ጋር ከመጥምቁ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ጀምሮ አብረውት ሲገቡና ሲወጡ የነበሩና በቀጥታ ከእርሱ ሥልጠናቸውን ተቀብለው የነበሩ ሰዎች ናቸው። በዚህም ብቻ ሳያበቃ በተጨማሪ ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳም በኋላ የትንሳኤው የዓይን ምስክሮችም ናቸው። በዚህም ምክንያት በልዩ አኳኋን “እናንት ምስክሮቼ ናችሁ” የሚለውን ጥሪ ወይም ተልዕኮ የተቀበሉ ናቸው (ማር. 3:14-15፤ 6:30)።

ስለዚህ ከ12ቱ ሐዋርያት እንደ አንዱ ሆኖ ለመቆጠር በትንሹ የሚከተሉት መሥፈርቶች ማሟላት አለባቸው።

  • በምድር ላይ ከጌታ ጋር የነበረ
  • ከሞት የተነሳውን ጌታ ያየ
  • ለአገልግሎቱ የተጠራ
  • የተለየ ተልዕኮ የተቀበለና
  • የሐዋርያነት ምልክት በሕይወቱ የታየ የሚሉት ናቸው።

ብዙ ክርስቲያን ቤተ እምነቶች “ሐዋርያ” የሚለውን የመዓረግ ስም የማይጠቀሙት ለአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ካላቸው ክብርና ይህ ስጦታ ከአንደኛው ምዕተ ዓመት በኋላ አቁሟል ብለውም ከማመን የመነጨ ይመስላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ

ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ሐዋርያነቱን የተቀበለው በቀጥታ ከኢየሱስ በመጣ ጥሪ እንደሆነ ይናገራል (ገላ. 1:1)። የአገልግሎቱ አድማስም አሕዛብን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነበር (ሮሜ. 1:5፤ ገላ. 1:16፤ 2:8)። ስለመጣለትም ጥሪ ሲናገር “ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ” ይላል። “ጭንጋፍ” ማለት “ያለ ወቅቱ የተወለደ” ማለት ሲሆን የርሱ የሐዋርያነት ጥሪ ከአስራ ሁለቱ ጋር አለመሆኑን ለመግለጽ የተጠቀመበት አገላለጽ ነው(1 ቆሮ. 15.5-8)። እርሱ እንደ ሌሎቹ አስራ ሁለት ሐዋርያት ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ከኢየሱስ ጋር አብሮ የመግባትና የመውጣት ዕድልን ያላገኘ ነበር። እንዲያውም እነዚህን የክርስቶስ ተከታይዎች ሲያሳድድ የነበረና ድንገት ኢየሱስ በደማስቆስ መንገድ ላይ ተገልጦለት “ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምጹን ከሰማ በኋላ “ለእኔ ልዩ መልእክተኛ ትሆናለህ” የሚል ጥሪ የተቀበለ ነው (I ቆሮ. 9:1፤ የሐዋ. 26:16-18)። ስለዚህ የእርሱ ሐዋርያ መሆን እንደ አስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት በቀጥታ ከኢየሱስ የመጣለት ጥሪ ነበር።

የጳውሎስም ሐዋርያነት እንደ እነርሱ የተለየ መልክ አለው። ጳውሎስ ራሱን ያለወቅቱ የተወለደ “ጭንጋፍ” በማለት ይጠራል (1 ቆሮ 15፡5-8)። ምንም እንኳ ያለጊዜው የተወለደ ቢሆንም የሐዋርያነት ፀጋ ተሰጥቶታል (ሮሜ 1፡5)፤ በተጨማሪም ጳውሎስ ሁሉም የሐዋርያነት ምልክቶች በአገልግሎቱ ታይተዋል። ይህም የተሰጠውን የሐዋርያነት ሥልጣን ያጎላል። አስራ ሁለቱ ሐዋርያት እነዚህ ሊካዱ የማይችሉ የሐዋርያነት ምልክቶች፣ ድንቅና ተዓምራቶች በአገልግሎታቸው ተፈጽመዋል፤ የነዚህ ምልክቶች በአገልግሎታቸው ውስጥ መታየት አገልግሎታቸውን በጌታ ኢየሱስ ሥልጣን እየፈጸሙ መሆናቸው ማሳያ ነበር (2ቆሮ. 5፡ 20)። ይህም የተሰጣቸው ሥልጣን ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ ሳይሆን ለመመሥረትና ለመገንባት ነው (2ቆሮ. 13፡10)።

የጳውሎስን የሐዋርያነት ጥሪ በተደጋጋሚ የሚገዳደሩ ቡድኖች እንደነበሩ አዲስ ኪዳን ላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። ለዚህም በሚመስል መልኩ ጳውሎስ ከአንድ ጊዜ በላይ ሐዋርያ መሆኑን ማስረጃ እያቀረበ ሲከላከል ይታያል (ገላ. 1፡1፤ 2ቆሮ. 1፡1፤11)። ክርክሩንም ሲቀጠል “ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም” ይላል (11፡6)።

ድንቅና ተዓምራቶች በተለያዩ ቦታዎች በጳውሎስ አገልግሎት ውስጥ ተፈጽመዋል። በኢስያ (የሐዋ. 19፡ 11-12)፣ በገላትያ (ገላ. 3፡5)፣ በመቄዶንያ (1ተሰ. 1፡5፤ የሐዋ. 16፡ 16-18)፣ በቆሮንቶስ (1ቆሮ. 2፡4፤ 2ቆሮ 12፡12)፤ እነዚህ ሁሉ ድንቅ ሥራዎች የተፈጸሙት ጳውሎስ የሚያስተምረውን ወንጌል ሰሚዎቹ ከአምላክ የተላከ መሆኑን ተገንዝበው ሐዋርያነቱን እንዲቀበሉት ነበር (ገላ. 3፡5)።

አዲስ ኪዳናችንን በደንብ አድርገን ከተመለከትን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት በተጨማሪ ጳውሎስና የኢየሱስ ወንድም (ያዕቆብ) “ሐዋርያት” ተብለው ለመጠራት ሐዋርያነታቸው ዕውቅና አግኝቶ ቤተክርስቲያንን ይመሩ እንደነበርና ሌሎችም ልክ እንደነርሱ “ሐዋርያት” ተብለው ይጠሩ እንደነበር እንረዳለን።

ሌሎች ሐዋርያት

ሌሎች ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በቤተክርስቲያኗ በኩል ለሐዋርያነት የተጠሩ አገልጋዮች ነበሩ፤ ከነዚህም ውስጥ በርናባስ (የሐዋ. 14:4፣14)፣ የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ (ገላ. 1:19)፣ አንዲራኒቆንና ዩልያን (ሮሜ. 16:7) (በነገራችን ላይ ዩልያን ወይም “ጁኒያ” የሚለው ስም የሴት ስም መሆኑ ይነገራል)፣ በተጨማሪ ሲላስና ጢሞቴዎስ በጳውሎስ “ሐዋርያ” ተብለው ተጠርተዋል (I ተሰ. 2:6)። ሌሎች ደግሞ ከቤተክርስቲያን ሲላኩ ወይም መልዕክት ይዘው ሲሄዱ “ሐዋርያ” ተብለዋል (ፊል. 2:25፤ 2ቆሮ. 8:23)።

የሐዋርያት የሥራ ድርሻ

የሐዋርያት ዋና የሥራ ሸክም መስበክ፣ ማስተማርና ማስተዳደር ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል ከማስተማርና ከመስበክ ባሻገር በማስተዳደር አገልግሎታቸው የተለያየ ግልጋሎት ይሰጡ ነበር። ከነዚህም ውስጥ ለክርስቲያኑ ማኅበረሰብ መንፈሳዊ ሕይወት መጎልበትና የበጎ አድራጎት በማከናወን ተግተዋል። እነዚህም የአምልኮን ፕሮግራም በመምራት፣ በጌታ ራት፣ በመካከላቸው የሚገኙትን ችግረኞች ለመርዳት ከምዕመናን የተሰበሰበውን ገንዘብ በማስተዳደር (የሐዋ. 3፡7)፣ በተለይ ይህን ገንዘብ የማሰባሰብና የማስተዳደር ሥራ ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ሸክም ሆኖ ቃሉን ለመስበክና ለማስተማር ያላቸውን ጊዜ ስለተሻማ ኃላፊነቱን ለሌሎች አስተላለፉ (የሐዋ. 6፡1-6)፣ የዲሲፕሊን እርምጃ (የሥነ ሥርዓት ቅጣትም) መውሰድ (የሐዋ. 5:1-11)፣ እየቆየም ሥራው እጅግ እየሰፋና እያደገ ሲመጣ ሐዋርያት በተለያየ አካባቢ ያለውን ሥራ መቆጣጠርና መጎብኘት ተጨማሪ የሥራ ኃላፊነታቸው እየሆነ መጥቶ ነበር (የሐዋ. 8:14፤ 9:32)።

ሌላ በተጨማሪ ይሰጡ የነበረው አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን እጃቸውን በመጫን ለምዕመናን ያስተላልፉ ወይም ያካፍሉ ነበር (የሐዋ. 8:15-17)። ጌታ በምድር በነበረ ጊዜ አጋንንትን እንዲያወጡና በሽተኞችን እንዲፈውሱ የሰጣቸው ጸጋ እርሱ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ እንኳ በሽተኞችን በመፈወስና አጋንንትን በማውጣት አገልግሎታቸው ቀጥለዋል (የሐዋ. 5:12፤ 2ቆሮ. 12:12)። በመጨረሻም ቤተክርስቲያኒቱ የገጠማትን የአስተምህሮት (የዶክትሪን) እና ሌሎች የአስተዳደር ግድርድሮሾችን፤ ሐዋርያት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ካሉ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ዴሞክራሲያዊ ሊባል በሚችል ውይይት ችግሮቹን ፈትተዋል (የሐዋ. 15:6፤ 6:3)።

የሐዋርያነት መመዘኛ

የሐዋርያነት ሥጦታ መመዘኛ አለው። እነዚህን መመዘኛዎች በመጠቀም በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ላይ የነበረችው የኤፌሶን ቤተክርስቲያን በወቅቱ ራሳቸውን “ሐዋርያ” ብለው የሚጠሩ አገልጋዮችን መርምራ “ሐዋርያ” አለመሆናቸውን ስላረጋገጠች ከጌታ ኢየሱስ ምስጋናን ተቀብላለች። “ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ” (ራዕይ 2፡2)።

ከዚህ በመቀጠል እውነተኛ ወይም ሐሰተኛ ሐዋርያትን እንዴት በዘመናችን መለየት እንችላለን ለሚል ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ መለያ መሥፈርቶችን እንመለከታለን።

የእውነተኛ ሐዋርያ ምልክት

ሐዋርያነትን የተቀበለ ሰው የዲያቆንና የኤጲስ ቆጶስነትን የሞራል ዝርዘር መሥፈርት የሚያሟላ መሆን ይጠበቅበታል። (1 ጢሞ. 3፡1-7)። ለምሳሌ የማይነቀፍ፣ በታመነ ቃል የጸና፣ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ሊመክርና ሊወቅስ የሚችል፣ ገንዘብን የማይወድ፣ ነውረኛ ያልሆነ፣ ረብ የማይወድ እነዚህ እና ተመሳሳይ የሞራል ብቃት ዝርዝሮች ማሟላት ይጠበቅበታል።

“በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተዓምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ”(2ቆሮ. 12፡12)። “ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው” (2ቆሮ. 11፡28)።

“እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና። እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ በዚህ ልክ ፍቅራችሁ የሚያንስ ነውን?” (2ቆሮ. 12፡13-15)።

“ምክንያቱም እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን፣ ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሰው ሁሉ መጨረሻ ያሰለፈን ይመስለኛል፤ ለዓለም ሁሉ፣ ለመላእክትም ለሰዎችም ትርኢት ሆነናል። እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንደ በደባለን፤ ያለ መጠለያ እንንከራተታለን፤ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን። ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን። እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጒድፍ፣ የምድር ጥራጊ ሆነናል” (1ቆሮ. 4፡9-13)።

ከላይ በተዘረዘሩት ጥቅሶች መሠረት እውነተኛ ሐዋርያ ሊኖሩት የሚገቡ የእውነተኝነቱ ማረጋገጫዎች በጥቂቱ ተገልጸዋል። እነርሱም የሞራል ብቃት፣ ያለነቀፋ መኖርን ጨምረው፣ በቃላቸው የሚታመኑ፣ ገበያ ተኮር ሆነው ነውረኛ ያልሆኑና ረብን የማይወዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። በተለይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮን ያስተዋሉና ይህንንም ለማስተማርና የተሳሳቱትን ለማረም የሚችሉ መሆን አለባቸው። በየቀኑ ሕይወታቸውም የምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያሳስባቸውና የሚያስጨንቃቸው መሆን አለበት።

በአገልግሎታቸውም ምልክት፣ ድንቅና ተዓምራት እንደ እውነተኛ ሐዋርያ ምልክት ሆነው በማያሻማ መልኩ ሊታዩ ይገባል። ይህንን አገልግሎታቸውን ሲሰጡም “በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” የሚለውን መመሪያ ተጠቅመው ነጻ ግልጋሎትን እንደነ ጳውሎስ መስጠት ይኖርባቸዋል። በሌላ አባባል አገልግሎታቸው ገንዘብ ተኮር ወይም ገንዘብን በመውደድ ወይም ጥቅምን በማግኘት ወይም አድናቆትን በመሻት መሆን የለበትም። ይህ ማለት ሐዋርያው የዕለት ተዕለት ሕይወቱን የሚመራበት ደሞዝ አይኖረውም ማለት አይደለም። ነገር ግን ምዕመናንን በገንዘብ ማስቸገር ወይም በተለያዩ ስልቶች ጥቅምን መፈለግ በሐዋርያው ሕይወት ሊታይ አይገባም። ለምዕመናን ያላቸውን ገንዘብም ሆነ ሕይወታቸውን ማካፈል እንጂ የምዕመናንን ንብረት የመቀማት አካሄድ ሊታይባቸው በጭራሽ አይገባም። በመጨረሻም አገልግሎቱ የሚጠይቀውን ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ሕይወት ያስፈልጋቸዋል።

የሐሰተኛ ሐዋርያት ምልክት

“ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” (2ቆሮ. 11፡3)።

“የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ?” (2ቆሮ. 11፡3-4)። ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በፃፈው መልዕክት መሠረት ልዩ ወንጌል የሚሰብኩ የተረገሙ ናቸው ብሏል (ገላ. 1:8-9)።

“የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና” (1ቆሮ 10 ፡18)።

“እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል” (2ቆሮ. 11፡13-14) (በሌላ አነጋገር ጭምብል አጥልቀው ይመጣሉ ነው የሚለው)።

“ማንም ባሪያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበላችሁ፥ ማንም ቢቀማችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁና” (2ቆሮ. 11፡20)። የዘመኑ ሐዋርያት ነን ባዮች እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው የሚታገሡና አሜን ብለው የሚቀበሉ ሳይሆኑ ትንሽ ከመስመር ያፈነገጠ የሚመስላቸውን በራሳቸው ጥበቃ ኃይሎች አፈር ከድሜ የሚያስገቡ ናቸው። “የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ” (ማር. 12፡40)።

“ምናልባት ክርክር፣ ቅንዓትም፣ ቁጣም፣ አድመኝነትም፣ ሐሜትም፣ ማሾክሾክም፣ ኩራትም፣ ሁከትም፣ ይሆናሉ፤ እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ”(2ቆሮ. 12፡20-21)።

ሐሰተኛ ሐዋርያትን ከሚያሳዩት ባህርያት አንጻር ለይቶ ማወቅ ይቻላል። ከላይ በተዘረዘሩት ጥቅሶች ላይ የሚገኙ መገለጫዎችን በመጠቀም ሐሰተኛ የተባሉ ሐዋርያትን መለየት ይቻላል። በተለይ የነዚህ ሐሰተኞች ባህርይ በ 2 ቆሮንቶስ መጽሐፍ ውስጥ በተለያየ መልኩ ተዘርዝሮ ይገኛል። እነዚህም ምዕመንን በማታለል የምዕመንን ሃሳብ ማበላሸት፣ ለክርስቶስ መሰጠት ከሚገባው ቅንነትና ንጽህና ምዕመንን ማደናቀፍ፣ እውነተኞቹ ሐዋርያት ከሰበኩት ውጪ ሌላ ኢየሱስ እና ሌላ መንፈስ ያለበትን ሌላ ወንጌል መስበክ፣ ራስን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ከፍ (ፕሮሞት) ማድረግ፣ በሰው ዘንድ ማንኛውም የክርስቶስ ሐዋርያ ሊያስብላቸው የሚያስችል፤ የጽድቅ አገልጋይ የሚያስብል ጭንብል ማጥለቅ፣ ሰዎችን ባሪያ አድርጎ መጠቀም (ካዳሚ ማድረግ)፣ ገንዘባቸውን በተለያየ ዘዴ መቀማት፣ ኩራት፣ ርኩሰትና ዝሙት የመሳሰሉት የሚታይባቸው ነው።

የዱሮና የዘንድሮ ሐዋርያት ንጽጽር

እስከ አሁን ስለ ሐዋርያና ሐዋርያነት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ባደረገ መልኩ ጥናት አድርገናል። ከዚህ በመቀጠል በዚህ ዘመን ራሳቸውን “ሐዋርያ” ብለው በሚጠሩና የጥንት ዘመን ሐዋርያት መካከል ያሉትን ልዩነቶች በንጽጽር መልክ ለመረዳት እንሞክራለን።

የድሮዎቹ ሐዋርያት የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚገነቡና የሚያሰፉ ሲሆን፤ በሚገርም መልኩ የዘንድሮዎቹ የራሳቸውን መንግሥት የሚገነቡና ስለ ባንክ አካውንታቸው ገንዘብ መጠን እጅግ የሚጨነቁ ሆነው ተገኝተዋል። የአገልግሎታቸውም ትኩረት “ገበያ መር እና ጥቅም ተኮር” ነው። ጳውሎስ ራሱን ከሐሰተኞች ሐዋርያ/ወንድሞች ጋር በማነጻጸር እንደሚነግረን እኛ “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን” (2 ቆሮ. 2፡ 17)።

እውነተኛው ወንጌል “ኑሮዬ ይበቃኛል ማለት እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው” (1 ጢሞ. 6፡6) ሲል፤ የዘንድሮዎቹ አገልጋዮች ግን ገንዘብን ማትረፊያ አድርገውታል። ድሮ ሐዋርያት “ሞኝ”፣ ምዕመኑ ደግሞ ተጠቃሚ (ብልጥ) ነበር። ዘንድሮ ግን በተገላቢጦሽ ሐዋርያት ብልጥ ምዕመኑ ግን ሞኝ መሆኑ የሚያስገርም ነው። የአንድ አገር መሪ እንደተናገሩት ድሮ ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዉ መገበ፤ ዘንድሮ ግን አምስት ሺህ ምዕመናን አንድ አጭበርባሪ ሐዋርያ ነኝ ባይ የሚመግቡ መሆኑ ያሳዝናል ብለዋል።

በሐሰተኛ ሐዋርያት የተታለለ ምዕመን ስለ ክርስቶስ ቅንነትና ንጽህና ያላቸው ሃሳብ ሊበላሽ ይችላል። በ2 ቆሮንቶስና በገላትያ መልዕክቶች ሐሰተኛ ሐዋርያት የሚሰብኩት ወንጌል “ልዩ ወንጌል” ተብሏል፤ በዘመናችን ደግሞ በሐሰተኛ ሐዋርያት እየተሰበከ ያለው “የብልጽግና ወንጌል” ሲሆን ይህንንም በጳውሎስ ጊዜ እንደተነገረው “ልዩ ወንጌል” በማለት ሊጠራ ይችላል። እውነተኛ ሐዋርያ በሚሠራው ሥራ ምስጋናውን የሚቀበለው ከእግዚአብሔር ነው፤ ሐሰተኛ ሐዋርያ ግን ራሱን ያመሰግናል፣ ያስመሰግናል፣ ራሱንም በመደጋገም ከፍ ከፍ ያደርጋል። በአዲስ ኪዳን የክርስቶስ ሐዋርያ የሚባሉ እንዳሉ ሁሉ ውሸተኞች ሐዋርያትም አሉ። የጽድቅ ባሪያዎች የተባሉ እንዳሉ ሁሉ ጭንብል ያጠለቁ፣ ራሳቸውን የብርሃን መልአክና የጽድቅ አገልጋዮች አስመስለው ለማጭበርበር እንዲመቻቸው “የበግ ለምድ” የለበሱ ሐዋርያት ይገኛሉ። ምዕመኑንም ከክርስቶስ ባሪያነት ወደ ሐሰተኛ ሐዋርያ ካዳሚነት ይለውጣሉ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምዕመናን “አልከብድባችሁም” በማለት ራሱን በፋይናንስ እየደገፈ ሲያገለግል ነበር። በአገራችን ፈልተው የሚገኙት የዘመናችን ሐሰተኛ ሐዋርያት ግን ትኩረታቸው ገበያ መርና ጥቅም ተኮር በመሆኑ የብዙዎችን “ቤት ይበላሉ፣ ይቀማሉ”፤ “ነውረኛ ረብ የሚወዱ” ናቸው። እውነተኛ ሐዋርያ እንደ ጳውሎስ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ ሲል ሐሰተኛ ሐዋርያ ደግሞ በቅጥረኝነት (በሞያተኝነት) መንፈስ የሚመላለስ ነው። የዘመናችን አጭበርባሪ ሐዋርያት ገንዘብ ካጡ ሥራውን አይሠሩም፣ ምዕመኑንም ከአደጋ አይጠብቁም።

በቅርቡ ለአገልግሎት የተጠራ እንድ ሰው “መጀመሪያ አካውንቴ ላይ አራት መቶ ሸህ ብር አስገቡ” ማለቱ ተደምጧል ። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል” (ዮሐ. 10፡11-13)።

እንደ ጳውሎስ ያለ እውነተኛ ሐዋርያ ግን አገልግሎቱ በተለያየ ግድርድሮሽ ውስጥ ቢያልፍም እንኳ በጽናት ይፈጽመዋል። እንደ ተቀጣሪና ችግር ሲመጣ ዞር እንደሚሉት ሳይሆን መከራን እየተጋፈጠም ያገለግላል። እንደሚታወቀው ቅጥረኛ አደጋ በመጣ ጊዜ በጎቹን በፍጥነት ትቶ ይሄዳል (ዮሐ 10፡12፤ የሐዋ. 20፡29-30)። በተጨማሪም ሮሜ 16፡18 ሐሰተኞችን እንደዚህ በማለት ይገልጻል፤ “እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ”።

ዘመኑ የከፋ ሆኗል። ሰዎች በግፍ ላይ ግፍ የሚፈጽሙበትና ለዚህም ደግሞ ሃይማኖትን መደበቂያ ያደረጉበት ዘመን ነው። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በማንበብ ለራሳቸው እውነትን ከማወቅ ይልቅ በሃሰተኛ ሐዋርያት ከንቱና ስሜትን ብቻ የሚነካ ንግግር ትኩረት በመስጠት ወደ ጥፋት እየተነዱ ነው። እጅግ በርካታ መረጃዎች እየወጡ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እየተናገረ ቢሆንም ሰዎች አሁንም ራሳቸውን ለስህተት ትምህርት አሳልፈው በመስጠት በጥፋት ጎዳና እየነጎዱ ነው። በማጭበርበርና በመረጃ ለሚደረግ ተዓምራትና ፈውስ ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውንም እያጡ ነው።

ስለዚህ እነዚህንና ከላይ የዘረዘርናቸውን ነጥቦች ልብ በማለት ራሳችንንና ወንድም እህቶቻችንን ሊያሳስቱ ከተነሱ ሐሰተኛ ሐዋርያት ልንጠነቀቅ ይገባናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይመክረናል፤ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” (ኤፌ. 5፡16)።                                                  

ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ

ዋቢ መጻሕፍት

ለዚህ ጽሁፍ በዋቢነት የተጠቀሱት “ነቢያት፤ ድሮና ዘንድሮ” ለሚለው ጽሁፍ የተጠቀሱት ናቸው።


1 thought on “ሐዋርያነት፤ ዱሮና ዘንድሮ”

  1. עיסוי אירוטי בירושלים

    Hello there! I simply want to offer you a huge thumbs up for your excellent information you have here on this post. I will be coming back to your website for more soon.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *